Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » በቅድሚያ ራሳችንን እንለውጥ (ይገረም አለሙ)

በቅድሚያ ራሳችንን እንለውጥ (ይገረም አለሙ)

ይገረም አለሙ

በኢትዮጵያችን ስለ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እየተዘመረ፣ ትግል እየተካሄደ፣ እየተሞተና እየተገደለ ከአንድ ትውልድ በላይ ዘመን ታልፏል፡ነገር ግን ለውጥ ጠያቂዎቹ/ፈላጊዎቹ  ራሳቸው ባለመለወጣቸው ሥልጣን ላይ ካሉት ገዢዎች ባልተናነሰ ራሳቸው የዴሞክራሲ አንቅፋቶች እየሆኑ ኢትዮጵያችን ለዴሞክራሲ ሾተላይ እንደሆነች አለች፡፡ዛሬ እኛ ዜጎች አይደለንም ፖለቲከኞቹ፤ እነርሱም አይደሉ ደደቢቶች ራሳቸው ባላሰቡት ሁኔታ በውስጣቸው አድገው አመች ግዜ ሲያገኙ ውስጥ ለውስጥ የደረጁትን ሀሳብና ያደራጁትን ሰው ይዘው ብቅ ያሉ የለውጥ ሰዎች በታዩበት ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰማው አሉታዊ ነገር የሚያሳየው ብዙዎቻችን ዛሬም ከአርባና ሀምሳ አመት በፊት ከነበረው የፖለቲካ አካሄድ ያለተለወጥን  መሆናችንን ነው፡፡ ይበልጥ አስገራሚው ነገር ደግሞ ከለማበት የተጋባባት እንዲሉ ሆኖ በዚህ በሽታ የተለከፉ ወጣቶች መታየታቸው ነው፡፡

በርግጥ ቅዱስ መጽሀፍ ከፍሬአቸው ታውቋችኋላችሁ እንደሚለው የአንዳንዶቹ አድራጎት በአንደበታቸው እንጂ ከምር ለውጥ ፈላጊ አለመሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ከተቀዋሚው ጎራም ሆነ ከራሱ ከወያኔ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያሰቡት/የሰጉት እንቅስቃሴ ከታዬ ከደደቢቶቹ ባልተናነሰ ለማጨነገፍ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ትንሽ ጠንከር ብሎ መንቀሳቀስ የጀመረና የህዝብ ድጋፍ ማግኘት የቻለ ተቀዋሚ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ብቅ ሲል በእርዳ ተራዳ ሲዘመትበት አይተናል ይሄው አሁን ደግሞ ከወያኔ ጉያ አፈትልከው በወጡ የለውጥ ኃይሎች ላይ የተያዘውን ዘመቻ ማየት በቂ ይሆናል፡፡ለአንዳንዶቹ ባሉበት ሁኔታ መቀጠል የወያኔ በሥልጣን መቆየት አስፈላጊ እንደሆነ ያመኑ  ይመስላል፡፡እርግጥ ነው መሰረታቸውም ሆነ እድገታቸው ብሎም ኑሮአቸው ተቃውሞ ሆኑ ወገኖች የሚቃወሙት ከጠፋ ይህን ሁሉ ያናጋባቸዋልና ስጋታቸው ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ከበአለ ስመታቸው ማግስት አንስቶ ግዜ ሳያባክኑ ከቦታ ቦታ እየዞሩ ስለ ፍቅር ሲሰብኩ ስለ ጥላቻ፣ ስለ አንድነት ሲናገሩ ስለ  ክልል ስለ ጎሳ ስለ መለያየት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ከልብ በእምነት ሲናገሩ ስለ ዘር ሰለ ክልል ወዘተ የሚናገሩ የሚጽፉ ሰዎች በርግጥ የዴሞክራሲ ናፋቂዎች የሀገራዊ ለውጥ ፈላጊዎቸ ናቸው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለውጠው ከግዜው ጋር መራመድ በመቻል የለውጡ አካል ቢሆኑ ለራሳቸው ይበጃቸዋል፣ ለሀገርም ይበጃል፤ታሪክና ትውልድም በክብር ያወሱዋቸል ይዘክሯቸዋል፡፡ ይህ የለውጥ ጥንስስ በእርግጥ በፈጣሪ ፈቃድ የተገኘ ከሆነ ማንም ሊያስቆመው አይችልምና እነርሱ ለዚህ ሊበቁ ካልታደሉ ለውጡ ይለውጣቸዋል ወይ ድጧቸው ያልፋል፡፡

ይህን ሳስብ አንድ ነገር ትውስ አለኝ፡፡ ግዜው 1992 ዓ .ም ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች በመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ቢሮ ተገናኝተናል፡፡ የመገናኘታችን ምክንያት በፓርቲዎች በጋራ ሊወጣ የታሰበ መግለጫ ረቂቅ ለየፓርቲዎቹ ደርሶ የየራሳቸውን ማስተካከያ አድርገው በሱ ላይ ለመነጋገርና መግለጫውን የመጨረሻ መልክ ለማስያዝ ከየፓርቲዎቻችን ተወክለን ነው፡፡ የእኔ ተራ ደርሶ በፓርቲዬ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠውን እርማት አቀረብኩ፡፡ አንድ ሰው እንዴ ! ይህን ሁሉ ወያኔ ከፈጸመ እኛ ምን ይዘን ልንቃወም ነው ሲል ተቃወመ፡፡ ያ ሰው በዛን ወቅት የብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ብዴህ) የአመራር አባል የነበረ አሁን የዘመናት ህልሙ ሰምሮለት የአንድነት ሊቀመንበር ለመባል የበቃው ትእግስቱ አዎሉ ነው፡፡ ወያኔ የሚነገረውን የማይሰማ የሚጠየቀውን የማይመልስ መሆኑ ከፋ እንጂ ተቀብሎ መሻሻል ሰምቶ መለወጥ ቢችል እኛ የተቀዋሚነት ሱስ የለብንም፡፡ ወያኔ ይህን ማድረግ ቢችል ፖለቲካችን ከመሰረቱ በተለወጠ ነበር ወዘተ በማለት ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ከእርሱ በቀር የተቃወመ ባይኖርም እሱ አሻፈረኝ እንዳለ በመጽናቱ  በወቅቱ ቀኝ አዝማች ነቅአጥበብ በቀለ ተሸኝተው ቦታውን በግዜአዊነት የያዙት(ከእስር ተፈተው) አቶ አሊ እንደሪስ ነበሩና እርሳቸው  ጋር ቀረብን ፡ጉዳዩን ካዳመጡ በኋላ ሌሎቹን እናንተ ምን ትላላችሁ በማለት ጠይቀው ፓርቲው ባቀረበው ማሻሻያ ለላይ ችግር አላየንበትም የሚል ምላሽ ስላገኙ ማሻሻያው ተካቶ መግለጫው እንዲጻፍ ወሰኑ፡፡  ምን ይዘን እንቃወማለን ሥጋት ወይንም የምንቃወም አታሳጣን ጸሎት ዛሬም የብዙዎቸ ሥጋት ሆኖ እየታዬ ነው፡፡

ሁላችንም ከምንለው በስተጀርባ የተደበቀ ፍላጎት ከሌለን በስተቀረ የምንሻውን ለውጥ ለማግኘት በቅድሚያ ራሳችንን በመለወጥ በምንችለው ሁሉ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖሮብናል፡፡ ራሳችንን ሳንለውጥ በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ምንይልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል አይነት ተግባር እያከናወንን ለውጥ ማግኘት አይቻልም፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሀም ሊንከን ናቸው አሉ የተናገሩት፡፡ ከተነገረ ዘመናት የተቆጠሩ ቢሆንም መልእክቱ  ዛሬም አዲስ ነው፡፡  «አንድ ትውልድ ያልፍና ሌላ ትወልድ ይተካል፣ ዓለም/መሬት ግን ለዘለአለም ትኖራለች፡፡ ጸጥ ረጭ ያለው ያለፈው ግዜ ፍልሰፍናዎች (ዶግማስ) አውሎ ነፋሳዊ ለሆነው ለዛሬው ችግር ለመፍትሄነት አይመጥኑም፡፡ ጊዜያችን ችግር ያዘለ ስለሆነ በአዲስ ሁኔታ ማሰብና በአዲስ ሁኔታም መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ ማውረድ ይገባል፡፡ ያን ግዜ አገራችንን ለማዳን እንችላለን፡፡ ታሪክን ልናመልጥ አንችልም፣ልንሸሸው አይሆንልንም፣ ክፉም ሰራን ደግ እንዘከራለን፣ (እንታወሳለን) ግለሰባዊ መታወቅ ወይም አለመታወቅ አንዳችንንም ሆነ ሁላችንን አያተርፈንም፣የምናልፍበት እሳታዊ ፈተና (ፍርድ) በክብር ወይንም በውርደት ማለፋችንን ይመሰክራል»

አዎ በቀይ ሽብር ነጭ ሽብር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አብዮት ወቅት አስተሳሰብ ላይ ተሁኖም  ሆነ በ1983 ዓ.ም በመላ ሀገራችን ተሰራጭቶ ከሀገራዊነት አልፎ ዓለም አቀፋዊነትን ሲሰብኩ የነበሩ ሰዎችን ሳይቀር ማጥመድ በቻለው የጎሳ አስተሳሰብ ያለንበትንና የማንፈልገውን ተሻገርን ወደ ለውጥ መስክ መድረስ አንችልም፡፡

ለነገሩ ሰሚና ተግባሪ ነው እንጂ የጠፋው አሸጋግሮ መጪን ማየትና ከራስ ባይ ለሀገርና ለህዝብ ማሰብ  የቻሉ ሰዎች አስቀድመው ይበጃል ያሉትን  ተናግረዋል ጽፈዋል፡፡ ይህን የታዘቡ አንድ ሰው ሙዳይ ትሰኝ በነበረችው መጽሄት ላይ ሀሳባቸውን ሲገልጹ ምን የሚባል አለ ብለነው ብለነው ሲያልቅብን ግዜ እየደገምነው ነው ብለው ነበር፡፡ ዛሬ ካሉ ምን ይሉ ይሆን!! እኔም ከተባሉት ለሀሳቤ ማጠናከሪያ ልጥቀስ፡፡

ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖለቲካና ምርጫ ፣በተሰኘው መጽፋቸው ለለውጥ ቅድሚያ ራስን የመለወጥን  አስፈላጊነት ሲገልጹ «እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ከልጅነት እስከ እውቀት በውስጡ የተመረገውን የጌትነትና የሎሌነት ባህል ፍቅፍቆ ማርገፍ አለበት፡፡ በግድ የአሰተሳሰብ የጽዳት ዘመቻ ያስፈልገናል፡፡ዓላማን የማጥራት ዘመቻ ያስፈልግናል፡፡ በግድ የነጻነትና የእኩልነት አራማጆች በቁርጠኝነት መነሳትና ማሳየት ያስፈልገናል፡፡ብዙዎቹ የተቀናቃኝ መሪዎች ላይ የሚታየው የድሮው መኳንንትና መሳፍንት ለመምሰል የመሞከር ጠባይና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሎሌዎችን በገንዘብ ሆነ በወደፊት እየገዙ የአገዛዝን ባህል ለማራማድ የሚደረገው ሙከራ የፖለቲካቸውን ሥርዓት አያራምድም፡፡ጥረቱ ሁሉ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ለመለወጥ እንጂ ሥርዓትን ለመለወጥ አይመስልም(ገጽ 32)

በእውነቱ አንዳንዶች ምን እንደሚፈልጉ ግራ የሚገቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ተንኳሰሰ እያሉ ሲጮኹ ከርመው ዛሬ ከማንምና ከምንም በላይ ስለ ኢትዮጵያዊነት ከልባቸው በእምነት የሚናገሩ የሚናገሩትን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል የሚገቡና የህዝቡን ድጋፍ የሚጠይቁ ሰዎች በየመድረኩ ሲታዩ ቃላት እየሰነጠቁ የልዩነት መንገድ እየፈለጉ መቃወም የለውጥ ፋላጎት ነው ሊሰኝ የሚያበቃ ምንም ምክንያት ሊቀርብለት አይችልም፡፡ ወያኔ በጎጥ ከፋፍሎ በሀይማኖት አለያይቶ ሲያጣላን ኖረ የሚሉ ሰዎች ከስንት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ አንድ ነን ስንደምር ደግሞ የማንወጣው ዳገት አይኖርም እያሉ ስለ ፍቅር የሚሰብኩ ስለ አንድነት የሚያዜሙ ሰዎች በመድረኩ መታየት ሲጀምሩ ለተቃውሞ መሽቀዳደም ወያኔን ከነ ደደቢት አስተሳሰቡ እድሜ ይስጥልን ከማለት የሚለይ አይሆንም፡፡

የፖለቲከኞቻችን ነገረ ሥራ ያስጨነቀው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን በአንድ ወቅት ሲናገር፡ “ኒሊሰን ማንዴላ እንደ ስምጥ ሸለቆ ቁልቁል የጠለቀውን “የልዩነት” መቀመቅ በዴሞክራሲ ድልድይ አስተካክሎ የመቻቻልን ጥበብ ለወገኑ ሲታደግ የእኛ ተቀዋሚዎች ፖለቲከኞች ግን በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል አዳዲስ ስምጥ ሸለቆዎችን አንዳይቆፍሩ እሰጋለሁ” ብሎ ነበር፡፡

ደደቢቶች ለሀያ ሰባት አመት እዚህም እዛም የቆፈሩትን የልዩነት መቀመቅ ሳንደፍንና በህዝቡ መካከል የኖረ አንድነቱን ፍቅሩንና መተሳሰቡን ሳንመልስ ሌሎች ስራዎችን ማሰብ ከንቱ ነው ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር  ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ከግዜ ጋር ሩጫ በተያያዙበት ወቅት ሌሎች ጉድጓዱን ለመድፈን ከማገዝ ያም ቢቀር በርጋታ የሚሆነውን ከመጠበቅ ይልቅ ደደቢቶች የቆፈሩትን ጉድጓድ ይበል ለማጥለቅና ለማስፈፋት ብሎም አዳዲስ የልዩነት ጉድጓድ ለመቆፈር ደፋ ቀና ሲሉ አይታዩዋችሁም፡፡ እግዚአብሄር ልብ ይስጣቸው፡፡

በአንድ ጀንበር የሀገር ችገር ያውም ለዘመናት የተከመረ ቀርቶ የአንድ ቤተሰብ ችግር አይፈታም፡፡በአንድ ጀንበር ቤት አይታደስም፤ከነበረ ወደ አልነበረ ፤ከተኖረበት ወደ ሚመኙት ወዘተ በአንድ ጀንበር መለወጥ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ነቃፊዎች፣ ተችዎች ለምን ይሄ አይሆንም ብሎ ጠያቂዎች ሰከን ብለው ዛሬን ሳይሆን ነገን አሸጋግረው እያዩ ቢናገሩ ቢጽፉ መልካም ይሆናል፡፡ አርቆ አሳቢ ለነገ ራዕይ ያለው ዛሬን በምንም ሁኔታ አያበላሽም፡፡ አበው ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ የት አባቷ ገድየ ሞቼ ማለት ጦም ማደርን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 23/1935 ለፓርላማ አባላት ካሰሙት ንግግር ተብሎ የሚጠቀሰው “ የሚመከረው ነገር በዝግታና በጥልቅ ታስቦ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትእግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ነው፡፡” የሚለው አባባላቸው ሰሚና ፈጻሚ ቢያገኝ የዘለዓለም ምክር ነበር፡፡አበውም በምሳሌዊ አነጋገራቸው የአነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ፤ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል ወዘተ የሚሉትም የአስቦና መክሮ መወሰንን፣ ሰከን ብሎ ትናንትን ከዛሬ እያመሳከሩ ከዛም እየተመከሩና እየተማሩ ከዛሬ ተነስተው ስለነገ እያለሙ የመስራትን ጠቀሜታ በአንጻሩ ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ነገር ርባና ቢስና ዘለቄታ የሌለው መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

በመሆኑም በአንድ ቀን ጀንበር ሁሉ እንዲለወጥ የምትሹ “አብዮተኞች” በአነበባችሁትም ሆነ በሰማችሁት ጉዳይ ታውሞ ስታሰሙ  ይህ ምን ማለት ነው ብላችሁ ጠይቃችሁ ሲሆን ከሌላ መክራችሁ ካልሆነም በራሳችሁ አብላልታችሁ ቢሆን ደግ ነው፡፡ መናገሪያውም መጻፊያውም ተመችቶአልና በቅጽበት እየወጣችሁ ተቃውሞ ማሰማት  ትችት ማብዛት ግን አልጠቀመም አይጠቅምም፡፡ ዛሬ ግዜው የሚጠይቀው አስቦ መክሮና ዘክሮ መወሰንን አስተውሎ መራመድን ነው፡፡በዚህ ረገድ የተያዘው ጅምር መልካም ነውና ዘለቄታውን ያሳምረው እያሉ በሚችሉት አቅም መርዳት የእውነተኛ ዜጋ ተግባር ይመስለኛል፡፤

“እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ርስ በርሳችን አንፈራረድ፣ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይንም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቁረጡ፤”(የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች  ም/Ú፬ ቁÚ፫)

One comment

  1. Dagmawi Gudu Kassa

    Good advice. But we need miracles to get rid of TPLF from its pivotal place in our politics. As far as any PM is elected by the will of TPLF, they are definitely their stooge or else they will get the sack sooner rather than later. To me it is so foolish to expect anything good from this apartheid system.
    Dear Yigerem, I understand your worries. As you said, it is good to give a chance to this young PM. Nevertheless, these crooked Woyannes will never allow him to go ahead with his promises. As you may know, they have controlled everything under the sun of Ethiopia. The army, the police, the security, the intelligence organ, the ministries, the economy of the country … the air, the water, the sunlight, even surprisingly God Himslef seems to favor them,… almost everything is under their control. So they don’t care who lives at Arat Kilo Palace as long as they enjoy Ethiopia’s milk as usual. It is when I see things from this perspective that I become desperate even after listening the titivating words of ‘our’ PM. On my behalf, I am not that much pessimist to get myself included among the nay-Sayers mentioned in your articles. But it is out of being option-less that makes me oppose anything done in the village of TPLF. I think a real change comes through sacrifice, though I am not clear with the direction that sacrifice comes from.
    I appreciate your piece of advice and share many of the ideas you mentioned. And please try to be less judgmental because we have been through harsh times especially in the past 27 years. No one shall not wrong us if we become suspicious of anything that comes from the womb of TPLF. You should remember the Amharic saying ‘ebab yaye bellit bereye` or ‘kaltazelku alamnim.’ The psychological bruise TPLF has been carving onto our brain for the last good number of years doesn’t easily allow us to be preys of your warnings and admonitions explained in your piece of writing. As you have the right to trust the newly ‘elected’ PM, allow others to mistrust him and/or the way he has come to such political scenario. But most of all, time will tell us everything and history will give us its last judgment. Until then it is better to respect differing views and we all should refrain from badmouthing each other.

Comments — What do you think?