Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » በፈረቃ መታገል በፈረቃ መገደል እሥከመቼ?

በፈረቃ መታገል በፈረቃ መገደል እሥከመቼ?

መንገሻ ዳኜ

የተቃውሞ ሰልፍ በወሊሶ

ፋሺሥታዊው የህውዓት አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ዕለት ጀምሮ ላለፉት 26 ዓመታት በሐገራችንና በሕዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ የበለጠ በማጠናከር የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም በመሯሯጥ ላይ ይገኛል።የሕዝብን የመብት ጥያቄ በኃይል በማፈን ህጋዊና ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል፤በየማጎርያ ካምፑ በማሰቃየትና በማሰደድ በየወቅቱ የሚነሳበትን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመጨፍለቅ በሚወስደው ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆነ ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል ፤ ቆስለዋል ፤ በየዕስር ቤቱ ታጉረዋል ፤ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ፤ ሐገር ጥለው ተሰደዋል ። አሁንም በመሰደድ ላይ ይገኛሉ።

ይሁንና ሕዝባችን የአገዛዙን አፈናና ግድያ በመቋቋም ለመብቱና ለነጻነቱ የሚያደርገውን የአልገዛም ባይነት የነጻነት ትግል አጠናክሮ በመቀጠሉ የተደናገጠው ፋሺሥታዊው የህውዓት አገዛዝ ሕዝባችንን በብሔርና በኃይማኖት በመከፋፈል የተወሰኑ ሆድ አደሮችን በጥቅም በመደለል የተነሳበትን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማኮላሸት ቀን ከሌሊት በመስራት ላይ ይገኛል። ካለፉት አመታት ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የመብት ጥያቄ በኃይል ለመደፍጠጥ ባሳለፍነው ዓመት ባወጣው የአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለጊዜው ትንፋሽ ያገኘ ቢመስለውም በመላ የሐገሪቱ ክፍል በተለይ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞና ህዝባዊ አመጽ ማሥቆም እንዳልቻለ ይታወቃል።ይልቁንም ህዝባዊ ተቃውሞውና አመጹ በይበልጥ ተጠናክሮ በተቀናጀ መልኩ የፋሺሥቱን አገዛዝ እያሽመደመደው ይገኛል። በዚህ ረገድ ቄሮ የሚል መጠርያ ይዞ በመላው ኦሮምያ ክልል የህውዓትን  ፋሺሥታዊ አገዛዝ ቁም ሥቅሉን በማሳየት ላይ የሚገኘው የኦሮሞ ወጣት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ ይገኛል።

ካለፈው ስህተቱ የማይማረው የህውሀት አገዛዝ በአብዛኛው የሐገራችን ክፍሎች በተለይ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በስፋት እየተከናወነ ያለውን የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግልና የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እንደለመደው በጠብመንጃ ኃይል ለመደፍጠጥና በጉልበት የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ሲውተረተር ይታያል። ዓላማውንም ለማሳካት አሁንም ባለፈው ዓመት ሞክሮ ያልተሳካለትን የአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ አውጆ በህዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ላይ ይገኛል። ይሁንና ያሁኑም የአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳለፈው ሁሉ ከማሥፈራርያነት አልፎ የህዝብን መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄ ለማስቆም የማይችል መሆኑንና በተቃራኒው ነጻነት የተጠማው ህዝባችን ትግሉን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያነሳሳው ህውሀቶች ሊገነዘቡት ይገባል።

የህውሀት አገዛዝ በሐገር ውሥጥ ህዝባችን ፍርሀትን አሥወግዶ መብቱን ለማሥከበር በሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል ተገዶ በግዛቴ ውሥጥ ምንም አይነት የፖለቲካ እሥረኛ የለም ሲል እንዳልነበረ ሁሉ በቅርቡ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች፧ የሙሥሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች እና ጋዜጠኞችን ከእሥር መፍታቱ ይታወቃል።ይሁን እንጂ የወያኔው አገዛዝ በአንድ በኩል የተወሰኑ የፖለቲካ እሥረኞችን እየፈታ በምትኩ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና የፖለቲካ መሪዎችን በማሰር እንዲሁም ግድያውን በይበልጥ በማጠናከር በነፍሰበላው አጋዚ ሰራዊቱ  በሐማሬሳ በወልቂጤ በወልዲያ በነቀምት በአምቦ አሁን ደግሞ በሞያሌ እና በተለያዩ ከተሞች በሚኖሩ ሰላማዊና ያልታጠቁ ወገኖቻችን ላይ እየወሰደ ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ በሥልጣን ላያ ያለው አገዛዝ ከሥህተቱ ሊማር የማይችልና በጭራሽ ለለውጥና ህዝባችን ለሚጠብቀው ሰላማዊ የመንግስት ሥልጣን ሽግግር ዝግጁነት የሌለው መሆኑን የሚያመላክት ነው።

በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱንና ህልውናውን ለማሥከበር ከምንጊዜውም በበለጠ መልኩ ዝግጁ የሆነ በመሆኑና ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ወደኋላ ሊመልሰው ከማይችልበት ደረጃ በመድረሱ አገዛዙ የህዝብን የለውጥና የመብት ጥያቄ በዓዋጅ ጋጋታ ሊያቆመው እንደማይችል የሚያረጋግጥ ሀቅ ነው።ይሁንና ህዝባችን እያከናወነው ያለው ጸረ ወያኔ ትግል በተባበረ መልኩና በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለመከናወኑ የህዝባችንን ሥቃይና መከራ እያራዘመው ይገኛል።

በመሆኑም የህዝባችን የነጻነት የፍትህ እና የዕኩልነት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እሥከሚያገኙ ድረስ በተናጠልና በፈረቃ እየተከናወነ ያለውን ጸረ ወያኔ ትግል አሥተባብሮ በጋራ በፋሺሥቱ የወያኔ አገዛዝ ላይ መዝመት አማራጭ የሌለው ዕውነት መሆኑን ተገንዝበን በህብረት የመቆሚያው ጊዜ ዛሬ መሆኑን ልናሰምርበት ግድ ይላል። በተናጠልና በፈረቃ የሚደረገው ትግል ጠላቶቻችን በየተራና በፈረቃ እንዲጨርሱን ዕድል መሥጠት እንደሆነም ካለፉት 26 የመከራና የሥቃይ ዓመታት መማር ይቻላል።

በመጨረሻም በሐገር ውሥጥም ሆነ በውጭ ሐገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጀመሩት የነጻነት ትግል መዳረሻው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ሆና ማየት በመሆኑ የጀመርነውን የነጻነት ትግል አጠናክረን የተረጋጋችና ከራሷ ጋር የታረቀች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት እንድንችል ትግሉን ከፈረቃ አውጥተን በጋራ በመቆም ሀገራችንን ከጥፋት ህዝባችንን ከዕልቂት እንታደግ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!