Home » ዜና » በአካል አየተራራቅን፡ በመንፈስ አየተቀራረብን የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ እንቋቋማለን!!

በአካል አየተራራቅን፡ በመንፈስ አየተቀራረብን የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ እንቋቋማለን!!

ጋዜጣዊ መግለጫ
ሚያዚያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ አሜሪካ
(ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት)

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE).

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE)

የኮቪድ-19 በሽታ በፍጥነት የአለም ሃገራትን እየወረረ ኢትዮጵያ መድረሱ ሲሰማ በውጭ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሌሎች ሃገራት ላይ ያስከተለውን ጉዳት በማየትና የሕዝባችንን የአኗኗር ባሕልና የኢኮኖሚ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በወገኖቻችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ እያሰብን በስጋትና በጭንቀት ተውጠናል።

ላለፉት ሰባት አመታት ዲያስፖራውን እያስተባበረ ለወገኖቹ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አለያንስ) የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን  አደጋ ለመከላከል የተጀመረውን አገር አቀፍ ዘመቻ ለማገዝ በድርጅቱ ፕሬዝዳንት በአርቲስትና አክቲቪስት  ታማኝ በየነ ቀስቃሽነት የጀመረው ዕርዳታ የማሰባሰብ ዘመቻ በዲያስፖራው ወደርየለሽ የአገርና የወገን ፍቅር በጥቂት ቀናት ውስጥ ከሰባት መቶ ዶላር በላይ በመድረሱ በዚህ አገር አድን ርብርቦሽ ለሚሳተፉ በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥልቅ የሆነ ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን።

ይህንን በአይን የማይታይ በእጅ የማይዳሰስ ረቂቅ አጥቂ በሽታ በሥጋትና በመጨነቅ ሳይሆን እውቀትን፤ ገንዘብን እና ጉልበትን አስተባብሮ በጥንቃቄና በጥበብ በተነደፈ ዕቅድ የሚመራ ዘመቻ በማድረግ ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል ቀደም ብለው ገፈቱን ከቀመሱት እና የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ከቻሉት ከቻይናና ከደቡብ ኮሪያ ልምድ መቅሰም ይጠቅማል።

ከዚህ አንፃር የአገራችን የጤና ባለሙያዎችና ወረርሺኙን ለመከላከል በግምባር ቀደምትነት የተሰለፉት ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ሁሉ የጀመሩትን የነፍስ-አድን ርብርቦሽ እያደነቅን፤ ሁላችንም በነፍስ-ወከፍ ራሳችንን እየጠበቅን፤ ለሌሎች እየተጠነቀቅን የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ታሪክ በመሰከረልን ኢትዮጵያዊ መተሳሰብና፤ በተባበረ ክንድ ይህንን ረቂቅ ጠላት የከፋ እልቂት ሳያደርስ ከአገራችን ለማባረር እንድንችል፤  በአገር ውስጥ የምትኖሩ ማንንም ሳትጠብቁ በራስ ተነሳሽነት በየሠፈሩ ከጎረቤቶቻችሁ ጋር እየተመካከራችሁ ባለሞያዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች እያንዳንዱ ቤተሰብ በትክክል ተግባራዊ ማድረጉን በመከታተል በበጎ ፈቃደኝበት እየተጋችሁ ላላቹሁ ውድ ወገኖቻችን እያመሰገንን፣ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንድንችል ማኅበረሰቡን በመቀስቀስና በማስተባበር እርስ በርስ በመተሳሰብ የደከመውን በመርዳት ይህንን የመከራ ጊዜ አብረን በመቆም እንድናሳልፈው ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን።

ከአገር ውጭ የምንኖረው ደግሞ የነፍስ-አድን አገልግሎት በመስጠት መስዋዕትነት የሚከፍሉት የጤና ባለሞያዎች ያለስጋት ተጠቂዎችን ለመንከባከብ የሚያስችሏቸውን ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችና በወረርሺኙ ምክንያት የሚፈጠሩ ሌሎች አንገብጋቢ እጥረቶችን ከዓለም ዙሪያ በማፈላለግ በፍጥነት እንዲደርስላቸው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በማቅረብ ወገኖቻችንን እንድንታደግ የጀመርነውን ዘመቻ አጠናክረን በትጋት እንድንቀጥል ግሎባል አለያንስ በአንክሮ ያሳስባል።

የመጀመሪያው የሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት በጥቂት ቀናት ውስጥ በዓብ ሜዲካል ማዕከልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትብብር ወደ አገር ቤት እንደሚደርስ እየገለፅን፣ ወረርሽኙ በአገር ውስጥ እየተስፋፋ ቢሄድ የሚያስፈልገውም እርዳታ በዚያው መጠን ሊጨምር ስለሚችል  ላልሰሙት በማሰማት የዲያስፖራው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ሕዝቡም ራሱን ከበሽታው ለመከላከል እንዲረዳው የተሰጡትን መመሪያዎች በመተግበር እንዲተጋ፤ መንግሥትም ተገቢው እርዳታና ድጋፍ በፍጥነትና በፍትሃዊነት እንዲከፋፈል በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ሁሉም የድርሻውን በብቃት ከተወጣ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቀነስ ብሎም በቁጥጥር ስር ለማዋል ስለሚቻል፤ በራስ የመተማመን የኢትዮጵያዊነት ወኔያችንን ታጥቀን በአካል እየተራራቅን በመንፈስ እየተቀራረብን፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር እና የቆየ የመረዳዳትና የመተባበር ባህላችንን በመተግበር ሁላችንንም ለማጥቃት የመጣብንን ጠላት በሁላችንም የተባበረ ኃይል ከአገራችን ለማባረር ቆርጠን ከተነሳን አብረን በመቆም ይህን የመከራ ጊዜ ለማሳለፍና የማይቀረውን ድል ለመቀዳጀት እንችላለን።

የኢትዮጵያ አምላክ ሕዝባችንን ይጠብቅልን!!

 

እርዳታዎን ለማድረግ:

https://www.gofundme.com/f/ethiopiansagainstcoronavirus

ለተጨማሪ መረጃዎችና የሚድያ ጥያቄዎች፡

ዳንኤል አርጋው

የህዝብ ግኑኝነት አስተባባሪ

877-477-2544

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት

One comment

  1. ከ700 በላይ የሚለው ከ 700 ሺህ ዶላር በላይ ተብሎ ተስተካክሎ ይነበብ

Comments — What do you think?