Home » ጦማሮች፣ አስተያየቶች እና ሌሎችም... » AlMariam Amharic » ኢትዮጵያ፡ ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው?

ኢትዮጵያ፡ ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው?

February 15, 2013

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

Click here for PDF

በዴሞክራሲ የአንድነት ጎዳና ላይ?

በጁን 2012 ‹‹ኢትዮጵያ፡ በሕገመንግስታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና ላይ›› የሚል ጦማር አቅርቤ ነበር፡፡ ‹‹በርካታማ ሕበረሰቦች ከጭቆና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግርን ሲያስቡና ሲንቀሳቀሱ፤ እንቅስቃሴያቸውን የሚገቱ በርካታ ፈተናዎች›› እንደገጠሟቸው በማስረጃ የተደገፉ ታሪካዊ እውነታዎችን ጠቅሼ ነበር:-

ከአረብ ‹‹መነሳሳት››ከታየው ልምድ በመነሳት ሕገ መንግስታዊ ቅድመ ውይይት እንደሚያስፈልግ ጠቁሜ አንዳንድ ሃሳቦችም ሰንዝሬ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ፍለጋና የዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት ግቡ ዙርያ ጥምጥም መንገድ፤ አድካሚና ተስፋ ሞጋች ይሆናል፡፡ይም ሆኖ የማይቻል አይደለም………..ግጭትን አስወግዶ ሰላማዊ ሽግግርን ተግባራዊ ለማድረግ፤ተፎካካሪ አለያም በተናጠል ያሉት ሁሉ በአንድ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በዋናው ግብ ላይስምምነትንና መቻቻልን መግባባትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ሕዝባዊ የሲቪክ ማሕበረሰብን በአዲሱ ሕገ መንግስት ዙርያ ማስተማርን ያካትታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ድርጅቶች፤ አመራሮች፤ ምሁራን፤ ሰብአዊመብት ተሟጋቾች፤ እና ሌሎችም የጉዳዩ አካላት፤ ስርአት ባለው ፕሮግራም ተካተው ትምህርትና አስተባብሮ ማሰለፍን መውሰድና ማዳረስ በዚህም ለዴሞክራሲ ሽግግር የሚጠቅመውን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ  ይኖርባቸዋል፡፡ ከጭቆና ስርአት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ስኬታማ የሆነ ሂደት ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን የመነጋገርንና የመመደራደርን ጥበብ ሊማሩ ይገባል…….››

እነሱ በታችኛው የጭቆና ጎዳና ላይ የኋሊት እየተዘወሩ ነው፤ እኛስ በዴሞክራሲ አውራጎዳና ላይ ወደፊት እየተጓዝን ነው?

ለአንዳንድ ሰዎች ለገዢዎች ባለስልጣኖች ወይንም ለመጪው እውነቱን መንገር ቀላል ነው፡፡ ያለምንም ችግር እነዚህን ስልጣንን አላግባብ የሚጠቀሙትን ጥፋት መስራታቸውንና ልክ አለመሆናቸውን ማሳወቅ፤ ጥፋታቸው ምን እንደሆነ፤ጥፋታቸውን እንዴት ማረም እንደሚችሉና ጥፋት ለፈጸሙባቸውም ትክክል በማደረግ ማሳረም አንደሚችሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹ማንነታቸውን›› መለየት በማይቻልበት “ተቃዋሚዎች” እውነትን ማሳወቁ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህም ላልታወቁት “ተቃዋሚዎች” ለማስረዳት ከሞመከር ይልቅ: “እነሱ በታችኛው  የጭቆና ጎዳና ላይ የኋሊት እየተዘወሩ ነው፤ እኛስ በዴሞክራሲ አውራጎዳና ላይ ወደፊት እየተጓዝን ነው? ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት እመርጣለሁ፡፡ ይህን መሰሉ ጥያቄ መሰንዘር ያለበት ‹‹ለተቃዋሚ አመራሮች ነው››:: ግን ለጥቂትጊዜያትም እነዚህ አመራሮች እንማንናቸው እንማንስ አይደሉም በሚል ግራ መጋባት ውስጥ ነበርኩ፡፡

ባለፈው ሴፕቴምበር ‹‹የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በዴሞክራሲ ማለዳ ወቅት?››  በሚል ርእስ አንድ ጦማር አቅርቤ ነበር፡፡ ድምጼን ከፍ አድርጌ (እስካሁን መልስ ባላገኝም) ‹‹በኢትዮጵያ ተቃዋሚው ማነው?›› ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ አሁንም ሆነ ያንጊዜ ግራ እንደተጋባሁ መሆኔን መናዘዝ እወዳለሁ፡፡

‹‹በአግባቡ የተደራጀና የማያወላውል አስተማማኝ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሌለ እረዳለሁ:: አንድም ጠንካራና ግንባር የፈጠረ የህብረት ፓርቲ  የገዢውንመንግስት ፖለቲካም ሆነ ፍልስፍና የሚሞግት የለም፡፡ በምሑራን ግንባር ቀደምትነት የተቀናጀና የተጠናከረ አንድም

ፓርቲ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉንም ሙያዎችና ማሕበራት፤ሃይማኖቶችን ያቀፈ የሲቪል ማሕበረሰብ ስብስብም የለም፡፡ ለወጥ ባለ አባባል፤ ‹‹ተቃዋሚው ያው ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ደካማ፤ ልፍስፍስ፤ ቅርጽ ያልወጣለት፤ ተጣምሮ አሁንም ከነድክመቱ፤ተከፋፍሎ፤ እርስ በርስ ለመናቆር የሚሽቀዳደሙትና ለገዢውፓርቲ የመጠናከርያና የግዛት ማራዘም አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ናቸው? ያው አሁንም በማጉረምረም ብቻ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የሚጥሩት፤ የሲቪክ ማሕበረሰቡን የሚያደራጁት፤ጋዤጠኞች ተብዬዎቹ አገልጋዮች፤ እና ፈራ ተባ የሚሉት ምሁራን ናቸው? በመሳርያ ገዢውን ሃይል ገርስሰው የሚጥሉት ናቸው ተቃዋሚዎች? እራሱን በተቃዋሚነት ፈርጆና ሰይሞ ያስቀመጠችው/ው ሁሉ ናቸው ተቃዋሚዎች:  ወይስ ከላይ የተዘረዘሩት አንዳቸውም አይደሉም?

የመጨረሻዋን እንጥፍጣፊ ብሬን ለውርርድ የማቀርብበት ጉዳይ ግን የመለስ ዜናዊ አምላኪ ደቀመዝሙራን ከዚህ በኋላ ወዴት ወዴት ነው የምትሄዱት ቢባሉ ለማስረዳት አንዳችም ችግር የለባቸውም፡፡ በእርግጠኛነትም: ሰማይና መሬት ቢደበላለቁም፤ በመለስ ‹‹ዘልዓለማዊ አሸብራቂ ኮቴ ፈለግ›› እየተመራን አሸሸ ገዳሜያችንን እያስነካን፤ ጮቤ አየረገጥን የሀደሰና ግድብ ሥር የተቀበረልንን ወርቅ ለማፈስና በየዓመቱም 10. 12. 15 በመቶ የኤኮኖሚ እድገት እያልን ከፍ ከፍ ብለን በመብረር መንገዳችንን እንቀጥላለን ይሉናል……….›› እኔም የጉዞ አውራ ጎዳና ቀይሶ ወደ የህልም  መንገድ መሄዱ  ክእጅና እግርን አጣጥፎ ማፋጨት ለእናት ሃገር ከመቆዘሙይሻላል ባይ ነኝ፡፡

ለመሆኑ ጥያቄው ተቃዋሚ መሆን ወይም አለመሆን ነው እንዴ? በተቃዋሚ ጎራስ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በተቃዋሚ ጎራ ውስጥስ ለመካተት አንድ ሰው ምን ሊያከናውን ወይም ሊያደርግ ይገባዋል? ተቃዋሚ መሆንስ ገዢውን ፓርቲና በውስጡ የተካተቱትን በመሳደብ በማጥላላት፤ በመፎከር፤ጥርስ በመንከስ፤ ስልጣንን አለአግባብ የሚጠቀሙትን በመውቀስና በመተቸት በስድብ ላይ ስድብ መከመር ነው? ስልጣንን አለአግባብ የሚጠቀሙበትንስ በመቃወም በተቃውሟችን የሞራል የበላይነትስ ማግኘት? እነዚህን አለአግባብ ማንኛውንም ጉዳይ የሚጠቀሙበትን ያለ እቅድ ያለግብ መቃወምስ ተቃዋሚነት ነው?

በተደጋጋሚ እንዳስቀመጥኩት የመለስ እምነቱ ‹‹ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ከሚያውቁት በላይ መለስ ተቃዋሚዎችን ማወቁ ነው››::

መለስ በተቃዋሚዎቹ ከምር የስቅባቸው ነበር፡፡ የተቃዋሚዎችን አመራሮች የእውቀታቸው ደረጃ ከሱ ታች አድርጎ ነበር የሚገምተው፡፡ባስፈለገው ወቅትና ጊዜ፤ ሊያፌዝባቸው፤ሃሳባቸውን ሊያጣጥል፤ ሊበልጣቸው፤ማንም ከማንማ ሳይል ሊያላግጥባቸው እንደሚችል ያምን ነበር፡፡እርባና ቢስ ብሎ ስለሚያስባቸው፤ ለስልጣኑ አስጊና ተቀናቃኝ ይሆናሉ የሚል ስጋት አልነበረውም፡፡ በሚያደርጋቸው ሕዝባዊ ዲስኩሮቹ ሁሉ እንዳፌዘባቸው፤ እንዳዋረዳቸው፤መሳቂያ መሳለቂያ ሊደርጋቸው እንደሞከር ነበር፡፡ ተቃዋሚዎቹን የዕለት ተዕለት ክትትልና ቁጥጥር  ከጥፋታቸው እንዲመለሱም ቁንጥጫና ትንሽም በሳማ ለብ ለብ እንደሚያስፈልጋቸው ጨቅላ ሕጻናት ነበር የሚያያቸው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነም ባለፉት የግዛት ዘመኑ መለስ ተቃዋሚዎቹን እንዳለውም በሁሉም መልኩ ቀድሟቸው በልጧቸው፤ ቀልዶባቸው፤ መሳቂያ አድረጓቸው ነበር፡፡አሁንም የመለስ ደቀመዝሙሮችና እሱ የፈጠራቸው በፈጠረላቸው ብቻ የሚመሩት የራሳቸው የሆነ አንዳችም ነገር የሌላቸው ‹‹ሰብ ግዑዛን›› በመራቸው መንገድ የውርየድንብራቸውን ለመጓዝ ነው እቅዳቸው፡፡

‹‹ተቃዋሚዎች›› አሁን የት ናቸው?

ምናልባት በኢትዮጵያ ያሉትን ‹‹ተቃዋሚዎች›› ከእንግዲህ ጉዟችን ወዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሻ ጊዜው አማካኝ ላይሆን ይችላል፡፡ይልቁንስ አሁን ተቃዋሚዎች የት አሉ (የትም የሉም) የሚለውን መጠየቁ አግባብ ሊሆን ይችላል፡፡ ለኔ አመቺው ነጥብ፤‹‹ተቃዋሚው በአሁኑ ጊዜ፤ ወደ በቃኝ፤ አጉራህ ጠኛኝ፤ ወደ ተስፋ መቁረጡ፤ ወደ መሳቀቁ፤  ገለል ወደ ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ተቃዋሚውን›› እንደተደገመበት አይነት ፈዝዞ ስልጣንን አለአግባብ ተከተለ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› ደህንነት ያጣ፤ አጀንዳ ቢስ፤ አቅመ ቢስ፤ አቅጣጫ ቢስ፤ ራዕይ የሌሌለው ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› ግራ የተጋባ፤ ተሸመድምዶ ያለ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ተቃዋሚው›› አንድ ላይ የሆነበት፤ በአንድ የቆመበት፤ጠላትን በአንድ ላይ የተጋፈጠበት፤እና በአንድ ላይ ለወህኒ የበቃበትም ጊዜ ነበር፡፡ የ2005 ምልሰት! ያኔ ‹‹ተቃዋሚው›› የዘርን፤ የጎሳን፤ የሃይማኖትን፤ የቋንቋን፤ የዓላማን እና ሌሎችንም ልዩነቶች ወደ ጎን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ በአንድነት የቆመበት ወቅት ነበር፡፡ ያ ራዕይ ደግሞ ተቃዋሚዎችን በወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ አስተሳሰራቸው፡፡ ‹‹ተቃዋሚው›› አንድ ሆኖ መለያየትን ትቶ በቅንጅት፤ ውስጣዊ መቆራቆስን በመተው ሊከፋፍሉትና ሊያለያዩትበሚጥሩት ላይ በአንድነት ቆሞ አሸነፋቸው፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት፤ ‹‹የተቃዋሚዎች›› የነጻነትና የዴሞክራሲ ራዕይ ቀስ በቀስ ባለመግባባትና በመወነጃጀል እየከሰመ ሄዷል፡፡በተቃዋሚው ጎራ መወያየት በመነታረክ ተተክቷል፤ ተግባርም ወደ ባዶነት፤ ሕብረት ወደመለያየት፤ መቀናጀት ወደ ግላዊነት፤ መሰባሰብ ወደ መለያየት፤ መፈቃቀር ወደ መጠላላት፤ መቻቻል ወደ አለመግባባት ተለውጧል፡፡

‹‹ተቃዋሚው›› ለውጥን ይፈልጋል:: በለውጡም ኢትዮጵያን ከጭቆና በማላቀቅ የዴሞክራሲ ባለቤት ሊያደርጋትይመኛል፡፡ ግን ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንዳሉት፤ ‹‹ለውጥ በመንኮራኩር ተጭኖ የማይቀር ነገር አይደለም: ሊገኝ አይችልም፤በማያቋርጥ የነጻነት ትግል እንጂ፡፡ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ለነጻነታችን መጣር አለብን፡፡ ወገብህ ለመጥ ካላለ ጠላትህ ሊጋልብህ አይችልም… ከልምድ እንዳየነው ጨቋኝ ገዢ ነጻነትን በፍቃደኛነት አይሰጥምበተጨቋኞች መገደድ ይኖርበታል››

የኢትዮጵያ ‹‹ተቃዋሚ›› ሃይሎች፤ ወገቡን ጠበቅ አድርጎና ጥርሱን ነክሶ ፍላጎቱን ማሳወቅና ማግኘት አለበት፡፡ ወገብን ማጥበቂያዎች በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ስለሰብአዊ መብት መከበር መናገርና፤ ገዢዎች የሚያደርሱትን በደል ግፍና ጭቆና መናገርም ወገብን ማጠንከር ነው፡፡ ጥፋቶች መስተካከል እንዳለባቸው መሞገትም ቀበቶን ማጥበቅ ነው፡፡ በእኩዮች ፊት ዓይን መግለጥና የተደፈነ ጆሮን እንዲሰማ ማድረግ ጠንክሮ መቆም ነው፡፡ ለማንም ቢሆን አግባብነት ከሌለው አሻፈረኝ ማለት መቻል ብርታት ነው፡፡ ለገዢ ባለስልጣናት ስህተታቸውን ማሳወቅ ጥንካሬ ነው፡፡ ዶ/ር ኪንግ እንዳሉት ‹‹የፍፁምነት ሕግ አለያም ምሉዕ ሕግ ከሰው ሰራሽ ደንብ ጋር የሚጣጣም የሞራል ሕግ ወይም የፈጣሪ ሕግ ነው፡፡ ሕጋዊነት ያጣ ሕግ ደሞ ከሞራላዊ ሕግ ጋር የማይጣጣም ነው::››  በጃንዋሪ 2011 ሳምንታዊ የሆነ ጦማር ‹‹ከአፍሪካ ጨቋኝና ግፈኛ ገዢዎች ውድቀት በኋላ›› አቅርቤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስቼ ነበር፡፡‹‹በአሸዋ የተገነባው የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ግንብ ሲደረመስና የቅዠት ቤተ መንግስታቸው ፍርስረሱ ሲወጣ አፍሪካ ምን ትሆናለች? አፍሪካ መላቅጡ የጠፋ ትሆንና መልሶ ለመገንባት የምታስቸግር ፍርስራሽ ትሆናለች? የፈላጭ ቆራጮቹስ መጨረሻስ ምን ይሆናል?

ባለፈው በጋ ወራት ያለፈው የጨቋኞች ስርአት ገንቢው መለስ ዜናዊ ካለፈ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የጭቃ ግንብ መስፋፋትን እያስመሰከረ ነው:: የታሪክ ሚስጥራዊነት ግን አሁን ያለው ጥያቄ እኩይ ገዢዎች ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ሊያደርጓት እንደሞከሩትና ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች ወይስ ትጠነክራለች የሚለው አይደለም፡፡ እነዚያ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ቀና ማሰብ የሚጎመዝዛቸው የእርኩስ መናፍስት ስሪቶች ከሚያመልኩትና አንቀጥቅጦ ሲያምሳቸው ከነበረው የቅዠት ሳጥን ሞት በኋላ እርስ በርሳቸው ወደ ፍርስራሽነት በመንደርደር ላይ

ናቸው፡፡ ባለሕልም እንጀራቸው ሲሞት የነሱም እንጀራቸው እያረረና እየሻገተ ነው፡፡ አባባሉ እንደሚያስረዳው‹‹በዕውራን አምባ አንድ አይና ብርቅ ነው›› አሁን እንግዲህ አይነ ብርሃናቸው የለም ከዚሁ ጋርም በራሳቸው ጥፋት፤ ተንኮል፤ ድክመትና መሰሪነት የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቷቸው በመደነባበር ላይ ናቸው፡፡

አሁን ‹‹አጣዳፊው ጉዳይ›› ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚ መሪዎች ለዴሞክራሲ ያላቸውን እቅዳቸውንና ራዕያቸውን በአስቸኳይ ማዘጋጀት ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በሕግ የበላይነት የሚመራ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ራዕያቸውን ማቀድ ያለባቸው አሁን ነው፡፡ኢትዮጵያዊያን የተቃዋሚ መሪዎችም የመገናኛ መረቦቻቸውን በጥንቃቄና በእርጋታ በመዘርጋት ከየአቅጣጫው ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በማሰባሰብና በመረቡ ግለሰቦችንም ሆነ ማሕበረሰቡን፤ በአንድ የማሰለፉ ወቅት አሁን ነው፡፡ ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገውን ሽግግር ምሁራን ማመቻቸት ያለባቸው አሁን ነው፡፡ ሁሉም ነጻነትና ዴሞክራሲን የሕግ የበላይነትን የሚፈልግ ሁሉ አሁን ነው

በአንድ ላይ ለመቆም ስምምነታቸውን ይፋ በማድረግ መንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ ካለፈው የግፍ ሰንሰለት ማነቆ እራሳችንን ማለቀቂያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ስንል የተጫነብንን የዘርና የጎሳ ፖለቲካ አሽቀንጥረን መጣያው ወቅት አሁን ነው፡፡ ለብሔራዊ አንድነት መቆሚያና መሰባሰቢያችን አሁን ነው፡፡ ለሃቅና ለይቅር ባይነት መወሰኛችን አሁን ነው፡፡ እራሳችንን ከጭቆና እኩይ ምግባርተኞች አላቀን፤ሰብአዊ ክብራችንን የምናረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ አሁን እርስ በርስ የመወነጃጀያና የመለያያ የጣት መቀሰርያ የእልህ መወጫና የእርስ በርስ መናቆሪያ ወቅት አይደለም፡፡ አሁን እስቲ ይሁና በማለት አፋችንን የምንለጉምበት ጊዜ አይደለም፡፡ አሁን አይናችን እያየ አላይም የሚልበት ጊዜ አይደለም:: ጆሯችን አሁን አይደለም አልሰማም ማለት ያለበት ሊከፈት ሊያዳምጥ ሊሰማ የግድ ወቅቱ ነውና፡፡

ከዚህስ በኋላ ጉዟችን ወዴት ነው? ከዚህ በኋላ የራሴን ጥያቄ እኔ አጠር አጠር እያደረግሁ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ተቃዋሚው ሃይል ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለመምራት በጎዳናው ላይ መሆን አለበት፡፡ በቅድመ ዴሞክራሲ ጭቆና የነበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት

ተቃዋሚው ሃይል የዴሞክራሲ ድርጊት እቅዱን በአግባቡ መንደፍ አለበት፡፡ ዋነኛው ካለፉት ሰባት ዓመታት ልንማርና መስወገድ ያለብን ለመቃወም በሚል ብቻ ዝም ብሎ መቃወም መቃወም መቃወም ያለግብና ዓላማ ሊሆን አይችልም፡፡ የተቃዋሚዎች ሚና በስልጣናቸው የሚባልጉትን መቃወም ከሚለው ባለፈ ሊሆን ይገባል፡፡ የተቃዋሚዎች ድርሻ በሃገሪቱ ላይ በሚመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ስርአት እቅድና ራዕይ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ የጨቋኞች የተጠያቂነትን ጉዳይ ሰምተው እንዳልሰሙ ሊያስመስሉ ይጥራሉ::  ያ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ተጠያቂነትን መቼ አምነውይቀበላሉ ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ጨቋኞች ያደረሱትን ግፍና በደል መቁጠርና በዚያ ላይ ማላዘኑ በቂ አይደለም፡፡

ተግባራዊ እንቅስቃሴ በአግባቡ በጥንቃቄ ታስበበትና ተመክሮበት ሊወጣ የግድ ነው፡፡

እንደ መግቢያ ተቃዋሚው ስለተጠያቂነትና ግልጽነት ጥርት ያለ አቋሙን ለሕዝቡ በማያዳግምና በማያወላዉል መልኩ ማስቀመጥ አለበት፡፡ለምሳሌ ስር ሰዶ ኢትዮጵያንና ሕዘቦቿን እየቦረቦረ በማጥፋት ላይ ያለውን የጨቋኞች ስሪት የሆነውን ሙስና ለማጥፋት ተቃዋሚዎች ምን ለማድረግ ነው ያቀዱት፡፡ የዓለም ባንክ በጥንቃቄ የተዳሰሰ 448 ገጽ ያለው ዘገባ ኢትዮጵያ በዓለም አሉ ከሚባሉት በሙስና የዘቀጡ ሃገሮች አንዷ እንደሆነች አስነብቧል፡፡ ከተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችም አለያም ከአባሎቻቸው ይህን ዘገባ ምን ያህሉ እንዳነበቡት አለያም በሙስናና በብክነት ላይ የራሳቸውን ዳሰሳ እንዳደረጉ መናገር ባልችልም፤ ይህን ዘገባ ያነበበ ማንም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ስር የሰደደ የሙስና ነቀርሳ ጥርጣሬ ሊኖረው አይችልም፡፡

ለሥልጣን ለሚበቃው እውነትን ማሳወቅ

ይህ የጻፍኩት አንዳንዶቹን ሊያበሳጫቸው ሌሎቹን ደሞ ሊያንድዳቸው ይችላል፡፡ ብዙዎችን ደግሞ የሚያበረታታቸውና ጠንካራና ደፋር እርምጃ ነው እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንዳንድ አቃቂር አውጪዎች እኔ በምቾት ፈረሴ ላይ ተኮፍሼ ‹‹ተቃዋሚውን እንደተሳደብኩ አድርገው በመውሰድ ምላሳቸውን ሊሰብቁ ይቃጣታቸው ይችላል፡፡ ተቃዋሚውን እያዳከምኩና ዝቅ አድርጌ እየተመለከትክ ነው ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ሌሎችም የተቃዋሚውን ሚና አጋነንክ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ለ‹‹ተቃዋሚዎች›› ባደረጉት መስዋእትነትና እኔ ከማደርገው በበለጠ ለሰብአዊ መብት መሟገታቸውን በማሳነስ የሚገባቸውን ከበሬታ አልሰጠሃቸውም ነፍገሃቸዋል ሊሉኝም ይችላሉ፡፡ እኔ የማደርገው ጨቋኝ የሆኑት አምባገነን ገዢዎች ከሚያደርጉት ጋር ተመሳሳይ ነው ሊሉም ይዳዳቸዋል፡፡ እኔ በተመቻቸ የምሁር ወንበሬ ላይ ተቀምጬ ያለሁ የተቃዋሚዎች ተግባርና አካሄድ ሊገባህ አይችልም ብለው ሊወቅሱኝ ይችላሉ፡፡ የሆነውይሁን!

ምንም እንኳን እነዚህ አባባሎች አቅጣጫ ማስለወጫ ቢሆኑም ሁላችንም ‹‹በተቃዋሚ›› ጎራ ነን የምንል ሁሉ ልንመልሳቸው የሚያስፈልጉን ሁለት ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጨቋኞችና አምባገነን እኩዮች በጨቋኞች ጎዳና ላይ እንደግመልሽንት የኋሊት እየተዘወሩ ነው እኛስ በዴሞክራሲ አውራ ጎዳና ላይ ወደፊት አየገሰገስን ነው? የተቃዋሚው ጎራ ከ2005ቱ ከነበረበት ሁኔታ ዛሬ በተሸለ ደራጃ ላይ ነው?

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2013/02/10/ethiopia_where_do_we_go_or_not_go_from_here

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::) ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

3 Responses to ኢትዮጵያ፡ ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጉዟችን (ወይም መቆሚያችን) ወዴት ነው?

  1. Haqq Reply

    February 16, 2013 at 4:14 pm

    የገዚው ፓርቲ መሰረታዊ የስልጣን መቆያ ዘዴ ህብረተሰቡን መከፋፈል ነው።ያልተከፋፈለ ን ህብረተሰብ መግዛት ያስቸግራልና። ለዝህ ደግሞ በህብረተሰቡ መሃከል ጥርጣሬ እንድስፍን ማድረግ ነው።

    ኢትዮጵያ ዛሬ በእንደስትሪ ከበለጸጉ ሃገራት ቀደም ብለው በሀገር ደረጃ ለዘማናት ከኖሩት ጥቂቶች ውስጥ አንዷ እንደነበረች በተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች የዘገቡ ቢሆንም ህወሃት ስልጣን እንደጨበጠ ይህንን የታሪክ መዝገብ ለመሰርዝ ወይም እድሜውን በ100 አመታት ለማሳጠር ዓላማው እንደነበረ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
    በርግጥ ገዢው ፓርቲ በዚህ ታሪክን የመቀየር ጉዳይ ከልብ ስለማመኑ አጠራጣሪ ቢሆንም ለመከፋፈል በዋናነት ስለመጠቀሙ ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው።

    ሃጋሪቷ የብዙ ብሄርና ብሄረሰብ ሙዛይክ በመሆኗ ሃይማኖቱን፤ ባህሉን ፤ቋንቋውን ልምዱን ወዘተ ጠብቆ ተቻችሎ እስከዛሬ አብሮ ኖሮአል። ይህም ሲባል ችግሮች አልነሩም ወይም የብሄር ብሄረሰብ እኩልነት በሁሉም መልኩ ተጠብቆ ነበር ማለት አይደለም።

    በሌላ በኩልም የህወሃቱ አቶ ስብሃት ነጋ “ለኢትዮጵያ ብሄርና ብሄረሰብ ጥያቄ በቂ ትንታኔ የሰጠና በተግባር የተረጎመ ህወሃት ብቻ ነው ለወደፊትም ሌላ ድርጅት አይኖርም. አፍሪካዊያን በኛ ህገ-መንግስት እየቀኑ ነው.” እያሉ ሀዝቡን ለማታለል ይሞክራሉ። በተቃራኒው በህወሃት ላለፉት 21 አመታት በተግባር ሲተረጎም እያየን ያለው ሃቅ ግን “ኢትዮጵያ በጉልበተኞች የተፈጠረች የትናንት ሃገር ናት ፤ አንተም ሆንክ እኛ (የትግራይን ህዝብ እንወክላለን ሰል ለምሉ) የየራሳችን ሃገር የነበረን ሰዎች ስለሆን ወደዚያ ወደ ድሮህ መመለስ አለብህ ለዝህም አንቀጽ 39ን በህግመንግስቱ ውስጥ አስቀምጠንልሃልና ተጥቀምበት” የሚለውን ነው።

    ህወሃት/ኢህአዴግ እስካሁን ስልጣን ላይ የቆየው ሊጋፈጠው የሚችል ጠንካራ አማራጭ ሃይል ካለመኖሩ ሌላ ህዝባዊ ባይሆንም በመካከላቸው በተቻለ መጠን አንድ ቋንቋ በመናገራቸው ጭምር እንጂ በህዝባዊነታቸውም ሆነ በጥንካሬያቸው እንዳል ሆነ የሚዘንጋ ካለ የዋህ ነው።
    የአማረጭ/ተቃዋሚ ሃይሎች ግን የጥንካሪያቸው ምንጭ ሊሆን የሚችል ህዘባዊ ቋንቋ ቢኖራቸውም የጋራ ማድረግ ግን አቅቶአቸዋል።ለዚህም ብዙዎች ከሚያቀርቡት ምክንያቶች ጥቂቶቹ የግል ስልጣን (personal ego)፤የአንጋፋነት አባዜ (seniority)፡ መናናቅ፤አለመተማመን፤በተናጠል ታግሎ አሸናፊ ፓርቲ ሆኖ የመውጣት ምኞት..ወዘተ ናቸው ይላሉ። ችግሮቹ በከፊል እንኳን እነዝህ ቢሆኑ እንዴት እስዛሬ ሃጋሪቷ ያፈራቻቸው ምሁራን፤ፖለቲከኞች፤የስብአዊ መብት ተከራካሪዎች ሁሉ በዝህ የተጠመዱ ይሆናሉ? ካልሆነስ ሌላ በአንድ ቋንቋ እንዳንናገር ያደረገን ምን ሊሆን ይችላል?።

    አይናችን እያየ አገራችን እሰካሁን በምናውቃት መልክ የመቀጠሉዋ ስጋት ከምንጊዜውም በበለጠ ከፍተኛ ነው።በ(Global Trends 2030)ሪፖርት መሰረት እንደ በፈረነጆቹ አቆጣተር በ2030 እንደ ዛሬዋ ሶማሊያ መንግስተ አልባ (failed state) ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱት አገሮች አንዷ ሀገራችን ኢትዮጰያ ናት። ይንን ያንዣበበን አደጋ ለመረዳት ሮኬት ሳይንቲስት መሆን አያሻም።ህወሃት ላለፉት 21 ዓመታት ለዚህ አደጋ እንድንጋለጥ ሲያዘጋጀን ቆይቷል።ዓለም በአንድ መንደር በምትሰባሰብበት ዘመን በቋንቋ፤ በሐይማኖት፡በዘር፡በሰፈር፡ በመንደር..ወዘተ ሊለያዩን ሞክረዋል እየሞከሩም ነው። ይህ የማለያየት ጥረታቸው የፈለጉትን ያህል ባይሳካላቸውም፤በህዘባችን አብሮ የመኖር ላይ ተጥኖ አላሳደረም ብሎ የሚያሰብ ያለ አይመስለኝም። ይልቁንሰ በጊዜ መፍትሄ ካለተፈለገለት አደጋው የከፋ ይሆናል።

    ባሁኑ ወቅት በአለማችን ውስጥ ለሚከናወኑት ማንኛውም የፖለቲካ፡ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት በታሪክ አጋጣሚ ብቸኛዋ ሃያል ሀገር የሆነችው የአሜሪካ ድጋፍ ማግኘት የግድ ይላል። እሷም እንደማንኛውም ለህዝቡ የቆመ መንግስት ለህዝቡዋ ስትል ዘላቂ ጥቅምን እንጂ ዘላቂ ጉዋደኝነትን ፖሊሲ አታራምድም።የሃጋራችን አማራጭ ሃይሎች ይንኑ ፖሊሲ በመከተል ሃገሪቱዋን ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን አሜሪካን ጨምሮ የሌሎች የምዕራባዊያን ሀገራት ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ።ታዲያ ለተግባራዊነቱ እነሱም ሊያናግሩዋቸው የምችሉት በአንድ ቋንቋ መናገር ሲቻል ብቻ ነው

    አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የተዋቀሩባቸው መሰረታዊ አላማዎች ስንመለከት ተመሳሳይ በመሆናቸው የግልና የቡድን መብት መከበርን፤ የስልጣን ምንጭ የሀዝቡ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መሆኑንና የዜጎች እኩልንትና የህግ የበላይነት የተከብረባትን የኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ናቸው።ብሄርን መሰረት አድርገው የተነሱትም ቢሆኑ እንወክለሃልን ለሚሉት ህዝብ ከላይ የተጠቀሱት አላማዎቸ መፍትሄ መሆኑን እየተገነዘቡ የመጡ ከመሆኑም በላይ በይፋ ለነዝህ አላማዎች ያላቸውን አዎንታዊ መልስ ያልሰጡትም ቢሆኑም ከዚህ ሌላ አማራጭ የሚያዛልቅ አለመሆኑን የሚረዱ የመስለኛል፡ ከጊዜ የአለም- አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ውጭ መኖር አይቻልምና። ይህም ሲባል ለነዚህ አላማዎች መተግበር የአካሄድ ልዩነት የላቸውም ማለት አይደለም፤ መሰራታዊ ልዩነት ግን አይደለም።

    ከቤተሰብ ጀምሮ ሁል ጊዜ በሁሉም ነገር መቶ በመቶ መስማማት አይኖርምና መሰረታዊ ባልሆኑ ልዩነቶች ሁሉ ለሚያስማማን መሰረታዊ ግብ ሲባል ላለመስማማት መስማማት መኖር የኖርበታል። በሌላ አባባል ሰጥቶ መቀበል የግድ ይላል።ታዲያ አላማቸንንና ግባችን አንድ ከሆነ በአንድ ቋንቋ መናገር ያቃተን ለምን ይሆን?ተቀራርበን ሃይላቸንን አጠናክረን ከፈለግነው ግብ ለመድረስና የህዝባቸንን የመከራ ጊዜ ካማሳጠር ይልቅ በየጊዜው አዳድስ ድርጅቶቸን እየፈጠርን ሃይላችንን በማዳከም የነጻነቱን ቀን የምናራዝመው ለምን ይሆን?
    በሌላ በኩል በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ/ህወሃት እንደ ቀድሞ መግዛት በማይችልበት ደረጃ ደርሶ ሃገሪቷን ተረክቦ በአግባቦ የሚመራት አጥታ አናርኪነት እንዳይፈጠርና ባልተፈለገ ቡድን እጅ ወድቃ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳናመራ ያለው ስጋት ሀያው ነው።ለዝህም የገዢውን ፓርቲና የደጋፊዎቻቸውን ሚዲያ መከታተልና በሃገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ ያሉት ደጋፊዎቻቸው መቅበጥበጥና በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚያደርጉት ማስፈራሪያ ከምልክቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው። በተለይም ህወሃት መሪውን በሞት ካጣ በኋላ የቀሩት በቅጡ እንኳን መዋሸት ወይም ማስመስል አልቻሉም ለዝህም በታሰሩት የሙስልም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የተሰራው ድራማ “ጂሃዳዊ ሃራካት” በቂ ምስክር ነው። ታዲያ እስከመቼ ድረስ ነው በየጊዜው ሃጋሪቷን በህዝብ የተደገፈ መሪ ድርጅት አልባ እያደረግን መጥፎ ታሪካቸንን የምንደጋግመው?

    ለነዝህ ጥያቄዎች መልስ ከላይ የተዘረዘሩት ሊሆኑ ቢችሉም ለችግሮቹ መወገድና ለዘላቂ መፍትሄ ግን የሁሉንም ርብርቦሽ የሚጠይቅ ይመስለኛል።

    አላህ ኢትዮጰያን ከነህዝቦቹዋ ይባርካት።

  2. Sergute Selassie Reply

    February 16, 2013 at 8:07 am

    ውስጥን ፈልጎ ያገኘ አሳሽ ፁሑፍ ነው። ማድረግ ከተቻለ … መሆን ከተቻለ … ማድመጥ ከተቻለ … መፍጠን ከተቻለ … ከፍላጎት ለመድረስ መንገድ ጠራጊና ገምጋሚ፤ ሃያሲ፤ ገንቢም ጸሑፍ ነው። ጸሐፊውን የተከበሩ ፕ/አለማዬሁ ገብረማርያምና ተርጎሚውን ነፃነት ሀገሬን አመስግናለሁ።

  3. Aladin Reply

    February 15, 2013 at 2:23 pm

    Can the dear professor Al please write in Amharic – it is after all for us ethiopians, no?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>