Home » ዜና » በኦሮሚያ ክልል በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተመታ (መሳይ መኮንን)

በኦሮሚያ ክልል በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተመታ (መሳይ መኮንን)

Strike in Ethiopia underway to demand the removal of the current repressive regime.

ከእንቅልፌ መንቃቴ ነው። ዛሬ አድማ እንደሚኖር ያወቀው መንፈሴ በወጉም እንቅልፍ እንዳይኖረኝ አድርጎታል። እናም የነቃሁት ሌሊት ነው። ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጎብኘት ሳደርግ ሀገሩ በአድማ ቀጥ ብሎ ጠበቀኝ። ቄሮዎች ቃላቸው መሬት ጠብ ብሎ አያውቅም። ያሉትን አደረጉት።

መንገዶች ጭር ብለውል። ሱቆች ተዘግተዋል። ትራንስፖርት ቆሟል። ከወለጋ እስከ ሀረርጌ፡ ከባሌ እስከ አምቦ አድማው በታቀደው መሰረት እየተካሄደ ነው። ድሬዳዋም ተቀላቀላች። አዲስ አበባ ዳራ ዳር እያላት ነው። ወዳጃችን አንዋር አንዋር ከአዲስ አበባ እንደነገረን በቀራኒዮ አከባቢ የተኩስ ድምጽ ይሰማል። ከአድማው ጋር ስለመገናኘቱ ግን እርግጠኛ አይደለንም። በአማራው አከባቢ ገና ነው። ምናልባት ሞቅ ሲል መቀላቀላቸው አይቀርም።

ፋና ደግሞ አንድ ዜና እንካችሁ ብሎናል። መቼም አድማውን ለማስቆም ሊሆን ይችላል። እነበቀለ ገርባ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑን በፋና በኩል ሰምተናል። እነ ቦንቱ በቀለ ገርባ አባታቸውን ከቤት አግኝተው እስኪነግሩን ለጊዜው ደስታችንን ቆጥበናል። ቢሆንም ትግሉ ይቀጥላል። ሁሌም እንደምንለው የታሰሩት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የታሰሩለት ዓላማ ሳይፈታ የሚመለስ ትግል አልተጀመረም።

ከሀማሬሳ ዛሬም ጥቃት መኖሩ እየተሰማ። ይሄ መጥፎ ዜና ነው። ትላንት የተገደሉ ወገኖቻችን ሀዘን እያንገላታን ሌላ ዙር ግድያ ማንዣበቡን ስንሰማ በቄሮዎች ጀግንነትን የሞቀውን ልባችንን በወገኖቻችን ስቃይና ሞት እያቀዘቀዘው እንዳይሆን ስጋት አለኝ። ለማንኛውም ሰኞን ጀምረናታል። ይሄ ሳምንት ትግሉ አንድ ምዕራፍ ጠጋ የሚልባቸው ክስተቶች የሚስተናገዱበት ይመስለኛል። የእስረኞቹ መፈታት ይጠበቃል። በተለይም ዋና አኣና የፖለቲካ መሪዎች በዚህ ሳምንት መፈታታቸው የማይቀር ነው። አገዛዙ የስንግ ተይዟል። ጫንው ከያቅጣጫው የሚቋቋመው አልሆነው።

የኤች አር 128 ጫና የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን መንደር ብርክ አሲዞታል። የህዝቡ የማያቋርጥ እምቢተኝነት አገዛዙን ትንፋሽ አሳጥቶ ውድቀቱን እያቃረበው ነው። እስከአሁን አሜሪካ ላስቀመጠችው ቀነ ገደብ ምላሽ አልስጠም። ፌብሯሪ 28 ኈለት ሳምንት ቀርቶታል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ያለአንዳች ተጽዕኖ በፈለገው ቦታና ጊዜ ምርመራ እንዲያደርግ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል ፍቃደኝነቱ ካልተገለጸ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ ይቀርባል። በውጤቱም የአገዛዙ ባለስልጣናት በቡድንና በተናጠል ማዕቀብ ይደረግባቸዋል። ያኔ እጃቸው ተጠምዝዞ፡ አፍንጫቸው ተይዞ ከተጣበቁበት ወንበር ይነቃላሉ።

የህዝቡ ትግል መቆም የለበትም። እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ወደ አመጽና ተቃውሞ እየተቀየረ አገዛዙን ፋታ ማሳጣት ይገባል። ይህ የህዝብ ትግል ኤች አር 128ን ፈጥሯል። የእነለማን ቡድን አምጦ ወልዷል። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን ትዕቢት ኩምሽሽ እንዲል አድርጓል። እናም መቀዝቀዝ የለበትም። ለአፍታም መቆም አይኖርበትም። ያ ከሆነ አደጋው ከባድ ነው። ኤች አር 128 በመጣበት ፍጥነት ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል። እነለማን ማዳከሙ አይቀርም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አፈር ልሶ የመነሳት ዕድል ሊሰጠው ይችላል። ይህ እንዳይሆን የህዝቡ ትግል በማንም ይጠራ፡ ይትም ይጠራ፡ መቀጠሉ ዋስትናችን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!