Home » ዜና » ዶ/ር ነጋሶ እርስዎም ህገ-መንግስቱን ለብቻዎ ሊሸከሙት ይችላሉ (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

ዶ/ር ነጋሶ እርስዎም ህገ-መንግስቱን ለብቻዎ ሊሸከሙት ይችላሉ (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

ብርሀኑ ተክለያሬድ

Negasso Gidada Solon was the 6th President of Ethiopia from 1995 until 2001.

ዛሬ በወጣችው ግዮን መፅሔት በባንዲራ ጉዳይ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በባህር ዳር ስቴዲየም የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዘው የወጡ ሰዎች ህገ መንግስቱን ያላከበሩና ህገ ወጦች መሆናቸውን ብሎም ጥቂት ግለሰቦችና የኢትዮጵያን ህዝብ ቀርቶ የአማራን ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸውን ሊያስረዱን ሞክረዋል የዶ/ሩ የአፍ ወለምታና ገደብ የለሽ የህገ መንግስቱ አፍቃሪነት ዛሬ የጀመረ ባይሆንም አሁን ሀገር ዳር እስከዳር በባንዲራው ጉዳይ በተስማማበትና አንዳንድ የመንግስት ባለ ስልጣናትም በባንዲራው ጉዳይ እንደገና ህዝቡ የሚፈልገውን ቆም ብለን ማሰብ አለብን እያሉ በሚናገሩበት ወቅት ዜጎችን በህገወጥነት መፈረጃቸው ከትዝብት ውስጥ የሚከታቸው ነው።

ለመሆኑ ዶር ነጋሶ እንዳሉት ይህ ባንዲራ የነገስታቱ የአፄ ሀይለ ስላሴና የምኒልክ ባንዲራ ያደረገው ማነው? እኔ እስከማውቀው ድረስ ይህ ባንዲራ ሀገር ዳር እስከዳር ተስማምቶ ወደ ዘመቻ ሲሔድ ይዞት የሚዘምት በድልና በደስታ ጊዜ የሚያውለበልበው “በባንዲራው” እያለ የሚምልበት የኢትዮጵያ ባንዲራ እንጂ ዶ/ሩ የጠቀሷቸው ነገስታት የግል አርማ አይደለም ሆኖም አያውቅም “በምኒልክ ጊዜ የደነቆረ ምኒልክን እያለ ይምላል” እንደሚባለው በ87 ዓ/ም በህገ መንግስት አርቃቂነታቸው ወቅት የሰሙት የነገስታቱ ጥላቻ ፍረጃ እያቃጨለባቸው ካልሆነ እንደ ታሪክ ተማሪነታቸው ይህን እውነት የሚያጡት አይመስለኝም።

ዶ/ሩ “ህገ መንግስቱን ተከትለው የወጡ ህጎችን ማክበር አለብን” ያሉትም ሌላው አስቂኝ አባባል ነው ከ1983ዓ/ም ጀምሮ በሀገራችን ያለው አገዛዝ ጉልበተኝነቱን በህግ ለማንበር ሲል ያወጣቸው ህጎች አዋጆችና መመሪያዎችን በሙሉ እያከበርን እንኑር ቢባል ኖሮ ምን ያህል ህገወጥና ኢሞራላዊ የሆኑ ተግባራትን ፈፅመን ነበር? ዛሬ እየተጀመረ ያለውን ለውጥ ያመጣውስ እንደ ፀረ ሽብር አዋጅ የሚዲያ አዋጅ የመያድ አዋጅና የማስተር ፕላን ረቂቅ የተሰኙ ህገ መንግስቱን ተከትለው ወጡ የተባሉ ህገ ወጥ አዋጆችን በመቃወም አደባባይ የወጡ ዜጎች የከፈሉት ዋጋ መሆኑን ዘንግተውት ይሆን? እርሳቸው በተደጋጋሚ “መርዝ የጫነች አዋጅ” የሚሉት እርሳቸው ከፕሬዝዳንትነት በተወገዱበት ወቅት የወጣው አዋጅም ህገ መንግስቱን ተከትሎ ወጣ የተባለ አዋጅ ነው ታዲያ ዶ/ሩ ህገ ወጥ አዋጅን ለመቃወም መስፈርታቸው የእርሳቸው ቤትና መኪና መቀማት ብቻ ይሆን??

ሌላው አስገራሚው ጉዳይ “ምልክት አልባው ባንዲራ አንድ አያደርገንም” ያሏት ንግግር ናት በእርግጥ ይህን ባንዲራ የማይቀበል ላለመቀበልም ምክንያታዊ ሀሳብ የሚያቀርብ ወገን ሊኖር ይችላል ነገር ግን እርሳቸውና 28ቱ ሰዎች ያለ ህዝብ ውይይት በክፉው መለስ ትእዛዝ ያፀደቁትስ ባለኮከቡ ባንዲራ ምን ያህል ህዝቡን አንድ አድርጎታል? አንድ አድርጎት ቢሆንማ በየበአሉና በየተቃውሞ ሰልፉ ወጣቶች ኮከብ አልባውን ባንዲራ እየለበሱ ባልተቃወሙ ነበር እንዲያውም ህዝቡ ከኮከብ አልባው ሰንደቅ በላይ ለባለኮከቡ ባንዲራ ጥልቅ ጥላቻ አለው ይህን ለማወቅም ብዙ መመራመር ሳይጠይቅ በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን መለስ ብሎ መመልከት በቂ ነው በእርግጥ ዶ/ሩ ከ1987 በፊት በባንዲራው ላይ ቀርቶ በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ጥርጣሬ ነበራቸው ነፍሱን ይማረውና ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ዶ/ሩ ከአንዲት የውጭ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ወግ “ኢትዮጵያዊ የምሆነው እኔ የምፈልጋት ኢትዮጵያ ስትመጣ ነው” እንዳሏትና ጋዜጠኛዋም የ”ማን ሀገር ፓስፖርት ይዘዋል?የማን ሀገር ማስታወቂያ ሚኒስትር ነዎት?” ብላ እንዳፋጠጠቻቸው ነግሮናል(በነገራችን ላይ ዶ/ሩ የአንድነት ፓርቲ ሊቀ መንበር በነበሩበት ወቅት ለስራ ወደ ቢሮአቸው ስመላለስ በጠረጴዛቸው ላይ ኮከብ አልባዋን ሰንደቅ በተደጋጋሚ ተመልክቻታለሁ)።

በመጨረሻም ዶ/ሩ የመሰላቸውን ሀሳብ መናገር መብታቸው ቢሆንም በባህር ዳር የተገኘውን የህዝብ ጎርፍ እንኳን ኢትዮጵያን አማራን አይወክልም ህገ ወጥ ነው ማለታቸው ሰልፉንም የአንዳንድ ግለሰቦች ስብስብ በሚል ኢህአዴጋዊ ዘዬ መግለፃቸው ግን የሚያስተዛዝብ ብቻ ሳይሆን “መትፋት ያስነውራል” ተብሎ ሊነገራቸው የሚገባ ነው ከአሰፋ ጫቦ እስከ ዋቆ ጉቱ ከታማኝ በየነ እስከ ብርሀኑ ነጋ… የሀገር ባለ ውለታዎችን ፎቶ ተሸክሞ ኢትዮጵያ እያለ ሲዘምር የዋለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብን ጥቂቶችና ህገ ወጥ እያሉ እርሳቸውና ዳዊት ዮሀንስን ጨምሮ 29 ሰዎች ብቻ የወሰኑትን ውሳኔ ህገ ወጥ ማለት የተደበቀች ግለኝነትን ማጋለጥ ካልሆነ በቀር በሳልነትን አያሳይም።

በቅርቡ በተለያዩ ከተሞች በተካሔዱ ሰልፎች ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች ተንፀባርቀዋል ከኮከብ አልባው ባንዲራ ባሻገርም የኦነግ ባንዲራ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሲውለበለብ ታይቷል ዶ/ሩን ጨምሮ ሌሎችም አፍቃሬ ህገ መንግስተሠውያን አይናቸውን የጣሉት ግን በባህር ዳሩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ ነው ይህም አንድነትን ከሚያቀነቅነው የለውጥ ሀይል በተቃራኒ መቆማቸውን ያሳያል።

ዶ/ሩም ሆኑ መሰሎቻቸው በባንዲራው ጉዳይ አንድ ነገር እንዲያውቁ እፈልጋለሁ እኛ አባቶቻችን የደሙለትንና ሀገር የጠበቁበትን ባንዲራ ለዘለአለም እንሸከመዋለን እናንተም እንከን የለሽ ህገ መንግስታችሁን ለዘለአለም ተሸከሙት ነገር ግን ጨዋና ፍቅር ፈላጊ ህዝብን በህገወጥነት መፈረጅ አይበጅምና ተውት።

አበቃሁ

2 comments

 1. ቀልድ ነው፡፡ ሰውየው ዘወትር ከሥራ መልስ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ያለ ኮምፑዩተሩ ፊት ለፊት ይቆማል፡፡ ኮምፑዩተሩ ወዲያው ወደ ሠፈሩ የሚሔድበት ባቡር ስንተኛው ሐዲድ ላይ እንደሚገኝ ይነግረዋል፡፡ አንድ ቀን ከምፑዩተሩን ለማሳሳት ፈለገና ፊቱን በጺም ሞልቶና ባልተለመደ ሁኔታ ተላብሶ ኮምፑዩተሩ ፊት ይቆማል፡፡ ኮምፑዩተሩም ወዲያው ስሙን ጠራና አንተ እኔን ለማታለል ስትሽሞነሞን የመጨረሻው ባቡር ሄደልህ አለው ይባላል፡፡
  ሁላችንም ባቡሩ እንዲያመልጠን አንፈልግም ፡፡ የጊዜያችን አብይ ጥሪ ይቅርታ ፍቅርና መደመር እንደሆነ ካልረሳንና ለሰላም እድል ከሰጥን ጉዳዮቻችን በሙሉ ለመፍታት በቂ ጊዜ ይኖረናል፡፡ ባቡሩ ማንንም ጥሎ በማይሄድበት ሁኔታ ተጠራርተን ተሳፍረን እየሔድን ችግራችንን እንፈታለን ችግራችንን እየፈታን አብረን እንጓዛለን

 2. *** በቅድሚያ አማራ ጠል የጫካው ማኒፌስቶ ሻዕቢያ፡ የህወሓት፡ ኦነግ፡ ኦብነግ የተገንጣይ አስገንጣይ ቃል ኪዳን ሲሆን የከተማው ሕገመንግስት ሲሆን ‘በልዩ ጥቅማጥቅም’ ሁሉን የጠረነፈ ነው። ሕጻን ልጅ እየበላ ያልቀሳል ይሏል የእነዚህ ዓይነት አልቅቶች ለራሳቸውም ለኦሮሞም አልሆኑም ጨዋና የዋሁን ሀገር ወዳድ ኦሮሞ አፍዘው አደንዝዘው ፵፬ ዓመት አስበሉት፡የበይ ተመልካች አደረጉት፡አረመኔ ጭፍጫፊ ተገንጣይ አሸባሪ አሰኙት እንጂ ምን አተረፉለት? እነኝህ ቁጥር መሙሊያ እንጂ ለሀገር ይጠቅማሉ ማለት ግን ዘበት ነው፡፡

  ዛሬም የተበከለ የማተራመስ አባዜ ያላቸው እርዝራዦቻቸው ሰላም! አንድነት! ፍቅር ! ሲሰበክ አይወዱም። ጥቅማጥቅማቸው ይነካል (በከብት ጋጣ) ክልል ታጉረው የሚበሉበትና የሚያባሉበት የቋንቋና ነገድ ተኮር ፌደራሊዝም፡ “ቋንቋ ባሕልና ሃይማኖታችንን ትበርዛላችሁ ልዩ ነን አትድረሱብን የእናንተ ግን የእኛም ነው” የሚሉ ቡጥቦጣቸው ይስተጓጎልባቸዋል ለነገሩ ዓብይ አህመድም ደርሶባቸዋል በወያኔ ትግሬ አመካኝተው የሚያደናቃቅፉትን የውስጡ ደንቃራዎች ቀስ እያለ ይመነጥራቸዋል! ‘በታወቁና በተከበሩ’ ኒሻን አጋጣሚውን ፈልገው አትርሱን እያሉ በየሚዲያው ወሬ ጠሽ! ዕጧ! እያረጉ ሞታቸውን ከመጠበቅ ውጪ ለድምር አልተፍጠሩም ።
  +++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
  መደ’መር ማለት…ለሀገረ ኢትዮጵያ ባለን ገንቢ ሐሳብ ላይ አዲስ ሓሳብ አፍልቀህ ጨምረበት” ማለት እንጂ ሰው ቆጠራ አደለም።አራት ነጥብ።
  ++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
  ነጋሶ ገዳዳ በቅርቡ ሕገመንግስቱን አሻሽላለሁ እያለ ሲደነፋ አልነበረም ዛሬ ምን ተገኘ ?….ይህ ሰው የአንድነት ፓርቲ መሪ ሆኖ መተዳደሪያ ደንቡ የገባው ሲባረር አደለም!? ሰለባሌጎባ ታሪክ አጥንቶ ስለሐረር የታሪክ መጽሐፍ የሚሸቅል አደለም!? ለመሆኑ የኢህአዴግ ፕሬዘዳንቶች ሥራቸው ምንድነው?
  ************************
  አሁን በሥራ ላይ ያለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እንዴት ነበር በህገ መንግስቱ የተካተተው ?
  በመጀመሪያ በህገ መንግስቱ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ብለን፣ ረቂቅ ሃሳቦችንና ጉዳዮችን ሰብስበን በዝርዝር አሰፈርን፡፡ በጥያቄ መልክ 73 ጉዳዮችን ነው በዝርዝር ያስቀመጥነው፡፡ እነዚህን 73 ጥያቄዎች ደግሞ ቅርፅ ያስያዙልን ኤክስፐርቶች (ባለሙያዎች) ነበሩ፡፡ ጥያቄዎቹ ተዘርዝረው የነበረው በመጠይቅ መልክ ሲሆን “ድጋፍ”፣ “ተቃውሞ” በሚል ተለይተው ነው፣ የህዝብ አስተያየት የተሰበሰበባቸው፡፡ የተቃውሞና ድጋፍ ውጤቱ የተሰላውም በመቶኛ ነበር፡፡
  እስቲ ለምሳሌ ያህል ይጥቀሱልን— ?
  ለምሳሌ አጨቃጫቂው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ማለትም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠልን የሚፈቅደው በመጠይቅ ዝርዝሩ ተካትቶ ነበር፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተመረጡ 23 ሺህ ቀበሌዎች ላይ ነው የህዝብ ውይይት የተደረገው፡፡ እኔ ለምሳሌ ደምቢዶሎ ላይ አወያይቻለሁ፡፡ ደምቢዶሎ ትልቅ ከተማ ነው። ህዝቡ ከ50 ሺህ አያንስም ግን እኔ ያወያየኋቸው ከ200 አይበልጡም፡፡ በዚህ አይነት ነው ውይይቶች የተካሄዱት፡፡
  በዚህ መሰረት ለምሳሌ አንቀፅ 39 (የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል) ላይ በክልል አንድ (ትግራይ) መቶ በመቶ ድጋፍ አግኝቷል። በክልል ሁለት (አፋር) ደግሞ ይህ አንቀፅ 98 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በክልል 3 (አማራ ክልል) 89 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 4 (ኦሮሚያ ላይ) 97 በመቶ ድጋፍ አኝቷል፡፡ ክልል 5 (ሶማሌ) 72 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 6 (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) 88 በመቶ ነበር ድጋፍ ያገኘው፡፡ ክልል 12 (ጋምቤላ) ደግሞ 59 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡
  የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ እንዴት በህገ መንግስቱ ላይ ተደነገገ ታዲያ?
  አርቃቂ ኮሚሽኑ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ መግባት አለበት ብሎ በራሱ አስገብቶት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በእንዲህ መልኩ የሰንደቅ አላማውን ጉዳይ በአንቀፅ 3 አስቀምጦ፣ ከየክልሉ ለተውጣጡትና የህገ መንግስት ጉባኤ አባላት አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህ አንቀፅ ስር ሶስት ንኡስ አንቀፆች አሉ፡፡ የአርማ ጉዳይን፣ የክልሎች ሰንደቅ አላማን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በጉባኤው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም ክርክር አልተካሄደም ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ውይይት የተደረገው፣ ለሁለት ቀናት ማለትም፣ ጥቅምት 29 እና 30፣ 1987 ዓ.ም የነበረ ሲሆን በሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎች 37 ብቻ ነበሩ፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ ድንጋጌ፣ 513 የጉባኤው አባላት ድጋፍ ሲሰጡበት፣ በ4 ተቃውሞና በ5 ድምፀ ተአቅቦ ነው ፀድቆ፣ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 በመሆን የተደነገገው፡፡
  በወቅቱ የአርማው መቀመጥ ጉዳይ ላይ የቀረበ ጠንካራ ተቃውሞ አልነበረም?
  ብዙም አልነበረም፡፡ አቶ ግርማ ብሩ (አሁን አምባሳደር) ብቻ ነበር “የአርማና የባንዲራ ልዩነት ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረበው እንጂ ብዙም ጠንካራ ክርክርና ጥያቄ አልተነሳም፡፡ ሻለቃ አድማሴም እንዲሁ ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡ ከክልል 5 (ሶማሌ) የተወከሉት አቶ አሊ አብዱ፤ ሶስቱ ቀለማትና አርማው እንዳለ ሆኖ፣ “ነጭ” ቀለም ይጨመርበት የሚል ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ከአፋርም እንዲሁ ነጭ ቀለም ይጨመርበት የሚል ሀሳብ ተሰንዝሮ ነበር፡፡ በዚህ የአርማ መጨመር ጉዳይ ላይ በተሰጠው የጉባኤው አባላት ድምፅ መሰረት፤ 517 ሰዎች አርማ መጨመር አለበት ሲሉ፣ 4 ተቃውሞ እንዲሁም 4 ድምፀ ተአቅቦ አድርገው ነበር፡፡
  የክልሎች ሰንደቅ አላማን በተመለከተስ — የተነሱ ሃሳቦችና ክርክሮች ነበሩ?
  አሁን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ተደንግጎ የሚገኘውና “የፌደራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ አላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል” የሚለውን በተመለከተ፣ ብዙም የተቃወመ አልነበረም፡፡ ነገር ግን “ብቻውን የሚውለበለብ ሳይሆን ከፌደራሉ ጋር ጎን ለጎን ነው የሚውለው” በሚለው ላይ የተወሰኑ ሃሳቦች ተሰንዝረው ነበር፡፡ በዚህ ጎን ለጎን መውለብለብ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ በተሰጠ ድምፅ፡- ድጋፍ 5፣ ተቃውሞ (ጎን ለጎን መሰቀል አያስፈልግም ያሉ) ደግሞ 517 ነበሩ፡፡ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉ 8 ነበሩ፡፡
  አሁን ግን ከፌደራሉ ጎን ለጎን መሆን አለበት የሚል መመሪያ ወጥቷል ….
  ይሄ እንግዲህ በህገ መንግስቱ ያልተወሰነ፣ ነገር ግን በመመሪያ የወጣ ይመስለኛል፡፡
  በፌደራሉ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የቀረቡ ሌሎች ሃሳቦችስ ነበሩ?
  እንግዲህ ይሄ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት በዓለም ላይ የታወቅንበት፣ የነፃነት አርማም ስለሆነ መቀየር አያስፈልግም፤ ነገር ግን በመሃሉ የሃይማኖት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትን የሚወክል አርማ የግድ መኖር አለበት—የሚል ሃሳብ ነው በስፋት የተሰነዘረው፡፡
  በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ ከፍተኛ አለመግባባትና ልዩነት እየተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?ቀደም ብሎ እኔ እንደማውቀው፣ የኢህአዴግ ስብሰባዎች ካልሆኑ በስተቀር ብዙ ጊዜ ህዝቡ ይዞ የሚወጣው ሌጣውን ነበር፡፡ በተለይ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል አካባቢ በተለይ ኮከቡ ያለበትን ሠንደቅ ዓላማ ተቃውሞ እንደሚቀርብበት በሚገባ የተመለከትኩት፣ በእነዚህ ሁለት ዓመታት (2008 እና 2009) ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ነው፡፡ በተቃውሞዎቹ በግልፅ በባለኮከቡ ሠንደቅ ዓላማ ያለው ተቃውሞ በአብዛኛው ታይቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሄን ሰንደቅ ዓላማ ይቃወማሉ፡፡
  አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ይህ አሁን መመሪያ ወጥቶለት በግድ ሊተገበር በታሠበው ሠንደቅ ዓላማና አርማ ላይ ህዝቡ ውይይት አላደረገበትም። በሌላ በኩል ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በእኩል በሂደቱ አልተሣተፉም፡፡ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ኢሠፓ ሌሎችም በዚህ ሂደት አልተሣተፉም። እነዚህ ኢትዮጵያውን ናቸው፣ ደጋፊዎች አሏቸው፤ ነገር ግን በሠንደቅ ዓላማው ጉዳይ ውይይት አላደረጉም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይም እንዲሁ። በሌላ በኩል፤ በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይም ሆነ በፀደቀው ህገ መንግስት ላይ ህዝቡ የራሱ ፍላጎት ስለመካተቱ የሚያንፀባርቅበት ህዝበ ውሣኔ አልተካሄደም፡፡ እንዳለ ወደ ህዝቡ ነው ፀድቆ የወረደው፡፡ የሠንደቅ ዓላማው ሆነ ሌሎች ችግሮች የሚመነጩት፣ አንደኛው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ህዝበ ውሣኔ ካልተካሄደበት ስርአቱ ወይም ህገ መንግስቱ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳለው ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻለውም ማለት ነው፡፡
  አሁንም የሚሻለው በህገ መንግስቱም ሆነ በሠንደቅ አላማው ጉዳይ ላይ የማሻሻያ ሃሣቦች ካሉ፣ ማሻሻያ ይደረግ የሚሉ አካላት ፊርማ አሠባስበው ቢያቀርቡና፣ ጉባኤ ተደርጎ፣ ለህዝብ ውሳኔ ቢቀርብ ነው፡፡ ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ህዝበ ውሣኔ ማካሄድ ነው፡፡(ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡- በሰንደቅ ዓላማና በህገ መንግስቱ ዙሪያ በጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ) ኦክቶበር 14/2017

Comments — What do you think?

Click here to connect!