Home » ዜና » ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ ያደረገውን የጥናት ውጤት ይፋ አደረገ

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ ያደረገውን የጥናት ውጤት ይፋ አደረገ

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ የተደረገ ጥናት ውጤት — የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

Ethiopian Citizens for Social Justice Party.

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የጥናት ውጤቱ በተጨባጭ እንዳረጋገጠው ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራ እና ሕገ ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ተድርጓል። የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የግል እና የመንግሥስት የሚዲያ ተቋማት፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና በጉዳዮ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይህን በጠራራ ፀሐይ የተፈፀመ ለከት የለሽ የሕዝብና ሀገር ሀብት ዘረፋ ሲያሳውቁ ቆይተዋል።

የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበር እና በግል ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል፣ በምንም መስፈርተ የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት እና የነዋሪነት መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የመሬት ወረራን በተመለከተ

በዋናነት በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸው እና በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል የሚሉ ግለሰቦች እና ወረራ የተፈፀመባቸው ቦታዎች አካባቢ ላይ የሚገኙ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ኃላፊዎች እና ፈፃሚዎች ናቸው፡፡ ጉዳዮን በማፋጠን ሕገ ወጥ ደላላዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ይህ በጠራራ ፀሐይ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን ነበሩ። በተለያየ መልኩ ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወረው እንዲይዙ አመቻችተዋል፤ የመንግሥትን ሥልጣን ለሕገ ወጥ ተግባር ከለላ እና ሽፋን እንዲሆን አድርገዋል፤ ከዚህም ባስ ሲል ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር እራሳቸው ወረራ ፈፅመዋል። ሕገ ወጥ የሆኑ የግንባታ ፍቃዶች፣ ካርታ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማዘጋጀት ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ሕጋዊ መስለው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል። በአጠቃላይ በመሬት አስተዳደር በግንባታ ፈቃድና በደንብ ማስከበር እንዲሁም በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች እና ፈፃሚዎች ግዴለሽነት እና የወንጀል ተባባሪነት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሃብት ተዘርፏል።

ይህ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በሃገራቸን አዲስ ያልሆነ እና በተለያዩ ጊዜዎች እና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ግን በዚህ ደረጃ እና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የመሬት ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ እንደሚስተዋለው በአገልግሎት ላይ የሚውሉት ቦታዎች ስፋት ከፍተኛ ከመሆናቸውም በላይ ወረራው የከተሞችን አረንጓዴ ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም ለመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል፡፡

• የመንግሥት አካላት ለሕገ ወጡ የመሬት ወረራ ግልፅ ትብብር ማድረጋቸውን በግልፅ ካሳዩት የጥናት ውጤቶች ውስጥ በዋናነት የሚከተሉት ይገኙበታል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ 3 ኮንዲሚኒየም አካባቢ ልዩ ስሙ ‹‹ቦርጋ›› ተብሎ በሚጠራው መንደር 10ሺህ ካ.ሜ ስፋት ያለው ቦታ ብዛት ባለቸው ሰዎች ታጥሮ ቤቶች በቀናት ውስጥ ተገንብተው ከተጠናቀቁ በኋላ ተዘጋጅተው ሲጠባበቁ የነበሩ የመብራት ኃይል እና የውሃና ፍሳሽ ሠራተኞች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ውሃ እና መብራት እንዲያገኙ አድርገዋል።

  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ 1 አደባባይ ዙሪያውን ለጤና ጣቢያ ለትምህርት ቤትና ለአረንጓዴ ልማት የተተው ቦታዎችን የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሆኑ ግለሰቦች ተከፋፍለው የተለያዩ የንግድ ሥራዎች ሲያከናውኑበት የመንግሥት አካላት በዝምታ ከማለፍ በላይ ቁርጥ ግብር እየከፈሉ እንዲሠሩ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ገላን ኮንዶሚኒየም በሚወስደው ቦታ ደንብ አስከባሪዎች እና የከተማው ፖሊስ ወጣቶች ሲያጥሩ ቆሞ ጥበቃ ሲያደርጉላቸው በአካል ተገኝተን ተመልክተናል፡፡
  • በመሬት ወረራው በዋናነት የሚያዙ ቦታዎች ለጤና፣ ለትምህርት እና ለአረንጎዴ ልማት የተከለሉ በመሬት ባንክ ስር የነበሩ ቦታዎች፤ በጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች መሃል ለተለያዮ ዓላማዎች ክፍት ሆነው የተቀመጡ ቦታዎች፤ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መተላለፊያዎች ናቸው። በዋናነት የመንግሥት አካላት በጉዳዮ ላይ በዋናነት ተሳታፊ በመሆናቸው የመሬት ወረራውን ለመከላከል አልተቻልም ። በተጨማሪም ወረራው ብዛት ባላቸውና በተደራጁ አካላት ስለሚፈፀሙ የአካባቢው ነዎሪዎች መንግሥት ከዛሬ ነገ እርምጃ ይወስዳል በማለት ዝምታን በመምረጣቸው ጉዳዩ ሕጋዊ እና መብት እስኪመስል ድረስ ያለከልካይ ተፈፅሟል።
  • የጥናት ቡድኑ በዋናነት ጥናት ያደረግባቸው በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወስኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። በዚህም መሰረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 96ሺህ 8መቶ ካ.ሜ (ጆሞ 3 መስታወት ፈብሪካ አልፍ ብሎ ለአረንጓዴ ልማት ተከልሎ የነበረ 50ሺህ ካ.ሜ፣ ጆሞ 2 ከ5 ዓመት በፊት ለአካባቢውና ለአጎራባች ቀበሌዎች እንዲያገለግል ታሳቢ ተደርጎ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት የነበረ የጤና ጣቢያ ቦታ 3ሺህ ካሬ፣ ጀሞ 1 መስታወት ፋብሪካ ጀርባ ኮሚኒቲ ፓሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት 2ሺ ካ.ሜ፣ ጀሞ 3 ቦርጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 10000ካሬ፣ ጆሞ 3 ኮንዶሚኒየም አካባቢ 300ካ.ሜ፣ ጆሞ 1 አደባባይ ግራና ቀኝ ለተለያዩ አገልግሎቶች የተተወ 20ሺህ ካ.ሜ፣ ለቡ ቫርኔሮ አካባቢ ለአረንጓዴ ልማት እና ለእግረኞች የተተወ 3ሺህ ካ.ሜ፣ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ገላን በሚወስደው መንግድ 2ሺ ካ.ሜ.፣ ጆሞ 3 ኮንደዶሚኒየም ጀርባ በቆርቆሮ የታጠረ ካርታ የተለጠፈበት 2ሺህ 5መቶ ካ.ሜ፣ ቻይና ትቦ ማከማቻና ጠጠር ማምረቻ አጠገብ ወረዳ 01 4ሺ ካ.ሜ፡፡
  • በየካ ክፍለ ከተማ 58ሺህ ካ.ሜ፦ (አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ወረዳ 13 በግለሰቦች ተወርሮ በቆርቆሮ ቤት የተሠራበት 3ሺህ ካ.ሜ፣ የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በቆርቆሮ የታጠረ 10 ሺህ ካ.ሜ፣ ልዮ ስሙ አንቆርጫና ጉራራ በተባሉ አካባቢዎች በእንጨት እና በቆርቆሮ ተሸንሽኖ የታጠረ 45ሺ ካ.ሜ
  • በቦሌ ክፍለ ከተማ 15ሺ ካ.ሜ ፦ ወጂ በሚባል አካባቢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጂ ቅርናጫፍ ገባ ብሎ ለአረንጓዴ ልማት የተተወና በመሬት ባንክ የነበረ ቦታ 5ሺህ ካ.ሜ፣ ቦሌ አራብሳ አካባቢ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፊት ለፊት 10ሺህ ካ.ሜ፡፡10
  • ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 21ሺህ 1 መቶ ካ.ሜ፦ ወረዳ 01 የገበሬ ልጆችን በሚሉ የታጠረ 11 ሺህ 5መቶ ካ.ሜ፣ ወረዳ 02 በቀለ ወፍጮ ቤት ጀርባ የታጠረና ለሦስተኛ ወገን የተላለፈ 9 ሺህ 6መቶ ካ.ሜ፣ እንዲሁም
  • በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 22ሺህ 5መቶ ካ.ሜ፦ ቂሊንጦ ኮንዶሚኒየም አከባቢ 2ሺህ 5መቶ ካሬ ኮየ ፈጬ ፀበል ቤት አካባቢ ለጠጠርና አሸዋ ማምረቻ የተተወ 20ሺህ ካ.ሜ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ የተያዙ ቦታዎችን ማግኘት ችለናል።ይሄም የሚያሳየው በተጠኑት አምስት ክፍለ ከተሞች ላይ ባጠቃላይ 213ሺህ 9መቶ ካ.ሜ የሚሆን መሬት በወረራ መያዙን ነው።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Comments — What do you think?