Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » በአንድ በረት ሁለት ኮርማ አያድርም (ይፍሩ ኃይሉ)

በአንድ በረት ሁለት ኮርማ አያድርም (ይፍሩ ኃይሉ)

በይፍሩ ኃይሉ
ኔው ሄቨን፤ ከነቲከት

PM Abiy Ahmed and Jawar Mohamed.

ለዛሬዋ ድርሰቴ “አንድ ባርያ ለሁለት ጌቶች አይገዛም” ብዬ ልሰይማት አቅጄ ጉዳዩን ጠለቅ ብዬ ስመልስከተው ቧጥጬ ከማልወጣው ጣጣ ውስጥ ይከተኝ ይሆናል አልኩና በረትና ከብቱን መረጥሁ፡፡”ወፍ እንዳገሯ ትጮሃለች”  ይባላልና፤ዞሬ፤ዞሬ፤ ከዚያዉ ተወልጄ፤ ድኬ፤ጥርሴን ነቅዬ ፤የመጀመሪያዎቹን አሥር ዓመታት በሳቅ በጫወታ ፈንድቄ ካደግሁበት አካክባቢ፤ልምድና ዘይቤ አልወጣሁም፡፡ብዙ ነገሮችን በዚህም፤በዚያም ብዬ፤ ከነዚያ ከመወዳቸው ያገሬ ልጆችና ወዳጅ ዘመዶች ጋራ አዛምደዋለሁ፡፡ የሚገርመው ልርሳህ እንኳ ብለው ጨርሶ አይረሳኝም፡፡የትላቱን አትጠይቁኝ እንጂ ከሃምሳ አመት በፊት የሰማህትንና ያየሁትን በትክክል መግለጥና ማስረዳት ማስረዳት እችላለሁ፡፡ ታዲያ ዛሬም ለአንባቢዎቼ ለማካፈል ላሰብኳት፤ወቅታዊም ከመሆኗም በላይ፤ቁም ነገርንም፤ዕውነትንም ይዛለች ብዬ አምናለሁ፡፡ የታሪኬ መጀመሪያም ሆነ ምጨረሻ ከዕውነተኛ ሰዎችና ቦታ ጋራ የተያያዘ በመሆኑ፤ ባለታሪኮቹ ዛሬ ምንም እንኳ በሕይወት ባይኖሩ፤ ልጆቻቸው፤የልጅ ልጆቻቸው፤ዘመዶቻቸው፤ ዛሬም በሕይወት ስለአሉ፤የቦታውንም ሆነ የባለታሪኮቹን ስም ላለምድለጽ እገደዳለሁ፡፡

ታሪኩ እንደዚህ ነዉ፡ በአንድ ነፋሻና ወይና አደጋ አካባቢ ሁለት ከባላባቶች የሚወለዱ፤ከአያት ከቅድመ አያት የወረሱትን እርስተ ጉልታቸውና የመልከኝነት መሬታቸዉን  እያሳረሱ፤የቀንድና የጋማ ከብት፤ ፍየልና በግ እያረቡ፤ነጭ ማኛ ጤፍና፤ማሽላናጨረቂት፤ሱፍና ሰሊጥ፤ስንዴና ግብሱን፤ ባቄላና ሽንብራዉ እያስመረቱ፤ እጅግ በጣም ተዝናንተው በተድላና በደስታ ተንቀባረው ይኖሩ ነበር፡፡ሲወርድ፤ሲዋረድ የመጣ፤ከያት ከቅድመአያት የወረሱትም ጀግነት በነሱም  ላይ ተላልፎ፤ እናት አገራቸውን በተለያየ የከፉ አጋጣሚዎች፤ ከአምስቱ የኢጣሊያ ወረራም በኋላ፤ በኮሪያም ጦርነት ሆነ በኦጋዴን ግጭት ያስመዘገቡት ድንቅ የጦር ሜዳ ዉሎ፤ ባላቸዉ ስመጥሩነትና ባለዝናነት በለይ የበለጠ ክብርና አድናቆትን እንዲያተርፉ አድርጓቸዉ ነበር፡፡ ከነዚህ ሁለት ድንቅ ባለዝናዎች ጋራ፤ በጋብቻም ይሁን በአበልጅነት፤ወይም በጡት ልጅነት ለመዛመድ የማይፈልግ አልንበረም፡፡ስማቸዉና ዝናቸው፤አገር አቋርጦ፤ወንዝ ተሻግሮ፤ ስንቱን ከያቅጣጫዉ ይጎተዉ እንደነበረ ዛሬም ቋሚ ያወራላቸዋል፡፡ “እነ አጅሬ! እነ አይደፈሬ!” በዚያዉም ልክ ጨዋነታቸውና ለጋስ ቸርነታቸውን ሁሉም ይመስክርላቸዉ ነበር፡፡”የታሰርን የሚያስፈቱ፤ የተቸገረን የሚረዱ፤ለክፉ ቀን ደራሾች ነበሩ፡፡” ይላቸዋል ያገራቸው ሰዉ ዛሬም በአክብሮትና በፍቅር፡፡ ታ ዲያ ምንደርጋል! አንደኛው ባላባት  ከሌላው ባላባት ዘምድ ጋራ በድንገት ተጋጨና የሰዉዬዉ ሕይወት በኢጁ አለፈበት፡፡በሁለት የአገር ባላና ምሰሶዎች መሃል  ታሪካቸው በማይደረቅ  የደም ቀለም መጻፍ ጀመረ፡፡

በሁለቱ ጀግኖች መሃል እልቂቱ ቀጠለ፡፡ ገዳይ ባላባት ሚስትና ልጆቹን በትኖ፤ ሃብትና ንብረቱን ትቶ፤የሞቀ ቤቱን ዘግቶ፤መዉዜሩን አንግቶ “ዱሩ ቤቴ!” አለ፡፡የሟች ወገኖችም፤ “እንኳን ዱር ገድል መግባት ይቅርና፤ከናትህ ሆድ ዉስጥ ተመልሰህም ብትገባ አዉጥተን ሥጋህን ለአሞራና ለጅብ እነስጠዋለን” ብለዉ ምለው ተገዝተዉ፤ባጭር ታጥቀዉ ተነሱ፡፡ እስከዛሬ ድረስ እጅግ በጣም የሚገርመኝ፤ በዚያ አካባቢ፤ስንት ቄስና መመኩሴ ባለብት አገር፤ስንት ጨዋ ሽምግሌ በተትረፈረፈብት አካባቢ፤ ማንም ደፍሮ ደም የተቃቡ ጠላቶችን፤ጠጋ ብሎ፤ነገሩን ለማብረድ የሚሞክርና ለማስታረቅ የሚቃጣ አንድም አይገኝም ነበር፡፡ሁሉም ቄስ መነኩሴ፤ጨዋ ሽማግሌ፤ “እንዴት ብለነዉ ደምህን እርሳ የምንለዉ! በራስ ላይ የማይወዱትን! ብሎ ሽሽቶ አርፎ ይቀመጣል፡፡ ግፋ ቢል፤ በዚያ አካባቢ ለዚህ ጥሩ መፍትሔ ነዉ ብለው የሚወስዱት እርምጃ፤ ገዳዩን፤ “መተላለቁ እንዳይቀጥል፤ ገዳይን “እባክን፤ አገር ጥለህ ወደ ዳር አገር ሄድህ፤ ተሰዉረህ ተቀመጥ፡፡” ማለት ብቻ ነበር፡፡ ባላመታደል የዚች አጭር አሳዛኝ ባለታሪክ ኝ መልሱ፤ “ማንን ፈርቼ ነዉ የትዉልድ አገሬን ለቅቄ ወዳር አገር የምሰደደዉ! ብሎ፤ አሻፎረኝ አለ፡፡ አሁን ትኩረቱ በሁለቱ አዛውንት ጀግ ኖች ላይ ብቻ አተኮረ፡፡ የሟች ወገን ባላባት፤ “በአንዲት  ትንሽ አካባቢ ዉስጥ ሁለት አለቃ ሊኖር ስለማይችል፤ ከእንግዲህ ይህ ጸብ በኔና በአንተ ብቻ ይወሰናል!” አለና እሱም ታጥቆ መነሳቱን ላከበት፡፡ይህን ሰዉዬ ከባላጋራው ለየት የሚያደርገው፤እስከአሁን የሰዉ ሕይወት በእጁ ስለአልጠፋ፤ በነጻነት እንደልቡ እየተዝናና፤ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ፤በየከተማው፤በየገበያው ዝናሩን አሳምሮ ፤ኮልቱን አገንድሮ፤ የተወለወለች ቤልጅጉን ይዞ፤ ሲጎማለል እንኳን ጠላቱን፤ ያየዉን ሁሉ ያስደነግጥ ነበር፡፡ እንዲያዉም ለባላጋራው፤” እንደአውሬ ከደን ዉስጥ ከምትሸጎጥና፤እንደ ሽኮኮ ከድንጋይ ዉስጥ፤ ተወትፈህ እየዋልክ፤ ማታ ጨለማ ለብስህ ወንድ ነኝ ከምትል፤ ቀን በቀን ግጠመኝ!” የሚል መልክት ላከበት፡፡አስተዉሉ! ለዚህ የሟች ወገን ሕግ በሱ በኩል ስለሆነ፤ነጭ ለባሹም፤ፖሊሱም የሱ ሰላይና ተባባሪ ነበረ፡፡ ተፈላጊው ሽፍታ ሳይወድ በግድ አቅሙን አመዛዝኖ፤ ጊዜና ቦታ እመረጠ ባለጋራውን መጠባበቅ ብቻ ጀመረ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፤ የሟች ወገን ባላባት ‘ይህንን ሽፍታ ከተደበቀበት ጉድጓድ ዉስጥ እንዴት እንድማወጣው እኔ አውቃለሁ ይልና፤ የሽፍታውን ሚስት ወዳጅነት ይይዛል፡፡ ይቺም ወሬ ሳትዉል ሳታድር ለባልጉዳዩ ከማንም ሳይሆን በሚስቱ አደበት ይነገረዋል፡፡ “ዕዉነትም ገና ዛሬ ሁለት ኮርማ በአንድ በረት ማደር አለመቻሉን ተረዳሁ!” ይልና ሚስቱን የሚመጣበትን ሰዓት ብቻ ንግሪኝ!ይላታል፤እሷም ቀንና ሰአት ትነግረዉና ይሄዳል፡፡ ሰዉዬውም እንደለመደዉ፤ አገር ጤና ብሎ ወደ አዲሷ ወዳጁ ቤት ይገባል፡፡ተዝናንቶ፤ትጥቁን ብቻ ሳይሆን ሱሪውንም ፈትቶ ልክ አልጋ ላይ ተኝቶ ሲዝናና ባለቤቷ ቤቱን በርግዶ ከፍቶ፤ አምስት የቃመ ቤልጅጉን አቀባብሎ በግ ንባሩ ላይ ይደቅንበታል፡፡

እግዚአብሔር ሲቆጣኝ ቀን ሲፈርድብኝ፤

ሱሪዬን ስፈታ ባልሽ መጣብኝ!”  ማለት ይህ ነው፡፡

”አሁን የምንግርህን ብቻ አዳምጥ፤ አይዞህ አልገድልህም! ግን ከኔ ደም ማፍሰስ የበለጠ የጎዳኽኝ አንተ ነህ፤ የኔ ጥፋት ከመቅጽበትና በድንገት ነዉ፡፡ ያንተ ገን አውጥተህ፤አውርደህ ያደረግኸው ድፍረት ንቀት ስለሆነ ሁለት ምርጫ እስጥሃለሁ፡፡ አሁን ከጆሮህ ወይም ከ___ምረጥ!” ይለዋል፡፡ምርጫዬ ይኸ ብቻ ከሆነ ጆሮዬን እደፈለግህ አድርግ፡፡” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ሰዉዬውም በምርጫዉ በጣም ተደስቶ’”መልካም ነው! ያየህ ሁሉ ጆሮህን  ምን ነካህ ሲልህ ዕዉንቱን ንገራቸዉ!” ይልና ቀኝ ጆሮውን ገሽልጦ የበረቱ ብቸኛ ኮርማ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ጆሮዉ የተቆረጠው ሰዉዬ ባለወገን ስለንበሩ አዲስ አበባ መጥተዉ፤ታክመዉ ድነዉ ዕድሜልካቸውን እንደ ቄስ ነጭ ሻሽ እንደጠመጠሙ ይኖሩ ነብር፡፡በይበልጥ የጎደለባቸው ግን እንደዚያ በየአደባባዩና በከተማው ኮልት እያገነደሩ፤ቤልጂኛ ዲሞትፈር እያሸከሙ፤ ከመጎማለል፤ በሰንጋ ፈረስና በሲናር በቅሎ እየተሽከረከሩ ከመኖር ተቆጥበው፤አንገታቸውን ፤አቀርቅረው መኖር ጀመሩ፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ የታላቅ ወንድማቸውን ልጅ እዚሁ ቨርጂኒያ አግኝቼ ስለ አዛዉንት አጎቷ አንስተን አንስተን ብዙዉን በመገረም እያስታወስን አወራን፡፡

ወዴት እያመራሁ ነው? እንደወንጭፍ ድንጋይ አራምባና ቆቦ ከመዝለሌ በፊት ወደ አቀድኩት ርዕስ ልግባ፡፡”አንድ ባሪያ ለሁለት ጌቶች አይገዛም ወይም ሁለት ኮርማ በ አንድ በረት አያድሩም” ብዬ የመረጥኳትን ይዤ እስኪ ወደ ዋናው ጉዳይ ላዝግም፡፡ ከሁሉ በፊት ግን “የፊት ምስጋና ፤ለኋላ ሃሜት ያስቸግራል” የምትለዋ የብልሆች አነጋገር ትያዝልኝ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ዶክተር አቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤በሚያስደንቅ ንግግራቸውና የሰውን ቀልብ በመሳብ ችሎታቸው ወዲያውኑ “እጅ ወደላይ!” ብለው ከተማረኩት በብዙ ሚሊዮን ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን መሃል አንዱ ነበርኩ፡፡ እኒህን አስገራሚ ግሩም ድንቅ ኢትዮጵያዊ ጉብል፤መልካም ቁመናን፤ ሰዉን በቅጽበት ከሚማርክ የአንደበት ለዛና ሌሎችን በቀላሉ የሚያሳምን የንግግር ችሎታ እንደዚህ የተሰጠው ማን አለ? ዐልኩ፡፡በረዥሙ የአገራችን አስደናቂ ታሪክ፤በዚህ በለጋ ዕድሜው፤ የአገሪቱን ሦስት ዋና ዋና ቁንቋዎችና የመላዉ አለም ሕዝብ መግባቢያ የሆነዉን የእንግሊዝኛ ቋንቋ አቀላጥፎ የሚናገር መሪ መቼ ኖሮን ያውቃል አልኩ፡፡ የአለምን ጂኦ ፖሊቲካና የጦር ኃይላቸውን አሰላለፍ፤ ባተማሩትና በሰለጠኑበት የጦር ትምህርትጠንቅቀው የሚያውቁ ብልህ መሪ ኢትዮጵያ ገና ዛሬ አገኘች አልኩ፡፡ሰዉዬዉ አማራም ኦሮሞም፤ክሪስቲያንም፤ሙስሊምም፤ኦርቶዶክስም ፕሮቴስታንትም፤ በደፈናው ሁሉንም ያሟሉ ግርኡም፤ድንቅ ኢትዮጵያዊ ከሳቸው በላይ ማን ሊመጥዐ! በጠቅላላዉ ዶክተር አቢይን ለመግለጽ የአልተጥዕቀምኩበት ቃለ አጋኖ! (Superlative) አልነበረም፡፡

ገና በትምህርት ቤት እያለሁ፤ እኔም ከሚጮሁ ጋራ አብሮ በመጮህ፤ ከተማሪዎች ንቅናቄ ዉስጥ ተነክሬ በመዳከር ላይ እያለሁ፤ የነጥርቅምቅሜ የደርግ መንግሥት በትግሉ ዉስጥ ዘሎ በመግባት፤ አገሪቷን ወደባሰ እልቂትና ብጥብጥ ዉስጥ ሲከታትና፤የልቂት ነጋሪቱን ሲጎስም፤ ከሚመስሉኝ አገር ወዳጆች ጋራ ቆሜ ደርግን መቃወም ጀመርኩ፡ እናንተ የጥይት ድምጽና የባሩድ ሽታ ያስከራችሁ ጠመንጃ አንጋጆች እባካችሁ ፖሊቲካዉን ለሚያቁ ልቀቁ፡፡በተናደዳችሁ ቁጥር ወጣቱንም የተኩስ መለማመጃ አታድርጉት .።” እያልኩ በምጽፍላቸዉ ደብዳቤ ክፉኛ ከጥርስ ዉስጥ ገበሁ፡፡ አባቴንም ቆሜ ለመቅበር ሳልበቃ ቀረሁ፡፡የማያልፍ ቀን የለምና ደርግ እንክትክቱ ሲወጣና ሥልጣኑን ወያኔ ከመንጋጋዉ ፈልቅቆ ሲወስድበትና በትረ መንግሥቱን ሲጨብጥ፤ እንደገና “ሀ” ብዬ ከወያኔ ጋራ ትንቅንቁን ተየያዝኩት፡፡ ይባስም ብዬ “የሚያልፍ ቀን “ በሚል ርዕስ አንዲት አጭር መጽሐፍ ጽፌ አሰራጨሁ፡፡ ወያኔን እጅግ አስቆጣችና “ኢትዮጵያን ደህና ሰብች በላት!’ የሚል ማስፈራሪያ ከየቦታዉ መጉረፍ ጀመረ፡፡ እንግዲህ ሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠዉን ሁሉ እየተቃወምሁ የምኖርም መሰለኝ፡፡ ታዲያ ዶክተር አቢይ ድንገት እንደመስቀል ወፍ ብቅ ሲሉና የተስፋ ጮራ ሲበትኑብን የተሰማኝ ደስታ ይህ ነዉ አይባልም ነበር፡፡አስተያዬቴንታዬንና ድጋፌንም በመግለጽ በተከታታይ በየማሕበራዊው ሜዲያው፤በቀጥታም ለራሳቸው ለዶከር አቢይ “ግልጽ ደብዳቤ” ጻፍሁ፡፡ ለዚህም ድጋፌና ልክየለሽ ደስታዬ ከአንዳንድ ጎጠኞችና አክራሪ ብሔረተኞች የተሰነዘረብኝን የስድብ ዉርጂብኝ እዚህ ላይ እንዲህ ነበር ብዬ ብደግመዉ እራሴን መልሼ መስደብ ይሆንብኛል ብዬ ትቹእዋለሁ፡ ለአሳየሁት ድጋፍና ተሰምቶኝ ለነበረው ደስታዬ ዛሬ  ጸጸት ገብቶኛል ማለቴ ግን በጭራሽ አይደለም፡፡ በወቅቱ ትክክል ነበርኩ ብዬ አምናለሁ፡፡የሚገርመዉ ዛሬም ያ ተስፋዬ ተሟጦ አላለቀም፡፡ ዶክተር አቢይን እስከመጨረሻዉ ድረስ እከተላችኋለሁ፤ ተዕግሥቴን አያስጨርሱኝም፡፡ በዚህ የጭንቀት ወቅት እሳቸዉን መቃወም ለኔ ያው ካለፉት ሁለት መንግሥታት ጋራ እንዳደርኩት፤ ዛሬም ያ የመቃወም ልምዱ አለቀቀኝም ማለት ይሆናል፡፡

የአማረበት ነገር ማስቀየሙ አይቀርምና፤ የዶተር አቢይም ያሁሉ “ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ እኔ አለሁላት! እኔ ደርስኩላት!” የሚለዉ በተስፋ የተሞላ አነጋገራቸዉ፤ ቀስ በቀስ እንደጉም እየተነነ መጥፋት ጀመረ፡፡ ላለፉት 27 አመታት ኢትዮጵያን ሃብቷን ዘርፎ፤ ሕዝቧን ቁምስቅሉን እያሳጣ፤ ሲገድለዉ፤ ሲያስረዉ፤ ለስደት ሲዳርገዉ፤ የቆየዉን የወያኔና አገር በቀሎች ወጀለኞችና ዘራፊዎች፤ ይዘው ለፍርድ ያቀርባሉ ስንል፤ እነሽፈራው ሽጉጤን፤ እነ አባ ዱላ ገመዳን፤ እነኃይለማርያም ደሳልኝን፤ እነ ዳዉድ ኢብሳን፤  አፍንጫቸው ስር አስቀምጠዉ እየሾሙ፤ እየሸለሙ፤ ወደ ትግራይ ጎራ አሉና “ወጀለኞቹን አስረክቡኝ !” አሉ፡፡ እንዶክተር ደብረጽዮን ምናቸው ሞኝ ነዉ! “ ይኸማ በዘር ላይ ያተኮረ ፍርደ ገምድልነት ነዉ!” እዚያ ከጉያህ ከኛ ባይበልጥ ከኛ እኩል ወንጀሉን የፈጸሙት እያሉ፤ እነሱን ሳትነካ ወደኛ ምን አሮጠህ? አሏቸው፡፡ ዶከትር አቢይ ጥላቸዉ የተገፈፈዉ ያነዕለት ነዉ ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ከዚያማ ምኑ ቅጡ! ችግሩም በተከታታይ በያለበት እንደ እንጉዳይ መፍላት ጀመረ፡፡ ትክክል ማስረጃና ከመግሥትም ሽፋንና መግለጫ ያልተሰጠው፤ የተዋቂዉ የኢንጂኔር ስመኘው በቀለ አሟሟትና፤በየአቅጣጫዉ በመቶ ሺህ የሚቆጠር፤ በተለይም የአማራው ሕዝብ መፈናቀል፤ የለገጣፎውና በቡራዩ የደረሰው  የሕዝብ በጭካኔ እልቂትና ብሎም ፈናቀል፤ በአዲስ አበባ ከተማ በፌደራል ወታደሮች ስለተጨፈጨፉት አምስት ወጣቶችና በሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባወጣቶች በግፍ ታስሮ መንገላታት፤በቂ ማስርጃ ባለማግኝቱ የሕዝቡን ቁጣ አጋለው፡፡

መቼ ይኸ ብቻ! ባለተገራው አንደበቱና ገደብ በሌለው ድፍረቱ፤የቄሮን መንጋና የኦነግን የታጠቀ ኃይል ከኋላና ከፊት ደጀንና ተገን አድርጎ፤ ጃዋር መሃመድ የተባለ አረህ አደግ፤ ”መደመጥና መሰማት ያለብኝ ብቸኛው አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ፡ የበርቱ ብቸኛ አለቃ እኔ ነኝ” አለ፡፡የኦነግ ያለትርገራ ወታደር፤እስከጥርሱ ድረስ ታጥቆ የምዕራብንና ደቡብ የኦሮሞን ክልል በመዳፉ ዉስጥ አስገብቶ፤በጠራራ ጸሐይ ባንክ መዝረፉን፤ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ የኦሮሞ ትዉልድ የሌላቸውን፤በተለይም የአማራ ተወላጅ የሆኑትን፤ በግፍ መግደልና ማፈናቀሉን ተያያዘዉ፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብም ንዴትና ቁጣ ሞልቶ ገነፈለ፡፡ ቁጣና ጩኸቱን በመሪውም፤በዶክተር አቢይ አሕመድላ ላይ ድምጹን ከፍ አድርጎ “ አንድ ይበሉን! እያለ ጮኸ፡፡ዶክተር አቢይ አሕመድም ከባለሟሎቻቸው ጋር መክረው፤ዘክረዉ፤ “ኦነግ ትጥቁን መፍታት አለበት!” ከሚል ዉሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡”ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም” ይባላልና፤ ሌላው ኮርማ አቶ ዳኡድ ኢብሣ፤በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ በተከራዩት  ከባለ አምስት ኮከብ ሆቴላቸው፤ከአማረ ሶፋ ላይ ተንጋለዉ፡(ተቀምጠው)” ሌሚሆኑ ማነው ቲጥቅ አስፈቺው! ማኒው ቲጥቅ ፈቺው?” አሉ፡፡ ይህንን ስንሰማ፤  በዕዉነቱ የሁላችንም ጥላ ነው የተገፈፈው፡፡ በርግጥ ዶክተር አቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበራቸዉ ላይ ተቀምጠው ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅድላቸዉን ሥልጣን በአግባቡ  እየተጠቀሙ ናቸወይ አልን፡፡ ከዚህም ሳናሰራራ፤ ልቡም፤ደንደሱም ያበጠበት፤የዘማንችን ሂትለር ጃዋር መሃመድ  ብቅ አለና፡”አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ;፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢትዮጵያ ሁለት መንግሥት አለ፡፡ አንደኛው በኔ የሚመራው የቄሮ መንግሥት ሲሆን፤ሌላው በዶክተር አቢይ የሚመራው የነፍጠኞች መንግሥት ነው፡፡ እኛ ቢንፈልግ ፊንፊኔን( አዲስ አበባን ማለቱ ነዉ) በሃያ አራት ሰእት ተቆጣጥረን፤ የዶከር አቢይን መንግሥት እንዲያበቃለት ማድረግ እንችላለን፡፡” እያለ ሲደነፋ፤አሁን ገና ይህ ዕብድ ዉሻ አለቀለት፤ ዶክተር አቢይ እጁን ጠምዝዘዉ ወደ ቂሊንጦ ይልኩታል ብለን በጉጉት ስንጠባብቅ” ቄሱም ዝም! መጽሐፉም ዝም!” ሆነ፡፡ ዶከተር አቢይ እንኳን እርምጃ ሊወስዱበት ይቅርና በተናገረዉም ላይ ማስተባብያ ወይም መግለጫ አልሰጡም፡፡ እንግዲህ እኒህ ያልታደሉ መሪያችን ባንድ በኩል የ ኦሮሞ አክራሪዎችና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚደትነት ሃላፊነታቸው፤ ለአገሪቷ የጠቅላይ ሚኒስተርነት ሥልጣን ጋራ እየተጋጨ ግራ የሚገምዳቸዉ ከሆነ፤ ከያዙት ሁለት ሥልጣን መሃል  አንዱን መምረጥ አለባቸዉ፡፡”ጃዋርና ቄሮ “በዚህ ዉጣ በዚህ ዉረድ!” እያሉ ግራ ሊገምዷቸዉ ሥልጣኑም፤ብቃቱም የላቸውም፡፡ ጃዋር በተከታታይ ለሚፈጽመዉ ወንጀል አንድም ቀን እንኳ ስሙን በአፋቸዉ ሙሉ ጠርተው “ለፈሰሰዉ ደምና ለደረሰዉ ጉዳት ሁሉ ተጠያቂ ነህ!” ብለዉት አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዉን የሚወዳቸውንና የሚያከብራቸውን ያህል፤ በሚያሳዩት ቆራጥነትና ድፍረት የጎደለው ከአንድ የሃገር መሪ የማይጠበቅ የወኔ ቢስነት ባሕሪ ግራ እየተጋባ ነዉ፡፡ ንዴቱም እያቃጠለዉ ነዉ፡፡

ጃዋር መሃመድ፤ በሱ ዕምነትና አገላለጽ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደሚሰማዉ፤ እንደሚያየዉና እንድሚታዘበዉ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ የታክስ ገንዘብ እየተከፈላቸዉ፤በሕዝብ ገንዘብ በጦር ስልት ስልጥነዉ፤ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀው; ጃዋር መሃንመድን አጅበዉ፤ አገፍ አገፍ ሲሉ ስንመለከት በዕዉነትም ዛሬ በአገሪቷ ዉስጥ ሁለት መሪዎች አሉ ለማለት ያስደፍራል፡፡ ጃዋር መሃመድ በአንዲት ቀጭን ተዕዛዝ፤ ለቄሮ ተከታዮቹ፤ ”ተከብቤአለሁና ድረሱልኝ!”ሲል፤ እልቆ መሳፍርት የሌለዉን የቄሮ መንጋ አንቀሳቅሶ ለ86 ንጹሃን ሕይወት ማለፍና ለብዙዎች የአካል መጎደልና በሚሊዮን ለሚቆጠር የሃብት ዉድመት፤ ለብዙ ቤተ ዕምነቶች መዉደምና መቃጠል ምክንያት ሲሆነ፤ ዶክተር አቢይ ያሳዩትን ተቃዉሞና እርምጃ፡ስንመለከት ምን ትርጉም እንስጠው? ፍርሃት ወይስ ተዕግሥት? ፍርሃት ከሆነ፤ ሠራዊቱ በጃቸዉ ስለሆነ ልክ ጃዋር ለቄሮ እንደሰጠዉ ተዕዛዝ፤ እሳቸዉም ሠራዊቱን ድረስልኝና እኔንም ሕዝቡንም አድን፤ አገሪቷን ተረከብ፡” ይበሉት፡፡ ትዕግሥትም ከሆነ፤ የሳቸዉ ተዕግሥት የሕዝብን ተዕግሥት እያስጨረሰ  መሆኑን እንዲያዉቁት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዶክተር አቢይን፤ዛሬም የሚያስታዉሳቸው፤ ገና ወደሥልጣን ሲመጡ የገቡለትን ቃልኪዳንና፤ በዚያ በጣፈጠ አደበታቸዉ ሊያጎናጽፉት የአቀዱትን ዲሞክራሲና፤ በአገሪቷ ላይ ስለሚያሰፍኑት ሰላምና የሕግ የበላነትን እያስታወሰ ነዉ፡፡ ሕዝባቸዉን ብዙ አሳዝነዉታል፤ ብዙ ቅር አሰኝተዉታል፡፡ የሚገርመዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም በሳቸው ተስፋ አልቆረጠምና፤ከ80 ሚሊዮን የሚበልጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ከጎናቸዉ ነዉና ለነ ጃዋርና ለመሰል ተከታዮቹ በመብርከክ እንዳያሳፍሩት አደራ እንላለን፡፡

ገና ወደ ሥልጣን ሲመጡ በጻፍኩላቸው ግልጽ ደብዳቤ ላይ አንድ ነጥብ ቁልጭ አድርጌ አስቀምጬ ነበር፡፡ይኸውም “ዶክተር አቢይ! የዛሬዉ ሽርጉድና፤ አይንፈስበዎት! ዘላቂና ዘለኣለማዊ እንዳይመስለዎት፡፡ አንድ ቀን ዕምነቱን ካጓደሉበትና ካዘንበዎት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ’አክ እንትፍ!፡” ይለዎታል፤ የተቀመጡበትንም ዙፋን የሾህ ወንበር ያደርግበዎታል፡፡ብዬ ጽፌ አስጠንቅቄ ነበር፡፡ምነዉ ተሳስቼ ቢሆን ኖሮ! በረንጆች አንድ አነጋገር አለ፤እንዲህ ይላል Once the toothpaste is out of the tube, it’s awfully difficult to put it back።” የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ጊዜ ዕምነቱ ከተጓደለበትና ፊቱን ካዞረ በኋላ፤ የዚህን የዋህ ሕዝብ  ዕምነት፤ ፍቅርና አክብሮት መልሶ ማግኝት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

የሚገርመዉ ዛሬም ሕዝቡ በመሪዉ ተስፋ አለዉ፡፡ ዶከተር አቢይ ሥራቸዉን በትክክልና በመሰላቸዉ መንገድ እንዳይመሩ የሚያደርጓቸዉ በብዙ እንቅፋቶችና መሰናክሎች ተከበዋል፡፡በግራም፤በቀኝም ከኋላም ከፊትም የከበባቸዉ የራሱን አጀንዳ ለማሟላት የሚፈልግ፤ ጎጠኛና የዘር ብሔርተኛ እንጂ፤ ሰፋ ያለዉን የናት አገር አጀንዳ  የሚያሳስበው/የሚመልከተዉ አይመስልም፡፡ በአንድ በኩል የኦሮሞዉ ተወካይ ይህን በዚህ አድርግ ሲል፤በሌላ በኩል የትግሬው፤ አይሞከርም! ይላል፡፡ ያንን አግባብቼ ወደ ደቡቡ ላተኩር ሲሉ፤አማራው በበኩሉ”የኔ ሳይሟላ ሌላው አይከጀልም ይላል፡፡ በነዚህ በሃሳብና በአስተሳሰብ አይን ለአይን ከማይተያዩ ተቃራኒ ኃይሎች መሃል ሆኖ ተቀፍድዶ የታሰረ እንደ ዶክተር አቢይ አሕመድ ያለ የለም ! የሚሉ ሞልተዋል፡፡

ዶክተር አቢይ በቅድሚያ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር  ሲሆኑ፤ በዚህም ላይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚደንት ናቸዉ፡፡እንግዲህ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒተር ሆኖ፤ በተጨማሪም የኦሮሞን ሕዝብ የቀን  ቅዥት የሚያሟላ ከኦሮሞም የመንገጠል ሕልም በላይ የአዲስ አበባ ከተማን ጠቅልሎ የኦሮሚያ ክልል የማድረግ ቅዠት ከሚያላጋው የነጃዋርን ፓርቲ በትክክለኛው መንገድና የአገሪቷ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደዉ ኢትዮጵያን እመራለሁ ማለት ዘበት ነዉ፡፡ አሁን በአገራችን  ዉስጥ ያሉን፤ በአንድ መዲና እየኖሩ አገሪቷን ለመምራት የሚሞክሩ ሁለት ኮርማዎች (ኃይሎች) ናቸዉ፡፡ ጃዋር የሚባለዉ ኮርማና የከበበዉ የኦነግና የቄሮ መንጋ” በሕግ አምላክ!” ካልተባሉና አንድ ዕርምጃ ካልተውሰደባቸው፤ ደም መፍሰሱ፤ክርስቲያን እንደ አውሬ እይታደነ መታረዱ፤ የቤተ ክርስቲያናት ቃጠሎው፤ የሕጻናትና፤የሴት ባልቴቶች፤ሽማግሌዎች እልቂት ይቀጥላል፡፡ ዶክተር አቢይ ሥልጣናቸውን ፤መቼ፤ የትና እንዴት እንደሚጠቀሙበትና የሃላፊነታቸውን ገደብና ቀደም ተከል ያወቁት አይመስለኝም፡፡ ዙሪያቸውን “ጸብ ያለሽ በዳቦ!”  እያለ የሚፍክርባቸው ጃዋርን አስቀምጠዉ ከአንድ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር “ጦርነት ዕገጥማለሁ” እያሉ ሲዝቱ እንዴት እንዳላፈሩ ይገርመኛል፡፡ እስክንድር ነጋ እኮ የስላም ሰዉና የሰባዊመብት ተሟጋችና አንድ ጋዜጠኛ እንጂ ፤እንደሳቸዉ በጦር ስልት የሰለጠነ ወታደር አይደለም፡፡ እስክንድር ነጋ በሕይወቱ ጥይት ተኩሶ፤ጠመንጃ ወይም ሽጉጥ ይዞ እንደማያውቅ በርግጠኛነት መናገር እችላለሁ፡፡ ዶከትር አቢይ፤ ጦርነትን እንዲህ የሚናፍቁ ከሆነ እነጌታቸዉ አሰፋ እኮ አስፍስፈዉ “ መጥተህ ሞክረን!” እያሉ እየጠበቋቸዉ ነዉ፡፡

አዬ የሰዉ ነገር! በሴኔ 15 ቀን፣ 2019 ዓም ያለቁት ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆችና የአማራው ሕዝብ አለኝታዎች፤የነጄነራል ሳእረ፤የነ ኢንጂኔር ስመኘው በቀለ ደም በግፍ ፈሶ በአግባቡ እንኳ ለሕዝብ መግለጫ ተስጥቶበት፤ ብሔራዊ የኃዝን  ቀን  በሥረአቱ አልሰጣቸዉም፡፡ አማሟታቸዉም እንድዚሁ በደፈናዉ” የመመፈንቅለ መንግሥት በተደረከዉ ሙከራ” ተብሎ ተድበስብሶ አለፈ፡፡ ደማቸው ግን ደመ ከልብ ሆኖ አይቀርምና፤ ዛሬም ያ በግፍ የፈሰሰ ደም  ወደ እግዚአብሔር  እየጮኸ ስለሆነ አንድ ቀን ሁሉን የሚችል አምላክ ይበቀለዋል፡፡ የሚገርመዉ ግን  ጣቶች ሁሉ የሚያመልከቱት ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ነው፡፡ ዕግዚአብሔር ይርዳን፡፡

 ዘረኝነት ጠፍቶ ኢትዮጵያ በክብርና በአንድነቷ ጸንታ ለዘለአለም ትኑር!!!

 

3 comments

  1. Excellent

Comments — What do you think?