Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » “ብንተባበር እንቆማለን ፤ ብንከፋፈል እንወድቃለን” (በተስፋዬ ዋቅቶላ)

“ብንተባበር እንቆማለን ፤ ብንከፋፈል እንወድቃለን” (በተስፋዬ ዋቅቶላ)

በተስፋዬ ዋቅቶላ

በቅጡ ያልተረዳነው መርሕ (ክፍል 1)

Dear Ethiopia, united we stand divided we fall.

ከአንድ መመራመር ከሚወድ ወዳጄ ጋር ስለመቆምና መውደቅ እንመራመር ነበር፡፡ የምንሄደው እንዳንቆም እንደሆነና ከቆምን እንደምንወድቅ እንፈላሰፍ ነበር፡፡ ልብ ብለን አንዳንድ ሰዎችን እያየንም እንስቅ ነበር፡፡ ሲሄዱ ደህና መስለው ሲቆሙ ግን መቆም የማይችሉ አሉ፡፡ እንዲህ እንደኛ መንግስት የሰከረ ሰው ላይ ባደረግነው ክትትል ደግሞ ሰካራም እንዳይወድቅ መሮጥ ብቻ ነው አማራጩ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡ ብዙ ሲቀመጡ የሚሄዱ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ በሽታን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፡፡ ቤት ሶፋ ላይ፣ ቢሮ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ፣ ከቢሮ እስከቤት ደግሞ መኪና ላይ የሚቀመጡ የመቆመጥ በሽታ ሳይዛቸው ቢቀር ነው የሚገርመው፡፡ ለመቆም መንቀሳቀስ እንጂ መቀመጥ አያስፈልግም፡፡

መቼም እንደ ግለሰብ ከሆነ ብዙ ብዙ እውቀት ያላቸው ሰዎች አሉን – በተለያዩ የሙያ ዘርፎች፡፡ ነገር ግን አስተባብረን የማንሰማው ዜማ ሙዚቃ አይባልምና የየሙዚቃ መሳሪያውን ብቸኛ ድምፆች ለያይተን መስማት ሕብር የለሽ ያደርግብናል፡፡ ቅጥ አልባ ፡፡ ስልተ ቢስ፡፡ ጎዶሎ ብቻ ሳይሆን ነጠላና ቅጥልጥል ስሜት ይፈጥርብናል፡፡ ይሰውረን ከዚህ የባቢሎን ቱማታ፡፡

ብሔራዊ ስሜት የሌለበት ማንኛውም ንቅናቄ ጉዞው ጫፍ ሲደርስ ማነቆ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ የሁሉም ነጠላ አካላት ሴራ የሚታወቀው መላ አካሉ ተባብሮ ሲሰራ አልያም ሲያጠፋ ነው፡፡ (ኢህአዴግ እንደገባ ሰሞን የታተመ አንድ የሥነ ግጥም መፅሐፍ ነበር “የአካላት ሴራ” ይሰኛል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መዋግዴ ነው፡፡) የሰው ልጅ እና አንድ አገር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥንታውያኑ ሊቃውንት ሀገራቸውን በሰው አካላት ይሰይሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ለኢትዮጵያ አንገት ሳትሆን ጆሮ ናት፡፡ለምን ሲሏቸው “በር ስለሆነች” ይሉናል፡፡ እንደ አለማየሁ ሞገስ መፅሐፍ አገላለፅ፡፡ እንደ አንድ አገር ስናስብ ጆሮ የሌለው ሰው ሆነናል ማለት ነው፡፡ እንደሊቃውንት አባቶቻችን አገላለፅ፡፡ (የሌሎቹን ክፍለ ሀገሮች አካላዊ ውክልና በስተ መጨረሻ እንዳለ አቀርብላችኋለሁ፡፡)

በአገላለፁ ባንስማማ እንኳን በአንድ ሰው መመሰሉ ግን የሚያግባባን ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም አካላችን ለሰውነታችን አስፈላጊ ነው፡፡ ከመጉደል ሙላት የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህ በተፈጥሮ አንድ የሰው ልጅ የተባበሩ አካላቱ ያስገኙለትን ስብዕና ወይም ትስብዕት በጥሩ ጥሞና ሊገነዘበው ይችላል፡፡ ይህ ስብዕና ጤናው ሳይጓደል እንዲኖር መትጋት የባለቤቱ ነው፡፡ ጤናው ሲጓደልም ያ ጉድለት ከምን እንደመጣ ለማሳከም ይጥራል እኒያ አካላትም ይተባበራሉ፡፡ ያለ አካላቱ ትብብር ጤና የለም፡፡ ያለ አካላቱ ሴራ ጤና ሊታወክም አይችልም፡፡ ትብብርና ሴራ እንደ አንድ ሞተር ውስጥ ያሉ ተቃራኒ ጊሮች ናቸው፡፡ በማሃበራዊ ሳይንሱም ግጭት አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አንድ ሰው አካላት ብቻ ሳይሆን ስሜት እና መንፈስም አለው፡፡ ይህ ስሜቱና መንፈሱም በተለያዩ ሁኔታዎች ሰውዬውን ይገልፁታል፡፡ ያ ሰው እንዲስቅ ወይም እንዲያለቅስ ያስቻሉትን ስሜቶችና መንፈሱን ያነቁት ሁኔታዎች ሰውዬው ደምፅ እንዲያወጣ አድርገውታል፡፡ በዚህም የተነሳ አካላቱ ከመታዘዝ ውጪ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እንባን ቢያምቁት ወደ ውስጥ መፍሰሱ አይቀርም፡፡

አሁን “አገራችን ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል” በሚለው እምንስማማ አካላት እንዴት እንደ አንድ አገር ሰው ማሰብ ያቅተናል፡፡ የሥድሳ ዓመታት ሴራችንስ እንዴት እንዲያጠፋን እንፈቅዳለን፡፡ ዘረኝነት ማለት የአንድ ጎሳ የበላይነት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አግባብ እጅ ብቻ ያላቸው ህዝቦች እንዴት እንሆናለን፡፡ ሁላችንም ደንጋይ ወርዋሪ ሁላችንም ተኳሽ ሁላችንም ተቧቃሽ፡፡ ባለእጁ ሁሉ እግር አለው አዕምሮ አለው ዓይን አለው ጆሮ አለው…ወዘተ ምሉዕ ነው አውቆ ካላደነዘዘው በቀር- የገዛ አካሉን፡፡

ድባቴ ውስጥ እንዳለን እንተማመን፡፡ በትክክል ተስፋ የምናደርግበትን የራሳችንን ማንነት አጥተናል፡፡ ስለዚህ ሌላ ማንነት እንፈበርካለን፡፡ ያ ማንነት ደግሞ በራሱ የሌሎችን ፈቃድ የሚጠይቅ ነውና ተስማምተን መኖር እንቸገራለን፡፡ በማንነት እጦት ሳቢያ ስብዕናችንን ልናጣ ተቃርበናል፡፡ ማንነታችን ግን ዋነኛው ትስብዕት ሲሆን ሌላኛው አገርነት ነው፡፡ መሲሑም ያለው “ሰው ቤተመቅደስ ነው” ነው፡፡ “አገር ነን” ስንል ትስብዕታችን ከፍ ይላል፡፡ አዎ አገር ነን፡፡

ከድባቴና ድብርታችን ስንነቃ ትልቅ አገር መሆናችን ይታወቀናል፡፡ “የእነ እገሌ አገር”፣ ለማለት የሚደፈርብን አገር ነን፡፡ ለእኔ ልዩ ጀግናዎቼ በሮማ አደባባይ ድል ያደረጉት ሁለት ሐበሾች ናቸው፡፡ ዘርዓይ ደረስ እና አበበ ቢቂላ፡፡ ሮማውያን ቢጠይቁኝ እነግራቸዋለሁ “የጀግናው ዘርዓይ ደረስ አገር ልጅ ነኝ” እላቸዋለሁ፡፡ እሱን መቀበል ካልቻሉ ደግሞ በትህትና “እኔ እኮ የአንዲት ምስኪን ደሃ አገር ሰው ነኝ፤ የመሮጫ ጫማ እንኳን ሳትገዛለት በባዶ እግሩ 42ኪሎሜትር ሮጦ ያሸነፈው የዚያ የማራቶኑ ንጉስ የአበበ ቢቂላ አገር ሰው ነኝ፡፡” ብዬ፡፡ ሁለቱም ለሰንደቋ ሲሉ መስዋዕትነትና ተጋድሎ ያደረጉ ጀግኖቻችን ናቸው፡፡ ይህ የታላቅ አገርነታችን ልዩ ምልክት ነው ለዘለዓለም፡፡ ይህቺ ሰንደቅ ገና ለዘለዓለም ትኖራለች፡፡እኛ ግን እስቲ አገር እንሁን፤ እንደ አንድ ሰው እንደአንድ አገር እናስብ፡፡ያኔ አንወድቅም ተባብርናልና፡፡

ለመቆም መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ከላይ ተፈላስመናል፡፡ ማንም በሌላው ድጋፍ መቆም አያዋጣውም፡፡ ስለዚህ ከውስጥና ውጪ አካላቱ ሴራ ነፃ ከሆነ ጤናማ ሰው ከሆነ መንቀሳቀስ አያቅተውም፡፡ ከተንቀሳቀሰ ደግሞ እንደአገር መቆም ብቻ ሳይሆን በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ እያለ የሚሄድ አገር ይኖረናል፡፡ ሕዝብ የአከላቱ ሴራ አካል ነው፡፡ በየክፍለ ሀገርና ክልልም ሲዋቀር እንደአንድ አካል መሆን መቻል አለበት፡፡

ለጊዜው ከላይ ወደታች ሰባቱን ላስተዋውቃችሁ፡፡ ምንጬ “መልክአ ኢትዮጵያ” የባለቅኔ አለማየሁ ሞገስ መፅሐፍ ነው፡፡

ራስ አዲስ አበባ
አንጎል ሸዋ
ዐይን ትግሬ
ጆሮ ኤርትራ
አንደበት ጎጃም
ቃል በጌምድር
አንገት ሲዳሞ

(ቀሪዎቹን ሰባቱን ደግሞ በክፍል 2 ፅሁፍ አቀርብሎታለሁ፡፡)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!