Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » ቃሎቻችን የተግባሮቻችን እውነተኛ ነፀብራቅ ይሁኑ! (ጠገናው ጎሹ)

ቃሎቻችን የተግባሮቻችን እውነተኛ ነፀብራቅ ይሁኑ! (ጠገናው ጎሹ)

ጠገናው ጎሹ
January 13, 2019

ቃላትን  (ፅንሰ ሃሳቦችን )  ስንጠቀም  ያለንበትን ተጨባጭ እውነታ  በትክክል ይገልፃሉ ከሚል መነሻነትና እምነት እንጅ  ለስሜቶቻችን ቅርብና ተስማሚ በመሆናቸው አይደለም ። መሆንም የለበትም  ።  ፖለቲከኞች (መሪዎች) እንደማነኛውም የአንደበተ ርእቱነት ተሰጥኦና ልምድ እንደሚኖረው ሰው የህዝብን (የታዳሚያቸውን) ስሜት ወይም ቀልብ ሊገዛ የሚችል አቀራረብና አንደበት ሊኖራቸው ይችላል ። እንደ አጠቃላይ መርህ ይህ ተሰጥኦና ልምድ የሚደነቅና የሚበረታታ እንጅ የምናጣጥለውና እንዳይበረታታ የምናደርገው አይደለም ። መሆንም የለበትም ። በሌላ በኩል ግን በተለይ የለየላቸው አምባገነኖችን ጨምሮ ስለነፃነት ፣ ስለፍትህ፣ ስለዴሞክራሲ፣  ስለሰላም፣ ስለፍቅር ፣ ስለአንድነት ፣ ስለሞራልና ስነምግባር ፣ ስለልማት/እድገት ፣ ወዘተ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያለምንም የህሊና ዳኝነት  በሰላ አንደበታቸው በሚደሰኩሩበት በዚህ ዘመን ቃላት ከተጫባጩ እውነታ ጋር ወደ መሬት ወርደው ህይወት አልባውን ፖለቲካ ህይወት ሲዘሩበት ማረጋገጥ የግድ ነው ። በዚህ ረገድ ያለብን ጉድለት እንዲህ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ደህና ሰንብት የምንለው አይደለም ።

ለዚህ አይነተኛውና በምንም መንገድ ልናስተባብለው የማንችለው ምክንያት የዓለም ጨራዎችና የተመፅዋችነት ተምሳሌት ያደረገን ልክ የሌለው የፖለቲካ ባህላችን ፣ የኢኮኖሚ አቅማችን እና የማህበራዊ አገልግሎታችን ኋላ ቀርነት ነው።ለዚህ ደግሞ አይነተኛው ምክንያት ግልፅና ግልፅ ነው። በጎውንና ክፉውን ( ክፉው ያመዝናል) ካየንበት የገንዛ ታሪካችን ተምረን የተሳካላትና ለሁሉም ዜጎቿ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ፣ የሰላም፣ የአብሮነት ፣ የብልፅግና እና የኩራት ምድር የሆነች ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ይልቅ ተቃራኔውን ያደረግነውና መልሰን እግዚኦ የምንለው እኛው እራሳችን ነን። ፈጣሪ የሰጠንን የአእምሮ ችሎታና የአካል ብቃት ተጠቅመን እጅግ ፈታኝና ወሳኙን ምእራፍ ለመወጣት እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ በሚገባን በዚህ ወቅትም “አዎ! ዋናው የተግባር ሰው ሆኖ መገኘት ነውና እጅ ለእጅ ተያይዘን እንገስግስ” ከማለት ይልቅ “የሚያዋጣን እግዚኦታ ብቻ ነው” የሚሉን የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪያን ብዙዎች ናቸው ።  እናም ቃልን  ወደመሬት አውርዶ ከድርጊት ጋር በማዋሃድ ረገድ ያለብን ፈተና ዛሬም ከቶ ቀላል አይደለም ።

በተለይ  ፖለቲከኞች (የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን ጨምሮ) የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን ለምንና እንዴት ? ብለን ሳንጠይቅ እንደወረደ እየተቀበልን የማስተጋባቱን ልማድ  ልብ ልንለውና ጨርሶ ማስወገድ ባንችልማ እንኳ   ቢያንስ በቅጡ ልናደርገው ይገባል  ።  ይህን ባለማድረጋችን አላስፈላጊው ልማድ እየዋለና እያደረ በሄደ ቁጥር  በመሠረታዊው  ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ  የሥርዓት ለውጥ ላይ ማተኮራችን ይቀርና (ይቀንስና) ሁለመናችንን ለፖለቲከኞች  በመተው  እነሱኑ ማምለክ እንጀምራለን ።

ፖለቲከኞችም (መሪዎችም) በዚህ የተመላኪነት ልክፍት ከተለከፉ ወደ ትክክለኛው የገሃዱ ዓለም ሃላፊነታቸውና ተጠያቂነታቸው ለመመለስ በእጅጉ ይቸግራቸዋል (አይቻላቸውም) ። በህግና በዴሞክራሲ አምላክ ወደ ትክክለኛው ህሊናችሁና ለህዝብ ወደ ገባችሁት ቃለ መሃላ ተመለሱ ቢባሉም አምኖ ለመቀበልና ለመመለስ በእጅጉ ይከብዳቸዋል ። በዚህ መካከል ነው አምባገነንነት ሰተት ብሎ ቤተ መንግሥት የሚገባውና ተመቻችቶ የሚያገኘውን መንግሥታዊ መዋቅር  እያተራመሰ አገሩን የሚያዳርሰው ። ለዚህም ነው የግለሰቦች (መሪዎችን ጨምሮ) ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ተቃውሟችንና ድጋፋችን ሊያሳምን በሚችል ምክንያታዊነትና ለእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ መሆን ይኖርበታል ማለት ትክክል የሚሆነው ። ከራሳችን የፖለቲካ ታሪክ እንደምንረዳው ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለባቸው የሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴዎች እየከሸፉ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚዎች እየሆን የዘለቅነውና አሁንም ከዚህ ለመውጣት እርግጠኞች ያልሆንበት አንዱ ምክንያት ከፖለቲከኞች (መሪዎች) ጋር የነበረን (ያለን/የሚኖረን) እጅግ የተሳሳተ ግንኙነት  ነው  ።

“ከለውጡ ወዲህ እኮ ተፎካካሪ ነው እንጅ ተቀዋሚ አይባልም” የሚል ከየዋህነት ወይም “ከእውቀት”  የሚመነጭ አስተያየት ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ ። ቃላትን (ፅንሰ ሃሳቦችን) ለመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ  የግድ የሚሉ ሁኔታዎች በመሬት ላይ ከመኖራቸው  ወይም  ካለመኖራቸው  አንፃር ሳይሆን ፖለቲከኞች  ለስሜታችን በሚስማማ ትርጓሜ  ሲነግሩን መልሰን እንደ በቀቀን (parrot style) በማስተጋባቱ ልማድ አልስማማም ።  በእውነት እየተነጋገርን ከሆነ   ለዘመናት  ውድቀታችን ዋናው ምክንያት የየራሳችን የአስተሳሰብ ድህነትና የተግባር ስንኩልነት  እንጅ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የሚል የቃላት ምርጫ (ጨዋታ ) ባለማሳመራችን አልነበረም ። ለዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚዎች ሆነን የዘለቅነው ስለ መድብለ ፓርቲ አስፈላጊነትና ምንነት የምንገልፅባቸው ቃላት ስሜትን የመኮርኮር ሃይል ስለአልነበራቸው ሳይሆን ቃላቶቻችን ወደ መሬት ሳይወርዱ መልስን ስለበላናቸው (ስለገደልናቸው) ነው ። አዎ ! ከዚህ አይነት እንቆቅልሽ (paradox) ለመውጣት ከቶ ቀላል አይደለም ። ነገር ግን  እውነተኛ ህዝባዊት፣ ዴሞክራሲዊት እና የበለፀገች አገር እንዲኖረን ከምር የምንፈልግ ከሆነ ፈተናውን በአርበኝነት ወኔ ከመጋፈጥ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም ።

አሁንም የበሰበሰውና ለእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን እንኳንስ በመሪነት በእውነተኛ አጋርነት ለመቆም የፖለቲካም ሆነ የሞራል እርሾ የሌለው  ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት  በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ተፎካካሪ እንጅ ተቃዋሚ አይባልም የሚል  የቃላት ጨዋታ ፖለቲካ መጫወት እራስን ከማታለል አያልፍም ። ልብ ይባልልኝና እያልኩት ያለሁት የህዝብን አልገዛም ባይነት ተከትሎ የነፃነት እንቅስቃሴውን  በውዴታ ግዴታ መሪነት የተቀላቀሉትና በጣት እየቆጠርን የምንጠራቸው ፖለቲከኞች አወንታዊና አበረታች የለውጥ ፍንጭ አላሳዩም አይደለም ። የሚታየውንና የሚጨበጠውን እውነታ መካድ ቀርቶ ማጣጣል  በምንም መመዘኛ ትክክል  አይደለምና እኔም እንዲህ አይነት የድንቁርና አስተያየት አልሰነዝርም ።

እያልኩ ያለሁት እነዚህ የለውጥ አራማጅ የምንላቸው መሪዎች  ለሩብ ክፍለ ዘመን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ተሳታፊ ሆነው የኖሩበት እጅግ እኩይ ሥርዓት ከሞት አፋፍ ተመልሶ እንደ ሥርዓት አሁንም “መንገድ መሪውም ሆነ አሸጋጋሪው እኔ ነኝ” በሚልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ተቀዋሚ የፖለቲካ ሃይል ብሎ መናገር ነውር እስኪመስለን ድረስ እራሳችን ማታለላችን ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ነው ።  አሁን ባለንበት እውነታ ተፎካካሪነት እንኳን በመሬት ላይ ሊኖር በአስተሳሰብ ደረጃም ጨርሶ ቅርፅ አልባ (amorphous ) በሆነበት ሁኔታ “እናንት ተፎካካሪዎች እየመጣችሁ በአጃቢነት ተደመሩና (  (ተጨመሩና) የምርጫ ዙር እየጠበቅን ዴሞክራሲን ዴሞክራሲ እናድርገው (እናስመስለው)” ስንባል  “ቃለ ህይወት ያሰማልን” የምንል ከሆነ ቆም ብለን ከምር እራሳችን መጠየቅ ይኖርብናል ።

የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች ከተበላሸው እንቁላል (ሥርዓተ ኢህአዴግ) በከፊልም ቢሆን አምልጠው በመውጣትና የነፃነት ትግሉን በመሪነት በመቀላቀል አወንታዊ ሚና ለመጫወት በመሞከራቸው ተገቢውን እውቅና እና ድጋፍ መስጠት ትክክል ቢሆንም ከገማው እንቁላል  (ሥርዓተ ኢህአዴግ)  ) ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥተዋል ብሎ አዋጅ ማወጅ ግን ራስን ከማታለል አልፎ ህዝብንም ማታለል ነው። መውጣት አልፈለጉም አይደለም እያልኩ ያለሁት ። በበሰበሰው እንቁላል ( የኢህአዴግ ሥርዓተ ፖለቲካ) እና የሱው ዋነኛ መገለጫ በሆነውና የህገ-መንግሥት ተብየው ዋነኛ ማሰሪያ በሆነው የጎሳና የመንደር ፖለቲካ ውሰጥ እየዳከሩ ነፃ ወጥተን ነፃ እያወጣን  ነው ብሎ ማወጅ ብርቱ ጥያቄ ሊያስነሳ አይችልም ማለት ወይ የፖለቲካ የዋህነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ “ብልጣብልጥነት” ነው ። ይህ ደግሞ  ከምኞት ሳይሆን ከምንገኝበት  የገሃዱ ዓለም ፖለቲካችን ጋር አገናዝቦና አመዛዝኖ ግልፅና ቀጥተኛ መልስ መስጠት  የሚያስችለውን የህሊናችን ሥልጣን (authority) ዝቅ ማድረግ ነው ።

አሁን ባለው የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ (context ) እውነተኛ  ተቀዋሚነት ጠላትነት ወይም  የለውጥ ተቀዋሚነት አይደለም ። ይልቁንም  ግዙፍ መስዋእትነት ያስከፈለው ክፉው የፖለቲካ ሥርዓት  እንደ ሥርዓት ሳይወገድ በሚካሄድ የተሃድሶ ወይም የጥገናዊ ለውጥ (reform) ፍርፋሪ ተመፅዋች  ከመሆን ይልቅ  አዲስና መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተረጋገጠባትና የእኩልነት አገር ባለቤት ለመሆን ፀንቶ የመታገልና የማታገል ፖለቲካዊ ሰብእና ነው ። ተቀዋሚነት የበሰበሰውና ከተጨማሪ ጥፋት በስተቀር የሚያስገኘው በጎ ውጤት የሌለው ሥርዓተ -ኢህአዴግ ተወግዶ በምትኩ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን የመታገልና የማታገል ፖለቲካ እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ቡድናቸው የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ የመቃወም ጉዳይ ጨርሶ አይደለም ።እነሱ ራሳቸው በበሰበሰው ሥርዓትና መወለድ ባለበት አዲስ ሥርዓት ከባድ ግጭት ውስጥ ማድረግ የሚችሉትን (ለራሳቸውም ጭምር ሲሉ) እየሞከሩ ያሉ እንጅ በራሳቸው ሥርዓት አይደሉም ። ሆኖም አያውቅም ። የእኛ የፖለቲካ አስተሳሰብም በእጅጉ የተሳሳተ የሚሆንው ቀልባችን የተሳበው አንድና ሁለት እያልን በምንጠቅሳቸው ፖለቲከኞች (መሪዎች) ላይ እንጅ በእውነተኛው የሥርዓት ለውጥ አስፈላጊነት ላይ ባለመሆኑ ነው።    ስለአገራችን የፖለቲካ ሂደት እጣ ፈንታ ስናወራ ስለፖለቲካ ሥርዓት እንጅ አንድና ሁለት እያልን  ስለምንቆጥራቸው ፖለቲከኞች አይደለም ።  አዎ! ይህ ራእይና ዓላማ እውን የሆነ እለት ነው ለተጨባጩ ሁኔታ ይበልጥ ይስማማል የምንለው የቃላት ምርጫ (ተፎካካሪነት) ከነሙሉ ትርጉሙ እውን የሚሆነው ።

አሁን ባለንበት እውነታ  የትኛው የመፎካከሪያ ሜዳ (ሁኔታ) ነው የተፎካካሪነት ፖለቲካን የሚያስተናግደው? “ተቀዋሚዎቼ ሳትሆኑ ተፎካካሪዎቼ ናችሁ” የሚለው የኢህአዴግ የፖለቲካ ጨዋታ  በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት አስፈላጊነት ላይ መሳለቅ  ነው የሚሆነው። እውነተኛ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ጎልቶ መውጣትን የሚደፍቅ እንጅ የሚያበረታታ ሜዳ (ሁኔታ) ኖሮባት በማያውቅና አሁንም ከቃላት (ከስብከት) የዘለለ ቢያንስ እንኳ በተስፋ ደረጃ መሬት ላይ ጎልቶ የሚታይ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥራ በሌለባት አገር ኢህአዴግና መሰሎቹ “ምርጫ በወቅቱ !” የሚል ዘመቻ መሰል ዲስኩር በየመድረኩ ማላዘናቸው ሌላው ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ነው ።ለነገሩ ተቀዋሚ ተብየዎች “የመዋዕለ ህፃናት ብርቅየዎች” መሆነቸውን አምነው  ተቀብለው ለዚያው ደረጃቸው የሚመጥነውን  ሥልጠና  አጠናቀው  ለምርቃ (graduation)  ባልተዘጋጁበት ሁኔታ ኢህአዴግና መሰሎቹ “የእኛ ድሉ” እያሉ ቢዘምሩ ለምን ይፈረድባቸዋል ?

በተለይ እንደ እኛ ባለ እንኳን ፊደል ያልቆጠረው ፊደል የቆጠረው የአገሬ ሰውም ከፖለቲካ ማይምነት (political illiteracy) ነፃ ባልወጣበት አገር ከተግባር ይልቅ የፖለቲካ ቃላት ጨዋታው የሚቀላቸው ፖለቲከኞች  በተዋቡ የቃላት ጨዋታ የሚዥጎደጉድትን ዲስኩር እየሰማ “ምኞቴ ሰመረ” ቢል  ያሳዝን እንደሆነ እንጅ አያስገርምም ። ለሩብ ከሩብ ክፍለ ዘመን  በጎሳ ዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማእከልነት የተሰባሰቡ ባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ሰለባ ሆነን የዘለቅነው ህብረት ወይም ትብብር ፣ ቅንጅት ወይም ጥምረት ፣ አንደነት ወይም አብሮነት ፣ ፍቅር ወይም የህሊና (የነፍስ) ቁርኝት ከሚሉና ከሌሎችም  ሰፊና ጥልቅ ትርጉም ካላቸው ቃላት (ፅንሰ ሃሳቦች) ይልቅ ለአርቲሜቲክ (ለቁጥር ስሌት) የሚቀርበውን መደመርን መሪ ቃላችን ባለማድርጋችን ከቶ አልነበረም ።  አሁንም አይደለም ። ግን ከሃቁ ጋር ተጋፍጦ ተገቢውን ከማድረግ ይልቅ የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን ያስደሰትን እየመሰለን ተራ የአርቲሜቲኩን ቃል እንደ አዲስና ተአምረኛ ቃል ከአንደበታቸው እየነጠቅን እንደ በቀቀን እንደግመዋለን ።

አዎ!የአያሌ ዘመናት የልኡላዊ አገርነትና የቀደምት ሥልጣኔ ታሪክ ባለቤትነትን ከዘመን ጋር ማዘመን አቅቶን በሁለንተናችን የዓለም ጭራዎችና ተመፅዋቾች ሆነን የዘለቅነው   ተቋሞቻችንን (መሥሪያ ቤቶቻችንን)  የሰላም  የፍቅር፣  የመደመር ወዘተ  የሚሉ ስያሜዎችን ለመስጠት  የቃላት ጨዋታችንን ባለማሳመራችን  ሳይሆን መሆን የሚገባንን ሆነን ባለመገኘታችንና ማድረግ የነበረብንን (ያለብንን) ባለማድረጋችን ብቻ ነው።   ከለውጥ ሂደቱ ጋር አብረው እንዲሄዱ ከማድረግ በስተቀር በመደበኛና መሠረታዊ ሃላፊነታቸውና ተግባራቸው ለውጥ ላልተደረገባቸው (ለማያስፈልጋቸው) የተለያዩ ተቋማት (መሥሪያ ቤቶች) አንድ ጣራ ሥር የጋራ ወይም አስተባባሪ የሚመስል ጽ/ቤት ከፍቶ ከዛሬ ጀምሮ የሰላም ሚኒስቴር”  ተብላችኋል ማለት በእኔ/በእኛ ዘመን የተደረገ ታሪካዊ ለውጥ ነው” ከሚል ደካማ  ፖለቲካዊ  እሳቤ በላይ  ስሜት የሚሰጥ አይመስለኝም ።  በአገር ሃብትና ገንዘብ አጠቃቀም ላይ  ያለው አሉታዊ ውጤት ግን  የሚናቅ አይደለም ። በሁለመናዋ የከፋ ድህነት መናኽሪያ በሆነችና የውጭ ምንዛሬዋን የነዳጅ ሃብት ትልቅ ካደረጋት ከሚጢጢ የአረብ አገር በልመና ብድር “ያሟላች” አገር  ለእንዲህ አይነት እጅግ ቅጥ ያጣ የመሥሪያ ቤት ሥራ ማስኬጃ በጀት መበጀትና  ሌላም ወጭ መመደብ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ። የሰው ሃይልና የፋይናንስ መስዋእትነት መክፈል ቢያስፈልግ እንኳ  ታጠፉ የተባሉ ሌሎች ከኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸው በነበሩበት እንዲቀጥሉ ማድረግ በተሻለ ነበር ።ሰላም መሥሪያ ቤትን “የሰላም” ብሎ በመሰየም ከቶ እውን አየሆንም ።ሆኖም አያውቅም ።

እናም ፖለቲከኞች (መሪዎች) በመሬት ላይ ላለው እውነታ ሳይሆን ስስ ለሆነው (በቀላሉ ለሚሸነፈው) ስሜታችን የሚስማሙ ቃላትን ወይም አባባሎችን  በነገሩን (ባሰሙን ቁጥር) ለምንና እንዴት? ሳንል  እየተቀበልን  የማስተጋባቱ  በቀቀናዊ (parott style) ልማድ ላለንበት በተስፋና በሥጋት መካከል ለተወጠረ የለውጥ ጅማሮ ስኬታማነት አይምጥንምና ልብ ልንለው ይገባል ። ለሩብ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭና ማስፈፀሚያ  ሆኖ የዘለቀው የኢህአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲ የፖለቲካ እምነት ፣  ህገ-መንግሥት  ፣ መርህ ፣ አደረጃጀትና አሠራር  ኢህአዴግ ራሱ እንደ ሥርዓት በቀጠለበት (በሚቀጥልበት) ሁኔታ የቃላት ጨዋታ አጨዋወትን  በማሳመር   መሠረታዊ  ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከቶ እውን ሊሆን አይችልም ። ለሩብ ክፍለ ዘመን እጅግ አስከፊ የሆነው የጎሳ ዲ.ኤን.ኤ ፖለቲካን  በህገ መንግሥት ደንግጎ እና በፖሊሲ ነድፎ   ህዝብን የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ አድርጎ የዘለቀው የአገዛዝ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ወደ ማይቀረው  ከርሰ መቃብር ካልገባ በስተቀር በተዋቡ ቃላትና በጥገና (reform) ፍርፋሪ የትም አያደረስም ።

 

 

Comments — What do you think?