Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » ልክ የሌለው የፖለቲካ ትኩሳት መዋዠቅ (ጠገናው ጎሹ)

ልክ የሌለው የፖለቲካ ትኩሳት መዋዠቅ (ጠገናው ጎሹ)

ጠገናው ጎሹ

እንደ መግቢያ

የሰው ልጅ ጤንነቱ ከመታወክ አልፎ ህልፈተ ህይወት ሊያጋጥመው የሚችል መሆኑን ከሚያመለክቱ ምልክቶች አንዱ የሰውነት የሙቀት መጠን ክፉኛ ሲዋዥቅና እያደር ከመሻል ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ሲመጣ ነው ።የእንዲህ አይነቱን የአደገኛ ህመም ምልክት ትክክለኛ  ምንጩን (ምክንያቱን) አውቆ በጊዜ  የሚበጀውን ማድረግ  አለመቻል ሞትን ቁጭ ብሎ መጠበቅ ማለት ነው።   ጊዜን ተሻምተው ከተጠቀሙበት ጨርሶ  ከመውደቅት (ከሞት) ይታደጋል ።  ከተንቀራፈፉበት ግን  እየጨፈላለቀ ያልፋል ። መቆም ይቅርና እያዘገሙ መጠበቅ ጨርሶ የጊዜ  ተፈጥሮና ባህሪ  አይደለም ። ጊዜን ለውጤታማ ሥራ ካልተጠቀሙበት ደግሞ  በራሱ ትርጉም አይኖረውም። ምክንያቱም ትናንት ዛሬ አይደለም ፧ ዛሬም ነገ አይሆንም ፧ ነገም ዛሬ  ሊሆን አይችልም ።

የትናንት ስኬትንና ውድቀትን በጥሞና እና በቅንነት  ተረድቶና ገምግሞ ዛሬን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግና ነገን ደግሞ በላቀ ስኬት ለመቀበል  ዝግጁ መሆን ሲቻለን ብቻ ነው የትክክለኛ ለውጥ ባለቤቶች መሆናችንን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ። ይህ ሲባል ለጊዜው ከሚኖረን አቅም በላይ ሆነው በሂደት ተፈፃሚ የሚሆኑ ፈታኝ ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም ። ይህ እንኳን እንደ እኛ በሁለንተናው ወደ ኋላ ለቀረ ማህበረሰብ በአንፃራዊነት  አደገ በሚባል ማህበረሰብም የሚያጋጥም የገሃዱ ዓለም  እውነታ ነው።

መሠራት  ያለባቸውንና መሥራት የምንችላቸውን ሥራዎች በጊዜው ለመሥራት (ለማከናወን) ተስኖን ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር  አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ከቀውስ ለመውጣትና ሌላ ቀውስ እንዳይፈጠር  አስቀደሞ ለመከላከል ጥረት ከማድረግ  ይልቅ   ከቀውስ ላይ ቀውስ እየደረቡ “በለውጥ ሂደት የሚያጋጥም ነው፧ ለዓመታት የተቆለለና የተወሳሰበ ችግር በአንድ ሌሊት አይፈታም ፧ ወዘተ” የሚሉ እጅግ ደምሳሳና ልፍስፍስ ሰበቦችን በተዋቡ ቃላትና በሰላ አንደበት መደርደሩ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም።

በዚህ  የተልካሻ  ሰበብ ድርደራ ላይ የጎሳ/የዘውግ እና ልክ የሌለው የግልና የቡድን ፍላጎትን የማሳደድ ባህሪና ሸፍጥ ሲጨመርበት የሚያስከትለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መሬት ላይ እየሆነ ካለው  መሪር ሃቅ  በላይ የሚነግረንና የሚያሳየን የለም። ለለውጥ ሂደት ግብአትነት የሚያግዙ (በራሳቸው ለውጥ ያልሆኑ) አዎንታዊ እርምጃዎች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ሂደቱ ከተጀመረ ብዙም ሳይቆይ የምናስተውለው የፖለቲከኞቻችን አካሄድ  የጤናማ ፖለቲካ ባህሪን (ጤናማ የፖለቲካ የሙቀት መጠንን) ጨርሶ  አያሳይም ።

ከልክ በላይ በሚወጣና በሚወርድ የፖለቲካ  ትኩሳት መሠረታዊ ዓላማን ወይም ግብን (እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን) እውን  ማድረግ የሚቻል አይሆንም ። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ሁኔታ የጤንነት ምልክት አይደለምና ።

በእርግጥ ሃላፊነትን በቅንነት ፣ በእውነተኝነትና በግልፅነት ለመወጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ በሚያጋጥም ስህተት የሚፈጠር ጤናማ ያልሆነ ትኩሳት አይኖርም ማለት የገሃዱ ዓለም እውነታ አይደለም። በዚህ የእውነተኛ ለውጥ (የሥርዓት ለውጥ) ፍለጋ እንቅስቃሴ ሂደትም ከዚህ እውነታ የሚመነጩና ከችግርነት አልፈው ወደ ቀውስነት ሊለወጡ የሚችሉ ጉዳዮች ፈፅሞ አይኖሩም ወይም መኖር የለባቸውም ብሎ መከራከር ትክክል አይሆንም።   ሃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ካለመቻል ወይም ድብቅ በሆነ የራስ ምክንያት (ulterior motive) አገር (ህዝብ) ቀውስ በቀውስ ሲሆን ሰንካላ  ሰበብ ( clumsy execuse) ለመደርደር በሚደረግ ጥረት ውሸትን የመፈብረክ የፖለቲካ ባህሪ እየተጠናወተ (ልማድ እየሆነ ) ይመጣል ። የአገራችን ፖለቲካ ደግሞ የእንዲህ አይነት መሪዎችና  ፖለቲከኞች ደሃ አይደለም። አለመታደል ሆኖብን ሳይሆን በእኛው በእራሳችን  ልክ የሌለው ውደቀት ምክንያት።

የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ የፖለቲካ ሥርዓት ካስከተላቸውና በቀላሉ ሊወገዱ ከማይችሉት የበሽታ አይነቶች አንዱና ዋነኛው ይኸው ነው ። የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን ፖለቲከኞችንም ከማዋዠቅ አልፎ በእጅጉ እየተፈታተናቸው ያለው ይኸው ክፉ ልክፍት ነው። ለዚህ ነው በግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተጀመረውና ጤናማ ይመስል የነበረው  የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ የሙቀት መጠን  ብዙም ሳይቆይ በሚያስገርም ፍጥነት ወደ ታች የመውረዱን እውነታ  ለምንና እንዴት? ብሎ መጠየቅ የግድ የሚለን ።

የፖለቲከኞችን ድንቅ ዲስኩርና አንደበተ ርዕቱነት በመሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር እያመሳከርን በጥሞና ለማጤን የሚያስችል የፖለቲካ አስተሳሰብና ቁመና ባለቤቶች ለመሆን እስከአሁን አልተሳካልነም ። 1966ቱ አብታዊ የመደብ ትግል አብዮት እና የ1983ቱ የህዝቦች/ብሄር/ብሄረሰቦች አብዮት ለተወሰነ ጊዜ (ባፍላው) የነበራቸው የፖለቲካ ሙቀት ከዚህ ኢህአዴግን ጠጋግኖ (reform) የማስቀጠል ፖለቲካ ጋር የሚመሳሰል ነገር ነበራቸው። የለውጥ ነፋስ ነፈሰ በተባለ ቁጥር ለምን? እንዴት? ወደ የት? ለማንና ለምን ? ሳንል በስሜታዊነት ፈረስ የመጋለቡ ክፉ ልማድ ይኸውና ዛሬም እንደተጠናወተን ቀጥሏል ።

የፖለቲከኞችን ማለቂያ የሌለው ፣ ወደ ገሃዱ ዓለም የማይወርድ እና አንዳንዴም መያዣና መጨበጫ የሌለው የፖለቲካ ዲስኩር እየተከተልን እራሳችን ብቻ ሳይሆን መከረኛውን ህዝብ ጨምሮ ግራ ማጋባታችንን ቆም ብለን ለማየት የሚያስችል የሞራል ወኔ የማጣታችን ጉዳይ ለመረዳት ያስቸግራል ።  በፍጥነት ሽቅብ ወጥቶ በፍጥነት ቁልቁል የሚወርድ የፖለቲካ ሙቀት የጤና ማጣት እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም ። ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ አሽሙር ወይም ስም ማጉደፍ ሳይሆን ግልፅና ግልፅ የሆነ መሪር እውነት ነው።

ግልፅ ፣ ቀጥተኛ እና  ተሽኮርማሚ ያልሆነ ሂሳዊ አስተያየት (ትችት) በተሰነዘረ ቁጥር “ለምን ተደፈርን” በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ  የሚሉ ፖለቲከኞችን በቅጡ ሁኑ ሊባሉ ይገባል።  ይህ አይነቱ የፖለቲካ ሰብእና  ወይ የለየለት ድንቁርና  ወይም  ልክ የሌለው ግብዝነት  ወይም ደግሞ ሸፍጠኝነት ነውና ወደ ትክክለኛው ህሊናችሁ ተመለሱ ማለት የግድ ነው ።  ቀን በተጠቆጠረ ቁጥር የሚታዩት የክፉ ነገሮች እየጎለበቱ ሲመጡ ፣  ሙገሳውና ሆይ ሆይታው እየቀነሰ ሂሳዊ ትችቱ እየጠነከረ ሲመጣ ፖለቲከኞች የባህሪ ለውጥ ማሳየታቸው የማይጠበቅ አይደለም ። ችግር የሚሆነው በሂስ የሚጠርባቸው በበዛ ቁጥር ወደ መሃል ከምጣት ይልቅ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየተጠጉ ሲሄዱ ነው ።  በዚህ አያያዛችን  እንዴትና በየት በኩል እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንደሚቻለን ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበረ ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ በተከታታይ ያደርጓቸው በነበሩ   ዲስኩሮቻቸው  የለውጥ ጅማሮውን ብልሃትና ትእግሥት በተሞላበት አኳኋን የማስኬድን አስፈላጊነት ለመግለፅ “ለብዙ ጊዜ ተዘግቶ ወይም ታሽጎ  የኖረ ቤት ሲከፈት በጣም መጥፎ የሆነ ሽታ  እንደሚያስትል  የታወቀ ነው “ የሚል ምሳሌያዊ አባባል ደጋግመው ይጠቀሙ ነበር ።

ትክክል ነው! ነገር ግን ዛሬም በግልፅ ስለሚታየው ተመሳሳይ ችግር (ፈተና) ለመናገር ወኔ ማጣት (አለመድፈር)  ትናንት ከነበረው  የፖለቲካ ክርፋት ከምር ለመውጣት (ለመላቀቅ)  በታማኝነትና በቁርጠኝነት መቆምን አያሳይም ።  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ለህዝብና ለጤናማ አየር ዝግ ሆኖ የኖረው የህወሃት/ኢህዴግ የእኩይ ፖለቲካ ማምረቻና ማከፋፈያ መዕከል (ቤተ ተውኔት)  በህዝብ አስገዳጅነት ተከፍቶ መጥፎው ሽታ (ግማት/ክርፋት) በዋናው በር መውጣት ሲጀምር በኦዴፓ/ኢህአዴግ እና በሌሎች በየጎሳቸው ተሸጉጠው በጎሳ/በዘውግ አጥንት ቆጠራ  ፖለቲካ ንግድ የሚነግዱ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስት ነን ባዮች አማካኝነት ተመሳሳይ መጥፎ የፖለቲካ ሽታ  በኋላ በር በኩል እየተተካ አገርን ማወኩን ልብ አለማለትና ተገቢውን እርምት አለማድረግ  የጤናማ ፖለቲካ ምልክት አይደለም ።

እናም በዚህ አስተያየቴ ውስጥ የማነሳው አይነተኛ ጥያቂ ለዘመናት የበከተና የከረፋ የፖለቲካ ሥርዓትን መሠረታዊ በሆነ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት የተመሳሳይ (ያለፍንበት)  የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባዎች ስለአለመሆናችን ምን ያህል እርግጠኞች ነን ? የሚል ነው። አቀራረቤ በግልፅ የሚታየውንና የሚሰማውን ወይም አገር ያወቀውንና ፅሐይ የሞቀውን የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ሸፍጥ  በተረዳሁትና በገባኝ መጠን አካፋን አካፋ ወይም ክርፋትን ክርፋት እስከ ማለት  የሚሄድ በመሆኑ የለውጥ አራማጅ የምንለውን ቡድን መቃወም ወይም ማደናቀፍ የሚመስላቸው ወገኖቼን እንደማይመቻቸው በሚገባ እረዳለሁና ምንም ቢሉ አይገርመኝም ።  እንደሚከተለው ልቀጥል 

የለውጥ ጅማሮውን የተረዳንበትና የተቀበልንበት ሁኔታ ነበር (ምን ይመስላል ) ?

የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራ የውርደት ሥርዓተ ህወሃት/ኢሀአዴግን በቃኝ በሚል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነት በውዴታ ግዴታ በመሪነት በመቀላቀል በአንፃራዊነት  አበረታች የሆኑና ለለውጥ እውን መሆን የሚያግዙ ተግባራት እንዲተገበሩ ያገዙትን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች  በአግባቡ የመቀበልና የመደገፍ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም ።

አጠያያቂ ከሆኑትና የለውጥ ሂደት ጅማሮው ብዙም እርቀትና ጥልቀት ሳይሄድ የፖለቲካውን የሙቀት መጠን በፍጥነት ቁልቁል እንዲወርድ ካስገደዱት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች መካከል   የለውጥ ሃይሎች የምንላቸውን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች የተቀበልንበት ሁኔታ ነው ።  ለማሳያነት ያህል እንደሚከተለው ልግለፃቸው ፦

 • የለውጥ አራማጆች የምንላቸው ፖለቲከኞች የለውጥ ፍለጋ መሠረታዊ አነሳሳቸው በአምሳሉ ፈጥሮና አሳድጎ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ የእኩይ ዓላማው አስፈፃሚ (ፍፁም ታማኝ አገልጋዩ) አድርጓቸው የኖረውን ህወሃትን ከጫንቃቸው ላይ ለማውረድና በተሃድሶ (reform) ስም ገዥነታቸውን ለማስቀጠል እንጅ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ እንዳልነበር ለመረዳት የፖለቲካ ሊቅ ወይም ባለ ልዩ ችሎታ ባለቤት መሆንን ጨርሶ አይጠይቅም ። እያደር ራሱን ግልፅ እያደረገ የመጣውና በሸፍጥ የታጀበው የፖለቲካ አካሄድ የሚነግረንን መሪር ሃቅ ለመቀበል ወኔ (ድፍረት) እያጣን ሰንካላ ምክንያት የመደርደራችን ክፉ ልማድ ሃቁን ጨርሶ አይለውጠውም።  አልሸሹም ዘወር አሉ በሚያሰኝ አኳኋን ብዙም ሳይራመዱ የአደባባይ ሚስጥር እያደረጉ ያሉትን  የህወሃትን የበሰበሰና የከረፋ የጎሳ/የዘውግ/የመንደር ፖለቲካ አካሄድ ለማስተባበል ከቶ አይቻልም ።

በዚህ ረገድ ኦህዴድ/ ኦዴፓ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ተሳክቶለታል ፤ ብአዴን/አዴፓ ደግሞ እንደለመደው የእኩልነቱን ሳይሆን የአጃቢነቱን ሚና በመጫወት  አይወድቁ ውድቀት ወድቋል።  መሪርነቱ እየከበደን ለመቀበል ወኔ ካላጣን በስተቀር  ከለውጥ ሂደቱ ጥቂት ወራት በኋላ አግጥጦና አፍጥጦ የወጣው እውነት ይህን ያህል ግልፅና ግልፅ  ነው ።  ግልፅ መሆኑስ ባልከፋ ። በለየለት የጎሳ/የመንደር/የቡድን ፖለቲካ ሸፍጠኝነትና ሴረኝነት እየታጀበ የሚሊዮኖችን ንፁሃን ዜጎች ህይወት የማመሰቃቀሉና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት  እውን የማድረግን ጥረት ከባድ ፈተና ላይ የመጣሉ ጉዳይ ነው የቅን አሳቢ ዜጋን ልብ በብርቱ የሚያደማው ።

 • የህወሃት/ኢህአዴግ ጭራቃዊ ሥርዓት አገልጋይነት በቃኝ ብለው የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ህዝባዊ እንቅስቃሴውን በመሪነት ከተቀላቀሉ ወዲህ ለለውጥ ሂደት አጋዥ የሆኑ በጎና አበረታች እርምጃዎች መወሰዳቸውን ያየንበትና የምናይበት የተንሸዋረረ አመለካከት ለፓለቲከኞች የተሳሳተ መልእክት አስተላልፏል (እያስተላለፍም ነው) ።   ከሦሥቱ የመንግሥት አካላትን  (ህግ አውጭዉን፣ ህግ ተርጓሚውንና ህግ አስፈፃሚውን ) ጨምሮ በልይ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ   ተካሄደና እየተካሄደ ነው የሚባለው የለውጥ እርምጃ ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት እና አንዳንዱም ከሸፍጥ ፖለቲካ የዘለለ አየደለምና ብዙም የምለው የለኝም ።

በበጎነት ጎልተው ከሚጠቀሱት  እርምጃዎች መካከል ሀ) ቀድሞም ቢሆን በግፍ ታስረው የነበሩ ዜጎች ከየእስር ቤቱና ከየማሰቃያ ማእከሉ መፈታታቸው ለ) የትጥቅ እና የሁለገብ የፖለቲካ ትግል እናካሂዳለን ይሉ የነበሩትን ተቃዋሚ ድርጅቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥ አሉ ለሚባሉት በአንፃራዊነት የፖለቲካ ምህዳሩ ከአደጋ ዞንነት ነፃ መሆኑ እና ሐ) ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የማንሸራሸር አንፃራዊ ነፃነት  ዋነኞቹ ናቸው ።  አዎ ! ምን ያህል ይዘልቃሉ ? የሚለው እንደተጠበቅ ሆኖ እነዚህን እንደ ጉልህ የለውጥ ሂደት ግብአቶች መቀበል አያስቸግርም ።

ነገር ግን አንደኛ   እነዚህን የአያሌንፁሃን ዜጎች  መስዋእትነት ውጤት የሆኑትን  አዎንታዊ  እርምጃዎች የአቢይና የጓዶቻቸው ችሮታ አስመስሎ የማየት ሁለተኛ የለውጥ ሐዋርያ ነኝ የሚለውን ቡድን እነዚህን የለውጥ ሂደት አጋዥ እርምጃዎች  ከመወሰድ ያነሰ ሌላ ምን አይነት የለውጥ አራማጅነት እርምጃ ሊወስድና ሊያስወሰድ እንደሚችል አለመጠያቅ ወይም ሂሳዊ ጥያቄ (critical) አስተያየት ለመሰንዘር ወኔ ማጣት ሦስተኛ  ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በላይ ከጨካኝ ሥርዓቶች ለመላቀቅ ግዙፍና መሪር መስዋዕትነት ለከፈለ ህዝብ እነዚህ አዎንታዊ እርምጃዎች ቢያንሱበት እንጅ አይበዙበትም ብሎ እውነቱን በግልፅና በቀጥታ ለፖለቲከኞች ለመንገር መሽኮርመም  የለውጥ ጅማሮውን የተቀበልንበትን ድክማት ያመለክታሉ ።

 • አያሌ መስዋእትነት የተከፈለበት የህዝባዊ እምቢተኝነት (ትግል) ተልኮውና ግቡ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን (እውነተኛ ለውጥን) እውን ለማድረግ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህ ማለት ደግሞ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭ በሆነ አደገኛ የፖለቲካ ቫይረስ (ተውሳክ) የተመረዘው የኢህአዴግ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ተወግዶ በአዲስና ጤናማ ሥርዓት ባልተተካበት ሁኔታ  ወደ ተፈላጊው ለውጥ ለመሄድ  የሚያግዙ አወንታዊ እርምጃዎችን  አንድና ሁለት ብሎ  በመቁጠርና በራሳቸው ለውጥ እንደሆኑ አይነት አድርጎ  በመውሰድ “ለውጥ ተካሄደ” እያሉ ከራስ አልፎ ህዝብን የማሳሳቱ የፖለቲካ አመለካከት አሁን ለምናየው ጤናማነት  ለጎደለው የፖለቲካ ሙቀት የራሱን አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል ።

ኢህአዴግ  ከሥርዓት ተቆጣጣሪነቱ ተወግዶ አገር በዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሥርዓት ወደ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ትሸጋገር ብሎ መጠቅ በወንጀል የማይጠየቁ ኢህአዴጋዊያን ከፖለቲካው ጨዋታ ይሁኑ ማለት አይደለም ። ጥያቄው የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው የጋራ እጣ ፈንታን በጋራና በነፃነት ለመወሰን  የሚያስችለውን የፖለቲካ ጨዋታ ይቀላቀሉ የሚል ነው ።  ይህን በግልፅና በቀጥታ ለመናገር የሚሽኮረመም ወይም ወኔ የከዳው የፖለቲካ ሰብእና እያየነውና እየሰማነው ላለው እያደር የመዝቀጥ የፖለቲካ አባዜ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጎል ።

እንዲያውም ለመሠረታዊ ለውጥ (fundamental change of a political system) እና ለተሃድሶ (reform) አቻ ትርጓሜ በመስጠት ለፖለቲከኞች የሸፍት ባህሪና አካሄድ ቡራኬ መስጠት የሚቃጣው ልፍስፍስ ፖለቲከኛ፣ ጋዜጠኛ ፣ አክቲቪስት ፧ ምሁር ፣ ወዘተ   ብዙ ነው ።

የሥርዓት ለውጥ በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ በበሰበሰና በሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ሠራሽ ወንጀል በተዘፈቀ ሥርዓተ ኢህአዴግ ፈፅሞ እውን ሊሆን አይችልም ። አዎ! እንኳን ከቃላትና ከርዕቱ አንደበት በስተጀርባ የጎሳ/የዘውግ ፖለቲካ ሸፍጥ ባህሪ በተጠናወታቸው ፖለቲከኞች እንደ መልአክ የሆኑ (ፈፅሞ አይገኙም እንጅ) ፖለቲከኞችን መንበረ ሥልጣን ላይ በማውጣትና በተሃድሶ (reform) የፖለቲካ ተውኔት የኢህአዴግን የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት የተቀደሰ ማድረግ ጨርሶ አይቻልም ።

አሁን በአገራችን የምናየው የኢህአዴግ ተሃድሶ (reform) የሥርዓት ለውጥን እውን የሚያደርግ ሳይሆን የበከተው የኢህአዴግ ሥርዓት እንደ ሥርዓት እንዳለ ሆኖ በህዝብ ያስጠሉትን ገፅታዎች እንደምንም የህዝብን ስሜት በሚያማልል አኳኋን የማስኬድ አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ (ተውኔት) ነው ። ይህን መሪር ሃቅ ለለውጥ ሂደቱ አጋዥ የሆኑ አወንታዊ እርምጃዎችን ድንቅ ለውጥ (ጥልቅ ተሃድሶ) በሚል እራሱን ከመደለል አልፎ መከረኛውን ህዝብ ግራ ለሚያጋባው የአገሬ ፖለቲከኛና ምሁር ተብየ ለመቀበል እንደሚከብደው እረዳለሁ ። አፍጥቶና አግጥጦ እየተፈታተነን ያለውን  ሃቅ ግን ጨርሶ አይለውጠውም ።

 • የአሁኑ የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴ ደም አፋሳሽ ባለመሆኑና አወንታዊና አበረታች ጎኖች ያሉት በመሆኑ በአግባቡ ለሚጠቀምበት ወደ መልካም ውጤት ሊያመራ የሚችል መሆኑን መቀበል አያስቸግርም።

ለዚህ  የሚያበቁ አማራጭ የፖለቲካ ሃይሎችን በራሳችን ልክ የሌለው ድክመትና ውድቀት ምክንያት ለመፍጠርና ለማዘጋጀት ባለመቻላችን ይኸውና የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች እንደቀደሙት ሁሉ (1966 እና 1983) “ከእኛ የተሻለና እኛን የሚተካ ስለሌለ እኛ ሥልጣን የለቀቅን እለት አገር ይፈርሳል” የሚል አይነት መልእክት ይነግሩናል ።

አዎ ! እውነታቸውን ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓመታት ተዘፍቀው የኖሩበትና አሁንም በመሠረታዊነት ያልተለወጠው ገዥ ቡድናቸውና መንግሥታቸው እንደአሸን እንዲፈለፈሉ ያደረጋቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ተብየዎችን ምንም አይነት ከምርና ከቅንነት የመነጨ  የጋራ አገራዊ የፖለቲካ ራእይ ፣ስትራቴጅና አጀንዳ በሌለበት “ሰብሰብ በሉና ተፍካክራችሁ ሥልጣኑን ውሰዱ” ብለው ሲሳለቁባቸው ከማጨብጨብ አልፎ ምርቃኑንና ሙገሳውን የሚያዥጎደጉዱ ፖለቲከኞች ባሉበት አገር ይህን የግብዝነት ፖለቲካ ዲስኩር  መስማት ያሳዝን እንደሆን እንጅ ጨርሶ  አያስገርምም።  ከዚህ የበለጠ የትውልድ ኮስማናነትና ውደቀት ግን የለም ።

 • አግባብነት ባለው ሂሳዊ አስተሳሰብና ድጋፍ (ተሳትፎ) ላይ ሳይሆን እጅግ ልክ በሌለው ስሜታዊነት ላይ በቆመ የፖለቲካ ምንነትና ማንነት  ለዘመናት የዘለቀውን ግዙፍና ውስብስብ የአገራችን የፖለቲካና የፖለቲከኝነት ባህሪና ወዴትነት  ተረድቶ ተገቢውን ለማድረግ ከቶ አይቻልም።   ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው የአገሬ ሰው የዚህ ክፉ ልክፍት ተጠቂ የመሆኑ ሃቅ ደግሞ በእጅጉ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው ። ከራሱ ውደቀት የተነሳ ለዘመናት ከዘለቀበት የመከራና የውርደት ህይወት መማር አቅቶት ዛሬም በየአደባባዩና በየአዳራሹ እየሰበሰቡ እንደ ጀማሪ ተማሪያቸው ሊያስተምሩት የሚቃታቸው ፖለቲከኞች ዲስኩር  ሳይገባው ወይም ለምንና እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ ጭብጨባውን ያቀልጠዋል። ታዲያ በእንዲህ አይነት አኳኋን የተቀበልናቸው ፖለቲከኞች የግብዝነትና የሸፍጠኝነት ሰለባ ቢሆኑ ምን ይገርማል
 • በአንፃራዊነት ከኢህአዴግ የበሰበሰና የከረፋ ፖለቲካ ተለይተው የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉትና የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች ለህዝብ ጆሮና ስሜት በእጅጉ እርቀው የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት፣ የአብሮነት፣ የሃይማኖታዊ እምነትና የሞራል እሴቶችን ጉልህ የንግግሮቻቸው ክፍሎች በማድረጋቸው “ከሰማየ ሰማያት የተላኩልን የዚህ ዘመን ሙሴዎች” እስከ ማለት የተሄደበት እርቀት ዛሬ እያታየ ላለው የምስቅልቅልና የሸፍጥ ፖለቲካ አስተዋፅኦው የጎላ ነው ። ለግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በሸፍጥ፣ በሴራ፣ በክህደትና በመከራ ከተሞላ የፖለቲካ ተሞክሮ በኋላም በእንዲህ አይነት እጅግ የወረደ የፖለቲካ ሰብእና ላይ የመገኘት አባዜ ይህን ትውልድ  ገንቢ በሆነ ቁጭት አነሳስቶ ከዚህ  አስቀያሚ አዙሪት  ለመውጣት የሚያስችል ትግል ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይገባል ።

የጠቅላይ ሚኖስትሩን የአንድ ዓመት ጉዞ አስመልክቶ በሚዘጋጁ መድረኮችና  የመገናኛ ዘዴዎች  የሚቀርቡ የምሁራን ወረቀቶች (በእውን ጥናታዊ ለማለት ያስቸግራል)  መሬት ላይ ካለው  የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምስቅልቅል ተነስቶ ፖለቲከኞችን  በግልፅና በቀጥታ ከመሞገትና ከጎሳ/ከዘውግ የፖለቲካ ማንነት ሸፍጥ እንዲወጡ ከማገዝ ይልቅ  አካደሚክ አይነት ዲስኩርና ተሽኮርማሚነት  የተጠናወታቸው ናቸው ።የዛሬ ዓመት ፖለቲከኞችን የተቀበልንበትን ልፍስፍስና አሳፋሪ የፖለቲካ አስተሳሰብና አቀራረብ አሁን ትርጉም ባለው ደረጃ እየተወጣነው አይደለም ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና አስተዳደራቸው

 የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ንግግሮች (ዲስኩሮች) በተደበላለቀ ስሜት ከሚከታተሉ  ተራ (ordinary)  ወገኖቼ  መካከል   አንዱ ነኝ ። ምንም እንኳ ንግግሮቻቸው ከወጥነት (consistency)  ፣ ከሸፍጥ (yhpocracy) እና  ከውስብስቡና ከባዱ የገሃዱ ዓለም  ፖለቲካ  አንፃር  ከእንጭጭነት አይነት (naivety) ችግር ነፃ ባይሆኑም በአጠቃላይ ግን ስሜትን የመግዛት ሃይል ያላቸው መሆኑን መካድ አይቻልም ። በንግግሮች ውስጥም በአወንታዊነት (በአበረታችነት) መታየት ያለባቸው ቁም ነገሮች መኖራቸውን መካድም  ስህተት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ጓዶቻቸውን ጥርሳቸውን ነቅሎ ካሳደገ የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሴረኛና ሸፍጠኛ የጎሳ/የዘውግ ፖለቲካ ማንነት የሚመነጭና  ጤናማነት የጎደለው የፖለቲካ ትኩሳት እየወጣና እየወረደ አገርን ጤና መንሳቱን ቀጥሏል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የለውጥ አራማጅ የምንለውን ቡድን ይህ ክፉ ልክፍት ካስከተለውና እያስከተለ ካለው ምስቅልቅል ሃላፊነትና ተጠያቂነት  ነፃ ለማድረግ  አይኑን ጨፍኖ የሚከራከረው ብዙ ነው ።

በመሬት ላይ እየሆነ ያለውንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ለስሜት ቅርብ የሆኑ ዲስኩሮቻቸውን አለመገናኘት  በግልፅ እያዩና እየሰሙ የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን ፖለቲከኞች በሰላ ሂስ ለመተቸት  (ለመሞገት) አለመድፈር  ወይ የለየለት ድንቁርና ፣ ወይም ተደጋጋሚ ውድቀት የሚያስከትለውን መከራና ውርደት የመለማመድ ክፉ ልማድ ፣ ወይንም ደግሞ የለየልት የአድር ባይነት ልክፍት ነው ።  ህወሃትንና በህይወት የሌለውን መሪውን እኩይ የፖለቲካ አስተሳሰብና ተግባር አምርሮ መጥላት  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ከደረሰውና  እየደረሰ ካለው እጅግ አስከፊ የዜጎች መፈናቀልና ሰቆቃ ሃላፊነት ጨርሶ ነፃ ሊያደርጋቸው አይችልም ።  አይገባምም ።  በተሃድሶ (reform) የበሰበሰውንና የከረፋውን ኢህአዴግን “ስሙንና ቅርፁን ቀይረን የኢትዮጵያዊነት ተሟጋችና የበጎ ትሩፋት ባለቤት እናደርገዋለንና   ለሽግግሩና ለመጭው ምርጫ እንከን የለሽነት በእኛ  ይሁንባችሁና አታስቡ”  በሚል ቅዠት ውስጥ ለሚገኙ ፖለቲከኞች ከዚህ ቅዠታቸው እንዲወጡ በግልፅና በቀጥታ ለመሞገት ወኔውና ችሎታው የሚያንሰው ትውልድ እውነተኛ ዴሞክራሲ ምኞቱ ብቻ  እንደሆነ የቀጥላል ።

ምን ለማለት እንደፈለግሁ ግልፅ ላድርግ ፦

 • በዲስኩሮችና መሬት ላይ ባለው ግዙፍና አሳሳቢ እውነታ መካከል ያለውን ልዩነት  ትርጉም ባለው አኳኋን ከማጥበብ ይልቅ በተጋነነና ውሸት (ሸፍጥ) በተቀላቀለበት አኳኋን ይባስ ማስፋት  የጤናማ ፖለቲካ ምልክት አይደለም ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ   የህወሃትን የፖለቲካ ጨዋታ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት ኦህዴድ/ኦዴፓ  ዋና ተዋናይነት  ለመተካት የሚደረገውን የሸፍት ፖለቲካ እንደማያውቁ በጅምላዊ የአነጋገር ስልት አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር የጤናማ ፖለቲካ ትኩሳት አይደለምና መላልሶ ማጤንን ግድ ይላል ።
 • ወጥነት (consistency) ማጣት ወይም ተመሳሳይ ችግር  ፈጣሪዎችንና ጉዳዮችን  በተመሳሳይ መርህ ላይ በተመሠረተ አኳኋን ፣ እይታና አቀራረብ ያለማስተናገድ (double standard) የፖለቲካ ሰብእናን ሳይመሽ ማረም የአዋቂነት ምልክት ነውና ልብ ሊባል ይገባል።
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደጉበትና አሁንም የሚመሩት ድርጅት/ግንባር ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ እጅግ ምስቅልቅልና ውስብስብ ያደረገውን የገሃዱ ዓለም ፖለቲካን “ለማቃለል” እረፍት በሌላው ድንቅ  ፖለቲካዊ ንግግር /ሰበካ (rehetoric or oratory) መጠመድ የፖለቲካውን የጤንነት ጠረን አያመለክትም  ።
 • በግልብነትና በስሜታዊነት ላይ የሚዥጎደጎድ ሙገሳን እንደስኬት መለኪያ በመቁጠር እራስን እጅግ በተለጠጠ የታላቅ መሪነት ዓለም ውስጥ አስገብቶ ከገሃዱ ዓለም ብርቱ ፈተና እየራቁ መሄድ የጥሩ ፖለቲካ ባህሪ የለውም ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ጓዶቻቸውን ህሊና እና አንገት የተሠሩት ዞሮና አዟዙሮ ለማየት ነው ይህን ሆናችሁና አድርጋችሁ ተገኙ ማለት የዜግነት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው ። ለለውጥ እውን መሆን በመንገድ ጠራጊነት የሚያገለግሉ አወንታዊ እርምጃዎችን (ኩነቶችን) እንደ ለውጥ መዳረሻ (ግብ)  በመቁጠር የድል ነጋሪት መጎሰም በምንም አይነት የእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግርና ምሥረታ ጣእም የለውም ። እናም በዚህ ረገድ ሃላፊነቱ የፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ ዜጋም ነውና ከምር ልብ ማለት ተገቢ ነው ።
 • ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአስፈፃሚነትና በፈፃሚነት ከተዘፈቁበት ሥርዓት ሙሉ በሙሉም ባይሆን ይበል በሚያሰኝ ሁኔታ ወጥቶ በውዴታ ግዴታ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ትግሉን በመሪነት የተቀላቀለ ሃይል ወይም ስብስብ ወይም ግለሰብ ንፁሃን እስረኞች እንዲፈቱ ካላደረገ ፣ የፖለቲካ ምህዳር የሚባለውን እንዲከፈት ካላስቻለ ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች (ሚዲያን ጨምሮ) በአንፃራዊነት እንዳይደፈጠጡ ካላደረገ ታዲያ ሌላ ከዚህ ያነሰ ምን ሊሰራ ኖሯል ? ብሎ እራስን መጠየቅ ፖለቲከኞች ከሚፈጥሩት ብዥታ ይታደጋል ያለዚያ እንደ ልዩ ችሮታ እኔ ባልገኝ ኖሮ ይህ ጨርሶ አይሆንም ነበር” የሚል አይነት ግብዝነት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ሰለባ መሆንን ያስከትላል ።  በንፁሃን ዜጎች  የቁም ስቃይና በህይወት መስዋዕትነት የተገኘን የለውጥ ብልጭታ ጠቅልሎ የራስ “ተጋድሎ ድል” በሚመስል አኳኋን የማይታመን ውጤት አስመዘገብኩ  እያሉ መመፃደቅ  ጤናማ የፖለቲካ ሰብእና ማሳያ እንዳልሆነም ግልፅና ቀጥተኛ መልእክት ማስተላለፍ የመልካም ዜግነት ባህሪና ግዴታ ነው ።

ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ በየአደባባዩ የወደቀውን ፣ በየማሰቃያ ቦታው የቁም ስቃይ ያየውን ፣ በየእስር ቤቱ የማቀቀውን ፣ ወገቡን አስሮ የደም እንባ ያነባውን ወላጅ እና ወዘተ ቢያንስ   በዲስኩር ደረጃ ለማስታወስ (ለመጥቀስ) እየተረሳ የራስ ገድል የሚተረክበት የፖለቲካ ትእይንት ስናየውና ስንሰማው የኖርነው የፖለቲካ ትዕይንት ክፍል (episode) ይመስላልና ልብ ማለቱ ጥሩ ነው ።

 • የጎሳ ፖለቲከኞች ሸፍጥ እና የኑሮ ጡዘት ናላውን ያዞረው የአገሬ ወጣት ድምፅ አልባ ህይወት አጥፊ መሳሪያ ይዞ አደባባይ እንዲወጣ በማድረግ  እዚች አካባቢ ድርሽ የሚል ካለ ደም እንፋሰሳለን” እያሰኘ ያስፎከረውን ጀዋር መሃመድን እና ቤተ መንግሥት ሥር ሆኖ በለውና አሳየው እያለ ቀጭን ትእዛዝ ይጥሰጥ የነበረውን የኦነጉን ዳውድ ኢብሳን በህግ አምላክ ሳይሉ  ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የዜግነት መብታቸውን ለመጠየቅና ሥጋታቸውን ለመግለፅ በሞከሩ ዜጎች ላይ በአደባባይ ታርፉ እንደሆነ እረፉ ያለዚያ ጦርነት እንከፍታለን” ከማለት የከፋ ምን  አይነት የፖለቲካ ሸውራራነት ይኖራል ?

ይህ ማስፈራሪያ (ማስደንገጫ) ቢጤ እንጅ እውነት ሊሆን አይችልም በሚል በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን  ለሚዲያ ሊያካፍሉ ወደ ሰላማዊ አዳራሽ ያመሩትን እስክንድር ነጋንና ባልደረቦቹን  እንደ ወንጀለኛ በፖሊስ አስገፍትሮ ካባረሩ በኋላ “ለደህንነትህ/ታችሁ  ብለን ነው” የሚል የፈጠራ ምክንያት መስጠት ጨርሶ  የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታ ካልሆነ ሌላ ምንሊሆን ይችላል?

አንድ የአገር መሪ ፍፁም ሰላማዊና አገር ወዳድ በሆኑና መብታቸውን በዚህ መሠረታዊ እምነታቸው መሠረት ለማስከበር የተንቀሳቀሱ ዜጎች ላይ በአደባባይ ጦርነት የማወጁን አሳፋሪነት  (ዝቅጠት)  ተገንዝቦ በስሜታዊነት የተሳሳተ አገላለፅ ተጠቅሚያለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ” ለማለት የሞራልና የፖለቲካ  አቅም ሲጎለው መታዘብ በእጅጉ ያሳስባል/ያሳዝናል  ።እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ጨዋታ የለውጥ ቻምፒዮን ነኝ ከሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመጣ  ደግሞ አሳፋሪነቱ   የከፋ ነው ።

 • በቅርቡ ከጋዜጠኞች ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ድርጅት (Information Network Security Agency) ጋር ተያይዞ ለተነሳባቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ውስጥ ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል አይነት ስሜት ኮስተር ብለው  መልስ ሲሰጡ  “ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም የፈፀምኩት መጥፎ ነገር የለም”  ሲሉ ልብ ብሎ ለሰማ ሰው እንደ እኔ ሌላ አብይ አህመድ ነው እንዴ? ብሎ ራሱን ሳይጠይቅ የሚቀር አይመስለኝም።

የመከራውና የስቃዩ ሰለባ የሆነው የኢትዮጵያ  ህዝብ ብቻ ሳይሆን  ዓለም የሚያውቀውን መሪር ሃቅ  ሽምጥጥ አድርጎ ከመካድ የባሰ የፖለቲካ ሰብእና ቁልቁለት ያለ አይመስለኝም ።   እንኳን በስለላ ( ደህንነት) ኢንፎርሚሽን መረብ ድርጅት በአንደኛና በሁለተኛ አለቃነት የሠራ ሰው ተራው የኢህአዴግ  የመንደር ጆሮ ጠቢና ጥላ ወጊ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ንፁሃንን ለሰቆቃና ለህይወተ ህልፈት አሳልፎ በሚሰጥበት አገር እንዲዚህ የለየለት ነጭ ክህደት  የለውጥ አራማጅ ነኝ ከሚል  ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት ሲወጣ ቢያንስ ለህሊና ይከብዳል ።

ለነገሩ እኔስ/እኛስ ምን አደረገሁ/አደረግን ? ብሎ ራስን ሳይጠይቁ በፖለቲከኞች ላይ ብቻ እግዚኦታውን ማዥጎድጎድ ጨርሶ ትርጉም አይሰጥም ። ክርስቶስን እንኳ ተከታዮቹ ያመኑትና የሚያምኑት ቃሉ ከድርጊቱ ጋር በመገኘቱ ነው ። እኛ ፖለቲከኞቻችንን “የዘመናችን ሙሴዎቻችን ናችሁ” ያልናቸው ከቃል በቀር ገና ምንም አይነት ትርጉም ያለው ድርጊት ሳናይ ነው ።ታዲያ እንዲህ አይነቱ  የፖለቲካ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ወደ እውነተኛ የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግረን እንዴት አድርጎ ነው

 • ህወሃት ወደ መሃል አገር የሚያደርገውን ግስጋሴ ወደ ማገባደዱ ሲቃረብ ሁለተኛው የሆነውን ልጁን (ዛሬ ኦዴፓ ተብያለሁ የሚለውን ኦህዴድን) ያለምንም ችግር (ሳያምጥ) ወልዶ ወዲያውኑ የጥፋት ፖለቲካ ተልእኮው ማስፈፀሚያ (አስፈፃሚ) መሣሪያው አድርጎ ማሰማራቱን እንኳን መካድ የሚያስችል ትንሽም ለመጠራጠር የሚያስችል አንዳችም ማስረጃ የለም ። 29ኛ የልደት በዓል (የጭንጋፍ ማለቱ ይሻላል) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መከበሩን ተከትሎ የወጣውን መግለጫ ልብ ለሚል ቅንና አስተዋይ ዜጋ ከወቅቱ ጋር እንዲስማማ የሚያደርጉ ማስተካካያዎች ከመጨመራቸው በስተቀር የሚተርክልን 27 ዓመት ሙሉ የተተረከልንን የድርጅት ተብየውን (የኦህዴድ/ኦዴፓን )  ገድል ነው ።

ይህ አይነቱ የፖለቲካ ጨዋታ ልክፍት  ኢህአዴግ አሁን ባለው ቅርፅም ቀጠለ ወይም በአንድ ፓርቲ ስም ተሰየመ ጨርሶ የሚለቅ አይመስልም ። ኢህአዴጋውያን በቅርፅና በስም አንድ ቢሆኑም የሥልጣን ክፍፍላቸውና አሠራራቸው (በይዘት) ከጎሳ/ከዘውግ/ከቋንቋ መመዘኛነት ነፃ የሆነ ህሊና ይኖራቸዋል ብሎ እንኳን ለማመን ለማሰብም የሚቻል አይመስለኝም ። ሸፍጥ በተቀላቀለበት የፖለቲካ ዲስኩርም ከቶ የሚታሰብ አይደለም ። ረዘም ያለ ጊዜና እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠይቃልና ። ይህም ሊሆን የሚችለው በበሰበሰውና በከረፋው የኢህአዴግ ሥርዓተ እምነት፣ ሥርዓተ መዋቅርና ሥርዓተ ቁጥጥር አይደለም ። የፖለቲካ ነጋዴዎች የተከሉት እርስ በርስ የመጠፋፋት የጎሳና/የዘውግ/የቋንቋ ፖለቲካ ማንነት በእነዚያው ወይም በተመሳሳይ የፖለቲካ ነጋዴዎች ፈፅሞ መፍትሄ አያገኝም ።  ኦህዴድ/ኦዴፓ የአዲስ አበባን ጉዳይና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፌደራሊዝምን አስመልክቶ በሚያወጣቸው መግለጫዎቹ አስረግጦ  የነገረን ይህንኑ ነው ። በማሻሻያ( በተሃድሶ) ስም በየመሥሪያቤቱ ህወሃትን በኦህዴድ/ኦዴፓ ለመተካት የሚደረገው ሸፍጠኝነት በግልፅ የሚያሳየን ይህንኑ መሪርሃቅ ነው ።

 • የመብት፣ የሰላምና የዳቦ መምጫ እንደሰማይ የራቀበትን መከረኛ ህዝብ ወደ መሬት ሊወርድ የማይችል ሸጋ/ድንቅ የዲስኩር ወይም የሰበካ ጋጋታና ቁልል ለመመገብ መሞከር በግፍና በሰቆቃ ዘመናትን ባሳለፈ ህዝብ ላይ መቀለድ ነው የሚሆነው ።
 • ይኸ ለእራስ ገፅታ ወይም ዝና ፍለጋ  ሲባል አፍጥጦና አግጥጦ ወገንን (አገርን) ክፉኛ እየተናነቀ ያለውን እጅግ ግዙፍና ጥልቅ መከራና ውርደት ለመሸፋፈን መሞከር ወይም ተልካሻ ሰበብ መደርደር ወይም ነባርና ዘመን አመጣሽ ሚዲያውን  ለምን አጋለጥከኝ በሚል  በየአደባባዩና በየአጋጣሚው ተጠያቂ ማድረግና ለማሸማቀቅ ያዙኝና ልቀቁኝ ማለት እንደግለሰብም ሆነ እንደ አገር መሪ ውድቀትን እንጅ ስኬትን አያሳይም ።
 • ጠቅላይሚኒስትሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ ስለታየው ለውጥ ሲናገሩ ለጉብኝት በሄዱባቹው አገሮች መንግሥታትን እየጠየቁ (እየለመኑ) እና ለጋሾችም በሃዘኔታ የለበጣ ከንፈራቸውን እየመጠጡና በአፍሪካው ቀንድ ያላቸውን የየራሳቸውን የተፅዕኖ ሚና እያሰሉ የብድርና የእርዳ እጃቸውን ለመዘርጋት ቃል መግባታቸውን በእኔ ታዋቂነት የተገኘ በሚል አይነት ኩራት ነግረውናል ።

እነዚህ የለጋሽ አገራት መንግሥታት እኮ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭ የነበረውን ሥርዓት  ቤተ መንግሥት ከማስገባት አንስቶ እስከመጨረሻውና  ጭራሹን  ታላቁ መሪ በሚል የኢትዮጵያውያንን ጩኸትና አቤቱታ እንዳልሰሙና እንዳላዩ ሆነው የዘለቁ ናቸው።

በነገራችን ላይ ለአያሌ ዘመናት የአማኞችና የቱሪስቶች መዳረሻ የሆነውን የቅዱስ ላሊበላን ቅርስ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ካልሆነ በተወሰነ መጠን (ምፅዋዕት በማያስጠይቅ አኳኋን) እድሳት ማደስ (መጠበቅ) አቅቶን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረንሳዩን መሪ ለምነው በአኩሪ ዜናነት ሲነግሩን ትንሽ እንኳ ምን ነካን? ሳንል “እውነትም የዘመኑ ሙሴ” የሚል አይነት አድናቆት ያዥጎደጎድን ሰዎች ነን ። መች ይኸ ብቻ በቃን ። እራሳችን በራሳችን አፈናቅለንና ለመከራና ሰቆቃ ዳርገን ተመልሰን የነፍስ አድንና የመልሶ ማቋቋማያ ምፅዋዕት የምንለምን ጉዶች እኮ ነን ።

የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ ጨዋታ እጅግ ውሰብስብ በሆነውና ከሞራል ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ የየራስን ፍላጎት በሚያሳካና የጥቅም መስፋፋትን በሚያራምድ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሃይል የሚዘወር ነው ። በሌላ አገላለፅ የዓለም አቀፉ መስተጋብር  (ግንኙነት)  በወረቀት ላይ ሰፍሮ እንደምናነበው  መርህና ህግ የሚቀል አይደለም ። በተለይም ለእንደ እኛ አይነቱ በሁለመናው ወደ ኋላ ለቀረ አገር በእጅጉ ከባድ ስለሆነ መሪዎችን ለምን ትለምናላችሁ ማለት ትክክል አለመሆኑን በሚገባ እረዳለሁ ።

ይህ ማለት ግን መሪዎቻችን የተበደሩትንና ለምነው ያገኙትን ምፅዋዕት እየደመሩ “የጥረታችን ውጤት” በሚል በኩራት ሪፖርት የማድረጉ አሸማቃቂ ታሪክ ጨርሶ ባይቆምም በቅጡ መሆን አለበት የሚል አስተሳሰብ ማራመድ ከአንድ መልካም ዜጋ የሚጠበቅ ነው።  ይህ ደግሞ ለዘመናት የዘለቀውንና አሁንም ትርጉም ባለው አኳኋን ያልተለወጠውን አሳፋሪና አጥፊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ መለወጥን የግድ ይላል ። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፈተናን ከፖለቲካዊ (ከነፃነትና ፍትህ መስፈን) ውጭ ማሰብ አይቻልም ።  መበደርና እርዳታ መጠየቅ የነበረ፣ያለና የሚቀጥል ቢሆንም ለየጎሰኛ/መንደርኛ የፖለቲካ ነጋዴ በህገ መንግሥት ደረጃ አውጆ  ክልል በመስጠት እርስ በርስ እያናከሱና እያፈናቀሉ ኮረጀ ይዞ ልመና ከመዞር የከፋ ማንነት ጨርሶ የለም።

ስለቻይና ለጋስነትም “አብሥረውናል ።” ሃምሳ ሶሰት የአፍሪካ አገሮች ከተመሠረተ ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በላይ  ለሆነው ለቀድሞው  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ የአፍሪ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት (Headquarters) ማሠራት አቅቷቸው ሙሉ በሙሉ በቻይና ግዙፍ ችሮታአስገንብተው ሉአላዊነታቸውን ወደ ታች ማውረዳቸውን ለሚገነዘብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለይ ስትራቴጅክ የተፈጥሮ ሃብትና መልከአ ምድር ያላቸውን የአፍሪካ አገሮች በብድርና በእርዳታ ስም ሉአላዊነታቸውን ሳይቀር ምን ያህል እየተፈታተነች እንደሆነ ልብ ለሚል   የቻይና ሥራ አጥ የሥራ ሃላፊ ሆኖ በመመደብ በምስኪኑ የአገሬ  ሰው ላይ ከግልምጫ አልፎ እርገጫን የሚቃጣው መሆን በቁጭት ለሚታዘብ የአገሬ ሰው፣ መንግዱ ተሠርቶ ተመረቀ በተባለ ማግሥት ጉድጎድ በጉድጓድ መሆኑን ላስተዋለ ሰው ፣ የቻይናን ጥራቱ እጅግ የወረደን ሸቀጥ በውድ ዋጋ ገዝቶ ገንዘቡ ከኪሱ ወልቆ የጠፋ ያህል የሚያማርረውን የአገሬን ምስኪን ሰው ልብ ለሚል፣ በፖለቲካ/ዴፕሎማሲ እና በሌላ የወዳጅነት መንገድ በሚፈጠር ግነኙነት አማካኝነት  በፕሮጀክት ሥራ ኮንትራት ሂደት የሚፈጠረውን ሚዛኑን የሳተ ግንኙነት (እከክልኝና ልከክልህ) ከምር ለሚታዘብ የአገሬ ሰው ይህ ቻይናን ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ነፍስ አድን ሽርከኛ አድርጎ የማሳየቱ ነገር ከፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃነቱ በስተጀርባ ያለው አደጋ ከባድ ነው ።

በእውነት ከተነጋገርን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨባጭ ፍኖተ ካርታ ፣ በዘላቂ ግብ ላይ የተመሠረተ ስትራቴጅ  እና  ፖሊሲ ነድፎ  በመንቀሳቀስ ውጤት ከማስመዝገብ  አንፃር   ያለምንም ጥርጥር ክፉኛ ወደቀዋል ። እጅግ የተለጠጠና መሬት ላይ ካለው  መሪር እውነት ጋር የማይናበብ የፖለቲካ ዲስኩር ወይም ሰበካ ችግሩ እዚህ ላይ ነው።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመጣንበትንና አሁንም መልኩን ቀይሮ አገርን ምስቅልቅሉን የሚያወጣውን /የጎሳ/የጎጥ/ዘረኛ ፖለቲካና በዴሞክራሲያዊ ፣ በሰላማዊ እና በህጋዊ ትግል አደብ እንዲገዛ እስከአልተደረገ ድረስ እንኳን በነፃነትና በብልፅግና  እየለመን የምንኖርበት አገርም አይኖረንም ። አገር የሚያፈርስን ህገ -መንግሥት ተናደና ተደፈጠጠ እያሉ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ከማድረግ ለውጡን ከእርሱው ከእራሱ  በመጀመር አገርን መታደግ   ግድ ይላል ።

በእኔ ግንዛቤና እምነት ይህ አይነት ቁርጠኝነት ኢህአዴግ ስምም ይቀይር  ወይም ተዋሃድኩ ይበል እንደሥርዓት ወይም እንደገዥ ፓርቲ በበላይነት በሚዘውረው ፖለቲካ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወደ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሸጋገር የሚቻል አይሆንም ። ይህን እውነት ከአሁኑ እያየነው ነው ። መንግሥታዊውንም ሆነ የድርጅቱን (የግንባሩን) መዋቅር በጎሳ/በዘውግ የፖለቲካ ማንነት የተቆጣጠረው በሚሊዮን የሚቆጠር እውቀት አልባና አቅመ ቢስ የካድሬ ሠራዊት በሆነበት አገር  በኢህዴግ መሪነት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይወለዳል ማለት የሚቻል አይመስለኝም ። ስለዚህ የሚሻለው በዚህ እጅግ ውስብስብና አሳሳቢ ጉዳይ ዙሪያ የሽግግር መንግሥትን (ምክርቤትን) የግድ ይል ይሆን? እስከሚል ጥያቄ ድረስ ሄዶ ቢያንስ ከምር መነጋገሩ (መወያየቱ) አስፈላጊ ነው ።

One comment

 1. Superb analysis .Thank.you.

  I want to add my take about the construction of the AU building, other African countries did not want to pay for the construction of the AU building in Addis Ababa because they knew water and electricity is scarce in Addis Ababa and lawlessness was on the rise.

  The African countries were hoping the building will be built in other African cities where there is no heavy homeless concentration as Addis , water is not scarce and electricity is not scarce. On the otherhand China wanted to build it in Addis Ababa because China knew if the building was built somewher else the African countries would pay for it and China’s help would not have been felt among Africans. Now Africans consider China as more of an an ally because China covered all the cost which was exactly what China wanted .

Comments — What do you think?