Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » እኩል ያልነበረ እኩልነት – ሠናይት ሠናይ (ዶ/ር)

እኩል ያልነበረ እኩልነት – ሠናይት ሠናይ (ዶ/ር)

ሠናይት ሠናይ (ዶ/ር)

እጅ እጅ ሲል ደግሞ ጨዋታ መቀየር ያስፈልጋል፣ ሁሉም ነገዶች በፊት ብሄረሰቦች ነበር የሚባሉት አሁን 84ቱን ነገዶቻችንን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ብላችሁ ስታስቀምጡ በሶስት ምድብ ያበላለጣችኋቸው መሆኑ አይገባችሁም? ወይስ ያንተ ቡድን “ብሄር” የሚለውን መጠሪያ ስላገኘ ሌላው ከብሄረሰብ ወደ ህዝቦች ሲወርድ አያገባኝም ነው? መቼ ነው ኢትዮጵያ አንድ ባህል ብቻ ነው ያላት ተብሎ የሚታወቀው? ዝምብሎ የተሰጠውን መቀበል (ሳይመረምሩ) መጨረሻው መጠቀሚያ መሆን ነው (እንደ አብዲ ኢሌ :) )። የህዝቡ ችግር የመደብ ጭቆና ነበር ከዚያ በተረፈ የህዝብ ቁጥርንም ሆነ አሰፋፈርን ሳይለይ ሁሉም ብሄረሰብ ነበር የሚባለው፡ አሁን የተወሰኑት ብሄር (ከፍ ባለ ማዕረግ) ከዛ ብሄረሰብ (መካከለኛ) እና ህዝቦች (ሶስተኛ ክፍል) ተደርጎ ተከፋፍሎ ቁጭ ብሎአል። በጣም የሚገርመው ደግሞ መመዘኛው አሻሚ መሆኑ ነው።

የፖለቲካ ምህዳሩን ደግሞ ስናየው አሁን ባለው የአውራ ገዢ ፓርቲ አሰራር ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እድል ያለው የትግራይ፣ኦሮሞ፡ደቡብ ህዝቦች እና አማራ ክልሎች ብቻ ናቸው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ግዜ የአፋር ህዝብ ተወካይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የአፋር ህዝብ መቼ እንዲህ አይነት ቦታ ሊያገኝ እንደሚችል ሲጠይቀው ምን ቢለው ጥሩ ነው? “ለህጻን ልጅ ብርጭቆ አይሰጥም..” ያኔ ሰው ሁሉ ስቆ አሳለፈው ነገር ግን የግዜው እኩልነትን ፌዝነት በዚያው አሳየበት። በጣም የሚያሳዝነው እነዚህ መሪዎች በህዝብ እንደዚ ሲቀልዱ በግለሰብ/ዜግነት ፖለቲካ ስርዐት ውስጥ ተመርጠው ቢሆን ኖሮ መብታቸው ነው ማለት እንችል ነበር ነገር ግን አንድ ሰው ጎሳን ወክሎ መቶ በሚወዳደርበት ስርዓት ፤ ስልጣን በሚይዝበት ግዜ የሚናገረው ሁሉ የተወከለበትን ህዝብ እንደሚያሳጣ ማገናዘብ ነበረበት። ለዚህ ነው ህውሃት ለትግራይ ህዝብ አያስብም የምንለው። ሌላው ቢቀር እንደዚ ጋጠወጥ ንግግሮችን ሲያደርጉ ይሄ ድርጅቴንም ህዝቤንም አይወክልም የራሴ አስተያየት ነው እንኳን አይሉም ነበር።

ስለዚህ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩልነት የሚለውን ትርክት “ህዝቦች” ብላችሁ ለነጠላችኋዋቸው ሰዎች እንዴት እኩልነት እንደሆነ ብታስረዱን። ከዛ ደግሞ ብሄር ማለት አገር ነው ስለዚህ ብሄረሰብ ደግሞ የአገሩ ሰዎች ማለት ነው፡ 84 ብሄረሰብ አላት ኢትዮጵያ ማለት ደግሞ በግልጽ 84 የተለያዩ ባህል ቋንቋ እና አኗኗር ያላቸው ነገዶች አሉ ማለት ነው። ስለዚህ እንዴት ነው ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር ብቻ ነበረች የሚባለው?ለማንኛውም ሁሉም ብሄረሰቦች ለኢትዮጵያ ጌጦቿ ናቸው። ምንም አይነት ስም ብትሰጡዋቸውም የሁሉም ደም ነው ይቺን ኢትዮጵያ ያቆማት። አሁንም ኢትዮጵያ የምትቀጥለው ይሄ ትውልድ ልክ አባቶቹ እንዳረጉት አብሮ ቆሞ ሊያስቀጥላት ከተስማማ ብቻ ነው ሁሉም ትውልድ ለራሱ ይወስናል።

የኛ ውሳኔ ለራሳችን ነው እንጂ ቅድመ አያቶቻችንማ የሚበጀውን ወስነው ኖረው አልፈዋል። ኢትዮጵያን ስንል ማሰብ ያለብን ምን ያህል ሰላሟና መረጋጋቷ ለኛ ሰላም መሆኑን አስበን ነው የሚሆነው። ያለፈውን ትውልድ ውሳኔ እቀለብሳለሁ/እበቀላለሁ ብሎ ያሁንን ቤተሰብና ወገንን የማያልቅ ግርግር ውስጥ መክተት ራስን መጉዳት ነው። የያንዳዳችን ዘር ማንዘሮች በፊት ያለፉት “ውይ እንዲ አደረጓት?” ብለው እንደማይናደዱ 100/100 አረጋግጥላችኋለሁ እነሱ በሰላም አሸልበዋል ስለዚህ አሁን የምናደርገው ነገር ለኔና ለወገኔ ይጠቅመኛል ወይ? ብለን ዛሬ ላይ ሆነን ነው ማሰብ ያለብን፡ አገር ስትረጋጋ እንደፈለክ የትም ብትሄድ ተከብረህ ትገባለህ አገር የለሽ ስትሆን ደግሞ ሁሉም በሩን ይዘጋብሃል። ሀገር ውስጥ የሚኖረው ወገን ሰቆቃ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ነው የሚሆነው። ይሄ ማለት ገና ለገና ለአገር ብለህ ተረገጥ ተገረፍ ማለት አይደለም ያ የሚሆነው ህዝብ ባለስልጣንን ሲያጠፋ ማውረድ የማይችልበት ሁኔታ ሲኖር ነው አሁን ግን ስርዓቱ እየተስተካከለ ያለው የመረረው ህዝብ በቃ ብሎ ስለተነሳ ነው። ያ ህዝብ አሁን መንገዱን አውቆታል ከአገር ወይስ ከነጻነትህ ብሎ የሚያስመርጠው አይኖርም። ነጻነቱንም አግኝቶ የፈለገውን ሠንደቅ አላማ እያውለበለበ የፈለገውን ቋንቋ እየተናገረ ሃገሩንም በሰላም ማስተዳደር የሚችል ትውልድ ነው። ሀገሩን ለመያዝ እና ራሱን ሆኖ ለሞኖር ደግሞ የግድ አንድ ብሄረሰብ መርጦ ጠላት ማድረግ እንደሌለበት አውቋል። ስለዚህ ሲፈልግ በአገሩ ሲፈልግ በብሄረሰቡ ሲፈልግ እንደግለሰብ ፖለቲካው ላይ በሰፊው እየተሳተፈ አገሩን ይጠብቃል። ከእንግዲህ ወይ ነጻነት ወይ ኢትዮጵያ ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ ሁሉም ብሎ ነው የሚመልሰው። ለዚህ ያደረሰን ፈጣሪ ይመስገን፡ ይህን ስነልቦና ተረድቶ ያንን የሚተገብር መሪ ስለመጣም ፈጣሪያችን አብልጦ ይመስገን።

Comments — What do you think?

Click here to connect!