Home » ጦማሮች እና አስተያየቶች » ወቅታዊ ሁኔታን በጨረፍታ (መሳይ መኮንን)

ወቅታዊ ሁኔታን በጨረፍታ (መሳይ መኮንን)

መሳይ መኮንን

ህወሀቶች በማያቋርጥ ስብሰባ ውስጥ ናቸው። ልዩነታቸው ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ መጥቷል። የበላይነት ይዟል የተባለው በስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድን ከሳሞራ የኑስ ላይ ወታደሩን የመንጠቅ ሙከራው የተሳካ ባለመሆኑ የአንዳቸውም አንጃ ገዝፎ መውጣት ተስኖት በር ዘግተው መጠዛጠዛቸውን ቀጥለዋል። መጨረሻቸው አጓጊ ይመስላል። ቦታ እየቀያየሩ የቀጠሉት ህንፍሽፍሽ ለኢትዮጵያ መፍትሄ ለማምጣት እንዳልሆነ ይታመናል። ከችግር ፈጣሪ መቼም የመፍትሄ ሀሳብ አይፈልቅም። የመለስ ዜናዊ አይነት ብልጣብልጥና ሴረኛ መሀላቸው ባለመኖሩ አንደኛው አንጃ ነጥሮ የመውጣትና ሌላኛውን ደፍልቆ ለማንበርከክ ያለው እድል እጅግ ጠባብ ነው። ዝሆኖች ሲጣሉ ጥሩ ነው።

TPLF ethnic apartheid members

የህወሀቶች ህመም መድሃኒት ያለው አይደለም። ፈውስ የለውም። ጠራርጎ ሊወስዳቸው ከሚችል ጽኑ ህመም ጋር እየሰቃዩ ለመሆናቸው በርካታ ክስተቶችን ማሳየት ይቻላል። አንዱና ዋና የኦህዴድ ሰሞንኛ እንቅስቃሴ ነው። አንዳንዶች ቲያትር ነው፡ ያለህወሀት ፈቃድ ኦህዴድ ስንዝር መራመድ አይችልም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። እኔም ይህን አስተያየት ሙሉ በሙሉ ውድቅ የማደርገው አይደለም። ነገር ግን ህወሀት ከገባበት ማጥ፡ ከተዘፈቀበት አረንቋ፡ ከሚያሰቃየው ጽኑ ህመም፡ ስር ከሰደደው የእርስ በእርስ ፍጥጫ አኳያ ከተወሰደ ህወሀት ለማሴር፡ ቲያትር ለመስራት አቅም ያለው አይመስለኝም። ህወሀት ተዝረክርኳል። ሀገሪቱ ዝናብ እንዳበላሸው ሰርግ መላ ቅጧ የጠፋባት ያለምክንያት አይደለም።

ለህወሀት መዳከም ትልቁ ማሳያ አባወራው መብዛቱም ነው። ለውጭ ዲፕሎማቶች ግራ እስኪያጋባ ድረስ የትኛው አለቃ፡ የትኛው አዛዥ እንደሆነ አይታወቅም። የአራት ኪሎው ቤተመንግስት ያዘዘውን የካዛንቺሱ መንግስት የሚሽርበት፡ የመቀሌው አለቃ የወሰነውን፡ የአዲስ አበባው ቡድን የሚያፈርስበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሰንብቷል። የውጭ ሀገራት ዲፖሎማቶች ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ከየትኛው አካል ጋር እንደሚነጋገሩ አያውቁትም። ባለፈው የቃሊቲን እስር ቤት ለመጎብኘት አዲስ አበባ የገቡት ዲፕሎማቶች ከአቶ ሃይለማርያም ፍቃድ አግኝተው ቃሊቲ ሲደርሱ በሌላኛው ቡድን ቀጭን ትዕዛዝ ጉብኝታቸው ተከልክሏል። የቅርብ ጊዜው የአቶ በቀለ ገርባ የዋስ መብት ውሳኔ የተሻረውና በኋላም የታገደው በዚሁ ምክንያት ነው።

አረናዎች ዛሬ በመቀሌ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍም የህወሀትን አቅም ማጣት ከሚያሳዩ ክስተቶች አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ። ህወሀት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዲኖረው ፈጽሞ አይፈቅድም። ”መስመሪ ህወሀት መስመሪ ህዝበ ትግራይ እዩ” የሚለው የእነመለስ ዜናዊ ዶክትሪን በትግራይ ምድር መቼም ህወሀትን የሚቀናቀን ፓርቲ እንዲኖር የሚፈቅድ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ሌላ ነገር እንዲያስብ ከቶም አይፈለግም። ህወሀትን እንደብቸኛ አዳኝ እንዲቀበል የህወሀት መዝገብ ውስጥ በስውር ተጽፏል። ከሌላው የኢትዮጵያ አከባቢ ይልቅ ትግራይ ለብዝሃነት ፊት ተነፍጓታል። ለአማራጭ ሀሳቦች እድል አልተሰጣትም። ህወሀትና ህወሀት ብቻ ትግራይ ምድርን ይሞሏት ዘንድ የህወሀት መጽሀፍ ቅዱስ ይደነግጋል። እናም አረናዎች ከነችግሮቻቸው ለትግራይ ህዝብ ያልተለመደ ድምጽ ለማሰማት የሚፍጨረጨሩት የህወሀትን መዳከም ተከትሎ ነው። ዛሬ በመቀሌ አረናዎች ይዘው የወጡት መፈክር የህወሀትን ዶክትሪን የሚወግዝ ነው። ”ህወሀትን ህዝቢ ትግራይን ዝተፈላለዮ ‘ዮም” – የትግራይ ህዝብና ህውሀት አንድ አይደሉም ነው ትርጉሙ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለስልጣናት ሀብት እያሸሹ ነው። የአንድን ስርዓት የመቃብር ጉዞ ከሚያሳዩት ምልክቶች አንዱ ይሀው የሀብት ሽሽት አሁን በስፋት እየታየ ነው። ህወሀት ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስ ተከትሎ በየቦታው የትግራይ ተወላጆች በስብሰባ ተጠምደዋል።በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ ለውስጥ የትግራይ ተወላጆችን መሳሪያ ማስታጠቅ መጀመሩንም የሚሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። የትግራይ ባለሀብቶች የወረሯቸው ትልልቅ የንግድ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዘዋል። ስጋት የገባቸው ባለሀብቶቹ ከሀገር ቤት ይልቅ እንቅቃሴአቸውን በባህር ማዶ አድርገዋል። በተለይ በበላይነት የተቆጣጠሩት የሪል ስቴት ቢዝነስ የቁልቁለት ጉዞ ለይ እንደሆነ ይነገራል። ብዙዎች ለመሸጥ እየሯሯጡ ቢሆንም የሚገዛቸው አላገኙም። ገንዘቡ ሌላው እጅ እንዳይኖር በማድረጋቸው የሚሸጡትን የሚገዛ አቅም ያለው ባለሀብት ሊገኝ አልቻለም። በሌሎች እንቅስቃሴዎችም ተመሳሳይ ነገሮች መከሰታቸው ይሰማል።

የኦህዴድ ጉዳይ

በዚህ ውጥንቅጥና ትንፋሽ በሚያሳጣው ፍጥጫቸው ውስጥ ሆነው ህወሀቶች የኦህዴድን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሞክረዋል። ግን የቻሉት አይመስልም። ኦህዴድ ከተሰመረለት ተሻግሮ ተጉዟል። ከጠርሙሱ ወጥቷል። በባለፈው ጽሁፍ እንደገለጽኩት የኦህዴድ አዲሱ እርምጃ የህወሀት ቲያትር ነው የሚል እምነት የለኝም። ህወሀት ተልፈስፍሶ ባለብት በዚህ ወቅት ለማሴር አቅም ከየት ያገኛል? ቲያትር ለመስራት ይቅርና ለማሰብም እኮ አቅም ይጠይቃል። እነለማ ከማንም በላይ የህወሀትን ስስ ብልት ያውቁታል። በደህንነት መስሪያ ቤት አብረው ለሩብ ክፍለዘመን ገደማ እንደመቆየታቸው ህወሀትን አብጠርጥረው የሚያቁ ናቸው። የጌታቸው አሰፋ የልብ ትርታ ከወዴት እንደሚመታ ከማናቸውም የኢህ አዴግ አመራሮች በተሻለ እነለማ ያውቃሉ ቢባል እውነት ነው። እነለማ የህወሀት ትንፋሽ ሳስቶ፡ ጉልበቱ ዝሎ፡ አንድ ሀሙስ እንደቀረው እየተገነዘቡ በህወሀት ሴራ ተጠልፈው ቲያትር ይሰራሉ ለማለት በጣም ይከብዳል። ህዝብ ከዳር እስከዳር ተነቃንቆ የህወሀትን መንግስት ወንበር በነቀነቀበት በዚህን ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ እነለማ የህወሀት ድራማ ተዋናይ ለመሆን የሚፈቅዱ አይመስሉኝም።

ከባህርዳሩ የእነለማ ጉዞ ይልቅ የእምቧጭ አረምን ለመንቀል የኦሮሞ ወጣቶች ያደረጉት ዘመቻ ቀልቤን ገዝቶታል። ዛሬ ባህርዳር ላይ በሙዚቃ ዝግጅቶችና በጥናታዊ ወረቀቶች እየተካሄደ ያለው የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ኮንፈረንስ የካድሪዎች ጋጋታ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። የኦህዴድና የብአዴን እፍ ያለ ፍቅር ይልቅ የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ልጆች የአንድነት ስሜት ትርጉሙ ከፍተኛ ነው። ለለማ የልዕካን ቡድን በባህርዳር የተደረገለት አቀባበል ራሱ የተመቸኝ አይደለም። ኦሮሚያ የሚባል ሀገር ፕሬዝዳንት፡ አማራ ወደሚባል ሀገር ሄዶ በአማራ መንግስት ፕሬዝዳንት የተደረገለት አቀባበል ይመስላል። ህወሀት የረጨው መርዝና ላለፉት 26 ዓመታት የተራገበው የልዩነት ፕሮፖጋንዳ እንጂ ኦሮሞዎች ባህርዳር ቢሄዱ ሀገራቸው ነው።እናም ለለማ የተደረገለት ፕሮቶኮል በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት የተገናኙ አይመስልም።

ምንም እንኳን ኦህዴድ ከህወሀት አንጻር የሚገዳደር አቅም እየፈጠረ ቢመጣም ሜዳውም ፈረሱም ሊለቀቅለት አይገባም። መሪዎቹ ወንጀለኞች ናቸው። በመጨረሻው ሰዓት ሃጢያታቸውን የሚያሰርይላቸውን መንገድ ቢጀምሩም የመሪነትና የትግሉ የአርበኝነት መድረክ ሊሰጣችው የሚገባ አይመስለኝም። በጎ ተግባራቸውን ማወደስ እንጂ መሪ ሆነው ህዝብ ለለውጥ እንዲያበቁ ተስፋ እንዲጣልባቸው ማደረግ ተገቢ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ትግል ባለቤት ኦህዴድ እንዲሆን መፍቀድ ትልቅ የታሪክ ስህተት ነው። ኦህዴድ የራሱን የተበላሸ ታሪክ የሚያነጻበትን እድል ከመስጠት ያለፈ የመጪው ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪ ተዋናይ እንዲሆን የሚደረገው ሩጫ አደጋው ከፍተኛ ነው። ሌላው ቢቀር በኦህዴድ አስፈጻሚነት ባለቁት በሺዎች የኦሮሞ ልጆች ደም መቀለድ ነው። ኦህዴድን ማንገስ የእነዚያን ውድ ወገኖቻችን መስዋዕትነት ማራከስ ነው የሚል እምነት አለኝ።

የባህርዳሩ ኮንፍረንስ ብዙም ያልማረከኝ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረግው ስብሰባው ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ነው። ቃል በቃልም ባይሆን ”በአባል ድርጅቶች መሃል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የእርስ በእርስ የመገናኛ መድረኮች በማመቻቸት ትግሉን በአዲስ ምዕራፍ መቀጠል” የሚል ውሳኔ በዚሁ የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ተላልፏል። በግልጽ ቋንቋ ይህ ውሳኔ የባህርዳሩን ኮንፈረንስ የሚመለከት ነው። በዚህም አያበቃም። በቀጣይ የህውሀቱ ሊቀምንበር አይተ አባይ ወልዱ ከ1ሺህ በላይ ልዕካንን አስከትሎ ባህርዳርና አዳማ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ከሆነ የፖለቲካ ግርግር እንጂ ብዙዎቻችን እንዳወደስነው አንዳች አዲስ የለውጥ አየር እየመጣ አይደለም።

ኦህዴድ ወደ ባህርዳር ከማቅናቱ በፊት የራሱ ኮንፍረንስ አድርጓል። በወቅቱም ኦህዴድ እያደረገ ያለው ያልተለመደውን መስመር የምር እንድንወስድለት አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርግ አሳስበን ነበር። ነገር ግን የተለመደው የካድሬዎች ኳኳታና ግርግር ሆኖ ተጠናቋል። እነለማ የግል ስብዕናን ከማሳመር ያለፈ ለሰሯቸው ሀጢያቶች ማካካሺያ የሚሆኑ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠበቃል። በብልጭልጭና ለታይታ ፍጆታ በሚሆኑ ግርግሮች የትም መዝለቅ አይችሉም። ይህ ሲባል እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ዋጋ የለውም ለማለት አይደለም። ከምንም እንደሚሻል መመስከሩ ተገቢነት አለው። በተለይ እነለማ በሚያስተዳድሩት የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትወርክ እየተላለፉ ያሉ ፕሮግራሞች ትልቅ ውዳሴና ምስጋና የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ስሜት ይገዛሉ። ተስፋ ይሰጣሉ።

እንደእኔም ሆነ አንዳንዶች እየገለጹት እንዳሉት ባለፉት 25 ዓመታት በህወሀት አቀናባሪነትና ፈጻሚነት፡ በኦህዴድ ተባባሪነት የተገነቡት የጥላቻ ግድግዳዎች እንዲፈርሱ ጊዜው አሁን ነው። እነለማ ይህን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ከኮንፈረንስና ስብሰባ ግርግሮች ባለፈ ወደመሬት የወረደ፡ ህዝቡ ውስጥ ዘልቆ የሚገባ የለውጥ መስመር በአፋጣኝ መዘርጋት አለበት። ለምሳሌ የአኖሌ ሀውልት እንዲፈርስ ማድረግ አንዱ አወንታዊ እርምጃ ነው። በእኔ እምነት የአኖሌ ሀውልት በአንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ለሚገለጸው ታሪክ እንኳን የሚመጥን አይደለም። የሚሉት የታሪክ ጠባሳ ተፈጽሞ ቢሆን እንኳን የጥላቻ ሀውልት መትከል መዘዙ ለትወልድ የሚተርፍ ነው። ክቡር የሆነውን የሰው ልጆ የሰውነት ክፍል በዚህ መልኩ አደባባይ ላይ መስቀል ለማንንም ትምህርት አይሆንም። እናም ይህን ጥላቻን ብቻ የሚያሳየውን ሀውልት ማንሳት ከእነለማ ቡድን የሚጠበቅ አንዱ እርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ

ወስኗል። ቆርጧል። ከእንግዲህ ወለም ዘለም የለም። በየትኛውም ቅርጽና መልክ የሚመጣን የህወሀትን መንግስት አገዛዝ አይፈልገውም። ለጥገናዊ ሳይሆን ለስርነቀል ለውጥ መስዋዕት ለመሆን ተዘጋጅቷል። ህወሀትን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዲያየው አይፈቅድም። በአራቱም አቅጣጫዎች የሚሰማው ድምጽ አንድ ዓይነት ነው ”ወያኔ በቃን”!!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው። ከእንግዲህ ለየትኛውም የማዛናጊያና ማታለያ እንቅስቃሴዎች እድል መስጠት አይስፈልግም። ህወሀት ቆዳ ቀይሮ እንደሚመጣ መጠበቅ አለበት። ተስፋ የሚቆረጥ ስርዓት አይደለም። ከመቃብር አፋፍ የተጠጋ ህወሀት እንዳያዘነጋው ነቅቶ መጥበቅ አለበት። እነለማ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ከሺህ ተግባራት እንደአንዱ መውሰድ እንጂ ብቸኛ የለውጥ ሃይል አድርጎ ልብን መክፈትና የወደፊትን መስመር አሳልፎ መስጠት ታሪካዊ ስህተት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

2 comments

 1. ገዳዩ ጉጅለ፦እግዚአብሔር “ኢትዮጵያውያን ሕዝቤን ልቀቅ።”ለማለቱ ምልክቶችን ደጋግሞ አሳይቶህማል፤ካላመንክ ሕዝበ-ሱናሚ-አመፅን ጠብቅ።

  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን የሙሴን ዕውነተኛ ታሪክ አንብበናል፤መንፈሳዊም ነው።ሙሴ የተወለበት ጊዜ እንኳን ለሕፃናት ለአዋቂዎች የሚመች አልነበረም፤ወንዶች ሕጻናት ገና ሲወለዱ ወዲያው እንዲገደሉ ለአዋላጆች ቀጭኝ ትዕዛዝ በአምባ ገነኑ የተሰጠበት ወቅት ነው።በሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናት እየታረዱ ሲገደሉ ሙሴ ግን ያንን ፈተና በተዓምር አልፎ ለአቅመ-ዓዳም በቃ።

  እናም እግዚአብሔር ሙሴን ሲያናግረው “የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ።”ስለዚህም አለው… በዚህም መሠረት ሙሴ እና ወንድሙ አሮን መጥተው(በዘመኑ አባባል አምባ-ገነኑን)ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦”የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦”ሕዝቤን ልቀቅ።”ኦሪት ዘጸአት ፭-፩።”እምቢዮ!!!”አለ ይባስ ፈርዖንም”በእነ ሙሴ ላይ እያላገጠ፦”እግዚአብሔር? ? ?…”ሳቅ ሳቅ ሳቅ፤ልክ አቶ ግርማ ሰይፉ በፓርላማዎች ንግግር ሲያደርግ “ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!!!”ብሎ እንደጨረሰ የነበረውን ዓይነት የማሽሟጠጥ፤አብዛኛው የፓርላማ አባል የየራሱን ሽሙጥ ሳቅ በአደባባይ ገለፈጠ።እንደገናም ሙሴና አሮን ፈርዖንን እንዲህ አሉት እነሆ ምልክቱ አሉትና፤ብትሪቱን ወደ እባብ ለውጠው አሳዩት።ይልቅ ፈርኦን እኔም አለኝ ሙዚቃ የሚል “አስማተ-እባብ”ለሙሴ እና ለአሮን አሳያቸው፤ሳይጠየቅ።

  ልክ በዘመኑ ያሉት ቅን ምሁራን የሆኑ የሕዝቡን በግፍ መገደል፣መቸገር፣መራብ፣ሰቆቃ፣ድርቅ፣ ወዘተ መኖሩን ለጠቅላይ ሚኒስቴር እና ክርስቲያን ነኝ ተብዬው ለኃይለማርያም ደሳለኝ ሲነግሩት፦”እንደዚህ ዓይነት ድርቅ እና ቸነፈር በሰለጠኑት አገር አሜሪካንም በሰሞኑ የዓየር መበላሸት ነው፤ልዩ ችግር አይደለም ብሎን ድርቁን ለምለም አደረገው”በቃላት።እሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት በረሃብ አለንጋ ሳይሆን በሞት ቸነፈር እየረገፉ ይገኛሉ፤እንዳይወራ ቢደረግም።

  ወደ እነሙሴ አስገራሚ ታሪክ ስንመለስ፦ጥያቄአቸውን ደጋግመው በትዕግስት ሰባት ቀናት የልቦና ጊዜ ሰጡት፣ለፈርኦን ግን ይባስ ትዕቢት እና ንቀት ተጠናወቱትና ልቅቅ የተባለውን ሕዝብ፣እስራኤላውያንን ይበልጥ ያሰቃያቸው ቀጠለ።ድንጋይ ሆነ ልቡ፤የፈርዖን ልብ ጸና፥ሙሴ እና አሮንን አልሰማቸውምም።ይባስ የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ላለመልቀቅ “እንቢ አልለቅም” አለ።

  የእግዚአብሔርን ታምር ማስረዳቱም በእነ ሙሴ ቀጠለ እና በመረጃነት፦ውኃውም ተለውጦ ደም ሆነ፣በወንዙም ያሉት ዓሦች ሞቱ ወንዙም ገማ።ቀጠለ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጣ፤ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ።እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች።ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን በፉክክር አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ ቢነግሩትም አልሰማቸውም።

  ትዕግስታቸውም ቀጠለ ጠየቁትም መልሱ ግን ያው እምቢዬው ሆነ።በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ።በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ።በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል አሉት፣ወረደም።በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ።እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ አለ። እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ።እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ!!!”ተባለ፤ፈርኦን ግን ጆሮ የሌለው መሰለ።

  የኛዎቹ ወቸገል ዜናዊን እና አባ ጳውሎስን በአንድ ጊዜ ባልፈለጉት ወቅት እና ባልተመቻቸው ጊዜ፤ባላሰቡበት መንገድ በግድ በሞት ነብሳቸውን ቀማቸው። ቀድሞም በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደተጻፈው”እግዚአብሔር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ይናገራል!!!”ነውና ለተቀሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች እና ጠላቶቿ ሐቁን አሳያቸው፤እያዩ ግን ዝም ብለዋል።ምስክሮች ባደባባይ ወጥተው እና ተፀጽተው ምሥክርነትም ቢሰጡ የሚያምኗቸው ባለሥልጣኖች ጠፉ።

  ማን ያምናል ሥልጣን እና ገንዘብ ያለው ሁሉ ሲደርስበት ነው፤ዘግይቶ የሚነቃው።አሁንም በሕይወት ያሉ ትዕቢተኞች እግዚአብሔርን ሊያስታውሱት አይፈልጉም።

  በቅርቡ የተፈፀመውን ሁለቱን ታምራት የበረከት ሰምዖን እና የአባ ዱላ ገመዳ ሥልጣን መልቀቅን አገናዝቦ ልብ ያለው በጭላንጭል ሊያይ ይችላል፤ሁለቱም ሥልጣን መልቀቁን ፈልገውት አይደለም።ሁለቱም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይቅር የማይለው ግፍ ፈፅመውበታል።አቶ በረከት ስምዖን ከወቸገሉ ማጭበርበር ቁማሩ ጀምሮ የተሻረከው ሲሆን፤ከሞቱ የውሸት መግለጫ ጀምሮ፣እስከ ግዴታ ለቅሶ አፈጻፀም ድረስ፣ሠይጣኑ ዜናዊ ሲቀሰፍ ቅዱስ ሰው እንደሞተ ሕዝቡን ያጭበረበረ ስንቱን ያስገደለ ግፈኛ ነው።

  አባ ዱላ የተባለው ደግሞ ከሃያ ሺህ የኦሮሞ ወታደሮችን ምርኮ አስገብቶ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ እሱ ግን በሹመቶች እየተንበሸበሸ በፓርላማ ሊቀመንበር ሥም”እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በምህረቱ ይባርካት”ተብሎ ባደባባይ በሚነገርበት ወቅት ምን እንዳደረገ ይታወቃል።ያጥፋት ሁሉ አልተረሳም፤አይነገርም እንጂ። በሌላ በኩል ቶለሣ ኢብሳ የሚባል ተራ ወጣት ደግሞ በሕዝብ መገናኛ መረብ ላይ አባቶች ሲያደርጉት የነበረውን የፍቅር ጥሪ ቢያሰማም ናቁት፤ይልቅስ እሱን ለመግደል አድራሻውን ይፈልጋሉ።ተራ ሰው የሆነው ቶለሳ ኢብሳ ከሚናገረው ዐቢይ ርዕስ በእግዚአብሔርን ዕመኑና የምታደርጉት ሁሉ መጀመሪያ ለፍቅር ብቻ አድርጉት አለ፤ እንደ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቀላል አቀራረብ ነበር፤ዳሩግን ለማያምኑት ተራራ ነው።

  እናም እግዚአብሔር ሙሴን ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ አለው።አደረገም፤ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም። አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው።በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ፤ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ።

  ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ፦እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ አለ።ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር በነፃነት ወጡ።

  ይህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ይጻፍ እንጂ ዛሬም “ትዕቢት” ፈሪሃ እግዚአብሔርን ይንቃል።ሥልጣን፣ገንዘብ እና ሐብት ያላቸው ሰዎች ጊዜ እየጠበቁ ሕዝብን ለመከራ እና ለችግር ያጋልጧቸዋል።ስለዚህም የሙሴ ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ነው፤መንፈሳዊ ሕይወትም መመሪያቸው ላላዳረግጉትም ለኑሮ አመክሮ ትምህርት ይሰጣል።እናም መሪዎች የተባሉት ይማራሉ ተብሎ ሳይሆን ለማንኛውም ዜጋ ማገናዘቢያ ትምህርት ይገኝበታል ተብሎ ነው።እናም ገዳዩ ጉጅለ እግዚአብሔር ደጋግሞ ምልክቶችን አሳይቶሃል፦”እግዚአብሔር ኢትዮጵያውያን ሕዝቤን ልቀቅ።”ለማለቱ ምልክቶቹን አሳይቶሃል፤ካላመንክ ሕዝበ-ሱናሚ-አመፅን ጠብቅ።

 2. Very sensible and realistic way of looking at what is happening on the ground and what politicians ( ruling elites of the ruling front ) are trying to play the game of survival.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!