Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ (በመስከረም አበራ)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ

PM Abiy Ahmed in the parliament.

ጠንካራ ነኝ ማለቱ ለበጎ ያልሆነው ህወሃት የማዕከላዊ መንግስቱን መዘወሩን ካቆመ ወዲህ የመጣው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከባት ኢትዮጵያ  በጉያ በጀርባዋ፣በእጅ በእግሯ፣በአፍ በሆዷ ውስብስብ ችግር አዝላ የምትጎተት ነች፡፡ይህ ችግር በድንገት በመጣው የዶ/ር አብይ መንግስት ቀርቶ በማኛውም እኔ ነኝ ባይ የምድር ጠቢብብ በአንድ አመት ውስጥ ሊፈታ አይችልም፡፡ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት እና ውዝፍነት የተነሳም ሆነ ከእርሳቸው ሰዋዊ ድክመት የተነሳ ችግር መፍታት ቢያቅታቸው እንኳን እሳቸው የሚያመጡት ተጨማሪ ችግር እንዳይኖር ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂነት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በመንግስታቸው አሰራር ላይ ጥያቄ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አላማው እሳቸውን ማጣጣል፣የጀመሩትን ጉዞ ማጨናገፍ፣ይበጃል ብለው እየሰሩ ያለውን ነገር ዋጋ ለማሳጣት ሊሆን አይችልም፡፡ይልቅስ ሃገራችን በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደመሆኗ መንግስታቸው በችግሩ አሳሳቢነት መጠን ያልተራመደ የሚመስለው ዜጋ ሊተቻቸው ይችላል፡፡ይህ አይነቱ ትችት የእሳቸውን ልፋት ገደል ለመክተት የተደረገ ክፉ ነገር አይደለም፡፡

እሳቸው ግን የሚቀርብባቸውን ትችት በበጎ ጎኑ የሚረዱት አልመሰለኝም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው ካሳዩት ሁኔታ የተረዳሁት የሃሳብ ልዩነትን እና የመንግስት ተጠያቂነትን እምብዛም እንደማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚፈትናቸው ነው፡፡የእርሳቸው ስሜታዊ መሆን ደግሞ የሚያጠፋው ብዙ ነው፡፡ወጣት መሪ መሆናቸው፣ሃገሪቱ ራስ አዟሪ ውስብስብ ችግር ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ወደስልጣን መምጣታቸው ተደማምሮ ብስጭታቸውን ሊያብሰው ይችላል፡፡ሆኖም መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ማሰቡ ለእራሳቸውም ለሃገራችንም በጎ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በግሌ ዶ/ር አብይ ውስብስብ ችግር ያዘለችውን ሃገር ሊመሩ መንበር ከጨበጡ ወዲህ ኢህአዴግ ውስጥም ኢትዮጵያ ትታየኛለች፡፡ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ በምጠረጥርበት ሃገር የማፍረስ ሴራ የዶ/ር አብይን ኢህአዴግ አልጠራጠውም፡፡ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ  ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ፡፡ህወሃት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ሲል ግን ስልጣኑን አጥብቆ እያሰረ እንደሆነ ብቻ እረዳ ነበር!ስለዚህ እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ከዶ/ር አብይ ጋር የሚያስማማው አንድ ጉዳይ አለ-የኢትዮጵያ ህልውና!

በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡ይህ መሰረታዊ አንድነት ሳይረሳ ጥፋት የጠፋ ሲመስለው የተቸ ቢያንስ ኢትዮጵያን በማለቱ ላይ ያለው ተመሳሳይ ምኞት ተረስቶ ለጥፋት የቆመ፣መተቸት ብቻ የሚያስደስተው፣የአሉባታ ሱስ ብቻ የሚያናገረው ተደርጎ በመንግስት ዘንድ የሚታሰብ ከሆነ ቀጣዩ ትዕይንት ጋዜጠኛን እና ተችን እያሳደዱ መሰር ነው የሚሆነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ በሰሞኑ የፓርላማ ውሏቸው ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ገሚሶቹ ስሜታዊ አድርገዋቸው ተችዎችን “እኛ የያዝነው እውነት ነውና ማሸነፋችን አይቀርም፤እናንተ ግን እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡ይህን ንግግራቸውን ስሰማ ዶ/ር አብይ ለትችት ያላቸውን ስስ ስሜት በደንብ ተረድቻለሁ፤ብዙ ነገርም ወደ ህሊናየ መጥቷል-ጭንቀት ጭምር! ዶ/ር አብይ የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲያገኛቸው ለፈጣሪ አሳልፈው የሰጧቸው ሚዲያዎች በውጭ ሃገር የሚገኙ፣በዩቱብ የሚሰራጩ እንደሆኑ አብረው ገልፀዋል፡፡ “ባህር ማዶ ስላላችሁ እኔ ምንም ላደርጋችሁ አልችልም” ሲሉም አክለዋል፡፡

አብይ በተችዎቻቸው ላይ የመለኮት ፍርድ እንድትመጣ የፈለጉት እነዚህ ሚዲያዎች ከእርሳቸው ግዛት ውጭ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡ይህ ንግግራቸው እና ብስጭታቸው ሚዲያዎቹ በአብይ ግዛት ቢሆኑስ ኖሮ ማስባሉ አይቀርም፡፡ከዚህመረዳት የሚቻለው ነገር በዶ/ር አብይ ግዛት ሆኖ መንግስታቸውን መተቸት እምብዛም እድሜ ያለው ፈለግ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡

ጠ/ሚው እያደር ስሜታዊነት እየታየባቸው መምጣቱ ሁለት አደጋ አዝሎ ይታየኛል፡፡ አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ ሁለተኛው በዶ/ር አብይ ዘንድ እየተተከለ የመጣ የተጠልቻለሁ ስጋት፡፡ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብይ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ሁለተኛው ችግር ሰውየው የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ያደርጋል፣ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ይቀንሳል፣በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ይህም ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ሊመራ የሚችል ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡

በበኩሌ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘቸው ሃገሬ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ ያለባት ተሰባሪ እቃ እየመሰለችኝ ከመጣች ዋል አደር ብያለሁ፡፡አሁን የቀድሞዋ የምትባለው ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ አንድ አመት በፊት የመፍረስ ምልክት ያልነበረባት መሆኗን የሰማሁ ነኝና “እንዴትም አድርገን ብንይዛት ኢትዮጵያ አትፈራርስም” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ ይልቅስ “ከአያያዝ ይቀደዳል” ባይ ነኝ! በተለይ የዘር ፖለቲካ የበላት ሃገር አትፈርስም ብሎ ከመተማመን ይልቅ ተቃራኒውን አስቦ አያያዙ ላይ ጠንክሮ መስራቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡አያያዙን ማሳመሩ የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም መንግስትን የሚዘውሩት ዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ አቋቋም ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

አብይ በቋፍ ያለችውን ሃገሬን በመሃል እጃቸው ይዘው የቆሙ ሰው ይመስሉኛል፤ሃገርን ያህክል ውድ ነገር እጃቸው ላይ ያስቀመጥንባቸውን ሰው በከንቱ ሊያስመርር ትችት ይዞ የሚመጣ አለመኖሩን ቢረዱ መልካም ነው፡፡እንዲህ ያለ ሰው አይጠፋም ከተባለም ነገሩን ንቆ የተሻለ ነገር ወደመስራቱ ማዘንበሉ ይመረጣል፡፡የጠሚው ስነ-ልቦናዊ ብርታት፣ የአስተሳሰብ ከፍታ፣እንደሚያወሩት የይቅርታ ሰውነት፣በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ነገር፣ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ቁርጠኝነት፣አለማዳላት፣የሚናገሩትን ሆኖ መገኘት በሃገሬ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነ አስባለሁ፡፡የተሳሳቱ ሲመስለኝ አካሄዳቸውን ብተችም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም እረዳለሁ፡፡በአንፃሩ ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይከለክላቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት፣ አለማድረግ ሲገባቸው ያደረጉት ነገር እንዳለም ይሰማኛል፡፡

ባፈው አንድ አመት የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚዲያቸውም ሆነ በጠመንጃቸው ያጠፉትን ጥፋት ሃይ አለማለታቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡ የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ ካድሬዎች የምስኪኖችን ቤት ያውም በክረምት እያፈረሱ ማባረራቸው እና እሳቸውም አልሰማሁም ማለታቸው ባያደርጉት ምንም የማይጎዳቸው ግን ወገባቸውን ታጥቀው የሰሩት ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ይህን ከባድ ጥፋት በሪፖርታቸው በአብዛኛው ሳይነኩት ከነኩትም አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡

በሰፊው እያነጋጋረ ያለው የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብሎ መሾምን በተመለከተ ሳይጠየቁ ራሳቸው አንስተውት “ኦሮሞ ያለአግባብ፣በማይገባው ሁኔታ ስልጣን ይዞ ከሆነ ከእኔ ጀምሮ ተጠያቂ እንደረግ” ብለዋል::መልሳቸው ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ኦሮሞ በዛ ብሎ ተሹሞ ከሆነም የሚገባውን ቦታ ነው የያዘው አይነት ሲሆን ሁለተኛው ኦሮሞ በዝቷል እየተባለ የሚባለው ነገር ከነአካቴው ውሸት ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡ አባባላቸው ኦሮሞ ብዙ ሆኖ መሾሙ ያለ አግባብ አይደለም ሲለሚገባው ነው የሚል ከሆነ የህወሃትን መጨረሻ እንዲያስቡ ከመምከር ውጭ ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡

ኦሮሞ ስልጣን ላይ በርከት ብሎ ተሹሟል የሚለው ነገር እውነት አይደለም የሚሉ ከሆነም በንግድ ባንክ የተሰገሰጉት፣በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ የበዙት፣በውትድርናው መስክም ቢሆን በስመ ምክትል ኢታማጆር ሹምነት ይዝ መምሪያዎችን ሁሉ ለጠቅልሎ መያዙን  አየር ሃይሉን፣የመከላከያ ሚኒስትርነቱን፣የሃገር ውስጥ ደህንነቱን፣የጠቅላይ አቃቤህግነቱን  ኦሮሞ የያዘ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምንም ችግር የለውም ብየ ስናገር መታመንን አገኛለሁ ብለው ከሆነ ይህ ከህዝብ የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ ነገር አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑትን አቶ ታከለ ዑማን የሾሙበት መንገድ ኦሮሞን ያለ አግባብ የመሾሙ ምልክት አይደለም ተብሎ ከሆነ የነገውን መፍራት ሊኖርብን ነው፡፡

በመንግስታዊ መዋቅሩ ላይ የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብለው ከመታየታቸው ባሻገር በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው እንደ ጃዋር ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚናገሩት፣የባሰባቸው ደግሞ በቪዲዮ ምስላቸውን እያሳዩ የሰው ህይወት እንሚያጠፉ የሚዝቱት እና ደግሞ ምንም የማይደረጉት፣ወደ ሃያ የሚጠጉ በንኮችን የዘረፈው የኦሮሞ ድርጅት ምንም አለመባሉ  ኦሮሞ ያለ አግባብ መብት እያገኘ ስላልሆነ ከሆነ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

የህገ-መንግስት መሻሻልን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱበት መንገድ አንድም ቅንነት በጎደለው ሁለትም የችግሩን አንገብጋቢነት በማይመጥን መልኩ የተመለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ጠ/ሚ አብይ መልሳቸውን የጀመሩት “ህገ-መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሰዎች ህገ-መንግስቱ ከሚሰጣቸው መብት  መጠቀማቸውን አልተውም” በሚል ንግግር ነው፡፡

በመጀመሪያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላ ህግ እንዲቀየርለት የሚጠይቅ አካል ጥያቄው ተሰምቶ ህጉ እስኪቀየር ድረስ ባለው ህግ የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ የማይፈልጉትን ህገ-መንግስት አክብረው መብቱንም የሚጠቀሙ ግዴታውንም የሚያደርጉ ሰዎች ሊመሰገኑ እንጅ ሊወቀሱ አይገባም፡፡አብይም መብትን ይጠቀማሉ ብለው ከሰሷቸው እንጅ ጠያቂዎቹ ህገመንግስቱ የጣለባቸውን ግዴታም እየተወጡ ነው፡፡ሁለተኛው እና ዋናው ነገር ህገመንግስቱ እንዲቀየር የሚጠይቁ ሰዎች ህገ-መንግሰቱ ሲረቀቅ አብረው ያላረቀቁ፣ባልተስማሙበት ህግ እንዲገዙ የተፈረደባቸው የዘር ፖለቲካው ባይትዋሮች  ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት አብይ እንደሚያስቡት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ከአማራ ክልል ህዝብ በተጨማሪ ህገ-መንግስቱ የማያውቃቸው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው፣ከሁለት እና በላይ ብሄሮች የሚወለዱ ሰዎች በአጠቃላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልተስማሙበት ህግ ይገዙ ዘንድ የሚጣልባቸው ዕዳ ከየት እንደመጣ ህገ-‘መንግስቱ ጫፉ አይነካ’ የሚሉ አካላት እንዲያስረዷቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው፡፡በተረፈ ‘ህገ-መንግስቱ እኔን እና ቤቴን ስለሚያረካ አናንተ እና ቤታችሁ እኛ ባወጣነው ህገ-መንግስት ትገዙ ዘንድ የተገባ ነው’ የሚሉ አካላትን እና  ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ውስጥ በአንዱ ንዑስ አንቀፅ ውስጥ እንኳን ፍላጎታቸውን እንዳያካትቱ የተፈረደባቸውን ዜጎች እኩል “ዋልታ ረገጥ” ብሎ መሰየም ቅንነት አይደለም፤ሚዛንንም ሰባራ ያደርጋል፡፡

ከሰሞኑ የሞት አጀብ አስከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ ጠ/ሚው ስሜታዊነታቸው በርትቶ፣እርግማናቸው በዝቶ አንድ ወገንን መልኣክ ሌላውን ሰይጣን የማድረግ መዛመም ታይቶባቸዋል፡፡ ወደ መልዓክት ወገን ሊያስጠጓቸው የከጀላቸውን፣በስም የጠሯቸውን ሟቾች(ዶ/ር አምባቸው እና ጀነራል ሰዓረን) የገደለውን  አካል እስከመግደል ያደረሰውን ምክንያት ሁሉ በፓርላማ ውሏቸው እንዲነግሩን አይጠበቅባቸውም፡፡ሆኖም ቢያንስ ገዳዮቹን ለዚህ እርምጃ ያበቃቸው አብይ የሚሉት ክፋት፣እርኩስነት፣ፍልቅልቅ ሰው ላይ የመጨከን እርኩሰት፣ያጎረሰ እጅን የመንከስ ውለታ ቢስነት ብቻ እንደማይሆን አውቆ ላልተኛ ሁሉ የሚሰወር ነገር አይደለም፡፡በአዴፓ መሪዎች መሃል ለተከሰተው መጋደል የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ማለትም የኢህአዴግን የፓርቲ ባህል አለማወቅ ነው፡፡

በተለይ አሁን አዴፓ ሆኛለሁ ያለው ብአዴን ለንጉስ የማጎንበስን የረዥም ዘመን ታሪክን ለሚያውቅ የገዳይ እውነት አብይ ከሚሉት እጅግ የተለየ ሌላ ሊሆን እንሚችል፤ፅድቃቸው በፌደራል መንግስት በጣም የተወራላቸው ሟቾችም መታዘዛቸው ፅድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር አይከፋም፡፡በተረፈ ገዳይ ተብሎ የተብጠለጠለው ቡድንም የራሱ ቤተሰብ፣ደጋፊ ያለው ለሃገርም ይበጃል ያለውን ሊሰራ የሞከረ በመሆኑ ቢያንስ ቀብሩ መዘገብ እንደነበረበት ለፍቅር እና ይቅርታ ሰባኪው ጠ/ሚ አብይ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በአንፃሩ በዓብይ መንግስት ድርጎ የሚሰፈርላቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሆኑ የአብይ መንግስት ፍቅር ያነሆለላቸው ወዶ ገባ የባሕር ማዶ ሚዲያዎች አስር ሰኮንድ ወስደው አብይ አምርረው የጠሏቸውን የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ቀብር መዘገብ አልፈለጉም፡፡ይህ የመረረ ጥላቻ አብይንም ሆነ ለአብይ መንግስት የሚያሸበሽቡ ሚዲያዎችን ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ድራማው ላይ ግድያውን የጀመረው ማን ነው? በዚህ ውስጥ የፌደራሉ መንግስት እጅስ የለበትም ወይ?የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል፡፡

 

 

4 comments

 1. ግራ የገባውና ለምንና እንዴት ብሎ የማይጠይቅ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሀገሩንና የዜግነት መብቱን ለማፍረስ ገዥዎቹን እያገዘ ያለ ህብረተሰብ

  መግቢያ
  አምላክ ስዎችን ሲፈጥር ለሁሉም እኩል መብትና ግዴታ ሰጥቶ ነው ወደዚህ አለም ያመጣቸው የሌላውን የአለም ክፍል ለጊዜው እንተውና የሀገራችንን ሁኔታ ብንመለከት ለምሳሌ ያህል ብቻ 50 አመታት የተፈጠሩትን ሁኔታዎች ብንመለከት በአንባገነንነት በላያችን ላይ የተቀመጡትን ብቻ ሳይሆን ስለእራሳችንም ሁኔታ መጠየቅ ይኖርብናል ለመሆኑ ገዥዎቻችን ሲቀያየሩብን አጨብጭበን ከመቀበል ያለፈ ለምንና እንዴት ብለን መጠየቅ የቻልን ስንቶች ነን? ይህ መጠየቅ ያለመቻላችን ውጤቱ ደግሞ በየዘመኑ ወደባሰ ቁልቁለት ውስጥ ይዞን እየወረደ ይገኛል

  በተፈጥሮ የተሰጠን ነጻነት ማለት ምን ማለት ነው

  ሁላችንም በአምላክ ፈቃድ ወደዚህ አለም ስንመጣ ከማንም ያነሰም ሆነ የበለጠ ሳይሆን እኩል መብትና ግዴታ ነው የተሰጠን ስለዚህ በፈቃደኝነት ከአምላክ የተሰጠንን ነጻነት አሳልፈን እንደኛው የሰው ፍጡር ለሆኑና ተደራጅተው በላያችን ላይ እራሳቸውን ጭነው ለሚቀመጡ ሃይሎች አጨብጭበን ከሰጠን ውጤታችን የሚሆነው አሳልፈን የሰጠነውን ተፈጥሮአዊ መብታችንን እነዚህ አምባገነን ሃይሎች እንደችሮታ ሲፈልጉ የሚሰጡን ሳይፈልጉ ደግሞ የሚነሱን ይሆናል ባለፉት 5 አስር አመታትና ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነው በመሬት ላይ ካለው ሁኔታ ደግሞ አሁንም ድረስ የገባን አንመስልም ዝም ብለን ነገሮችን እየደጋገምን እየቆዘምን ነው ያለነው

  ማንነት ሲባል ምን ማለት ነው?

  ማንኛውም ሰው አምላክ በአምሳሉ የፈጠረውና ወደዚህ አለም ሲመጣ ወይም ስትመጣ በተመሳሳይ ሁኔታ ማንነቱ የሰው ፍጡር ወንድ ወይም ሴት ነው ከዚህ ውጪ ምንም አይነት ነገር ይዞ አይፈጠርም ስለዚህ የሁላሽንም ማንነት በተመሳሳይ መንገድ ወደዚህ አለም እስከመጣን ድረስ ማንነታችን የሰው ዘር ነው እንጂ ሌላ ምንም ተቀጽላ ሊኖረን አይችልም
  ማናቸውም ነገር ለምሳሌ ቅዋንቅዋ ባህልና የመሳሰሉ ነገሮች ከኛ ቀደም ብለው የመጡ ሰዎች እርስ በእርስ ለመግባቢያና እንደህብረተሰብ የእለት ከእለት ኑሮአቸውን ለማከናወን የሚጠቀሙባቸው መገልገያዎች ናቸው እንጂ የማንነታችን መገለጫ ሊሆኑ አይችሉም ደግሞም አምላክ በራሱ አምሳል ሲፈጥረን ከሌሎች ፍጥረቶቹ በተለየ መልኩ የምናስብበትና በምድር ላይ ስንኖር ነገሮችን እያመዛዘንን ኑሮአችንን መምራት እንድንችል አእምሮን ሰጥቶናል
  በተለያየ የመልክአ ምድር አካባቢ የተፈጠሩ ሰዎች በተፈጥሮ እንደሰው የተሰጣቸውን አእምሮ በመጠቀም በየእለቱ ኑሮአቸውን ለመምራት እንዲቀላቸው የሚግባቡበትን ቅዋንቅዋ እያዳበሩ እንደህብረተሰብ ደግሞ አካባቢያቸው የሚገኙ ነገሮችን በመጠቀም ኑሮአቸውን እንዲያቀልላቸውና የዘወትር ህይወታቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ አየገፉ ሲሄዱ እንደባሀል እየቆጠሩት ይሄዳሉ ይህ ግን እንደሰው ለመኖር የሚጠቀሙበት ዘዴና መሳሪያ ሆኖ ከማገልገል ያለፈ የሰውነት ማንነታቸውን አይለውጥም ምክንያቱም አንድ ሰው እንደተወለደ ወላጆቹ ወደ ሌላ አካባቢ ይዘውት ቢሄዱና አዲስ ቦታ ላይ መኖር ቢጀምሩ አዲሱ ህጻን የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ የአዲሱን አካባቢ ቅዋንቅዋም ሆነ ባህል እያወቀ ያድጋል ወላጆቹም ደግሞ በአዲሱ አካባቢ ላይ መኖር ሲጀምሩ በቀላሉ እራሳቸውን ከአዲሱ አካባቢ ቅዋንቅዋና በህል ጋር አመሳስለው ኑሮአቸውን ይመራሉ ስለዚህ ማንኛውም ሰው እንደሰው በአምላክ ፈቃድ ከተፈጠረ በሁዋላ በየትኛውም የአለም ክፍል ቢዘዋወር አምላክ በተፈጥሮ የሰጠው አይምሮ ስላለው እራሱን በቀላሉ አላምዶ በየትኛውም ስፍራ ላይ እንደሌላው ሰው መኖር ይችላል እንጂ ቅዋንቅዋና ባህል የሱን የተፈጥሮ የሰው ዘርነት ሊለውጡበት አይችሉም

  ሀገር ነጻነትና ህዝብ

  በተለይ ባለፉት 3 አስር አመታት ማለትም በ TPLF የሚመራው EPRDF የ TPLF Manifesto የሆነውን ህገመንግስት በጉልበት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደመመሪያ ተደርጎ በማንአለብኝነት ሲጫን ከጥቂት ዜጎች በስተቀር አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የተፈጥሮ መብትንና የሀገር ዜግነት መብትን ባለመረዳትም ሆነ ወይም በፍርሃት በደርግ አገዛዝ ዘመን ግፍ ደረሰብኝ ሲል ከርሞ ለምንና እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ በድጋሚ TPLF በአናቱ ላይ ሲጫንበት ያለምንም ጥያቄ ተቀብሎ መኖር ጀመረ ይህ ደግሞ ብዙ ለተፈጥሮአዊ መብታቸው ለመቆም ምንግዜም ወደሁዋላ የማይሉ ዜጎችን የህይወት ዋጋ አስከፍሎአል በይፋ ያየነውና የሰማነው ነው የ TPLF/EPRDF ፖለቲከኞች ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቻቸው እራሳቸው በጻፉት ማኒፌስቶ “ህገመንግስት” ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ለማጥፋት ፌደራል አስተዳደር በሚል ሰበብ ሀገሪቱን በቅዋንቅዋ መልክአምድር ከፋፍለው የሰው ዘርነታችንን ነጥቀው ቅዋንቅዋን እንደዘር በእያንዳንዳችን ላይ ለጥፈው 9 የተለያዩ ሀገራትን ከመሰረቱ 28 አመት አለፈ እኛም ለምንና እንዴት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ የነሱ አጫፋሪ በመሆን ለመዋሸት ካልፈለግን በስተቀር እገዛ እያደረግን ቆይተናል አሁንም እያደረግን ቀጥለናል በዚህ ምክንያት ስቆቃው ከምንግዜውም በበለጠ ቀጥሎ ይገኛል በጣም የሚገርመው ደግሞ EPRDF ሀገሪቱን በቅዋንቅዋ በ 9 ሀገሮች መከፋፈሉ ሳይበቃው አማርኛ ቅዋንቅዋ ተናጋሪውን ህዝብ ሌላው 8ቱ ሀገር እንደጠላት እንዲቆጥረው በማድረግ ባለፉት 28 አመታት ይህ አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ኢላማ ተደርጎ ሲፈናቀል ሲገረፍ ገደል ሲወረወር ሲታረድና ሲገደል ቆይቶአል አሁንም ከመቼውም ግዜ በበለጠ መልኩ በደሉ ቀጥሎበታል የሰውነትና የዜግነት መብቱ ሙሉ በሙሉ ተገፎአል ማለት ይቻላል በተለይም ደግሞ ባለፈው 1 አመት እስከአሁኑ ሰከንድ ድረስ ይህ አትዮጵያዊ ህዝብ መከራው በየቀኑ እየተደራረበበት ነው ያለው
  ሁላችንም እንደምናውቀው በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2008 ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ህዝቡ በ TPLF/EPRDF ላይ የሚያደርገውን መራራ ትግል እየጨመረ በመምጣቱና TPLF/EPFDF የሰሩት ማለቂያ ያልነበረው ኢሰብአዊ ወንጀልና በስልጣን ላይ የመቆየታቸው ሁኔታ ስላሳሰባቸው ለየት ያለ እስትራተጄ ለመንደፍ ተገደው ነበር እናም ለዚህም ነው ሳይወዱ በግዳቸው የህዝቡን ማእበል ጋብ ለማድረግ እንዲረዳቸው ሲጠሉትና ሊያጠፉት ቀንና ሲተጉበት የነበረውን ኢትዮጵያዊነትን ህዝቡን ለማማለል ያመቻቸው ዘንድ ያላቸውም ምርጫ አንድና አንድ እሱ ብቻ መሆኑን በመረዳት በወሬና ዲስኩር ደረጃ የኢትዮጵያዊነትን መፈክር በማንሳት በመጀመሪያ TPLF ወደ ትግራይ ለ VACATION በመላክ EPRDF እራሱን 360 % አዙሮ ከ TPLF/EPRDF ወደ OPDO/EPRDF ለወጠ ይህን ድራማ ለመስራት የአፍ ቁጭበሉዎችን ማዘጋጀት ስለነበረበት አብይ አህመድ ለማ መገርሳ የሚባሉ 2 ቁጭ በሉዎች በስራቸው ብዙ የ EPRDF አባላትን አሰልፈው ድራማቸውን ከጀመሩ 1 አመት አለፈው ህዝቡም እንደተለመደው እንዴት ለምን ብሎ አልጠየቀም እንደገና እነዛው ለ27 አመታት ሲገሉት የነበሩ አካሎች የስም ቅደም ተከተል ብቻ ለውጠው ሲያማልሉት ኢትዮጵያ ሱሴ ስወለድ ኢትዮጵያዊ ስሞት ኢትዮጵያዊ ምናምን እያሉ ባዶ ቃል ብቻ ለፓለቲካ ትርፋቸው ሲሉ ስላወሩለት ከሀገር ውስጥ እስከውጭ ሀገር ሆ ብሎ አጨብጭቦ እንደገና ገዳዩን ተቀበለ በተለይ በዚህ ሰአት የነበረው አቀባበል የሚያሳየው ሰው በተፈጥሮ አምላክ የሰጠውን መብት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባው መሆኑና እንደውም አቢይ አህመድ የተባለውን ቁጭ በሉ እንደመልአክ የቆጠሩና እስካሁንም ድረስ ደንዝዘው የሚጉዋዙ እንዳሉ ተገንዝበናል ለምሳሌ አንድ ታዋቂ ነኝ የሚል ግለሰብ በአደባባይ ላይ ወጥቶ ነጻነቴን የሰጠኝና ቤተመንግስት ያስገባኝ አብይ ነው ሲል ሰምቼው በጣም አሳፍሮኛል እንዴት የሰው ልጅ አምላክ ሲፈጥረው እንደሌላው ሰው እኩል ነጻነት መብትና ግዴታን ሰጥቶ ፈጥሮት በገዛ ፍላጎቱ ለመጣው ሁሉ እያጨበጨበ ተፈጥሮአዊ መብቱን አሳልፎ በፍቃደኝነት እየሰጠ ሌላው ተቀያሪ ሲመጣ ደግሞ ነጻነቴን ሰጠኝ እያለ እድሜ ልኩን ይኖራል???
  ተቃዋሚ ነን ሲሉን የነበሩትም በግለሰብ ደረጃ በሀገር ውሰጥ እስር እንግልትና የህይወት ዋጋ ድረስ እስከመክፈል ለደረሱት አሁንም ያለን አክብሮት የተጠበቀ ሆኖ እንደድርጅት ግን ድሮም የስልጣን መሻት እንጂ የህዝብ አጀንዳ እንዳልነበራቸው አረጋግጠውልን እራሳቸውን በአንድ ጀንበር አፍርሰው አሁን ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ እያሉ በ TPLF MANIFSTO “ህገመንግስት” ስር ምርጫ እንወዳደራለን እያሉ ከአብይ ጋር ጭራቸውን እየቆሉ እንደገና ያላዝኑብናል እንደውም የአብይ መስካሪና ቃል አቀባያ እንደመሆንም ያደርጋቸዋል

  ለመሆኑ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች ወይ???

  እራሳችንን ለመዋሸት ካልሞከርን በስተቀር ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የቀድሞው TPLF/EPRDF ሆነ የአሁኑ OPDO/EPRDF የሚጠቀሙበት በ International ደረጃ ማንኛውንም አይነት እርዳታና ብድር በኢትዮጵያ ስም ለመቀበል ካልሆነ በስተቀር እንደሚታወቀው 9 መንግስታት ነው ያሉት እንደውም አሁን OPDO/EPRDF ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ኦሮሞ ብሎ እራሱን የሚጠራው ስብስብ ( ኦፒዲኦ ኦነግ አክራሪ እስላማዊ ኦነግ ማለትም ቀደም ሲል በአደባባይ አንገት አንገቱን በሜጫ እያልን ሲሉን የነበሩትንና ሌሎችንም የኦሮሞ ድርጅቶችን ጨምሮ) ደቡብ የሚባለውን መንግስት እያፈራረሱት እንደሆነ አይተናል ምናልባትም ምክንያቱ ከዛ አካባቢ ወደራሳቸው ለመጠቅለል የሚፈልጉት መሬት ይኖራል ኬኛዎቹ ሁሉንም የኛ ነው እያሉን ስለሆነ

  መረሳትና መዘንጋት የሌለበት ነገር ግን Vacation ላይ ያለው TPLF አሁንም ከ OPDO/EPRDF ጋር በተቀናጀ መልክ በስተጀርባ ሆኖ እንደሚሰራ አንዳንድ ማሳያዎች ይታያሉ በተለይም ደግሞ የአማርኛ ቅዋንቅዋ ተናጋሪው አካባቢ አዲስ አበባን ጨምሮ ለ OPDO/EPRDF እና ለ TPLF ዋና እና አሳሳቢ እንቅፋቶቹ ስለመሆናቸው ባለፉት 28 አመታትም ሆነ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰአት ከሚደረጉት ወቅታዊ ሁኔታዎች በደንብ የምንረዳ ይመስለኛል
  ለዚህም እንደምሳሌ የሚሆነው ”ህገመንግስት” በሚሉት የ TPLF MANIFESTO መሰረት ባደረገ እንኩዋን የአማራ ቅዋንቅዋ ተናጋሪውን እንደ ትግርኛና ኦሮምኛ ቅዋንቅዋ ተናጋሪው አካባቢ ተጠናክሮ እንዳይደራጅ በ EPRDF ተለጣፊ ተወካያቸው ብአዴን አማካኝነት ያሳለፍነውን 1 አመት ሲጎትቱት ከርመው በመጨረሻ ላይ አሁን ከ 2 ሳምንት በፊት በትንሹ እየተደራጀ መሆኑን ማሳየት ሲሞክር ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር ለተፈጸመው ድርጊት መነሻ ምክንያት በመሆን ከመቼውም ግዜ በበለጠ በወረራ መልክ በገዛ አካባቢው ላይ ተሰማርተው እያፈረሱትና ወጣቶችን ወደ እስር ቤት እያጋዙ ይገኛሉ እስሩ በተመሳሳይ መልክ በአዲስ አበባም እየተካሄደ ነው ይህ በግልጽ የሚያሳየው ለእነሱ እራስ ምታት የሆነባቸው ኢትዮጵያን ለሁሉም ለዜጎችዋ እንድትሆን እድርጎ ለመመለስና ካለፉት የ 28 አመታት የዘር ጉተታ ለታደግ የሚችለው የዚህ የአማርኛ ተናጋሪው አካባቢና የአዲስ አበባ ህዝብ ተደራጅቶ መነሳት ዋናው ሞተር መሆኑን ጠንቅቀው ስለገባቸው ነው

  የዚህ የአማርኛ ተናጋሪውና የአዲስ አበባ ህዝብ ተደራጅቶ ጎልብቶ መውጣት ደግሞ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ዜጎች የተለያየ ቅዋንቅዋ ተናጋሪ ሰዎችን ትግርኛና ኦሮምኛ ቅዋንቅዋ ተናጋሪ ዜጎችን ጨምሮ የትግሉ የአሸናፊነቱ አካል እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም
  ስለዚህ አሁንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብን የሚወክል የሀገር መከላከያ ፖሊስ የደህንነት ተቁዋም የለም ጥሩ ግለሰቦች በውስጡ ሊኖሩ ይችላሉ በተቁዋም ደረጃ ግን እነዚህ ተቁዋሞች ቀደም ሲል ለ TPLF/EPRDF አሁን ደግሞ ለ OPDO/EPRDF የሰሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን እየገደሉና እያሰቃዩ ያሉ ናቸው ህዝቡን አይወክሉም ስለዚህ በነዚህ ተቁዋማት ውስጥ አባል የሆኑ ንጹህ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለቀው በመውጣት ህዝብን መቀላቀል ይኖርባቸዋል

  ሌላው ኢትዮጵያዊ በአሁኑ ሰአት ሀገሪቱ የምትተዳደረው በቅዋንቅዋ የ TPLF MANIFESTO “ህገመንግስት” ስለሆነ እሾህን በእሾህ ነውና እንደእስትራተጂም በመጠቀም ወዶ ሳይሆን በመሬት ላይ ባለው የሀገሪቱ ሁኔታ አስገዳጅነት እራሱንና ኢትዮጵያን ለማዳን በአማራ ቅዋንቅዋ ተናጋሪነት እየተደራጀ ካለው ህዝብ ጋር ተናቦና ተባብሮ መስራት ሀገርን የማዳን አማራጭ የሌለው አንድና አንድ መፍትሄ ነው የአዲስ አበባም ህዝብ ከመጣበት አደጋ ለመከላከልና ለመውጣት ከዚህ ከአማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ጋር አብሮ ተናቦ መስራት ብቻ ነው

  በመጨረሻም እንደመደምደሚያ በማወቅም ሆን ባለማወቅ አሁን ለአለው የዘርና የጥላቻ ስርአት መጠቀሚያ ሆነው ህዝባቸውን ሲበድሉ የኖሩ ከህሊናቸው ጋር በመነጋገር ስርአቱን ለቀው ከህዝብ ጋር ሊቀላቀሉ ይገባል እስከመቼ ድረስ ሌሎች ዜጎች ወንድሞችና እህቶቻቸው ከሞቀ ቤታቸው እየተፈናቀሉና ከገዛ ሀገራቸው ላይ መጤና ወራሪ እየተባሉ ሲገፉ እያዩ የ EPRDF አገዛዝ የሚሰጣቸውን ገንዘብ እየተቀበሉ ሆዳቸውን እየሞሉ ይኖራሉ እንደ አምላክ ፍጡር ሰው ሆነው ማሰብ መጀመር ይገባቸዋል
  TPLF MANIFESTO “ህገመንግስትም” ሆነ EPRDF ነን ብለው ለ 28 አመት ሲገሉን የነበሩ 4 ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ከነግሳንግሶች ተቅዋሞቻቸው እስከመጨረሻው ላናያቸው መፍረስ አለባቸው ምክንያቱም ጸረ ሰብአዊነትና ጸረ ኢትዮጵያውያን ናቸው
  ኢትዮጵያ አምላክ ለእናቱ በቃል ኪዳን የሰጣት ሀገር ነች ስለዚህ ወደ አምላክ ጸሎት አድርገን ይቅርታን በመጠየቅ ከእንግዲህ በሁዋላ ማክበር የሚገባን ህግ ከሌላው አለም እየቀዱ የሚያመጡልንን ሳይሆን አምላክ በሙሴ አማካኝነት ጠቅለል አድርጎ የሰጠንን አስርቱ ቃላትን ነው አስርቱ ቃላት በዚህ አለም ላይ ስንኖር ማድረግና አለማድረግ የሚገቡንን በእያንዳንዱ ቃል ስር እንደመመሪያ በመተንተን አምላክ የሰጠንን ጸጋ ተጠቅመን ሌላውን በአግባቡ እያከበርን ተፋቅረን መኖር እንችላለን

  እግዚአብሄር የኢትዮጵያን ህዝብና ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

 2. I used to enjoy reading the article this lady writes but lately she has become adopting one sided view and lost her balance in favor of the Amhara extrimist view reflected by the ANM (ABEN) and the so called ethio 360 losers and by the way Tewodros Tsegaye her favorite jornalists. I see how she misinterprete the PM’s view on the diaspora based hate prechers as being his bad stance on jornalism in general and tried to portry him as an anti-free speach dictator. To critisize is one thing but to hate and propagate hatered is another thing so girl please come to your sense and write critical and constructive view from which others learn and progress. The way she try to indirectely attack ESAT is really unfortunate and led me to lose my trust on her and that is too bad.

 3. Meskerem,thank you for your opinion as usual. The real Abiy is coming out now from his hideouts. He is coming out from his disgusting disguise. Most of his latest explanation at the parliament is unpalatable and sugarcoated and with hidden agenda and double standard . Cursing by a leader of secular government is naive and not acceptable.May be he has ill-intention of winning the hearts and minds of religious Ethiopians. By the way Jesus prohibits cursing in his famous preach.

  Please fellas, let’s tell this PM to stop the non sense rhetoric and walk the talk as he initially promised

 4. His anger is uncontrollable since he is diagnosed with the high blood pressure that came from all the greasy kitfo he consumed in his life .

  High blood pressure is what most senior officials of EPRDF including Meles Zenawi suffered from due to their greedy hodam natures.

Comments — What do you think?