Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » የቆንጆዋ ልጅ ጸሎት! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የቆንጆዋ ልጅ ጸሎት! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ወላጆችዋ የልጃቸውን ወግ እና ማዕረግ በጉጉት ይጠብቁ ነበር። “የሰርግሽ ቀን…” እያሉ ስለሚጣለው ድንኳን፤ ለሙስሊም እና ለክርስቲያን ስለሚታረዱት በሬዎች ብዙ ተነጋግረዋል። እነዚያ ቀናቶች ግን እንደዋዛ አለፉ። እናም ቆንጆዋ ልጅ በቆመችበት ቀርታ… ለሚዜነት የታጩት ጓደኞቿ ግን፤ ገና ዱሮ አግብተው… ወልደው… ከተመነደጉ ቆዩ። ለአበባ ያዥነት ከተመረጡት ህጻናት መካከል ሁለቱ፤ አምና እና ካቻምና በተከታታይ አግብተዋል። ቆንጆዋ ልጅ ግን አሁንም ድረስ ሳታገባ እንዳለች አለች። እንኳንስ ወላጆችዋ ቀርተው በሰርጓ ላይ እንዲገኙ ሊጠሩ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች… ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።  በቤተሰብ ላይ በደረሰው ተከታታይ ሃዘን ምክንያት፤ ባል ሳታገባ ብዙ ቆየች። አሁን ግን ባል ማግባት ቢቀር፤ ፈጣሪዋ አንድ ልጅ እንዲሰጣት። አምርራ ተማጸነች።

ዳዊት ከበደ ወየሳ

ባለንበት ዘመን… ከእለታት ተከታታይ ቀናቶች… እንዲህ ሆነ። ቆንጆዋ ልጅ ተንበረከከችና ድምጿን ከፍ አድርጋ ለፈጣሪዋ ጸሎት አቀረበች።

“አምላኬ ሆይ! በቂ ገንዘብ አለኝና ‘ሃብት ስጠኝ’ አልልህም። ቤትም መሬትም ስላለኝ፤ የዚህ አለም ነገር ከንቱ ነውና ረዥም እድሜ አ’ለምንህም። ወንድ ሞልቶ በተረፈበት አለም ላይ ሆኜ፤ ባል ስጠኝ ብዬም አለምንህም። ነገር ግን… አንድ ልጅ ብትሰጠኝ።” አለችና ጸለየች።

ወትሮም በክፋት የተሞሉት ሰዎች ግን፤ ጸሎትዋን ሰምተው ተሳለቁ። “ደግሞ እሷን ብሎ ባለ ልጅ…” ብለው በመገረም ተሳሳቁባት።

በሚቀጥለውም ቀን፤ “ጌታ ሆይ! ምነው ሰቆቃዬን አበዛኸው? እንኳን እኔ ቀርቶ፤ እንደአምባሰል ዳመና የማትጨበጠው ጓደኛዬ ሳትቀር፤ የአንገቷን ድንብል በጥሳ… የወርቅ ሃብል አላጠለቀችምን? አምላኬ ሆይ ምነው እረሳኸኝ?” አለች።

አሁንም ጸሎትዋን የሰሙት የሰፈር ሰዎች… “እቺ ደሞ! መጸለይ አይሰለቻትም እንዴ? ለእግዜሩም ቢሆን ፋታ አልሰጠው አለች እኮ!” አሉና ተንሾካሾኩ።

የቆንጅየዋ ልጅ ጸሎት ግን አላበቃም። በሌላም ቀን ለጸሎት ተንበረከከች። “ልዑል የሰራዊት ጌታ… አምላኬ ሆይ! ለኔ የሚሆን ባል ብታጣ፤ ለኔ የሚሆን ልጅ ምነው ነሳኸኝ?” ብላ እንደራሄል ስቅስቅ ብላ ስታለቅስ፤ የእንባዋ ጩኸት፤ ወደ ኤሎሄነት ተቀይሮ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ተሰማ… እነሆን አንድ ልጅም ጸነሰች።

ቆንጆዋ ልጅ መጽነሷን ባወቀች ግዜ… የሆነውን ሁሉ ማመን አቅቷት፤ “እልልል” ብላ ፈጣሪዋን በይባቤ አመሰገነች። ቆንጅየዋን ልጅ የሚያውቋት ሁሉ መጽነሷን ሰምተው ሃሴት አደረጉ። ለሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናትም፤ የደስታ መግለጫዎች ከየአቅጣጫው መጣላት። ስጦታ በየአይነቱ የቤቷን በር እያንኳኳ፤ ከሁሉም አቅጣጫ ጎረፈላት። ቤተሰብ እና ጓደኛ፤ ጎረቤት እና የዳር አገር ሰዎች ጭምር፤ “እንኳን ደስ አለሽ” አሏት።

አገር ምድሩ በሆታ እና በእልልታ ደስታቸውን ሲያቀልጡት፤ “ስትወልጂ፤ እኔ አርስሻለሁ” ብለው፤ በልጅነት ያሳደጓት ሞግዚት፤ በስተርጅና ቤቷ ገቡ።

የቆንጅየዋ ልጅ ጸሎት እንዲሳካ፤ የማይፈልጉት ሰዎች ጭምር፤ ደንግጠው ዝም አሉ። ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ ቆንጅየዋ ልጅ የሚሄዱት ሰዎች እየበዙ ሲመጡ ግን፤ ዝም ያሉትም ሰዎች መናገር ጀመሩ። ለመጀመሪያ ግዜ አፍ አውጥተው… “እኛም መጥተን እንጠይቃት?” አሉና የመልካሞቹን ሰዎች የእግር ዳና ተከትለው፤ ወደ ቆንጆዋ ልጅ ሰፈር ተከታትለው ሄዱ።

የክፋት መልክተኞቹ… ቆንጅየዋ ልጅ ሰፈር ሲደርሱ፤ መጀመሪያ ግራና ቀኙን አማተሩ። ማንም የሚያውቃቸው ሰው እንደሌለ ሲረዱ፤ ወደ ቅጽር ግቢው፤ ፈራ ተባ እያሉ ጠጋ ብለው፤ በአጥሩ ቀዳዳ አሾልቀው ወደ ውስጥ አሻግረው አዩ። ከልካይ እንደሌለባቸው አረጋግጠው፤ ወደ ግቢው ገቡና በረንዳው አካባቢ አንዣበቡ።

በዚህ ግዜ ቆንጅየዋ ልጅ፤ ከቤት ወጥታ… “ወደ ቤት ግቡ እንጂ!” ብላ የፍቅር አቀባበል አደረገችላቸው። እጅ ነስተው ወደ ውስጥ ገቡና ወንበር ስበው ተቀመጡ። ትንሽ ቆይተው… አዲስ እንግዳ ሲመጣ የሚቀበሉት እነሱ ሆኑና አረፉት። ጨዋታ እየደራ ሲመጣ… “ከዚያ በኋላ…” ብሎ ቀጠለ፤ ከመጡት ሰዎች መካከል… ነገር አዋቂ የሚመስለው – ነገረኛ ሰውዬ።

“ከዚያ በኋላ… ወላጆቿ ሰርጓን ሊያደርጉላት አስበው፤ በሰርጉ አዘጋጆች መካከል ጭቅጭቅ ተነሳ። የጭቅጭቁ መነሻ ደግሞ… በሰርጉ ላይ የሚዘመረው  የሰርግ ህብረ ዝማሬ እና የሚሰቀለው ሰንደቅ አላማ ጉዳይ ነበር።”

“እንደዛ ነው ነገሩ?” በማለት ጠየቀ፤ ታሪኩን የማያውቅ ልጅ እግር ቢጤ – ልጅ።

“ይሄን አታውቅም ነበር እንዴ?” አለና ነገሩን በትንሽ እሳት ለኮሰውና ወሬውን ቀጠለ። “አየህ የጸቡ መንስዔ ሰንደቅ አላማው ሳይሆን፤ ከሰንደቅ አላማው ጀርባ የነበረው አላማ ነበር!” አለና ግራና ቀኙን ሲመለከት፤ ምራቁን ዋጥ ካደረገው ሰውዬ ጋር አይን ‘ላይን ተጋጩ።  ሰውዬው ረጋ ባለ መንፈስ መናገር ጀመረ።

“ከሰንደቁ ጀርባ ምንም የለም። አረንጓዴው ልማትን፣ ቢጫው ነጻነትን፣ ቀዩ መስዋትነትን ነው የሚያመለክተው!” ብሎ ዝም አለ። ሆኖም የሌሎች ክልሎች ባንዲራ ጉዳይ፤ ርዕስ ሆነና… ስለትርጉማቸው ሲወራ ክርክሩ እየናረ እየናረ ሄዶ፤ ቤቱ በብሄር ብሄረሰቦች ጫጫታ ተሞላና የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ ጠፋ።

በመጨረሻ… ቆንጅየዋ ልጅ፤ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ “ይሄ ጉዳይ ከኛ በፊት በነበሩ ሰዎች መካከል ክርክር ካስነሳ፤ እርስ በርስ ካለያየና ካጋደለ፤ ታሪክን በታሪክነቱ እናቆየው እንጂ፤ ወደ ኋላ እያየን… የምንሄድ ከሆነ፤ የሁላችንም መጨረሻ ተያይዘን ገደል መግባት ይሆናል።” አለች፤ በቀኝ እጇ ሆዷን ደገፍ አድርጋ።

አመሻሽ ላይ… ክርክሩ ለግዜው ቆመና ሁሉም ወደቀዬው እና ወደ የመንደሩ ተመለሰ። ሆኖም በየደረሱበት ጉሽምታና ሽኩቻው፤ ጉምጉታና ሹክሹክታው ተባብሶ ቀጠለ።

ምሽት ሲሆን ወጀብ እና ወጨፎ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ ብዙም ደስ አይልም። ሆኖም ቆንጅየዋ ልጅ፤ መስኮቱ ጋር ቆማ፤ ውጭውን አሻግራ እያየች እንጉርጉሮ ቢጤ ጀመረች። ሞግዚትየዋም ሞቅ ያለ ነገር ለማቅረብ ከምድጃው አጠገብ ተፍ ተፍ እያሉ ነው። ቆንጆዋ ልጅ ጎንበስ አለችና ለጸነሰችው ልጅ አንጎራጎረች።

“ኧረ ዘራፍ፣ ኧረ ዘራፍ፣ ኧረ ዘራፍ፤

የኛ ዲሞክራሲ፣ በጸሎት ተረግዞ፤

 (ኧረ ዘ.ራ..ፍ፣ ኧረ ዘራፍ!)”

ሞግዚቷ…. ባዶ ጥርሳቸውን ማሳየት የፈለጉ ይመስል፤ ሳቅ አሉና፤ “ቤት መድፊያ የሌለው እንጉርጉሮ!?” ብለው በስላቅ ሳቁ።

“ግጥሙ ጠፍቶብኝ ነው” ቆንጅየዋም ልጅ ፈገግ አለች።

ሞግዚቷ ጉሮሯቸውን ጠራርገው “እንዲህ ነው እንጉርጉሮው” አሉና ማንጎራጎር ጀመሩ።

“እሹሩሩ ልጄ እሹሩሩ፣ ልጄ እሹሩሩ…

ለብዙ አመታት፣ (እህ) አንተን ተሽክሜ (እህ)፤

እባክህን ውረድ፣ (እህ) አልቻለም አቅሜ። (እህ)… እሹሩሩሩ ልጄ እሹሩሩ” አሉና አሮጊቷ እንደገና ፈገግ አሉ።

ቆንጅየዋ ልጅ፤ ያሞጠሞጠ ሆዷን ደገፍ አድርጋ… “እህ… ፖለቲካማ ጥሩ አይደለም።” ከማለቷ…

“ኡኡቴ! ቦለቲካውን ማን ጀመረውና…” ብለው ገራገሩን እያወሩ፤ ወጋቸውን የውጭው መብረቅ እና ነጎድጓድ እየዋጠና እያጀበው፤ ከጨረቃ በታች በጨለማው ቤታቸው ውስጥ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰዳቸው።

ቆንጅየዋን ልጅ ጠዋት የቀሰቀሳት፤ ሁካታ እና ጫጫታ ሳይሆን… ፊቷ ላይ የተረጨው የጠዋት ጨረር ነበር። እንቅልፏን የጨረሰች ቢመስላትም፤ ድንገት የተሰማት የማቅለሽለሽ ስሜት፤ ወደ መታጠቢያ ቤት እስከምትሄድ አላቆያትም። ሞግዚቷ እስከምትመጣ ድረስ ወደ ላይ ይንጣት ጀመር።

ሞግዚቷ “አይዞሽ ልጄ! ፅንጹ ጸጉር እያበቀለ ነው ማለት ነው…” ሲሏት፤ ህመሟ ወደ ሳቅ ተቀየረ።

ቢሆንም… ከዚያን ቀን ጀምሮ፤ ቆንጅየዋ ልጅ ጥሩ አልሰማት አለ። እያንዳንዱ ቀን ለሷ የህመም ቀን ሆነባት። አንድ ቀን ጭንቅ ብሏት፤ “ሁሉም ልጅ ግን፤ እንደዚህ ነው እንዴ የተወለደው?” ስትል ሞግዚቷ ባዶ ጥርሳቸውን ብልጭ አደረጉላት።

የቆንጅየዋ ልጅ ህመም፤ ከጠዋት ማቅለሽለሽ ወደ ውጋት እና ወደ ለየለት ጭንቀት ተቀየረ። እያንዳንዱ ቀን የመከራ ቀን ሆነባት።

አንድ ቀን… ባህላዊ የቡና ተርቲም ተተርትሞ ሳለ፤ “አይ ፈጣሪ… ስቃዩ እንዲህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ፤ ልጅ ስጠኝ ብዬ አላስቸግህም ነበር።” አለች ቆንጆዋ ልጅ – የ’ውነት ምርር ብሏት።

“አየሽ ልጄ… ማማረር አያስፈልግም።” ብለው በቡናው ጭስ መሃል፤ ከሰሉ ላይ እጣን ጨመሩበትና ማጽናናታቸውን ቀጠሉ።

በዚህ መሃል… ቡና አጣጭ ጎረቤታቸው አፏን በነጠላ ሸፈን አድርጋ፤ “ጆሮ መቼም ለባለቤቱ ባዳ ነው ” እያለች ገባች።

“ምን ተፈጠረ?” የሞግዚቷ ጥያቄ ነበር።

“አልሰማችሁም እንዴ?” ጎረቤትየዋ ነገሩን አጋነነችው።

“ምኑን?” ሁለቱም ጠየቁ።

“እነዛ ነገረ ሰሪዎች ተሰብስበው እየዶለቱ ነው እኮ!”

“ምን እያሉ?” ሁለቱም በመገረም ጠየቁ።

“አይይይ… እውነትም ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው። እነሱማ የሚሉት… ‘ አንደኛ ሳታገባ ለምን ጸነሰች?’ አሉ። በዚህ ቢያበቁ ጥሩ ነበር። በዚያ ላይ ‘የልጁ አባት ማነው?’ የሚል ጥያቄ አስከተሉ። ሶስተኛ…”  ብላ ልትቀጥል ስትል የቆንጅየዋ ልጅ ፊት ተለዋወጠ።

ቆንጆዋ ልጅ፤ መናገር ፈለገችና ጉሮሮርዋ ጋር ንዴት እና እልህ ተናነቃት።

ሞግዚቷ ፈጠን ብለው፤ “ኧረ ለመሆኑ… ማንስ ይሁን ማን ምን አገባቸው?” በማለት ወሬውን ለመቀየር ሲሞክሩ፤ ጎረቤትየው ዋናውን ጉዳይ ፍርጥ አደረገችላቸው።

“መች በዚህ ብቻ አበቁ? ‘የሚወለደው ልጅ… ብሄሩ መታወቅ አለበት’ ብለዋል። አባትየውም ቢሆን… የዚህ ክልል ሰው ካልሆነ ልጁ ሊወለድ አይገባም። ተባባሪ በመሆን ያዋለደ፤ ሆስፒታል የወሰደ፤ የጠየቀ ጭምር ወየውለት!’ ብለዋል።” አለችና የለሰችውን ነጠላ፣ እያጣፋች ማስተካከል ጀመረች።

“ወይ ጉድ… ‘ልጁ ተጸነሰ’ ሲባል፤ እንደዚያ ሆ ሆ ሆ እንዳልተባለ… ሁሉም ነገር ወረት ሆኖ ቀረ ማለት ነው? እኮ ደግሞስ ምን አገባቸው? ማን አማላጅ፣ ማን አዋላጅ፤ ማንስ ዜግነት ሰጪ አደረጋቸው?” አሉ ሞግዚትየዋ። ቆንጆዋ ልጅ መናገር እየፈለገች መናገር አቅቷት፤ ህመሟን ችላ… እንደምንም ብድግ ብላ ወደ መታጠቢያው ክፍል ስትሄድ፤ ጎረቤትየዋ ሹክሹክታ በሚመስል ድምጽ…

“እሷም ብትሆን የምትኖርበትን አገር መምረጥ አለባት” አለች።

ሞግዚቷ ውጪ ያሉ ሰዎች እንዲሰሙ ጭምር፤ ፊታቸውን ወደ ደጅ አዙረውና ጮክ ብለው፤ “የማንም ሰው አገሩ፤ ራሱንና ልጁን የወለደበት ቦታ ነው። ወላጆቿ ዘር እና ብሄር ሳይጠያየቁ፤ ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት… ልጃቸውን ደግሞ በስጋና ደም ስለወለዱ፤ አገራቸው እዚህ ሆነ። ‘ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች’ እንደተባለው፤ መንግስት እስካለ ድረስ፤ የማንም ሰው አገሩ… ራሱን የወለደበት ወይም ልጁን የወለደበት ቦታ ነው።”

ጎረቤትየዋ፤ ‘አልገባኝም!’ በሚል የግዴለሽነት ስሜት፤ ትከሻና አንገቷን ደሰቅ ሰበቅ አድርጋ ዝም አለች።

ቆንጅየዋ ልጅ ወደ መታጠቢያ ክፍል ገባችና፤ ሆዷን ደገፍ አድርጋ… ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች፤ “አምላኬ ሆይ! ምን በደልኩህ? ምነው ስቃዬን አበዛኸው? ምነው ሳይጸነስ ቢቀርስ? በምን ቀን ነው ‘ልጅ ስጠኝ’ ብዬ የለመንኩህ? ከዚህ ስቃይ፤ ምናለበት ጽንሱ ውሃ ሆኖ ቢቀር?” አለች። አምርራ ከመጮዃ የተነሳ፤ ጎረቤትየዋ ጭምር ሰምታ፤ በማስተዛዘን አይነት እንዲህ አለች።

“እውነቷን ነው። አዎ ምነው ቢቀርስ?” አለችና፤ ምክር በመስጠት አይነት “ለሁሉም ነገር… መፍትሄ አለው እኮ። ከዚህ ሁሉ ስቃይ… ምናለበት ጽንሱን ብታስወርደው?” ብላ ምክረ ነገር ለገሰች።

ሞግዚቷ ቱግ ብለው፤ “ይኸው እኮ ነው የኛ ነገር! ድሮ ልጁ ራሱ ‘አልወለድም’ ይል ነበር አሉ። አሁን ደሞ ግዜው ተቀይሮ አላስወልድም አላቹህ…” ብለው ከመጀመራቸው… ጎረቤትየዋ “እኔ ም’ናረኩ? እኔን ለቀቅ አድርጉኝ።” እንደማለት ብላ በገባችበት በር፤ ሹክክ ሹልክ ብላ ወጣች። የሞግዚቷ ቁጣ እና ንግግር፤ የጎረቤትዋን እግር ተከትሎ ውጪ ድረስ ተሰማ።

ውጪ የነበሩ ሰዎች የሞግዚቷን ጩኸት በጨረፍታ ሰሙ። የቆንጆዋ ልጅ የምሬት ጸሎት ግን… ገና አልተሰማም። ነገረ ሰሪዎቹም በዚህ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ስብሰባ አድርገዋል። “ጽንሱን በማጨናገፍ እና በሌሎች ተመሳሳይ አጀንዳዎች ላይ መነጋገራቸውን፤ የያዙት ቃለ ጉባኤ ያሳያል። ሁሉም በየደረሰበት በየራሱ መንገድ መሄዱን ቀጥሏል። ሞግዚቷ ጭምር… ትክዝ ብለው የማይወዱትን እንጉርጉሮ ማንጎራጎር ጀመሩ።

“ኧረ ዘራፍ፣ ኧረ ዘራፍ፣ ኧረ ዘራፍ፤

የኛ ዲሞክራሲ፣ ያልተወለደው፤ … የኛ ዲሞክራሲ፣ ያልተወደደው…” አሉና… ለግጥሙ ቤት መድፊያ ከሰማይ የሚወርድላቸው ይመስል፤ አይናቸው እንባ እንዳቀረረ ወደ ላይ አንጋጠው ብዙ ቆዩ።

በሚቀጥለው ቀን… ቆንጆዋን ልጅ እያስታመሙ፣ ከጎኗ ቁጭ ብለው፤ ከንፈራቸውን መጥጠው “አየሽ የኛ ነገር እንደዚህ ነው።” ብለው በወቀሳ የተለወሰ ጨዋታ ጀመሩና “ግዴለም ይሄም ያልፋል” ብለው ምክረ ወጋቸውን ጨረሱ።  ህይወት ግን በማያቋርጥ ሂደት ላይ ናት… የቆንጆዋም ልጅ ጸሎትና ፈተና ገና አላበቃም።

Comments — What do you think?