Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » ህይወትን ከማዳን የበለጠ ክቡር ስራ የለም (ከአንተነህ መርዕድ)

ህይወትን ከማዳን የበለጠ ክቡር ስራ የለም (ከአንተነህ መርዕድ)

ከአንተነህ መርዕድ
ሚያዝያ 2020 ዓ ም

በ1974 ዓ ም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት እስር ቤት ነበርሁ። በፖሊስ ታጅቤ ደብረማርቆስ ሆስፒታል ሄጄ ያየሁት የህይወቴን አቅጣጫ ቀየረው። አንዲትን አርሶ አደር ሴት ብዙ ሰው ከቦ በጥያቄ ያዋክባታል። የቻለችውን እሷ ያልቻለችውን ባሏ ይመልሳሉ። እንደ እሷና ባሏ አባባል ለሊት ተኝታ እባብ በአፏ ሲገባ ነቃች። በድንጋጤ ለማውጣት ስትታገል እባቡ በሃይል ወደሆዷ ገባ። ለዚህም ነበር እርዳታ ለማግኘት ሆስፒታል መጥታ የሚረዳት ሳይሆን በጥያቄ የሚያዋክባት በዝቶ ያየሁት። ከሚጠይቋት መካከል በርካታ ነጭ ጋውን የለበሱ የጤና ባለሙያዎች ነበሩ።

ስሜ ተጠርቶ ከአጀበኝ ፖሊስ ጋር ስገባ ዶክተሩ ጠበቀኝ። ይህን ዶክተር ገበሬዋን ከከበቡት መሃል አይቼው ነበር። “እባብ ገብቶብኛል ያለችው ሴት ለእርዳታችሁ መጥታለች። እውነት አይደለም ብላችሁ ብታምኑ እንኳ ከመንፈስ ጭንቀቷ ለመገላገል አልሞከራችሁም። በጥያቄ ስታዋክቧት ነበር። እንዴት አስቸኳይ እርዳታ የማልፈልገው እኔ ቀድሜ እንድታከም ፈቀድህ?” ብዬ ቁጣዬንና ጭንቀቴን ሳወርድበት ያጀበኝ ፖሊስ እየተቆጣኝ ነበር። በሁኔታው የተጸጸተው ዶክተር ደንግጦ “እሽ ልክ ነህ” ብሎ ሰትዮዋን አስጠርቶ ከረዳት በኋላ ህክምናዬን ጨርሼ ወደ ወህኒ ቤቴ ስመለስ ቁጭቴ አልበረደም። የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብት አልተከበረም፣ ጭቆናው ይቅር ብለን ስንታገል ብዙ ለጋ ጓደኞቻችን በደርግ ጭካኔ የረገፉበት፣ የተረፍነውም በእስር የምንማቅቅበት ፍትህ ማጣት በገዢዎች ብቻ ሳይሆን ዜጋ ለዜጋው በሚያደርገው ግዴለሽነትም መቀጠሉ ያንገበግብ ነበር።

ወህኒ ላሉ ጓደኞቼ ያየሁትን ዘግኛኝ ሁኔታ ነግሬያቸው “ ከእስር ለመፈታት ብንበቃ፤ ከቻልን ብዙዎቻችን ሃኪም ነው መሆን ያለብን። ሌላው ሁሉ ሙያ ስርዓቱን እንድናገለግል የሚያደርገን ሲሆን ህክምና ግን ምስኪን ታማሚ ኢትዮጵያዊውን እንድንረዳው ያደርገናል” እያልሁ ተማጸንሁ። ለራሴም ይህንኑ ወሰንሁ። በ1975 ዓ ም ከእስር ተፈታሁና ያቋረጥሁትን ትምህርቴን ባህርዳር ለመቀጠል ተመልሼ ሳይንስ ለማጥናት አመለከትሁ። “ቀድሞ የተመደብከው ሬኮርድ የሚያሳየው አካዳሚ ስለሆነ ሳይንስ ክፍል አትገባም” ተባልሁ። ብዙ ለማሳመን ብጥርም አልተሳካልኝም። ህልሜን ውሃ በላው። ዩኒቭርስቲ ብገባም እጣዬ ጋዜጠኝነት ሆኖ ቀረ። አንዱ የእስር ቤት ጓደኛዬ ህክምና መርጦ ሲገባ በደስታ አንገቱ ላይ ተጠምጥሜ “እንዴት ህክምናን መረጥህ?” ስለው “ወህኒ ቤት ቃል ያስገባሃንን አልረሳሁትም” አለኝ። ይህ ጓደኛዬ እኔም ከተመኘሁት በላይ ነው የሄደው። ገና ከመመረቁ በሆስፒታል ተቀጥሮ ታማሚ ወገኖቹን በማከም አልረካም። ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ክሊኒክ ከፍቶ ከማገልገል አልፎ የግል ሆስፒታል ሰርቶ ለብዙ ሰዎች ህይወትና እንጀራ የከፈተው ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በሌላም ዘርፍ አገሩን በከፍተኛ ደረጃ እየረዳ ነው።

የጋዜጠኝነት ስራዬም በስርዓቱ ባለመወደዱ በተደጋጋሚ ከታሰርሁ በኋላ ለስደት በቃሁ። ሳይማር ያስተማረኝ፣ ራሱ ሳይታከም የጤና ታክስ እየከፈለ ያሳደገኝን የአገሬን ድሃ እዳዬን ሳልከፍለው ዛሬ በስደት ዓለም ሁሉም ነገር የሞላላቸውን ፈረንጆች ድሮ በምወደው ህክምና ሳስታምምና ሳገላብጥ ወገኖቼን እያስታወስሁ በውስጤ አለቅሳለሁ። በተለይም በአሁን የአገሬ ህዝብ ምንም ዝግጅትና ቁሳቁስ ሳይኖረው ጨካኙንና አስፈሪውን የኮሮና ቫይረስ በባዶ እጁ ሲጋፈጥ በህሊናዬ ባየሁ ቁጥር መሪር ሃዘን አጥንቴ ድረስ ይዘልቃል። በኮሮና ቫይረስ የተጠቁትን ለመርዳት ጭንብል ተከናንበን ራሳችንን ሆነ ሌላውን እንዳያጠቃ የምናደርገርገው ዝግጅትና የምናባክነው ቁሳቁስ ሳስተውል በቂ መከላከያ የሌላቸው ኢትዮጵያ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችበፊቴ ይደቀናሉ። አባቶቻቸው ከላይ ከአውሮፕላን መርዝና ቦንብ እየወረደባቸው በሁዋላ ቀር መሳርያ ያለምንም መከላከያ እየተጋፈጡ ህይወታቸውን ሰጥተው አገርና የትውልዱን ህይወት እንዳተረፉት ሁሉ እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸው ወድቀው ሌሎችን ለማዳን የሚተናነቁ የጊዜአችን ጀኞች  አድርጌ አያቸዋለሁ። ህይወትን የማዳን ያህል ክቡር ነገር ምን አለና!

ምስኪን ወንድሞቻቸውን ለመግደልና ለማጋደል ቆንጨራ፣ ፍላጻና ክላሽ ይዘው ጥላቻን ይዘሩ የነበሩ የኛ ፈሪዎች ይቅርና ኒውክለር የታጠቁ “ሃያላን” እቡያን ለአንዲት ነፍሳቸው ኮረናን በመፍራት ዋሻ ሲገቡ አይተናል። የሶርያ፣ የሊብያ፣ የየመን፣ የኢራቅ ህጻናት ላይ ቦንብ ያወርዱ፣ ህይወት ይቀጥፉ፤ ያለመጠለያ ያስቀሩ፣ ለስደት ይዳርጉ የነበሩ “ሃያላን” ብቻ ሳይሆኑ በቴሌቪዥን ዜናውን እያየ ምንም እንዳልተፈጸመ ይመለከት የነበረና ከነዳጁ ዘረፋ ትሩፋቱ ይደርሰው የነበረ ህዝብም በሺ የሚቆጠር አስከሬን ያለቀባሪ ሲቀር፣ ሞት በቴሌቪዥን እስክሪን ብቻ ሳይሆን በገሃድ በሩን ሲያኳኳበት ያዳምጥና ይሸበር ጀመር። የት ሊገባ? እያንዳንዱ እጁ ላይ የንጹሃን ደም ፍንጣቂ አለበትና። ድምጽ ሰጥቶ የመረጣቸው ባለስልጣናት፣ ግብር ከፍሎ ያስታጠቃቸውን ወታደሮች ግፍ አልገሰጸምና። በአገራችን ደግሞ “ክልልህ አይደለም ውጣልኝ” ብሎ ከማፈናቀል ያለፈ በገጀራ ይገድል፣ ዘቅዝቆ ይሰቅል የነበረ ሁሉ ዛሬ ቀበሌው ሳይሆን ቤቱ እንኳ የእሱ እንዳልሆነ አይምሬው ኮሮና አሳይቶቷል።

ከህክምና ይልቅ ጋዜጠኝነቱ እየጎተተኝ እቸገራለሁና ይቅር በሉኝ። አሁን ምን እናድርግ? ወደሚለው ብሄድ ይሻላል። የኮሮና ቫይረስ ለዓለም አዲስ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጥንቃቄዎችን ከማድረግ በተጨማሪ የራሱ ልዩ ባህሪ ስለአለው በየቀኑ በሚወሰደው ልምድ ብዙ የመከላከያ መንገዶች ተዘርግተውለታል። ሁሉንም መንገዶች እንከተል ማለት በእኛ አገር ሃቅም የሚቻል አይሆንም። ዓለም ሳይዘጋጅበት ከተፍ ያለ ቫይረስ በመሆኑ በሃብትና በእውቀት ይኩራሩ የነበሩ ሃገሮችን ሳይቀር ስርዓታቸውና እውቀታቸው ብዙም እንዳልጠቀመ አሳይቷል። በሃብቱ ሳይሆን በእምነቱ ጽኑዕ የሆነ ህዝባቸን ፈጣሪውን ከመለመን በተጨማሪ መቅሰፍቱን ለመከላከል ብሎም ጉዳቱን ለመቀነስ እንቅስቃሴው ሁሉ አቅሙን ያገናዘበና ከሁኔታዎች የተስማማ ሊሆን ይገባል። ዕንደዛሬው ህክምና ባልተስፋፋበት ዘመን በዕኛ እድሜ ሳይቀር ተስቦ፣ ፈንጣጣን፣ ኩፍኝና ልዩ ልዩ ተላላፊና ቀሳፊ ወረርሽኝ የተከላከለበትን በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ልናሳውቅ መልሰንም ልንጠቀምበት ይገባል።

እኔ ባደግሁበት አካባቢ ተስቦ ሲገባ በገባበት ቤት እስታማሚ ሲቀር መንደሩ ሁሉ ቦታውን ለቅቆ ይሸሻል። የቤተሰብ አባል አስታማሚው ቤቱን ዘግቶ እያገላበጠና የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይውላል። በንክኪ ብቻ ሳይሆን በመተያየትና ስም በመጥራራትም በሽታው ይተላለፋል ተብሎ ስለሚታመን ጠያቂዎች በለሊት መጥተው ስም ሳይጠሩ “ሞረሽ” ይላሉ። አስታማሚውም “አቤት” ይላል። “እንዴት ዋላችሁ? እከሌስ እንዴት ሆነ? ተሻላችሁ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። በሩን እንደዘጉ ከውስጥ ሆነው የእያንዳንዱን ታማሚ ሁኔታ ያስረዳሉ። “እህልና ውሃ አምጥተናል። ውጭ እንተውላችኋለን። የሚያስፈልጋችሁ ካለ ንገሩን” ብለው ይሰናበታሉ። የሞተም ካለ አስታማሚው ከፍኖ አስከሬኑን ወደበር ያስጠጋላቸዋል። በጥንቃቄ ወስደው በለሊት ይቀብሩና ህዝቡ ባለበት በቀን በምስል (አስከሬን ያለ በሚመስል ሳጥን) ይለቀሳል። በዚህ መልክ በሽታው በተወሰነ ቦታ ተከልሎ እንዲቀር ይደረጋል። በትንንሽ የጥንቃቄ ጉድለትና ድፍረት በሽታው የሚሰራጭበት ሁኔታም አለ። ዛሬ ራስን ማግለል ወይም ኳራንቲን ወላጆቻችንም በአቅማቸው ከበሽታ ለመትረፍ ያደርጉት የነበረ ነውና ራስን ማግለል አዲስ የወረደ መዓት ልናደርገው አይገባም። እንዲያውም እኛ የግንኙነትና የልዩ ልዩ እውቀት ውጤቶች (ስልክ፣ ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ መብራት፣ ውሃ፣ መድሃኒት፣ የንጽህና ቁሳቁስ) ተጠቃሚ በመሆናችን ከወላጆቻችን የቀለለ ፈተና ነው ያለብን። እኛ ከወላጆቻችን የተሻለ ዕድል አለን እንበል እንጂ ከቀረው ከሰለጠነውና ከበለጸገው ዓለም ደግሞ ያነስን በመሆናችን የምናደርገው ሁሉ ከአቅማችንና ከዕውቀታችን ጋር የተገናዘበ ሊሆን ይገባል።

የኮሮና ቫይረስ የበለጸጉ ዓለማትን እያተራመሰ እኛ ዘንድ ቀለል ያለ መሆኑ ከዓለም ያለን የኝኙነት መጠን ውስንነት ያመጣው እንጂ ሌላ ምክንያት አይመስለኝም። በአንድም ሆነ በሌላ ስህተት፣ ንዝህላልነት በማህበረሰባችን ውስጥ መሃል ገብቶ ከተገኘ የሚያመጣውን መዓት ማሰብ አልፈልግም። በደረቅ የአየር ጸባይ ደን ውስጥ እሳት እንደመለኮስ ነው። የምናቆምበት አቅም ውስን ነው።ለዚህም ነው ሁሉንም ዓይነት ጥንቃቄ ከአሁኑ ማድረግ ያለብን። “ሞት ሲዘገይ የቀረ ይመስላል” እንደሚባለው የታማሚዎች ቁጥር ማነስ ሊያማልለን አይገባም። ከሁሉም በላይ ከወረርሽኙ ጋር ፊት ለፊት የሚጋፈጡት የህክምና ባለሙያዎች በቂ መከላከያ እንዲኖራቸው ማድረግ ተቀዳሚው ተግባር ሊሆን ያስፈልጋል። ምክንያቱም ህመምተኞችን የሚደርሱላቸው እነሱ ብቻ ከመሆናቸውም በላይ ለመሰራጨቱም ምቹ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከኮረና ቫይረስ ተጠቂዎች መካከል ብሶባቸው ልዩ ህክምና እንደሪስፓይራቶሪ ዓይነት መሳርያ የሚያስፈልጋቸው ጥቂቶች ከመሆናቸውም በላይ በተሟላ ህክምና እንኳ የሚተርፉት በእጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በአንድ ትልቅ የበለጸገ አገር ሆስፒታል ውስጥ የሚኖረው ልዩ ከፍተኛ የህክምና ክፍል (አይ ሲ ዩ) በጣም ጥቂት ነው። ለዚያውም ብዙ መሳርያዎች ያስፈልጉታል። አንድ ሪስፓይራቶር ብቻ ሩቭ ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣል። በዚህ አጭር ጊዜ ይህን አገራችን ማሟላት አይቻላትም። አሜሪካኖችም አልሆነላቸውም። ስለዚህም ትኩረታችን ብዙሃኑን ለማዳን በሚውሉ ቁሳቁሶችና በሽታው እንዳይሰራጭ በሚያግዙ ነገሮች ላይ ትኩረት ቢደረግ ውስን የሆነውን አቅማችንን በተገቢ ቦታ እንድናውል ያደርጋል። አንዳንድ የዲያስፖራ ሰዎች ሪስፓይራቶር ስለመግዛት ሲጨነቁ አያለሁ። ቁሱ ብቻ ሳይሆን ስልጠናውና የተለያዩ ነገሮች የሚያስፈልጉት መሆናቸውን ከዚያም በላይ ሊያተርፍ የሚችለውን የሰው መጠን ስንመለከት ለጊዜው አንገብጋቢ አድርጌ አላየውም። ከዚያ ይልቅ ሆስፒታሎች የኦክስጂን አቅርቦታቸው፣ የተለየ ማስታመምያ ቦታ፣ የጤና ባለሙያዎች መከላከያ፣ የግሉኮስና ልዩ ልዩ መድሃኒቶች እንዲሟሉ ማድረግ ተመራጭ ይሆናል።

ራስን ማግለል ወይም ኳራንቲን በከተማ ውስጥ ከባድ ይሆናል። ቢሆንም የድሮ የቀበሌ አወቃቀርን ለጊዜውም በመጠቀም ምግብና መሰረታዊ እርዳታ ለማቅረብ፣ መራራቁ ተግባራዊ መሆኑን ለመከታተል፣ ህመሙ በህብረተሰቡ መካከል ከተከሰተም ተገቢ እርምጃ ለመውሰድ መጠቀም ያስፈልጋል።

ራስን ማግለል በገጠር የህዝቡ አኗኗሩ ተራርቆ በመሆኑና አብዛኛውም የራሱን ምግብ በማምረቱ ቀላል ይሆናል። የሚከፋው መገናኛው ምቹ ባለመሆኑ ማሳወቁን ያከብደዋል። አሁንም የቀበሌ መዋቅርን መጠቀምና በዘመቻ ማስተማር ያስፈልጋል።

ሳይደግስ አይጣላም ( a blessing in disguise ) ይባላልና ህይወትን የማትረፍ ሳይሆን ሞትን የሚደግሱ “አክቲቪስቶች” እና ውሻ በሽንቱ ወሰኑን ከልሎ እንደሚናከስ “በክልሌ አትግባ” የሚሉ የጎጥ “የዘር” ፖለቲከኞችን ምንነት ጊዜው በሚገባ አሳይቶናል። ካልተባበርን ሞት የጋራ ጽዋችን መሆኑን ተገንዝበናል። ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማባላት ስራችን ባደረግንበት ሰዓት የሃይማኖት አባቶች ተገድደው አንድ ላይ ሆነው ለፈጣሪያቸው ምስጋና እንዲያቀርቡ ሆነዋል። ሰው በቋንቋው፣ በዕምነቱና በዞጉ ምክንያት እንዲገደል ያደረግንም፣ ሲገደል ዝም ያልንም፣ በቴሌቭዥን ያየንና በፌስቡክ ያሰራጨንም ቅጣቱን በጋራ እየተጎነጨን ነው። በዕያንዳንዳችን እጅ ላይ የንጹሃን ደም ፍንጣቂ አለ። የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን አሸዋ ውስጥ ራሷን እንደቀበረችው ሰጎን አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታችን የወንጀሉ ተሳታፊ ነበርን። የሰውን ህይወት ከማዳን የበለጠ ክቡር ስራ የለም። የሰውን ህይወት ከማጥፋትና ሲጠፋ ዝም ብሎ ከማየት የከበደ ወንጀልም የለም።

የኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመታደግ ያለበቂ መከላከያ በግንባር ለተሰለፋችሁ የጤና ባለሙያ የአገሬ ልጆች ከፍ ያለ ክብርና ኩራት አለኝ። አያቶቻችሁ አድዋ ላይ ከእነሱ በተሻለ የታጠቀና የተደራጀ ጠላትን ድል አድርገው በዓለም ፊት አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ታሪክ ሰርተዋልና እናንተም የእነሱን ገድል ትደግማላችሁ። ህይወት በማጥፋትና በማስጠፋት የሚታወቁበትና የገነኑበት ጊዜ እንደጉም ይበናል፣ እንደጤዛ ይተናል።

ይህም ያልፋል! ብዙ እንማርበት!

Comments — What do you think?