Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » እውን ኢትዮጵያ “ብቁ መሪ” አገኘች ይሆን በስተመጨረሻ? (ዶ/ር ዘላለም ተክሉ)

እውን ኢትዮጵያ “ብቁ መሪ” አገኘች ይሆን በስተመጨረሻ? (ዶ/ር ዘላለም ተክሉ)

ዶ/ር ዘላለም ተክሉ
7/8/2018*

Professor Mesfin Woldemariam's opinion about Ethiopia's new PM Dr. Abiy Ahmed.

 1. መግቢያ

ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ የሚኒስተርነቱን ቦታ ከያዙ ወዲህ እየታዩ ያሉትን ፈጣን ፖለቲካዊ ለውጦች ያላስደሰተው ኢትዮጵያዊ ካለ “የቀን ጅቦቹ” ብቻ ናቸው ብል ማጋነን እንደማይሆንብኝ እርግጥኛ ነኝ፡፡ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሲታሰር፣ ሲገረፍ፣ ሲገደል፣ ሲሰደድ፣ ሲራብ፣ ሃብቱንና ንብረቱን ሲነጠቅ፣ በዘር መድሎ ከመኖሪያ ቀዬው ሲፈናቀል የኖረው ህዝባችን በሶስት ወር ጊዜያት ብቻ የተቀዳጃቸውን ድሎች ስንመለከት አብዛኞቻችን ግራ ሁሉ ተጋብትናል፣ ማመን ሁሉ አቅቶናል፣ ተመልሰውም የሚነጠቁ መስሎናል፡፡

በዚች አጭር ጊዜ ውስጥ የተፈቱትን የፖለቲካና የህሊና እስረኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጋዜጠኞች፤ በወያኔዎች ብቻ በሞኖፖል የተያዙት ቁልፍ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደህንነትና የፋይናንስ ተቋማት በሙያቸው ብቁ በሁኑ ግለሰቦች መተካቱ፣ በሃሰተኛ አሸባሪነት ህግ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የፖለቲካ መሪዎችና በውጪ የሚገኙ የቲሌቪዥን ጣቢያዎችን በሃገራቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መወሰኑ፣ የኢትዮ- ኤርትራ ድምበር ኮሚሽንን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበልና ሌሎች ጆኦ-ፖለቲካዊ ልዩነቶች ለመፍታት ድርድሮች መጀመራቸው፣ ህዝቡ ሃሳቡን በነጻነት ባደባባይ የመግለጽ መብቱን መልሶ እንዲያገኝ መደረጉ፣ በመንግስት የሚተዳደሩትን ትላልቅ የንግድና ኢንዱስትሪዎች ተቋማት ወደግሉ ይዞታነት እንዲዘዋወሩ መወሰኑ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት አፋኝ የሆኑት የአሸባሪ፣ የነጻ ፕሪስና መያድ ህጎች ማሻሻያ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው፣ የህግ እስረኞችን ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ሲያሰቃዩ የነበሩትን የወህኒ ቤት አስተዳዳሪዎች ከስልጣናቸው ማውረድና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መውሰኑ እና ወደፊት ዘላቂ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ ሁኔታዎች የማመቻቸት ሂደት መጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በመሆናቸው እንጂ ሌላ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁላ ለውጥ በዚህ ፍጥነት ይመጣል ብሎ መገመት እንደሚያስቸግር ብዙዎቻችንን የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡

ይህንን በአጭር ጊዜ የተመዘገቡ ለውጦች ስመለከት ነው እንግዲህ “ እውነት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቁ መሪ አግኝታ ይሆን እንዴ?” የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ የተጫረብኝ፡፡ ለዚሁ ጥያቄዬ መልስ ለማግኘት የተለያዩ የማኔጅመንት መጻህፍትን በማገላበጥ የብቁ መሪ ትርጉምና ዋና ዋና ባህርያትን የሚያስረዱ መረጃዎችን አሰባስቤአለሁ፡፡ በዚሁ ጥናቴ መሰረት ያገኘሁትን መረጃ ከዶ/ር አብይ ባህርይና የሶስት ወር የአመራር ውጤቶች ጋር በማነጻጸርም የሚከተለውን ትንታኔ አካሂጃለሁ፡፡ የትንተናዬን  ተቀባይነት ለማጠናከርም ከአቶ መለስ አመራር ብቃት ጋር ለማነጻጸር (comparative analysis) ሞክሬያለሁ፡፡

 1. የብቁ መሪ ትርጉምና ዋና ዋና ባህርያቶች

ሮቢንስ፣ ኮልተርና ዲቼንዞ በጻፉት Fundamentals of Management የአካዳሚክ መጽሃፍ አተረጓጎም መሰረት፡

“ብቁ መሪ ማለት የተሰጠውን የማስተደደር ስልጣን በመጠቀም የብዙ ቡድኖችን ወይም ህዝቦችን ሃሳብ በበጎ መልኩ መቀየር የሚችልና ተጸኖ ፈጣሪ የሆነ ግለሰብ ማለት ነው”፡፡

ብቁና ውጤታማ የሆነ መሪ የሚከተሉትን ስምንት ባህርያት እንደሚያሟላም ይሄው መጽሃፍ ያስረዳል፡

 • ተነሳሽነት (Drive) – ብቁና ውጤታማ መሪ ያቀዳቸውን አላማዎች ለማሳካት ከፍተኛ ተነሳሽነት ያለው፣ የጀመራቸውን ስራዎች ሳያሳካ ደከመኝ የማይልና ያለውን ሃይል ሁሉ የሚጠቀም ብርቱ ግለሰብ ነው፣
 • ለመምራት ፍላጎት ያለው (Desire to Lead) – ብቁና ውጤታማ የሆነ መሪ ጠንካራ የሆነ የመምራትና ተጽኖ የመፍጠር ፍላጎት አለው፡፡
 • ታማኝነትና የሞራል ብቃት (Trust & Integrity) – ብቁ መሪ ሃቀኛ በመሆን የተከታዮቹን ሙሉ እምነት ያገኛል እንዲሁም ቃል የገባቸውን ሁሉ ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ የሞራሉ ብቃቱን ያረጋገጠ ነው፡፡
 • በራስ መተማመን (Self Confidence) – ትክክለኛ መሪ ለያሳካ የተነሳሳባቸውን አላማዎችና የወሰናቸው ውሳኔዎች ትክክለኛ መሆናቸውን በሙሉ ራስ መተማመን ካረገጠጥ ብዙ ተከታዮች ይኖሩታል፡፡
 • የአእምሮ ብቃት (Intelligence) – ብቁ መሪ ብዙ መረጃዎችን ባጭር ጊዜ በመሰብሰብ፣በመተንትንና በመተርጎም ችግሮችን የመፍታትና መፍትሄ እርምጃዎችን የመውሰድ የአእምሮ ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡
 • ከስራው ጋር ተያያዥነት እውቀት (Job Related Knowledge) – ውጤታማ የሆነ መሪ ስለሚመራው ድርጅት ወይም ሃገር ጥልቅ የሆነ እውቀት ያለውና ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች ጥቅምና ጉዳት አስቀድሞ ግንዛቤ ያለው መሆን አለበት፡፡
 • በጣም ተግባቢ የሆነ (Extraversion) – እውነትኛ መሪ ህዝብ ወዳድ፣ ተግባቢ፣ ተጫዋችና በማህበራዊ ኑሮዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡
 • ጥፋትኝነቱን አምኖ የሚቀበል (Proneness to Guilt) – ብቁ መሪ ጥፋቱን አምኖ የሚቀበል ነው፣ ምክያቱም ለጠፋው ጥፋት ሃላፊነቱን ሲወስድ በተከታዮቹ ታማኝነቱ ይጨምራል ሌሎችም የሱን አርአያ እንዲከተሉ ያደርጋል፡፡
 • /ር አብይ የብቁ መሪነትን ትርጉምና ባህርያቶች ምን ያህል ያሟላሉ?

እንግዲህ የብቁ መሪ ሳይንሳዊ ትርጉምና ባህርያቶቹ ከላይ በተዘረዘረው መልኩ ቅርበዋል፡፡ ታዲያ ዶ/ር አብይ ከነዚህ የመሪነት ትርጓሜና ባህርያቶች ውስጥ ምን ያህሉን እንደሚያሟሉ እስቲ እንመልከት፡፡

መሪ ማለት የተሰጠውን የማስተደደር ስልጣን በመጠቀም የብዙ ቡድኖችን ወይም ህዝቦችን ሃሳብ በበጎ መልኩ መቀየር የሚችልና ተጸኖ ፈጣሪ የሆነ ግልሰብ ማለት ነው ተብሏል፡፡ አቶ አብይ ሃገር የመምራት ስልጣኑን ህዝቡ በምርጫ የሰጣቸው ሳይሆን ድርጅታቸው ኢህአዲግ ነው በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምትክ የሾማቸው፡፡ ነገር ግን በሶስት ወራት ጊዜ ብቻ በዙ አበረታች ለውጦችን በማምጣታቸው የህዝቡን ቀልብ ስበዋል፡፡ ከህውሃትና ጥቂት ደጋፊዎች በስተቀር መላው ኢትዮጵያዊ ባመራራቸው ተደስቷል፣ ወደፊት ከጎናቸው በመሰለፍ ማንኛውንም ድጋፍ ሊያደርግላቸው ቃል ገብቷል፡፡ እያደርጉ ያሉትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያውና የህግ ለውጦች የሚያደናቅፉ ወገኖች ካሉ መስዋእትነት በመክፈል ሊከላከል ቃል ገብቷል፡፡ በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊም ለ 27 አመታት ኢህአዲግ ሲቃወም ነበር የቆየው፡፡ ዶ/ር አብይ የኢሃዲግ አመራር ቢሆኑም እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ የድጋፍ ሰልፎችን በአሜሪካና በአውሮፓ እያደረገ ይገኛል፡፡ ዲያስፖራው ገዥውን ፓርቲ ለማዳከም ባለፉት ስድስት ወራት የሪሚታንስ ተአቅቦ ዘመቻ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በሳቸው አመራር እየመጣ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ሲል የተአቅቦውን ጥሪ አንስቷል፡፡ ስለዚህ የዶ/ር አብይ አመራር በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ባለው ህዝባች ላይ ትልቅ ተጸኖ ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡

አዎ አቶ መለስም የተሰጣቸውን የማስተደደር ስልጣን በመጠቀም የህዝቦችን ሃሳብ መቀየር የቻሉ ግለሰብ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአብዛኛውን ህዝብ ሃሳብ በቀና መልኩ የቀየሩ ባለስጣን አልነበሩም፡፡ በስልጣናቸው ተጽእኖ በመፍጠር ሃገሪቷን ወደመገነጣጠል የሚወስድ ህገ- መንግስት እንዲጸድቅ አድርገዋል፣ ኢትይጵያ በብሄር ብሄረሰብ በመከፋፈል ህዝብን ከህዝብ የሚጋጭበት ሁኔዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ ጥቂት የትግራይ ቡድኖች የሃገሪቷን እኢኮኖሚ እዲዘርፉ፣ የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ መብት በመግፈፍ ለስቃይ፣ ለመከራ፣ ለስደትና ለረሃብ እንዲዳረግ የሚያስችል የአሰራር ስርአት ዘርግተዋል፡፡ ስለዚህ የአቶ መለስ አመራር በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ባለው ህዝባች ላይ ቀና ያልሆነ ተጸኖ በመፍጠሩ ሃገሪቷ በከፍተኛ ተቃውሞ፣ እርስበርስ ግጭትና ሽምቅ ውጊያ የሚካሄድባት ሃገር አድርገዋታል፡፡

ተነሳሽነትን በተመለከት ዶ/ር አብይ በበአለ ሲመታቸ እለት ሊፈጽሙ ቃል የገቧቸውን ፖለቲካዊና ህጋዊ ማሻሻዎችና ለውጦች ለመፈጸም ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው ጠንካራ ግለሰብ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ በዛ ንግግራቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን በነጻነት እንዲገልጽ ይደረጋል ብለዋል፣ በውጭ ያሉት የገዢ ፓርቲ ተፎካካሪዎች ሁሉም ወደ ሃገር ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጋብዘዋል፣ ከኤርትራ ጋር ያለውን የብዙ አመታት ፍጥጫ ለፍታት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ በዝች ሶስት ወራት ውስጥ ቃል የገቧቸውን ብዙዎች ግቦች ሁሉ እንዲሳኩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን ስራ የሚሰሩ ብርቱና ብቁ መሪ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ አብዛኛውን ቃል የገቧቸውን ተግባራት ወይ ፈጽመዋል ወይ ደግሞ ለቀጣይ አፈጻጸም መስመር እያስያዟቸው ነው፡፡

አቶ መለስ በ 1995* አሜሪካ መጥተው “በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀን ሶስት ጊዜ ራሱን እንዲመግብ እናደርጋለን” ብለው ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገ ግን ይህንን እቅዳቸውን ለማሳካት ጥረት ባለማድረጋቸው እስካሁን እንኳዋን በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ቀርቶ አንድ ጊዜም የማይበሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ረሃብተኞች ያሉባት ሃገር እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ አቶ መለስ ድርጅታቸው በህዝቡ ላይ አዛዥ ናዛዥ የሆኑ ባለስልጣናት ሳይሆኑ ለህዝብ ታዛዥና አገልጋይ የሆኑ አመራሮችን እንመድባለን እያሉብለው በተደጋጋሚ ቃል ይገቡ ነበር፡፡ ይህንን የገቡትን ቃል ለማስፈጸም ተነሳሽነትና ፍላጎት ባለማሳቸው ምክንያት ለህዝብ አገልግይ ሹመኞች ሳይሆኑ ሙሰኞች፣ አድሎኞች፣ ዘረኞች፣ ጨካኝና ጨፍጫፊ አስተዳዳሪዎች ነው ከላይ እስከ ታች መዋቅሮች ጥለውልን ነበር ከእዚች አለም የተለዩት፡፡

ዶ/ር አብይ ከፍተኛ የሆነ የመምራት ፍላጎት አላቸው፡፡ ከራሳቸው አንደበት እንደሰማነው ከልጅነቱ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መሪ በመሆን ለውጥ ለማምጣት እንደሚፈልጉ ይገልጽ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን እንደምናየውም በአብዛኛው የኢትዮጵያን ችግር ለምፍታት በቀዳሚነት አመራሩን እየሰጠ የሚገኝው፣ በየክልሎቹ መካከል የተከሰተውን የብሂር ብሄረሳቦች እርስ በርስ ግጭት ለምፍታት፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት፣ በየውጭ ሃገራቱ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማስፈታት፣ በሙስሊሙ መጅሊስና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት፣ በስደተኛውና በሃገር ውስጥ የኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች መካከል ያለውን ግጭት ለመፍታት፣ የኢትዮጵያንና የኤርትራ ግጭት ለመፍታት ሁሉ የመሪነቱን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ዶ/ር አብይ ነው፡፡

አቶ መለስም ከፍተኛ የመምራት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ የመምራት ፍላጎታቸው ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ እንዲባባሱ የማድረግ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ በየክልሎች መካከል የተፈጠሩትን የየብሂር ብሄረሳቦች እርስ በርስ ግጭት ለምፍታት ምንም ጥረት አላደራጉም፡፡ አማሮች ክጎራፈርዳ ሲፈናቀሉ ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ ተፍናቃዮቹ አማሮች ደን ጨፍጫፊዎች ናቸው ብለው የወነጅሉበት ሁኔታ የማይረሳ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ በየውጭ ሃገራቱ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከማስፈታት ወይም ስለመብታቸው ከመከራከር ይልቅ አናውቃቸው ብሎ መካድ፣ በሙስሊሙ መጅሊስና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መካከል ያለውን ችግር ከመፍታት ይልቅ የኮሚቴው አመራሮችን ባአሸባሪነት ከሶ ለእስር መዳረግ፣ በስደተኛውና በሃገር ውስጥ የኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች መካከል ያለውን ግጭት ከመፍታት ይልቅ ስደታኛውን ሲኖዶስ ከአሸባሪዎች ጋር መፈረጅ፣ የኢትዮጵያንና የኤርትራ ግጭት ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሁለቱ ሃገራት በጠላትነት እየተያዩ እንዲቆዮ በማድረግ ከብቁ መሪ የሚጠበቅ ሚና ሳይጫዋቱ እንደቀሩ ሁላችንም የምናውቀው እውንታ ነበር፡፡

ዶ/ር አብይ ህዝባችን በእኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ያገጠመውን ችግሮች ሁሉ ተረድተው፣ ኢህአዲግ ለነዚህ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ መሆኑን አምነው፣ ችግሮቹን ባጭር ጊዜ ለመፍታት ቃል የገቡ በመሆኑና አብዘኛዎቹን መሰረታዊ ችግሮች በአጭር ጊዜ የፈቱና እየፈቱ ያሉ በመሆናቸው የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እምነት አትርፈዋል፡፡ አቶ መለስ ያመጡት አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት ፍልስፍና ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና መፍትሄ ናቸው ብለው በእውነት የታየው ግን የብሄር ብሄረሰብ ግጭት፣ ተደጋጋሚ ረሃብ፣ ስራ አጥነት፣ ስደት፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና ጥቂት ብሄርተኞች ብቻ የከበሩበት ሁኔታ በመሆኑ በህዝባችን ታማኒነት አጥተዋል፡፡ በሳቸው አመራር ላይ እምነት በመታጣቱ ምክያትም ነው በመላው ሃገሪቱ ተቃውሞና፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የትጥቅ ትግል እየተካሄደ ያለው፡፡

ዶ/ር አብይ በሚያደርጉት ንግግርም ሆነ የለውጥ እርምጃዎች የሚወስዱት ከፍተኛ የራስ መተማመን በተሞላበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ድምበር ኮሚሽን ባድመና ሌሎች አካባቢዎችን ወደኤርትራ እንዲካለሉ የወስነውን ውሳኔ ያምንም ቅድመ ሁኔታ ለማስፈጸም መነሳታቸው ሲገልጹ ከትግራይ ክልልና ህውሃት ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ባድመ ወደ ኤርትራ እንድትካለል የተስማሙት እሳቸው ሳይሆኑ አቶ መለስ መሆናቸውንና እሳቸው ያንን ውሳኔ በአገሮቹ መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዘላቂ ልማት ሊያመጣ እንደሚች በመተማምን ሊያስፈጽሙት መነሳታቸውን በከፍተኛ ራስ መተማመን ሲያስረዱ አብዛኛው የፓርላማ አባል እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ በደስታ ነው የተቀበላቸው፡፡ አቶ መለስ የፈረሙትን ስምምነት ወደማስፈጸሙ ሂደት እንዳይገባ ከ20 አመታት በላይ አፍነው ያስቅሩበትን ምክንያት በተደጋሚ ሲያስረዱ ምንም የራስ መተማመን አይታይባቸውም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ውሳኔውን በመርህ ደረጃ ተቀብለነዋል ነገር ግን ድምበሩ ከመካለሉ በፊት ተነጋግረን መፍታት የሚገቡን ብዙ ሌሎች ጉዳዮች አሉን ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ “እኛ ዝግጁ ነን አቶ ኢሳያስ ነው እምቢ ያለው” እያሉ በመወላወል ነበር አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያባከኑት፡፡

ዶ/ር አብይ ከፍተኛ የአእምሮ ብቃትና ከስራቸው ጋር ተያያዥነት ያለው እውቀት የተጎናጸፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ በአካዳሚ እውቀት በኮሚተር ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ቢዝነስ አድሚኒስትርሬሽንና ፖሊቲካል ሳይንስ ትምህርቶች ከባችለር እስከ ዶክተሬት ዲግሪዎች የተጎናጸፉ ሲሆን፡፡ በስራ ልምድም በመካላከያ ከተራ ውትድርና እስከ ኮለኔልነት ማእረግ የደረሱ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት (INSA) እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት በአመራርነት ከፍተኛ ክህሎትና ልምድ ያካበቱ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  ስለ ኢትዮጵያና የአለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ታሪካዊና ወቅታዊ እውንታዎች በንባብ ራሳቸውን ብቁ ያደረጉ መሪ መሆናቸውን በተለያዩ መድረኮች ካደረጓቸው ንግግሮች መረዳት ይቻላል፡፡ የአገራቸንን ባህልና ወግ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውንም አቀላጥፈው ከሚናገሩት ኦሮምኛ፣ አማርኛና ትግርኛ ቋንቋዎችና ወጎች መደምደም ይቻላል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የዳበረ እውቀት፣ ልምድና መልካም የግል ባህርያት በሶስት ወራት ጊዜያት ካስመዘገቡት አበረታች ለውጦች ጋር ሲደመር ዶ/ር አብይን ብቁ መሪ ያደርጓቸዋል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ ከአንደኛ አመት ዩኒቨርሲቲ አቋርጠው ወደ ጫካ በመግባት ከደርግ ጋር የተደረገውን ትጥቅ ትግል የመሩ ግለሰብ ናቸው፡፡ የአካዳሚ እውቀትን በተመለከተ ከ1991* ወዲህ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ በኋላ ነው በተለእኮ ትምህርት የማስተሪት ዲግሪያቸውን ያገኙት፡፡ በፖለቲካው መስክ የበሰሉና ርቱእ ተናጋሪ ይሁኑ እንጂ ከስራቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ምንም ልምድና እውቀት ሳይኖራቸው ነበር የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ማገልገል የጀመሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በግልም ይሁን በመንግስት መስሪያ ቤት ምንም የስራ ልምድ አልነበራቸውም፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ጄኦ-ፖለቲካል እውቀቶችም ይሁን ልምዶች በቅድሚያ ሳይኖራቸው መምራት መሞከራቸው ሊሆን ይችላል ሃገሪቱዋን አሁን ካለችበት አስከፊ ደረጃ እንድትደርስ ያስቻሉ ፖሊሲዎችና ህጎችን እንዲጫንባት ያደረጉት ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

ዶ/ር አብይ ህዝብ ወዳጅ፣ ተግባቢና በማህበራዊ ኑሮዎች ንቁ ተሳታፊ መሆናቸውን በዚች ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ አስማስክሯል፡፡ ሰኔ 23, 2018* በመስቀል አደባባይ ሰልፉ ሲካሄድ በፈነዳው ቦምብ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ሆስፒታል ድረስ ተመላልሰው በመጠየቅና ደማቸውን በመስጠት እንዲሁም በሟቾቹ ቤተሰቦች ለቅሶ ላይ በመድረስ ከተራው ህዝብ ጋር ያላቸውን ፍቅርና ማህበራዊ ትስስር አሳይተዋል፡፡ አቶ መለስ እንኳን የታመሙና የቆሰሉ ወገኖች ሊጠይቁ፣ ደም ሊሰጡና በሟች ቤተሰቦች ለቅሶ ሊደርሱ ቀርቶ ሶማሊያ ውስጥ አልሸባብን ሲፋላሙ የተሰዉትን በሺሆች የሚቆጠሩ ወታደሮቻችን በስርአቱ ቀብራቸው እንኳን እንዲከናወንና እናቶቻቸውም እርማቸውን እንዲያወጡ ያልፈቀዱ ግለሰብ ነበሩ፡፡

ዶ/ር አብይ ኢህአዲግ በ27 አመታት ውስጥ በህዝቡ ላይ ለፈጸማቸው በደሎችና ጥፋቶች ሁሉ ሃላፊነት በመውሰድ የአመራር ብቃታቸውን አስመስክረዋል፡፡ በተለይ ከፓርላማ አባላት “አሸባሪ እስረኞችን ለምን ይፈታሉ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እስረኞችን በጨለማና ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ አስሮ በማሳቃየት፣ በመግረፍ እና አካል በማጉደል አሸባሪዎች እኛ እንጂ እስረኞቹ አይደሉም” እቅጩን ነግረው መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ የስጡት ምላሽ ምን ያህል ብቁና ታማኝ መሪ እንደሆኑ አረጋግጧል፡፡ ስህተትን ማመንና ሃላፊነቱን መውሰድ በህዝባቸው ታማኝነትን ያጠነክራል ለወድፊትም የተሻለ አሰራር ትምህርት ይሰጣልና፡፡

አቶ መለስ ለስህታቸው ሃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ በሌላው ላይ ማላከክና ማላገጥ የተለመደ ባህርያቸው ነበር፡፡ የ 2005* ነጻ ምርጫ ውጤት በመቀልበሱ የተነሳ የተቃውሞ ስልፍ ሲያደርጉ የተገደሉትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ባንክ ሲዘርፉ ወይም ፖሊስ በመግደላቸው ነው የተገደሉት ብለው ጥፋታቸውን ክደዋል፣ ጥፋቱንም በተጎጂዎች ላይ አላከዋል፡፡ የኢትዮ የኤርትራ የድምበር ኮሚሽን ባድመን ወደኢትዮጵያ እንድትካለል ወስኗል ተብሎ ለህዝቡ ስለተዋሸው ዜና ሃላፊነት አልወሰዱም፡፡ በተደጋጋሚ አመታት በተከሰቱ ድርቅና ረሃብ ምክንያት የሞቱ ወገኖች ስለመኖራቸው አምኖና ሃላፊነት ወስዶ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ምንም ስው እንዳልሞተና ረሃብም እንዳልተከሰተ ያለምንም ሃፍረት ተናግረዋል፡፡ ህዝባችን በድህነትና በኑሮ ውድነት እየተሰቃይ እያለ በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል፣ አድገናል ተመንድገናል እያሉ በተደጋጋሚ አለምን አሳስተዋል፡፡

 1. ማጠቃለያ፡

ከላይ ባደረኩት ዳሰሳዊ ትንተና አገራችን ኢትዮጵያ ብቁ መሪ አግኝይታ ይሆን ብዬ ያነሳሁትን ጥያቄ ለመመለስ ሞክሬያለሁ፡፡ ምናልባት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሶስት ወራት ጊዜ ብቻ ወስዶ ድምዳሜ ላይ መድረስ የተቻኮለ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ዶ/ር አብይ በእዚች አጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገቧቸው ለውጦች በሌላ ግለሰብ ወይም አስተዳደር ቢሆን ኖሮ ከ 5 እስከ 10 አመታት ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ካለፉት የሃገራችንና የአለም ልምዶች ግምት ውስጥ ሲገባ ያደረኩት ግምግማ ውሃ ይቋጥራል ብዬ እገምታለሁ፡፡

የማኔጅመንት ጽንሰ ሃሳብን መሰረት በማድረግ የተደረገው ይህ የዳሰሳ ትንተና እንደሚያመላክተውም ዶ/ር አብይ ስምንቱንም የብቁ መሪ ባህርያት ያሟሉ ተወዳጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ብዬ ማጠቃለል ችያለሁ፡፡

ይህ ሲሆን ግን ጠ/ ሚኒስትር አብይ ምንም እንከን የማይወጣላቸው፣ ምንም ስህተት የማይሰሩ ፍጹምና ዘላቂ መሪ ናቸውና ምንም ትችት፣ ግምገማና ተቃውሞ ሊደርስባቸው አይገባም ማለት እንዳልሆነ ሁላችንም ልንረዳ ይገባናል፡፡ በተለያዩ አገራት እንደዚሁ ብቁና በህዝባቸው ተዋዳጅ ሆነው የወጡ መሪዎች መጨረሻቸው አምባገነት፣ ሙስናና ዘረኝነት ሆኖ በመገኘቱ በውርደት ከስልጣናቸው እንደተባረሩ ወይም እንደተገደሉ ከታሪክ ልንማር ይገባል፡፡

የጀመሩትን ዲሞክራሲያዊ ለውጥ የበለጠ ስኬታማና ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ ህዝቡ በጉልበቱ፣ በሃብቱና በእውቀቱ መደገፍ ይገባዋል፣ ሲሳሰቱም መተቸትና የማስተካከያ ሃሳቦችን መሰንዘር እኝህን መሪ የበለጠ ብቁና ውጤታማ ያደርጋቸዋል እንጂ አይጎዳቸውም፣ አያዳክማቸውምም፡፡

በመጨረሻም እኝህን መሪ እግዚአብሄር መንገዳቸውን ሁሉ ይባርክልን፣ ከ “ቀን ጅቦቹ” እንቅፋትና ጥፋት ይጠብቅልን እላለሁ!!!

*ሁሉም ቀኖችና አመተ ምህረቶች እንደ ኤ.ሮጳውያን አቆጣጠር የተመዘገቡ ናቸው፡፡

Comments — What do you think?

Click here to connect!