Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር (ለውይይት የቀረበ)

ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር (ለውይይት የቀረበ)

በኢትዮጵያ ስለ ሕገ መንግሥት፤ ስለ ነፃ ፍርድቤት፤ ስለ ሕግ በላይነት፤ ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፤ ስለ ሕዝብ የመምረጥና የመመረጥ መብት፤ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች፤ ስለ ክልል መንግሥት፤ ስለ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ለመገንባት  ለውይይት የቀረበ ልዩ መርሐ ግብር።

Ethiopia, Eritrea map

ወሰኔ ይፍሩ [ፕሮፌሰር]
ናሽቪል; ቴነሲ
ሕዳር  2010 ዓ.ም .

ማሳሰቢያ በእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ ብዙ ነገሮች ተካትዋል፤ የመጀመሬያው ድብዳቤ የተላከው ለተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ መሀመድ ወደ አሜሪካ ለግብኝት በመጡበት ግዜ ነው። ደብዳቤው ጠቅላይ ሚንስተሩ ስለለውጡ ቃል በገቡበት መሰረት “ሕገ መንግሥቱ” ከሁሉ አስቀድሞ መሻሻል እንዳለበት የሚያመልክት ነው። ከአንድ እስከ አራት ክፍል የተጻፈው ድብዳቤ ለመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት አርዕስቶች ላይ ተወያይቶ አዲሱን ሕገ መንግሥት እንዲያጸድቅ በማለት ታስቦ ነው። ግልባጩም ለየክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ለወይዘሬት ብርቱካን መደቅሳ የኢትዮጵያ ብሔራዌ አስመራጭ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ጉዳዩን በቅርብ እንዲከታተሉትና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ በማሰብ ነው። ይህ የሕዝብ ውይይት ከተደረገ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው። ይህንን ከግቡ ለማድረስ ኢትዮጵያዌ ሁሉ መታገል ይኖርበታል። ዲሞክራሲ ያለትግል አይመጣም፤ በአሁኑ ስዓት የተድረገገውን ወንጀል ሁሉ እንዳልተድረገ በማድረግ በተፈጸመው ግዲያ፤ እስር፤ድብደባ፤ ሌብነት፤ ዝርፊያ ሲሳለቁበት ማየት የሰው ልጅ ሆኖ መፈጠርን ያስጠላል፤ ጥቂት ወንበዴዎች በተደረገው ድርጊት ሁሉ እያፌዙ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ይህን ግፍ ሁለተኛ እንዳይደረግ ሕዝብ በቀና ልቦናና በተረጋጋ መንፈስ ሆኖ መወያየትና ወንጄሎኞቹን ወደፍርድ እንዲቀርቡ ማደርግ የእያያንዳችን ኃላፌነት ነው። በተለይ የመገናኛ ብዙሃን የትግሉ አጋር ሆነው መቅረብ አለባችው፤ መልካም አስተዳደር ከሊለ ማንም በሰላም ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ይህንን ጽሁፍ ለሕዝብ በተገኘው መንገድ ማሰራጨት “ታላቅ” የሆነ ታሪካዌ ግዲታ ነው፤

ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አህመድ፤ ለተከበራችሁ የኢትዮጵያ የክልል ርዕሰ መስተዳድር፤ ለተከበሩ ወይዘሪት ብርቱካን መደቅሳ የብሔራዌ አስመራጭ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ። ከሁሉ አስቀድሜ የከበረ ሰላምታዮን አቀርባለሁ።  ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተሩና ለመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ የጻፍኩትን ግልጽ ደብዳቤዎች አባሪ በማድረግ ለክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርና ለወይዘሪት ብርቱካን መደቅሳ የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ለሚካሂደው ለውጥና ወደ ፊት ለሚደረገው ምርጫ ለሕዝብ የቀረበዉን የውይይት አጀንዳ በታላቅ አክብሮት አቀርባለሁ። በደብዳቤዎቹ ላይ በዝርዝር እንደተጻፈው አሁን በሂደት ላይ ያለው ለውጥ በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የያዘ ነው። ውይይቱም በመላው መስተዳድር ውስጥ በሕዝብ ተካሂዶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በናፍቆት የሚጠብቅውን “መልካም አስተዳደር” ያመጣል ብሎ በማሰብ ነው።

ወደ ውይይቱ ከመግባታችን በፊት “የክልል መስተዳድር” ተብሎ ስለሚጠራው መንግሥት አጠር ያለ ውይይት ማደርግ አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ ውይይቱ ስለ “ክልል” እንጂ ስለ “ርዕሰ መስተዳድር” አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ “በክልል” የተገደቡ ብዙ አገሮች ለምን አስፈለጉ? እዚህ  ላይ ሕዝብ በቅጡ እንዲገባው “ክልል” የተባልውን ቃል ምን እንደሆነ መወያየት አስፈላጊ ነው። “ክልል” ማለት በአካባቢው ከአሉት ስፍራዎች “ተከልሎ” ለብቻው የቆመና ራሱን አግሎ የሚኖር ማለት ነው። ርዕሰ መስተዳድር ተብሎ ቢሰየምም እንደ መንግሥት ሆኖ ሊቀንሳቀስ አይችልም፤ ከባላይ አስተዳዳሪ አካል ስለአለበት ተጠሪነቱ ለእሱ ነው፤ ምንም አይንት ስልጣን የለዉም፤ ስለተከለለም  ከጎረቢቱም ሆነ ከሊላ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግ አይችልም። የዚህ “ክልል” ጽንሰ ሃሳብ የመጣው የቅኝ ገዥዎች ታዳጊ አገሮችን ከፋፍለው ለመግዛትና ለኢኮነሚው ጥቅማቸው ብለው የተጠቀሙበት ዘዴ ነው። ለምሳሌ የበርሊን ጉባኤ [The 1884/85 Berlin Conference] ተብሎ የሚጠራው ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ በአጠቃላይ የአፍሪቃ አገሮች “በክልል” ተከፋፍለው አንድነት እንዳይኖራቸውና በአንድ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይግባቡ የተደረገበት “ሁኔታ” ነው። በዚሁ አይነት በደቡብ አፍሪቃ “የአፓርቴይድ” [Apartheid] ስርዓት በሕግ ተደንግጎ አፍሪቃውያን በገዛ አገራቸው ከኢኮነሚውና ከፖለቲካው ድርሻቸው ላይ የተገለሉበት “ሁኔታ” ነው [ For instance see the history of South Africa Segregation Acts such as: “ The Franchise and Ballot Act of 1892;” The Natal Legislative Assembly Bill of 1894”; “ The General Pass Regulations of 1905”; “ The Asiatic Registration Act of 1906”; “ The Native Act of 1913 –Apartheid”] እነዚህ ሁሉ “አዋጆች” የሚያመለክቱት “ክልልን” ነው። አፍሪቃዌ ከተከለለበት ቦታ በስተቀር ወደሊላ ሊሂድ አይችልም፤ ይህንን ሕግ ከተላለፈ ቅጣቱ ከባድ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሞት ነው፤ ከሚሊዮን የሚበልጡ ዜጋዎች ተወልደው ከአደጉበት አገር ተፈናቅለዋል፤ ተገድለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ስለዚህ ነው የአሚሪካ ሕዝብ የዓለም አቀፍ ሬድዮ ዜና [ NPR- the worst human Rights Violations in the planet: Report 12/5/2018] በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ የሰው ልጅ ሰብአዌ መብት ጥሰት ብሎ የዘገበው። ቬኒቶ ሙሶለኒ ኢትዮጵያ ውስጥ ጎሳዎችን ከፋፍሎ “የክልል” አገዛዝ ለማምጣት ዕቅድ ነበረው፤ ኢሕድግ አሁን በፌዲሪሽን ስም በጥቅም ላይ ያዋለው የሙሶሊኒ ዕቅድ ነው። ይህንን ዕቅድ ሕዝብ ተወያይቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን መልሶ ማስከበር አለበት፤ ይህም መሆን ያለበት በውይይት ነው።

ለጠቅላይ ሚንስተሩ በተላከው ደብዳቤ ላይ የመጀመሪያው ጥያቄ “ሕገ መንግሥቱን” በሚመለከት ነው [ደብዳቤ ውን ይመልከቱ]። የወይዘሪት ብርቱካን መደቅሳ የምርጫውን ቦርድ መምራት ታላቅ ኃላፊነት ነው።ነገር ግን ከሁሉ አስቀድሞ “ሕገ መንግሥቱን” የሚያረቅ ኮሚሽነር ተሰይሞ ስራውን ከአልሰራ የምርጫ ቦርዱ ስራ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤ ሕጉ ተረቆ በብሔራዌ ሽንጎ ከአልጽደቀና የምርጫው ደንብ በሕግ ከአልተደነገገ፤ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ፍርድ ቤት ከሊለ፤ የመገናኛ ብዙኃን ከፖለቲካ ነፃ ከአልሆነየምርጫ ጣቢያዎች በክልል ሳይሆን በጂኦግራፊ ወይም በአውራጃ ወይም በወረዳ ወይም እንደቀድሞም በክፍለ ሐገር ደረጃ በሕዝብ ስምምነት ከአልተደራጀ [በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥናቶች ስለተደረጉ ሕዝብ የመረጠዉን መስተዳድር መቀበል ግዲታ ነው] ሕዝብ የሚፈልገዉን ከራሱ ውስጥ ሊመርጥ አይችልም። በክፍል አራት ላይ እንደተጠቀስው የምርጫው ሂደት በምርጫ ቦርዱ በግልጽ መቀመጥ አለበት፤ ከሶስት የማያበልጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና አግኝተው እንዲወዳደሩ ማደርግ የምርጫው ቦርድ ኃላፊነት ነው፤ ለምሳሌ “የወጣቱ” “የሰራተኛው” “የአርሶ አደሩ” የኢትዮጵያን ችግር ሙሉ በሙሉ ስለሚያጠቃልሉ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በእነዚህ ፓርቲዎች ስር ሊጠቃለሉ ይችላሉ። ፖለቲካ ፓርቲዎች በየቀበሌው ተወዳድረው “በማጣራያው” እና “በማለፊያው” አልፈው ለሕዝብ ምክር ቤት [ለመምሪያና ለመወሰኛው] መመረጥ ይችላሉ። ለፕሪዚዳነትም የሚወዳደሩት በማጣሪያውና በማለፊያው አልፈው ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ ሁለት ተወዳዳሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲወዳደሩ ማድረግ። ይህ ሊሆን የሚችለው የአሜሪካን ሞዴል ከተመረጠ ነው፤ ሌላም ሞዴል ከአስፈለገ ለሕዝብ ቀርቦ በወይይት መወሰን ይኖርብታል። እነዚህ ሁሉ ስራዎች በተባለው ሁለት ዓመት ውስጥ ተሰርቶ ስለማይጠናቀቅ አስፈላጊው ጊዜ ተጨምሮ በጥንቃቄ መሰራት ይኖርበታል። እውነተኛ ዲሞክራሲን ለመመስረት ቢያንስ አምስት ዓመት ሊወስድ ይችላል፤ ይህንን የጊዜ ገደብ የምርጫ ቦርዱ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ተወያይቶ መወሰን ይኖርበታል።

ስለ ሕገ መንግሥት ሂደት፦ ሕገ መንግሥቱ በሕግ ባለሙያዎች ተረቆ ለብሔራዊ  ሽንጎ ለውይይት መቅረብ አለበት፤ በየቀቤለው፤ በየወረዳው፤ በየአውራጃው፤ በሕግ አርቃቂው ኮሚሽነር አማካይነት ሕዝብ ተወያይቶ በድምጽ ይጸድቃል፤ በከፍተኛ ድምጽ ከጸደቀ የአገሩ “ሕገ መንግሥት” ተብሎ ይታወጃል። የዚህ ሕገ መንግሥት የበላይነት ታውቆ ማንም ሰው ቢሆን ከዚህ ሕግ በላይ መሆን ያለመሆኑን ማሳወቅና ማስተማር አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የአገራችንን ሕግ አክባሪነት ነው፤ በተለምዶና በባሕላችን እኛ ኢትዮጵያዊያኖች እንዲህ እንላለን “ በሕግ አምላክ ሲባል እንኳንስ ሰውና ውሀም ይቆማል” ይባላል ። በየጎሳችን ውስጥ መልካም የሆኑ ስርዓቶች አሉን፤ ለምሳሌ የኦሮሞ ገዳ ስርዓት፤ የአማራ ፍትሕና ፍርድ፤ የጉራጌ ማሕብረሰባዊነት፤ የሲዳማና የከምባታ አገር ወዳድነት፤ ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ ጎሳዎች በባሕል አንድ ብሔር የሚያደርጋቸው ስለሆነ ሊከፋፍላቸው የሚችል ኃይል የለም፤ ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እስክ ዛሬ ድረስ አትኖርም ነበር።

የብሔራዌ ቋንቋ፦ በሕገ መንግሥቱ የብሔራዊ ቋንቋ መታወጅ አለበት፤ አንድ አገርን ነፃ የሚያደርገው የራሱ የሆነ የመሥሪያ ቋንቋ ሲኖረው ነው፤ አማርኛ በዙዎቹ እንድሚያስቡት አይደለም፤ በብዛት የኢትዮጵያ ጎሳዎች የሚናገሩት ቋንቋ ነው፤ ከዚያም አልፎ በጽሁፉም ሆነ በንግግር ሁሉም ጎሳዎች በእኩልነት ከዚያም አልፎ በማቀላጠፍ  የሚጠቀሙበት ከአማራ በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ቋንቋው የዳበረና ጥንታዌት ስለሆነ ለአገር እንደቅርስ ሆኖ መታየት አለበት፤ ከዚያም ሌላ ፊደሉ ጽንፈኞችና ዘውገኞች እንደሚሉት ሳይሆን የዳበረው ከአምስት ሺህ ዓመት በፊት በአባይ ሸለቆ በሚኖሩ በግዜው “ከሜት” በሚባሉ አፍሪቃውያን ነው፤ እነዚህ አፍሪቃውያን ፊደል እንፍጠር ብለው ሳይሆን እርስ በርሳቸው ሊግባቡበት የሚችል ምስል በመሳል [pictorial image]ያዳበሩት የመግባቢያ ምልክት ነው፤ ለምሳሌ አይን ለማለት የአይንን ምስል ይስላሉ፤ በቋንቋቸው “አይን” ማለት [እንደ ግዕዙ] አይን ነው፤ ስለዚህ የአይንን “መነሻ”[ግዕዝ-Consonant] ፊደልን “አ” ማለት ይሆናል፤ “ቤት” ደግሞ በቋንቋንቸው እንደ ግዕዙ “ቤት” ነው፤ በሰእል “የቤት በር” የሚያሳየው ቤት ነው፤ ከዚያ ላይ “በ” የሚባለው ፊደል ይወጣል፤ እንደዚህ እያለ ነው ፊደሎች የተፈጠሩት፤ ግዕዝ፤ ኢብራይስጥና ሌሎቹም ለምሳሌ [Moabite,Canaanite, Phenician,Akadian Aramaic,Palmyrian, Samaritan, Syriac, Nabatean, Arabic and Latin]. እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ቋንቋዎች ፊደላቸው የመጣው በዚህ አይነት “ሁኔታ” ነው፤ አማራ ፊደልን አልፈጠረም ከሳባዌያን የወሰደውን ፊደል አዳብሮ ይጽፍበታል [ see reference about the origin of the script at the end—The Nile Valley civilization]. አማርኛና ፊደሉ የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው፤ ሁሉንም ጎሳዎች ሊያስተባብር የሚችል መሳሪያ ነው፤ ይህ ማለት ሌሎች የጎሳ ቋንቋዎች ይጥፉ ማለት አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጎሳ ቋንቋዎች እንዳይጠፉ መንከባከብ አስፈላጊ ነው፤ ትምሕርት ቤትም የሁሉም ጎሳ ተማሪዎች እንዲማሩት ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ የአገር ቅርስ ስለሆኑ መጠበቅ አለባቸው። የብሔራዌ ቋንቋ ሕዝብ ተወያይቶበት መወሰን አለበት።    

የመንግሥት ኢኮኖሚክ አቋሞች ሕዝብ ተወያይቶ የሚወስነው ጉዳይ ስለሆነ አሁን በስልጣን ያለው መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ መውሰድ የለበትም። 

በክፍል አራት ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው ተሰሩ ለተባሉት ወንጀሎች ኢሕአዴግ በአዋጅ ምሕረትም ሆነ ይቅርታ ሊያደርግ አይገባም። በሕገ መንግሥቱ መሰረት አዲስ የተመረጠው መንግሥትና ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ፍርድ ቤት ብቻ ነው ዳኝነቱን መስጠት የሚችል።

በመጨረሻ አሁን በአመራር ላይ ያሉት ከግንዛቤ ሊያስገቡት ነገር ቢኖር  የአለፈዉን “ታሪክ” ነው፤ በሁለተኛው ክፍል ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀስው በአለፈው ሶሥት ትውልድ [90 ዓመት] በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሂደውን የፖለቲካ ሂደት ነው፤ በየግዜው የተፈጠረው “ሁኔታ” መልካም አስተዳደርን ማምጣት የሚያስችል ነበር። ነገር ግን ይህንን “የታሪክ” አጋጣሚ ትውልዱ አልተጠቅመበትም። አሁን ያለው “ሁኔታ” ከምንም ግዜ በፊት “ታሪካዊ” ነው፤ መልካሙ ትውልድ በመክራ ተፈትኖ ተወልዷል፤ ብዙ ሕዝብ መስዋዓትነትን ክፍሏል፤ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ወንጀል ተሰርቷል፤ ይህንን “የታሪክ” አጋጣሚ ተጠቅማችሁ “ለመልካም አስተዳደር” ብትቆሙና ስልጣንን ለሕዝብ ብታስረክቡ ሕያውነትን ትጎናጸፋላችሁ። ኢትዮጵያ በሕዝቧ ጸንታ ለዘለዓለም በክብር ትኑር። መልካም ውይይት።

2 comments

  1. እጅግ ጠቃሚ መረጃ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፈተናዎች፤ ያለፉትን ችግሮች አስተውሎ መፍትሔዎቹ ላይ በጋራ ከመስማማት እና ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ሁሉንም ነገር የራስ “የግል” አድርጎ መፍትሔው እኔ ብቻ ነኝ ካልሆነ አፈርሳለሁ “ፉከራ” ነው። ይህ ችግር ያለው ነጻነትን ታግሎ በሚያመጣው ሕዝብ መካከል ሳይሆን፤ ከመስዋዕት በኋላ ፊት ለመሆን “ጥምብ” እንዳየ ያረጄ “ጅብ” በሚሽቀዳደሙ ሸንካላና “ሰነፍ” ግለሰቦች መካከል ነው። እነዚህ ግለኞች፤ ነገሮችን መረዳት አይፈልጉም፣ ትእግስት የላቸውም፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የራቃቸው ጨካኞች ናቸው፣ መሆን የማይችሉትን “ሁልጊዜነት” ያልማሉ፣ የዕውቀት ጠላቶችና መግባባትን ፈሪዎች ናቸው።
    ዶ/ር ወሰኔ፤ የምታቀርባቸው ሃሳቦች በእኔ ችሎታ የተስማሙኝ ሲሆን፤ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች ተጫማሪ አርገው ለመነጋገሪያ ቢያቀርቡት ተደጋፊነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።

  2. ለሀገርና ለትውልድ የሚበጅ እጅግበጣም ጥሩ አቅጣጫ የሚያመለክት ድንቅ ሀሣብ ነው::

Comments — What do you think?

%d bloggers like this: