Home » ዜና » ስለ ፓስተር ዳንኤል ዝም ማለት አልቻልኩም (ማህሌት ፋንታሁን)

ስለ ፓስተር ዳንኤል ዝም ማለት አልቻልኩም (ማህሌት ፋንታሁን)

ማህሌት ፋንታሁን

Ethiopian pastor, Daniel

ፓስተር ዳንኤል

ፓስተር ዳንኤል በ2006 ሃምሌ ወይም ነሃሴ ወር ላይ ቃሊቲ በእስር በነበርንበት ወቅት እኔና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬን መጥቶ አናግሮን ነበር። ማእከላዊ እያለን እኛን ለማግኘት በተደጋጋሚ ጠይቆ እንዳልፈቀዱለት በመጥቀስ ስለማእከላዊ እንዲሁም የቃሊቲ ሁኔታችን ጠየቀን። በማእከላዊ ከቤተሰብ እና ከጠበቃ ጋር እንድንገናኝ የተፈቀደልን ሶስት ወር ከቆየን እና ቃል ከሰጠን በኋላ መሆኑን፣ በምርመራ ወቅት መርማሪዎች እራቆታችንን እያስቆሙ እና ከባባድ እስፖርት እያሰሩ ያላደረግነውን ነገር እንድናምን እንደሚያስገድዱን፣ ዱላ፣ ዛቻ፣ ማስፈራራት እና ማመነጫጨቅ እንደነበረ በተጨማሪም ለ “ምርመራው” በአብዛኛው የምንጠራው ማታ እና ለሊት እንደነበረ ፤ ቃሊቲ ከገባን በኋላም ሌሎች በቀጠሮ ያሉ ሴት እስረኞች ሊጠይቃቸው የመጣ ቤተሰብ እና ጓደኛ ሁሉ ጠዋት እና ከሰአት በስራ ሰአት ባለ ጊዜ እንደሚጠየቁ እኛ ግን ልዩ አጃቢ ለየብቻችን ተመድቦልን ጥቂት ቤተሰቦቻችንን ብቻ በምሳ ሰዓት ባለ ጊዜ ለ15 እና 20 ደቂቃ ብቻ እንደምንገናኝ፤ ሌሎች እስረኞችም ከኛ በሽብር ከተከሰሱ ጋር እንዳያወሩ ጫና እንደሚደረግባቸው ነገርነው። ፓስተር ዳንኤል ከሰማን በኋላ ምንም አልመሰለውም። እንዲያውም “እናንተ በጣም ደህና ናችሁ። ጥሩ ሁኔታ ላይ ናችሁ። ” ብሎ ከኛ በፊት ታስራ የነበረች የፓለቲካ እስረኛን ጠቅሶ ሞራሏ በጣም ተጎድቶ እንደነበረ እና ለሷ ብዙ እገዛዎችን ማድረጉን ገለፀልን። እኛ ስለደረሰብን ነገር ሲጠይቀን ሳንደብቅ የነገርነው የሚፈይድልን ነገር አለ ብለን ተስፋ አድርገን ሳይሆን እውነቱን ይወቀው በሚል ነው። ምክንያቱም በኛ ላይ የደረሰው እና ይደርስ የነበረው የመብት ጥሰት ከኛ በፊት የታሰሩ እስረኞች ላይም ነበረ፤ ከኛ በኋላም የቀጠለ ነገር ነው። ይህን ነገር ለማስቆም ከተፈለገ (ወይም በሪፖርት ለማቅረብ) ደግሞ አመታት የሚፈጅ አስቸጋሪ ጉዳይም አልነበረም።

ፓስተር ዳንኤል አናግሮን ሲጨርስ በየወሩ እንደሚመጣ እና ጉዳያችንን እንደሚከታተል እንዱሁም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስለሚደርስብን መገለልም በተመለከተ ሃላፊዎቹን እንደሚያናግር ነግሮን የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ከቃሊቲ እስክንወጣ ድረስ ድርሽ ብሎ አያውቅም።

ታዲያ ትላንት ፓስተር ዳንኤል ዋልታ ቲቪ መሰለኝ ቀርቦ አልፎ አልፎ መጠጥ ጠጥተው የሚገቡ መርማሪዎች ለሊት ምርመራ ከሚያካሂዱ በቀር የለሊት ምርመራ መቅረቱን እና ሰብአዊ መብት ጥሰት መቀነሱን ሲያወራ እኔ ለሱ አፈርኩለት። በማእከላዊ ያለፍን በርካቶች በህይወት እያለን ይህን ክህደት መስማት ሊያውም ገለልተኛ ነኝ ከሚል ግለሰብ ያበሳጫል። መንግስት እንኳን የፍትህ ስርአቱ ላይ ጥፋት አምኖ እስረኞችን መፍታት እና ሌሎችም እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት፤ የመንግስት ሚዲያዎች እንኳን ሳይቀሩ እየዘገቡ ባለበት በዚ ሰአት የፓስተር ዳንኤል የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲያደርጉ ለነበሩ ተከላካይ ሆኖ መቅረቡ ይገርማል። ወይ እንደበፊቱ ዝም ቢል ይሻል ነበር። ምን ነክቶት ነው ግን?

Comments — What do you think?

Click here to connect!