Home » ዜና » በሞያሌ በግፍ ስለ ተጨፈጨፉት ወገኖቻችን የተሰጠ የኃዘን መግለጫ

በሞያሌ በግፍ ስለ ተጨፈጨፉት ወገኖቻችን የተሰጠ የኃዘን መግለጫ

መቆሚያ ያጣው የኢትዮጵያ እንባ

በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ከአውስትራልያ ሀገረ ስብከት

የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቋልና ስለዚህ አለቅሳለሁ ዓይኔ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል ሰቆቃ ኤር 116

ይህ ጩኸት የኢትዮጵያ የእየለቱ ጩኸት ሁኖ ሲቀጥል ዓመታት ተቈጠሩ። ያለፈውን የወገኖቻችን እልቂት ሰምተን እንባችን በወጉ ሳንጠርግ አሁንም በየቀኑ ከሚፈሰው የንጹሐን ደም ባለፈ በሰላማዊ መንገድ በሥራ ቦታቸው ያሉ ወገኖቻችንን በጅምላ ጨፍጭፎ በስሕትት ነው እያለ  የሚንቅና  የሚቀልድ  አካል ልባችንን አድምቶታል። ይህ ተግባር አንድ አገር እመራለሁ ከሚል አካል ይቅርና በሰው ደረጃ ከሚንቀሳቀስ ጤናማ አእምሮ የሚከናወን ድርጊት አይደለም።Ethiopian orthodox church cross

ኤርምያስ በነበረበት ዘመን መከራና ስቃይ ለሚደርስበት ሕዝብ የጮኸው የኃዘን ጩኸት ፣ ዛሬም በኢትዮያ ምድር የሚጮኽ ጩኸት ነው ። ነቢዩ የሕዝቡን መከራ እያየ ዝም ማለት አቅቶት ይህንን የመከራ እሮሮ አንጎራጎረ ። እኛም ዛሬ በባዕድ ምድር ሁነን የወገኖቻችንን እልቂት ስንሰማ የመረረ ኃዘን ውስጥ ሁንን ነው ይህን አጭር የልብ ስብራታችንን የሚገልጥ መግለጫ ያወጣነው።

ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ “በስሕተት ነው” የሚለው ቀልድ ነው ።  አንድ የታጠቀ ኃይል በጦር ሜዳ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ይህን ያህል ሰው ለመግደል እንዴት ሊሳሳት ይችላል ? ይህ ከሆነ አእምሮው የተነካ ሰው መሆን አለበት ፣ በሠለጠነው ዓለም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አእምሮው የተነካ ይባላል ። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሰው ማኅበረሰቡን እንዳይጎዳ ወደ ጥብቅ የእሥር ወይም የጥበቃ ቦታ ይገባል ። መሣሪያ ከእጁ እንዳይገኝ ጥንቃቄ ይደረጋል ። በኢትዮጵያ አእምሯቸው የተነካው የሚባሉት ታዘው የተኮሱት ሳይሆኑ ፣ አዛዦቹና ሰው እንዲገድሉ ሥልጣን የሚሰጠውን “የአስቸኳይ ጊዜ” የተባለውን የጥፋት አዋጅ ያወጡት ግለሰቦች ናቸው ። መሣሪያቸውንና የሚገለገሉበትን አዋጅ መነጠቅ ያለባቸው እነሱ ናቸው።

አሁን በኢትዮጵያ በሕወኃት የሚመራ ሥርዓት ፥ በሥልጣን ወዳድነት የአዕምሮ መቃወስ የገጠማቸው ግለሰቦች የተጠራቀሙበት ስለ ሆነ ለአገርና ለሕዝብ አደጋ ነው ። ስለሆነም መታሰር ያለበት ይህ ሥርዓት ነው።

ሥር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይሆን በሥልጣን አጣለሁ በሽታ የተያዘ ፥ ከጤናማ ሰው አእምሮ ውጭ እንደ አውሬ የሚያስቡ የግለሰቦች ስብስብ እንጂ መንግሥትን በመንግሥትነት ሊመራ የሚችል ሥርዐት አይደለም።

ይህን የምንልበት ምክንያት ሰውን ያህል ፍጡር ትንፋሽን የሚቈጣጠር አዋጅ አውጥቶ ዘወትር ሰዎችን እያስገደለ “በስህተት ነው” የሚለው አባባል ተቀባይነት ሊያግኝ የሚችለው የእእምሮ ጤና በጎደላቸው ሰዎች ዘንድ ብቻ መሆን አለበት እንጂ ፤ በትክክለኛና በጤናማ አእምሮ የሚያስብ ማኅበረ ሰብ ይህን የዕብዶች ሥርዓት አይቀበልም ። እንዲያውም ሊያውግዘው ይገባል።

ከሁለት ሰው በላይ በአንድ ቦታ ላይ መቆምና መሄድ አትችሉም የሚለውን አዋጅ ያወጅኩት ለሕዝብ ነጻነት ስል ነው የሚለው አባባል በተጨባጩ ዓለም ላይ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ። በዚህ አዋጅ መሠረት በትዳር የሚኖሩ ጥንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር መሄድ አይችሉም ፥ ሁለት ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለማድረስ ሁለት ጊዜ መመላለስ አለባቸው ፣ አባት ወይም እናት ከሁለቱ ልጆቻቸው ጋር ሲሄዱ ቢገኙ አዋጁን ጥሳችኋል ተብለው ሊገደሉ ወይም ተደብድበው ሊታሰሩ ይችላሉ። ምክንያቱም ሕጉ ይህን አዋጅ የሚያስከብሩት አካላት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋልና ነው።

እነዚህ ወታደሮችም ይህን የመግደል አዋጅ ተጠቅመው ነው ንጹሐን ወገኖቻችንን በጥይት ጨፍጭፈዋል ።  በመሆኑም ነፍሰ ገዳዮች መባል ያለባቸው ወታደሮቹ ሳይሆኑ አዋጁን ያወጀው አካል ነው። መታሰርና መሣሪያውን መቀማት ያለበትም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እያሉ የሚቀልዱበት ወያኔ የሚመራው ሥርዓትና መንግሥት ነው ። ስለዚህ በሞቱ ወገኖቻችን መሪር ኀዘናችንን እየገለጥን ፣ የሕወኃት የጦር አዛዦችና ባለ ሥልጣኖቹ ለፍርድ እዲቀርቡ ፥ በአውስትራልያ ሀገረ ስብከት ስም እንጠይቃለን።

በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ወገናችን ሆይ ! የትኛውንም ቋንቋ የምትናገር ፥ በየትኛውም ነገድ የምትጠራ ፥ በየትኛውም ሃይማኖት የምታመልክ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬ በሞያሌና በሌላውም የኦሮሞኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን እየፈሰሰ ያለው ደም ያንተ ደም ነው ። ሞታቸው ሞትህ ነው ፣ ስደታቸው ስደትህ ነው ፣ እየተንገላታ ያለው የአንተ አካል መሆኑን እወቅ ። መቃብር የገባው የአንተ የራስህ አካል ነው ። ስለዚህ ዛሬ አንተ ስላልሞትክ ለነገ ዋስትና ያለህ አይምሰለህ ። ነገ ጧት ስትወጣ ከአንድ ጓደኛህ ጋር ስትገናኝና ሁለት ሁናችሁ ትምህርት ቤት ወይም ሥራ እንዲሁም ገበያ ልሂድ ብትል አንተም ሞያሌ እንደ ሞቱት ወገኖችህ ትሞታለህ ፥ እነርሱም አንተን ናቸው ፥ አንተም እነርሱን ነህ።

ስለዚህ ይህን የኢትዮጵያን ሕዝብ በማያቋርጥ ኀዘን ውስጥ እንዲገባ ያደረግ ሥርዐት ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲያበቃ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ እንዲተባበር ፣ የተሰደዱት በያሉበት እርዳታ እንዲያገኙ እንድታደርጉ በግፍ በተጨፈጨፉት ወጎኖቻችን ስም ጥሪ እናቀርባለን።

የሞቱትን ነፍሳቸውን እንዲምር ለወገኖቻቸውና እንዲሁም ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታትን ጽንአትን ኅብረትን እንዲሰጥ ወደ አምላክችን እንጸልያለን ። የፖለቲካ መሪዎች ፥ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ፥ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አቀንቃኞች ሁሉ የሕዝባቸውን መከራ ለማሳጠር ሲሉ እንዲተበባበሩና ይህን ሰላማዊ የሕዝብ ትግል ከዳር እንዲያደርሱ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ጩኸት ጥሪ እናቀርባለን።

አባ ጴጥሮስ

የአውስትራልያና የኒውዝላንድ ሊቀ ጳጳስ ።

ሜልቦርን አውስትራልያ

One comment

  1. A very sound call specially to those who create all kinds of reasons and try to divide the people’s power to give Wayane/TPLF free ride and free hand to kill and massacre Ethiopians.Let, it be known that our people have no guaranty if they can wake up the next morning and leave the house and return.Their live is in the hands of the soldier with machine gun controlling the streets.People this is not a life any country in the World has no acceptance for and is Nazysim.For a minute put your selves in the shoes of the Ethiopian people in particular Moyale.Some of them were begging for their lives to be speared falling on their knees when the fascist army took their lives away from them for nothing and make a mockery out of it.
    As the statement justified it when you kill your are killing also part of you not only they are human beings but are Ethiopians and part of you.Please those of you who stand on the side and spread none sense staffs to wicken the Qere and the Fano stay away.Zip it.Ethiopia and Ethiopians will be saved by our unity.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!