Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » በኢትዮጵያ የመፈናቀል ችግርና የመፍትሄ ኣሳብ (ገለታው ዘለቀ)

በኢትዮጵያ የመፈናቀል ችግርና የመፍትሄ ኣሳብ (ገለታው ዘለቀ)

ገለታው ዘለቀ

Displaced Amhara people from Benishangul-Gumuz Zone.

መግቢያ

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዛሬይቱ ዓለማችን ወደ 40 ሚሊዮን ሰዎች በገዛ ሃገራቸው ውስጥ ተፈናቅለዋል ይባላል። ዘወትር ችግር ከማያጣው የሰሃራ በታች ቀጣና ደግሞ ወደ 8.1 ሚሊዩን ሰዎች ባሳለፍነው ዓመት ብቻ የተፈናቀሉ ሲሆን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ የእኛው ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሃገራት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የሰብ ሰሃራ ሃገራት የመፈናቀል መንስኤ ከሌላው ክፍለ ዓለም የሚለየው በዚህ ሪጅን ብዙው ሰው የሚፈናቀለው በግጭቶች ሲሆን በሌላው ዓለም ግን የተፈጥሮ ኣደጋ ዋና መንስኤ ሆኖ ይታያል። ሰብሰሃራ ውስጥ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ ከተፈናቀለው 8.1 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 5.5 Million (68%) ያህሉ ሰው ሰራሽ በሆነ ግጭት የተፈናቀለ ነው። ምስራቅ ኤሽያ እና ፓሲፊክ ሪጅን ዘጠኝ ሚሊዮን    ሶስት መቶ አምስት ያህል ሰው የተፈናቀለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ  8.6 Million የሚሆኑት በተፈጥሮ ኣደጋ የተፈናቀሉ ናቸው። በግጭት የተፈናቀሉት 705,000 ወይም 7.5% ያህሉ ብቻ ናቸው። በዚህ ሪጅን ለመፈናቀል የተፈጥሮ ኣደጋ ዋና ጉዳይ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሰብ ሰሃራ ኣገራት ዋናው ምክንያት ሰው ሰራሽ ግጭት ሆኖ ይታያል።

በዚህ በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ መፈናቀል በከፍተኛ ደረጃ ኣድጎ ከሶርያም በልጦ የዓለምን ሪከርድ ሰብሮ እንደነበር ብዙ ተቋማት ዘግበዋል። የኖርዌይ ረፊውጂ ተቋም እንደገለጸው በ 2018 ዓመተ ምህረት በውስጥ መፈናቀል ኢትዮጵያ  ከዓለም ሃገራት ቀዳሚ ስፍራ ይዛለች ብሏል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መፈናቀል እያደገ የመጣና እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። በየጊዜው ያድጋል። በዚህ በዛሬው ጽሁፌ ለማየት የምሞክረው ይህ ኣሳሳቢ ችግር መንስኤው በዋናነት ሲስተሚክ መሆኑን ለማሳየት:: መፍትሄው ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ አማራጭ ሃሳብ ለማቅረብ ነው። በርግጥ ስለመፈናቀል ስናነሳ የኢትዮጵያ ችግር የውስጥ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን አገር እየጣለ የሚጠፋው ለበረሃ የተዳረገው፣ በየውቅያኖሱ የሚቀረው ወገናችን ኣያሌ ነው። በዓለም ላይ ዓለምን በፍልሰት ካስጨነቁ ሃገራት መካከል ከአፍሪካ ኢትዮጵያና ኤርትራ ቀዳሚ ናቸው። በየቀኑ በተለይ አምራቹ ወጣት አገር ጥሎ ይተማል። በሱዳን በኩል ብቻ በየቀኑ እስከ መቶ ሰው ድረስ ድንበር እያቋረጠ ይወጣል። በርግጥ ግን በዚህ በዛሬው ውይይታችን በጥልቀት የምንመረምረው የውስጥ መፈናቀል ጉዳይን በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እንወያያለን። ኢትዮጵያውያን በአንድ በኩል ኣገር ጥለው እየጠፉ ይህ እያሳዘነን እያለ ስለምን ነው እንደገና በገዛ ሃገራቸው ያውም በማንነታቸው የሚፈናቀሉት? የሚለውን ዛሬስ አምርረን ልንወያይበት ይገባል።

በሃገራችን የሚታየው የውስጥ መፈናቀል ጉዳይ በተለይ ከስርዓቱ ጋር መያያዙን  በጥልቀት ማጥናት ስንጀምር በተለይ በፌደራል ስርዓቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁለት የሚጋጩ ኤለመንቶችን እናያለን። እነዚህ ሁለት ኤለመንቶች በፌደራል ስርዓቱ ውስጥ ዘና ብለው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ተቃራኒ ሃይላት አላቸው። እነዚህ ተቃራኒ ሃይት ሳቢና ገፊ ሃይላት ሆነው እናገኛለን። እንዴት በሲስተሙ ውስጥ እነዚህ ህጎች እንደሚሰሩ እንመልከት።

በተፈጥሮ ሳይንሳዊ የሆነ የፌደራል ስርዓት በደም ስሩ ውስጥ ሳቢ የሆነ ሃይል እናገኛለን። ስቴቶች ሲፈጠሩ እነዚህ በትልቁ ጠገግ ስር የሚኖሩ ክፍሎች ሁሉ ቤታቸውን ለማሳመር የሚተጉት ክፍላቸው ለዜጎች ሁሉ ምቹ እንዲሆን ዜጎች በምቾቱ እንዲሳቡ ነው። በሚሰሩት ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩና ወደፊትም በዚህ ክፍል ውስጥ መጥተው መኖር ለሚጀምሩ ሁሉ ሳቢ ሁኔታን ይፈጥራል። የስቴቶች ፍክክርም የበለጠ ምቹ በመሆን ሳቢ ሆኖ ለመገኘት ነው። በምንም ዓይነት ገፊ የሆኑ ከባቢዎች በስቴቶች ክፍል ውስጥ እንዳይኖር የፌደራል መንግስትም ስቴቶችም ጠንክረው ይሰራሉ።

ወደ ሃገራችን የብሄር ፌደራል ስርዓት ስንመጣ ሁለት ግዙፍ ችግሮችን እናያለን።

 1. በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ውስጥ ሳቢ ሃይሉ (pulling force የምንለው) በተገቢው መንገድ አልተገጠመም (Install አልተደረገም)
 2. ሳቢ ህጉ ወይም ሃይሉ በትክክል ስላልተገጠመ ሌላ ገፊ ሃይልን (pushing force) ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ በፌደራል ስርዓታችን የደም ስር ውስጥ ሳቢና ገፊ ሃይሎች አየተጋጩ የሚንቀሳቀሱበት ስርዓት አድርጎብናል።

ከፍ ሲል እንዳልነው በአንድ የፌደራል ሃገር ጠገግ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ በሚኖሩት የፖለቲካ ዩኒቶች ውስጥ ሳቢ ኤለመንቶች መኖር ኣለባቸው። ሳቢ ኤለመንት ማለት በአንድ የሃገር ጠገግ ስር የሚኖሩ የፖለቲካ ዮኒቶች በሚኖራቸው ህግና ኣሰራር በአጠቃላይ በሚፈጥሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ከባቢዎች ዜጎችን ሁሉ የሚስብ ነገር ሊኖራቸው ይገባል። በሃገሪቱ ጠገግ ውስጥ ባሉ ዜጎች ዘንድ የሚፈጥረው ስበት አብሮ መኖርን ያበረታታል። ብሄራዊ ማንነትን ያጎለብታል፣ ይመለከተኛል ወይም እኔም ኣለሁበት (sense of belongingness) ስሜትን በዜጎች ህይወት ያዳብራል። የፌደራል ስርዓት ሲቋቋም ይህ ስርዓት የተለያዩ ስቴቶችን ይመሰርትና እነዚህ ስቴቶች የየራሳቸውን ህገ-መንግስት ኣውጥተው በራሳቸው ህግ ይተዳደራሉ። ስቴቶቹ ደግሞ በሶሻል ወል ፌር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበራዊ ኣገልግሎት፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መልካም ፍክክር ያደርጋሉ። ይህ ፍክክር ለዜጎች ሁሉ ምርጫን ይሰጣቸዋል። የፍክክሩ ኤነርጂ የሚፈጠረው ግጭትን ለማምረት ሳይሆን ስበትን ለማምጣት ለአጠቃላይ ለዜጎች እድገት ስለሚረዳ ነው። በእውነተኛ የፌደራል ስርዓት ውስጥ እያንዳንዱ ስቴት ቤቱን ወይም ክፍሉን ምቹ ለማድረግ የሚተጋው ለዜጎች ነው እንጂ ለሆኑ ዘውጎች ኣይደለም። የፌደራል ስርዓት ኣንዱ ትሩፋት ይህ ነው። ዜጎች ተስበውበት በሄዱበት ስቴት የሚገፋቸው ፋክተር (Pushing factor) እንዳይኖር ጥንቃቄ ይደረጋል። ገፊ የሆነ ኤለመንት እንዳይኖር ከፍተኛ ህጋዊ ከለላ ዜጎች ይጎናጸፋሉ። በመሆኑም ስርዓቱ በሳቢ ጉዳዮች ብቻ እንዲሞላ ጥረት ይደረጋል።

ወደ ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ስንመጣ ግን የስበት ህጉ የተለየ ከመሆኑም በላይ በስርዓቱ ደም ስር ውስጥ ገፊ (push) ኤለመንቶችም ዘና ብለው ይንቀሳቀሱበታል።  በስርዓቱ ውቅር ጊዜ ከመነሻው የስበት ህጉ ሲፈጠር ማንነትን መሰረት ያደረገ ነበር። ሁሉም ወደራሱ ማንነት እንዲሳሳብ ነው የተፈለገው:: ማንነት በፖለቲካ ዮኒት ውስጥ ዋና ሳቢ (puling force) ህግ ሆኖ ስርዓቱ ሲዋቀር ይህ ማንነትን መሰረት ያደረገው የስበት ህግ በራሱ ማንነትን ከሚገልጽበት ራስ (self) ውጭ የሆኑትን ማንነቶች የሚገፋ ሃይልን ፈጠረ ማለት ነው። በርግጥ ስርዓቱ ሲዋቀር ገፊ የሆነ ስበት እንፍጠር በሚል ኢንቴንሽን ዝንባሌ ላይሆን ይችላል። ስርዓቱን ስናዋቅር መሳሳቡን በብሄር ማንነት ላይ እናድርግ ሲባል ይህ የብሄር መሳሳብ በብሄር ማንነቶች መካከል ሌላ ገፊ ሃይልንም እንደሚያመርት ካለማየት ይሆናል። ማንነትን ለመጠበቅ የብሄሮችን መብት ለመጠብቅ ይሆናል ኢንቴንሽኑ ወይም ዝንባሌው። ነገር ግን ይህ የስበት ህግ በየዩኒቶቹ መካከል ገፊ ፋክተር በመፍጠሩ የፌደራል ስርዓቱ ሳቢና ገፊ ኤለመንቶችን እያጋጨ እያላተመ እንዲሄድ ኣደረገው። እነዚህ የመሳሳብና የመገፋፋት ህጎች በአንድ ጊዜ በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ ሲፈጠሩ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭትን በሰፊው ታየ። ተመሳሳይ ማንነቶች ሲሳሳቡ ሳይፈለግ ሌሎች ማንነቶችን የሚገፍ ተቃራኒ ሃይል መነጨ:: ስርዓቱ ማንነትን እያጋጨ እገጭ እጓ እያለ ሲሄድ የማንነቶች ግጭት አንዱ መገለጫ መፈናቀል ሆኖ ተገኘ ማለት ነው። ምክንያቱ የመሳብ ሃይሉ በፌደራል ስርዓቱ ደም ስር ውስጥ በትክክለኛው መንገድ ባለመገጠሙና ሳይታሰብ የግፊያ ሃይል ስላመረተ ነው። መፈናቀልን፣ ግጭትን አምራች የሆነ የፌደራል ስርዓት ገነባን ማለት ነው። በመሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ በድንበር ጥያቄ ብሄሮች የሚጋጩት የፌደራል ስርዓቱ ማንነትን ከመሬት ጋር ስላጣበቀ ነው። ስርዓቱ በፈጠረው ከባቢ ችግር የተነሳ አካባቢና ማንነት ስለተጣበቁ፣ አካባቢያችንን ለብሄራዊ ማንነት ስላልሰዋን በድንበር እንጋጫለን። በዚህ ዓመት ብቻ በምእራብ ጉጂና በጌዲዖ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት 1,391,000 ሰው ተፈንቅሎ እንደነበር Internal Displacement Monitoring Center ዘግቧል። displacement and conflict producing federal system.

ስርዓቱ ሲዋቀር ማንነትን ስለሚስብ ተማሪዎች ተምረው ወደ ብሄራቸው የመሳብ፣ ነጋዴው ኣትርፎ ወደ ብሄሩ የመሳብ፣ ምሁሩ ተምሮ ሊቅ ሲሆን የብሄሩ ለሂቅ ለመሆን የአካባቢውን ችግር እያጠና ለመፍታት እንዲህ ያለ መሳሳብን ሲፈጥር በየክልሉ ተሰባጥረው በሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ዘንድ የመግፋትን ሃይል ኣመረተ። ባለ ብዙ ብሄሮችን (dual ethnicity) ይህ የማንነት መሳሳብ ወጣጠራቸው ሊገነጣጥላቸው ተነሳ ብሄራዊ ማንነትን የሚደፈጥጥ የብሄር ጡንቻዎችን አመረተ። በተለይ ድሃው ገበሬና የወላጆቻቸውን መምጫ ጠንቅቀው የማያውቁ ዜጎችን ኣደጋ ላይ ጣለ። ከሁሉም በላይ በሃገሪቱ የሰው ሃይልና የካፒታል ንቅናቄን ገደበ። ስበቱ ማንነትን በመሆኑ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ኣካባቢ ሄዶ ለመስራት ኣስቸጋሪ ሁኔታን ፈጠረ። ስርዓቱ ማንነትን የሚስብ ማንነትን የሚገፋ የስበትና የግፊያ ህግ ስለያዘ ኣንዳንድ ኣካባቢ ግጭቶች ሲነሱ ኢትዮጵያውያንን ለማፈናቀል ዋና መንስኤ ወይም የመንስኤ መንስኤ ሆኖ ወጣ። ኢትዮጵያውያንን ከቀያቸው አፈናቃይ ስርዓት ሆኖ ቀረ። ከዓለም የሚለየን ይሄ ነው። መፈናቀልና ግጭት በጅጉ ስርዓታዊ ከመሆናቸው ጋር መያያዙ ከሌላው ዓለም መፈናቀል መንስኤ ይለየናል።

መፈናቀል የሚባለው ነገር በሁለት ይከፈላል። አንደኛው የምኞት መፈናቀል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአካል (physical) መፈናቀል ነው።

የምኞት መፈናቀል ማለት የሰው ልጅ በብዙ ገፊ ሁኔታዎች ሲከበብ የሚኖርበትን ቀየ ጠልቶ ልቡ ውጭ ሲያድር ነው። ይህ ሰው ገፊ ነገሮች እየገፉት የሚኖር፣ ጥሎ ለመሄድ ወቅት የሚጠብቅ፣ የአካባቢው ባለቤትነት ስሜት (Sense of belongingness) የጠፋበት ሰው ነው። የስነ ልቡና ተመራማሪዎች ለሰው ልጅ Sense of belongingness  ልክ እንደ ምግብና ውሃ ነው ይላሉ። በሚኖርበት ኣካባቢ የሚገፋው ከባቢ ካለ ምሉእ ሰው አይሆንም።  ይህ ሰው በሃሳብ ተፈናቅሎ ሲኖር ምርታማ ኣይሆንም። በአካል እዚህ ብናየውም በሃሳብ ተፈናቅሏልና ይህንን እንደመፈናቀል ልናየው ይገባል።

ዶክተር አክሎግ ቢራራ “ድርጅታዊ ምዝበራ” በሚለው መጽሃፋቸው  ላይ 76 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት መሰደድን ይመኛል ይላሉ። ይህን የሚያህል ሰው ብን ብሎ መጥፋት ካሰኘው አልተፈናቀለም አገሩ ሰላም ነው አይባልም። የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ለምኞት መፈናቀል መጥፎ ከባቢ ፈጥሯል። በየክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ከሚያዩት ገፊ ነገሮች የተነሳ መሰደድን እየተመኙ ሊኖሩ ይችላሉና በዚህ ረገድ ስርዓቱ ኣደጋ ነው። በሌላ በኩል ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ለመሄድ ያለው የምኞት መሳብ በስርዓቱ ውስጥ በጣም ዝቅተኛ ነው። የስርዓቱ መሳሳብ በማንነት ላይ ያተኮረ ስለሆነ በዜጎች የመነቃነቅ ምኞት ላይ ሳንካ የፈጠረ ስርዓት ነው። ለምሳሌ አንድ ወለጋ የሚኖር ኦሮሞ እስቲ መቀሌ ሄጄ ልኑር ስራ ልፈልግ ብሎ እንዲመኝ የሚያደርግ ሳቢ ስርዓት የለም። ይህ ሰው በሃሳቡ ትግራይ የበለጠ ለምታለች፣ የተሻለ የስራ እድል አለ ብሎ ያምን ይሆናል። ነገር ግን ወደዚያ ክልል ለመሄድና ለመስራት ኣይሳብ ይሆናል። ምክንያቱ የኢኮኖሚ ስርዓቱ፣ የፌደራል ስርዓቱ ማንነት ላይ ስበቱን ስላደረገበት ነው። ስለዚህም ትግራይ ውስጥ የተተከለ አንድ ፋብሪካ ተነቅሎ እሱ ሰፈር እንዲመጣ ቢመኝ ይቀለዋል። ስርዓቱ የፈጠረው ስሜት በዚህ ደረጃ ብዙ ግጭቶችን የያዘ ነው። ሶማሌው ኦሮምያ ክልል ሄዶ ለመኖር፣ ጉራጌው ጋምቤላ ሄዶ ለመኖር የሚመኘው ምኞት ላይ ሳንካ ያለው ስርዓት ነው የፌደራል ስርዓቱ። ክልሎች የሚያወጧቸው ህጎች ያሏቸው ህገ-መንግስቶች ሁሉ ንቅናቄን ይገድባሉ። ለምሳሌ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ-መንግስት ይህ ክልል በዋናነት የአራት ብሄሮች ብቻ መሆኑን ይገልጻል:: ሌሎችን ሳቢነት የለውም። ይህ ህግ በራሱ ገፊ ነው። በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ የሃይማኖት ድርጅቶች ሁሉ ፕሮግራሞቻቸውን በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲያደርጉ የሚለው ዜና ገፊ ነው። በአጠቃላይ ዜጎችን በምኞት የሚስብ ወይም የሚያማልል ስርዓት ፍሬ ከብሄር ፌደራል ስርዓት ዛፍ ኣይለቀምም።

ሁለተኛው መፈናቀል በተግባር ሰው ቤቱን ጥሎ እንዲሄድ የሚያስገድደው የመፈናቀል ኣይነት ነው። ከፍ ሲል እንዳልኩት ሃገራችን በዚህ የዓለም መሪ የሆነችው ኢትዮጵያውያን ኣብሮ መኖር ስለሚያቅታቸው ሳይሆን ስርዓቱ ገፊ ኤለመንቶችን ያመረተ በመሆኑ ነው። በቅርቡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ተወላጆች ኦሮምያ አካባቢ ተገደሉ የሚለው ዜና ሲሰማ ቤንሻንጉል አካባቢ ያሉ ኦሮሞዎችና ኣማሮች ተፈናቅለዋል። ወደ ዘጠና ሺህ ህዝብ ነው የተፈናቀለው። በዚህ ግጭት ውስጥ የመንስኤውን መንስኤ ስናይ  ስርዓቱ ነው። በቀሉ በመደባደብ አይወጣለትም:: ከአካባቢ እስከማፈናቀል  ይሄዳል። በቀሉ አካባቢያችንን ልቀቁ በሚል በማፈናቀል ነው የተገለጸው። ተፈናቃዮቹም ስርዓቱና የክልሉ ህገ መንግስት የክልሉ ባለቤት ስላላደረጋቸው ዝም ብለው ይፈናቀላሉ። የዚህ ስርዓት ችግር ግጭቶችን ሁሉ ከማንነት ጋር እንዲያያይዝ የሚያደርግ በመሆኑ ማንነት ዋና የፖለቲካ ዮኒቶች መጫወቻ በመሆኑ ችግሮች ሁሉ ወደ መፈናቀል እንዲያመሩ ያደርጋል።

ሌላው ባለፉት ጊዚያት በተለይ ይታይ የነበረው መፈናቀል ደግሞ የመሬት ነጠቃን መሰረት ያደረገው ነበር። በተለይ በጋምቤላ፣ በኦሮምያ፣ አዲስ ኣበባ ዙሪያን ጨምሮ የታየው ችግር ደግሞ ልማት የሚገፋቸው የሚያፈናቅላቸው ሰዎች ጉዳይ ነው። ይህ ችግር ምንም እንኳን ከፌደራል ስርዓቱ ጋር በቀጥታ የማይገናኝ ቢሆንም ለኢትዮጵያውያን መፈናቀል ግን መንስኤ ሆኖ ቆይቷል።

ወደ ዋናው የትኩረት ነጥባችን ስንመለስ በኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን መሰረት ያደረገው መፈናቀል ሌላ ልዩ ባህርይ ደግሞ አለው። ይህ ባህርዩ የተፈናቀሉ ዜጎች መጨረሻ ወይም መልሶ ማቋቋሙ ላይ ያለው ችግር ነው። ማንነትን ተገን ኣድርጎ የሚፈጠረው መፈናቀል በተለይ በሆነ ኣካባቢ የጥገኝነት ጊዜ ይኖራቸውና ከዚህ በሁዋላ እነዚህ ዜጎች ወዴት እንደሚሄዱ ለመንግስትም ግራ ሲያጋባው ይታያል። ቀድመው  ወደ ነበሩበት ቦታ እንዳይመለሱ የተፈናቀሉበት ምክኛት ሲስተሚክ ነውና ኣሁንም ለሌላ ችግር ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ይስፈሩም ቢባል የማይፈልጉት ቦታ፣ መሰረተ ልማቱ ያልተሟላበት ቦታ ስለሚሆን ስንት ንብረት ያፈሩ ዜጎች ኑሮን እንደገና ሊጀምሩ መሆኑ ተስፋቸውን ያጨልማል። ደግሞስ ለምን ሰው በገዛ ሃገሩ ይፈናቀላል። በሌላ በኩል ማንነታቸውን ወደሚገልጹበት ክልል ለመሄድ ደግሞ በተለይ መሬት የመንግስት በመሆኑና ብዙዎቹ ገበሬዎች በመሆናቸው በመልሶ መቋቋማቸው ላይ ችግር ኣለው። ስርዓቱ ማንነትን የሚስብ ሁኔታ ፈጥሯል እንበል እንጂ እነዚህን ድሃ ገበሬዎች ለመቀበል በጣም ያመነታል። የፖለቲካ ዩኒቶች ማንነትን መሳሳቢያ ቢያደርጉም በየቤታቸው ግን ለማንም የማይመቹ መሆናቸው ደግሞ ሌላ ችግር ነው። ይህ በራሱ የሚያሳየው ስስታም በሆነ ስርዓት ውስጥ መውደቃችንን ብቻ ሳይሆን በየቤቱ ደግሞ ኣምባገነናዊ ስርዓት ማሳደጋችንን ነው። ከሁሉ በላይ ግን ሁሉም ክልሎች የኔ ብሄር የሚሉትን በቤተሰብ ዛፍ መዝግበው የያዙ ኣይደሉምና ነገሩ ሁሉ ኣስቸጋሪ ያደርገዋል። ስለዚህ ስርዓቱ የፈጠረው ችግር ለመሳደድ መንስኤ ይሁን እንጂ የተሰደዱትን ጥገኞች ደግሞ መልሶ ለማቋቋም ብዙ እምቅ ችግሮችን ይዟል። እንደዚህ አይነት ስርዓት ላይ ነው ሃያ ሰባት አመት የኖርነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ግጭቶች ሲነሱ ማንነትን የሚገፉ የሚያሳድዱ ችግሮች እየሰፉ መጥተው ዛሬ ከሶርያም የበለጥነው ችግራችን በጣም ሲስተሚክ በመሆኑ ነው ብለናል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን ማንነትን መሰረት ያደረገ  የመሳሳብ ስርዓት በልቡ የማይቀበለው ቢሆንም ስርዓቱ እንደስርዓት ግን በየትኛውም ጊዜ እየፈነዳ ኢትዮጵያውያንን ሊያፈናቅል እምቅ ሃይል ኣለው። ከዚህ በተጨማሪም ለወንበዴዎች ሽብር ፈጣሪዎችና የኢትዮጵያን ሰላም ለማይሹ የውጭ ሃይላት ሰፊ የግጭት እድልን ይሰጣል። በመሆኑም የምንፈልገው መላ መዋቅራዊ ለውጥ መሆን ኣለበት። ሲስተማችን ውስጥ ያለው የመሳብና የመግፋት ህግ በመንጋው የሚኖረውን ህዝብ ሰላም የሚያሳጣ ነውና ለዚህ ችግር ኣስተማማኝ መፍትሄው ስትራክቸራል ለውጥ ብቻ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ውስጥ የሚገኙትን የመሳሳቢያ ኤለመንቶች ስናይ፣ ደግሞ በሲስተሙ ውስጥ የሚገፋ ኤለመንት መኖሩን ስናይ ይህ ልዩ ባህርይ የኢትዮጵያን የፌደራል ስርዓት ከፌደራል ስርዓት ተራ ያወጣዋል። ሌላ ዓይነት ስርዓት ነው ያለን ማለት ነው። የፈደራል ስርዓት ተቃራኒ የሆኑ ኤለመንቶችን የሚያንሸራሽር በመሆኑ የፌደራል ስርዓት ልንለው ኣንችልም። በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ የማይታይ ስርዓት ያለን ሲሆን ምን አልባት ይህንን የእኛን ስርዓት ሊገልጸው የሚችለው ቃል የብሄር ክልል ስርዓት ነው። የክልል ስርዓት ደግሞ አንድ ኔሽን ገንብተን እንድንኖር ኣያደርግምና ከመፈናቀል አያድነንምና ወደ ተሻለ ስርዓት መሻገር ኣለብን። በመሆኑም የሚከተለው አሳብ ለሽግግር ይረዳናል።

መፍትሄ

 1. አዲስ ኪዳን መግባት

ኢትዮጵያውያን አንድ የረባ የጋራ ቃል ኪዳን ሳይኖራቸው ይኖራሉ። ለአንድ ህዝብ ደግሞ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ኪዳን ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያውያን በፈጠሯቸው የፖለቲካ ዩኒቶች መካከል ያንተ መሬት የኔም ነው፣ የኔ መሬት ያንተም ነው፣ የኔ የኔ የምንለው የለም ሀገራችን የእኛ ናት የሚል የረባ ቃል ኪዳን የለንም። ህገ-መንግስታችን ኢትዮጵያን የብሄሮች ጥርቅም ብቻ ያደርግብናል። መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የሚያቀራምት የፖለቲካና የፌደራል ስርዓት ውስጥ ሆነን በመፈናቀል ልንደነቅ ኣይገባም።

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ታላቅ ቃል ኪዳን ይሻሉ።  እኛ ኢትዮጵያውያን ከእግዚኣብሄር በታች የማንከፋፈል ኣንድ ህዝብ ነን የሚል ቃል ኪዳን ያስፈልጋቸዋል We are one nation under Godindivisible.  ይህ ኪዳን ገፊ ነገሮችን ከፖለቲካ ዮኒቶቻችን ውስጥ ያስወግዳል ። መሳሳብን ፍቅርንና መደመርን በሲስተማችን የደም ስር ውስጥ ያፈስልናል።

ስደተኞችን የተገፉን ሁሉ ኢትዮጵያውያን እንደሚቀበሉ ቃል ቢገቡ ገፊ ኤለመንቶችን ከሲስተማችን እናባርርና መሳሳብን እናዳብራለን። ይህ መሳሳብ ደግሞ ተቆርቋሪነትን ለሃገር እንድናደርግ ኣንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም እኩል እንዲሰማው ያደርጋልና መፍትሄው ኣዲስ ኪዳን ለኢትዮጵያ መግባት ነው።

 1. ህገመንግስቱን ማሻሻል የፌደራል ስርዓቱን ሳይንሳዊ በማድረግ የስበት ህጉን በዜጎች መካከል እንዲሆን ማድረግ

ከፍ ሲል እንዳልነው የፌደራል ስርዓት ትሩፋት ለዜጎች ምርጫን መጨመር ነው። ምርጫው ደግሞ ለዜጎች ሁሉ ነው። በመሆኑም ማንነትን የፖለቲካ መሳሪያ ከማድረግ ኣውጥተን ብሄራዊ ማንነትን ለፖለቲካ መሳሪያ ለስበት ህጎቻችን ማጠንጠኛ ማድረግ ያስፈልገናል።  ይህንን ስናደርግ በጠገጉ ውስጥ በሚኖሩ የፖለቲካ ዩኒቶች መካከል ማንነት ኣጋጭ ሃይል ኣያመነጭም። የስቴት ባለቤትነት (state ownership) ከብሄር ባለቤትነት ማላቀቅና ለብሄራዊ ማንነት የሚሰጥ የፌደራል ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። የኢትዮጵያውያንን አዲስ ኪዳን መሰረት ያደረገ ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። በፖለቲካ ዮኒቶች መካከል የሚኖር ወሰን ከማንነት ጋር እንዳይያያዝ ኣድርጎ ጂኦግራፊን፣ ቋንቋን፣ ኣብሮነትን፣ ለአስተዳደር ኣመቺነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ መፈናቀልን ከስር መሰረቱ ያጠፋል።

 1. የአርበኞች ቤት ማቋቋም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ማንነት ከባድ ጉዳይ ሆኗል። በርግጥም ቡድኖች መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል። ኢትዮጵያውያን እጅግ ብዙ እንቁ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ባለቤቶች ነን። ፖለቲካችን ከዘውግ ይላቀቅ ስንል፣ የፌደራል ስርዓቱ ከብሄር ይውጣ ስንል ለብሄር ጥሩ ጠገግ ሰርተን መሆን አለበት። ይህ ቤት ደግሞ ከየባህሉ የተውጣጡ የባህል ቡድኖች ተወካዮች የሚመሰረት ቤት ነው። ከፖለቲካው መንግስት ተነጥሎ በራሱ ነጻ የሆነ ቤት ፈጥረን ባህላችንን ባህላዊ ማንነትን መጠበቅ እኩልነትን ማሳየት መከባበርን ማሳየት እንችላለን። ሰላም እርቅን ለማምጣት ይህ ቤት ይረዳናል። የኬር ቴከር ስራን ይሰራል። ይህ ቤት እያለ ማንነትን መሰረት ያደረገ መፈናቀል ኣይኖርም። በመሆኑም የውስጥ መፈናቀልን ለማስቆም ብሎም ኣጠቃላይ ሲስተማችንን ለማሻሻል እንዲህ ኣይነት የመዋቅር ለውጥ ማምጣት ኣለብን። ይህን ቤት ስንፈጥር ዘውጎች በአንድ ጊዜና ቦታ በሰላም ማኖር የሚያስችል የመሳሳብ ህግን እናመርታለን።

 1. የቋንቋ አጠቃቀማችንን ማሻሻል

ስለቋንቋ ስናነሳ ከመፈናቀል ጋር ምን ያገናኘዋል? እንደማትሉኝ ተስፋ ኣለኝ። እኔ የማወራው ኣጠቃላይ የፖለቲካ ጨዋታችን ማንነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ማንነትን አንድ ነገር ልንለው ካልቻልን፣ ለማንነት  መገለጫዎች የተሻለ ኣሰራር ካላመጣን ከማንነት ፖለቲካ ስለማንወጣ ነው። ከማንነት ፖለቲካ ካልወጣን ደግሞ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና መፈናቀሎች ስለሚቀጥሉ ነው ይህንን የማንነት መገለጫ የሆነውን የቋንቋ ኣያያዝ ችግር መላ ልንለው ይገባል የምላችሁ። በመሆኑም ቋንቋዎችን ሁሉ በታችኛው ርከን ላይ ኦፊሺያል ኣድርገን አንድ የዩኔን ቋንቋ ቢኖረን የተሻለ ይሆናል። ይህ ኣሰራር ግጭቶችን ቀንሶ ማንነትን ጠብቆ በጋራ ደግሞ ኣያይዞን ይኖራልና ይህንን ማድረግ መፍትሄ ነው።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ለመፈናቀል ዋናው ምክኛት ማንነት በመሆኑ የስበት ህጉን በማሻሻል የግፊያ ህጉን ማጥፋትና ለsub sahara ሃገራት ምሳሌ መሆን እንችላለን። እንግዲህ ይህን የምለው ሲስተሚክ ለውጥ በማምጣት የተረጋጋ ህይወት ማንነትን መሰረት ያደረገ መፈናቀል የሌለበትን ህይወት እንድናይ ነው። ነገር ግን መዋቅራዊ ለውጡ እስኪመጣ መፈናቀሉ ቀጥሏልና ከስትራተጂኩ መፍትሄ በተጨማሪ ኣፋጣኝ መፍትሄ መስጠትም ይገባል። በመሆኑም ኣሁን ለተፈናቀሉ ወገኖች:-

 1. ተገቢውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ
 2. ያሉትን ኣንዳንድ ህጎች በመጠቀም ገፊዎችን ማስቆም:: ተፈናቃዮችን ቀያቸው መመለስ።
 3. ያልተጻፉ እሴቶች እያነሱ ኣብሮ መኖርን ማበረታታት ማስተማር
 4. የሃይማኖትና የባህል መሪዎችን በማሳተፍ መፈናቀል ርጉም እንደሆነ ማስተማር
 5. ተቋማዊ ለውጥ በጎዳና ላይ እንደሆነ አብሮ የሚያኖረንን ኣዲስ ኪዳን ልንገባ እንደሆነ ተስፋ ለህዝቡ መስጠት
 6. የመደመርና የፍቅርን ስሜት በቅስቀሳ በኪነ ጥበብ ስራዎች ማስረጽ
 7. በመጨረሻም ሰው በምኞቱም በኣካልም ሳይፈናቀል የሚኖርባትን ሃገር ለመፍጠር እንድንችል ተቋማዊ ለውጡን ማበረታታት ያስፈልጋል። የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት ደግሞ አዲስ ሃገራዊ ኪዳን መግባት የግድ ያስፈልጋል። ስለተገፉ መቆም በሃይማኖቶች፣ በባህሎች በአለም ህጎች በሰው ልጅ ህሊና ሁሉ ቅዱስ ኣሳብ ነውና ኢትዮጵያውያን ይህንን ችግር ለማጥፋትና አዲስ ኪዳን ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንትጋ። አለምቀፉ ማህበረሰብም የኢትዮጵያን አዲስ ሃገራዊ ኪዳን በሙሉ ሃይሉ እንዲደግፈን እንጠይቃለን። ወደ አዲስ ኪዳን በፍጥነት እንሻገር።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

One comment

 1. ገለታ and ው ዘለቀ
  Not bad hope and enthusiastic guideline.

Comments — What do you think?

Click here to connect!
%d bloggers like this: