Home » ዜና » ከአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ከአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

Press Release, Ethiopia

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የደርግን ወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት ለመታገል እንደ ኤሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1975 ዓ/ም በሱልጣን አሊሚራህ ተመሰረተ።

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲዉ በተለያዩ የአፋር አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የደርግን አምባገነናዊ ስርዓት በትጥቅ ትግል በመፋለም እ.ኤ.አ እስከ 1991 ዓ/ም ድረስ ሲታገል ቆይቷል። ከዚያም በመቀጠል የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከስልጣን እንደተወገደ፣ አገራችንን በእውነተኛ ፍትህና ዲሞክራሲ ለመግንባት በነበረን ከፍተኛ ፍላጎት፣ የተነሳ በወቅቱ ከተሳተፉት 86 ብሄራዊ ግንባሮች መካከል ድርጅታችን አንዱ ነበር።

ሆኖም ግን በጠባብ ብሄረተኝነት በሽታ የተለከፈውና ፈጽሞ የኢትዮጵያዊነት ባህሪ የሌለው የወያኔ ሐርነት ትግራይ ቡድን፣ ከጥቂት ሆድ አደር ምንደኞችን በጊዚያዊ ጥቅምና ስልጣን በመደለል፣ የተጀመረውን የፍትህና የዲሞክራሲ ሂደት አዳፍኖ፣ የአንድ ፖርቲ የበላይነትን አጠናክሮ በመቀጠል ወደለየለት አምባገነናዊ ስርዓት ተቀየረ። የጠባብ ብሄረተኛው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቡድን፣ ከጊዜ ወደጊዜ ያላንዳች ተቀናቃኝ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ህዝብን ከህዝብ በማጋጨትና የአገሪቱን አንጡራ ሃብት እየመዘበረ ለጥቂቶች መጠቀሚያነት በማከማቸት፣ የቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ የግፍ አገዛዝ ስር በመውደቁ፣የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ የወያኔን ፀረ ህዝብነትና ማንነት በሚገባ ከተረዳ በኋላ፣ ከዚህ ፀረ ህዝብ አቋም ካለው ድርጅት ጋር መቀጠል እንደማይቻል ስለተረዳ ወያኔን በህዝብ ትግል ለመታገል ተገዷል።

የአቋም መግለጫ

1. በአሁኑ ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ በከባድ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የገባች እና አገራችን ወደፊት እጅግ ወደከፋና ወደባስ ደረጃ እየተሸጋገረ፣ የህዝቡም ህልውና ወደ-አደገኛ ጎዳና እያመራ፣ ብሩህ ተስፋ በማይታይበት ጉዞ ላይ ስለደረስን፣ ከዲሞክራሲና ከፍትህ ጥያቄ አልፎ ወደ ነፃነት ትግል እየተሸጋገረ ነው፣ ይህን አማራጭ የሌለው ወሳኝ የህልውና ትግል በቆራጥነት ዳር ለማድረስና ለመጋፈጥ ድርጅታችን ቃል ይገባል።

2. የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ፣ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ፣ ለሚያደረገው ትግል ሁሉ፣ የድርሻውን ለመውጣት፣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ለመግለፅ ይወዳል።

3. ድርጅታችን በአገራችን ኢትዮጲያ ለሁሉም ህዝባችን የሚሆን ትክክለኛና ፍትሃዊ ፌደራላዊ ስርዓትን ያማከለ ጠንካራ አንድነት እንዲገነባ አጥብቆ ይታገላል::

4. ድርጅታችን በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ብለው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካና የስብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመሰራት ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ይወዳል።

5. ድርጅታችን የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ለማጎልበት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት፣ በርካታ ሴቶች በአባልነት፣በከፍተኛ አመራርና ሃላፊነት በማገልገል የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አድርጓል:: ይህም የድርታችን የእድገት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና ወደፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ለምናደርገው የጋራ ትግል ከፍተኛ አስተዋፅዎ እንሚያደርግ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው።

6. ድርጅታችን የአፋርን ህዝብ ከለም መሬቱ በግዳጅ በማፈናቀል የሚፈጸምበትን ግድያ፣ እስራት እና ስቃይ እንዲቆም፣ ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና ለተፈናቃይ ህዝባችን ተገቢውንና በቂ የካሳ ክፍያ እንዲደረግ አጥብቀን እንታገላለን።

7. የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የመከላከያውን ኃይል በሙሉ በህወሃት ፓርቲ ስር ወድቆ፣ ሲፍልግ የሚገደል፣ ሲፍልግ ሚያስር፣ ሲፈልግ የአንድን አገር ሉአላዊነት በመጣስ እንደወራሪ ጠላት የአገርን ዳር ድንብር ለባዕዳን አስልፎ የሚሰጥ፣ በመሆኑና ህዝብን እያፈናቀለ መሬትን እንደቅርጫ ስጋ እየቸረቸረ የሚሽጥ፣ የወያኔ ሃርነት ትግራይን ቡድንን አምርሮ ከመታገል በቀር ሌላ ምንም አይነት አማራጭ ስለሌለና ይህን አሳሳቢ ችግር መፍታት የምንችለው በአንድነት ስንቆምና በጋራ ስንታገል መሆኑን ድርጅታችን በፅኑ ያምናል፣ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ አገርን ለማዳን በሚደረግ ትግል ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆናችን እየገለፅን፣ላለፍት አመታት በኦሮሚይ (ለምሳሌ በእሬቻ በአል ላይ ፣ በአወዳይ በአምቦ) እንዲሁም በአማራ ክልል በጎንደር ፣ በባህርዳር፣ በጎጃም፣ በኮንሶና በጋንቤላ ፤ ሰሞኑን ደግሞ በጨለንቆ ፣ በወልዲያ ፣ በቆቦ ፣ በመርሳና በሲሪንቃ የተፈፀመውን ዘግናኝ ግድያ ድርጅታችን በፅኑ ያውግዛል።

8. በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድን ፓርቲ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ለፍትህ፣ ለስብዓዊ መብትና ለዲሞክራሲ መከበር ስለጠየቁ ብቻ ስበብ እየተፈለገ በሃሰት ውንጀላ፣ በግፍ ታስረው የሚማቅቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ አጥብቀን እንጠይቃለን።

9. ህወሃት የአፋር የሱልጣኔት ባህላዊ አስተዳደርን በማጥፋት ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ ከአገር እንዲሰደዱና የአፋር ህዝብ ያለ ባሀላዊ አመራሩ እንዲቀር የሚደረገውን አሻጥር እያወገዝን ፤ የአፋር ህዝብ በራሱ በህልና ወግ እንዲመራ አጥብቀን እንታገላለን።

10. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ፣ የትግል እንቅስቃሴውን በተፈለገው መጠን ገፍቶ ከመሄድ የገቱትን ተግዳሮቶች ለይቶ በመፍታት በአሁን ሰአት ድርጅታችን በውስጥ አደረጃጀትም ሆነ በፖለቲካ እንቅቃሴ በጠንካራ መሰረት ላይ ይገኛል። ስለሆነም በአገር ውስጥ ከህዝብ ጋር ያለውን ቁርኝት የበለጠ በማጠናከርና በአገር አቅፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ በጋራ ለመታገልና በቁርጠኝነት ለመጋፈጥ ቃል እንገባለን።

የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!