“ታላቅ ዕድል ነው!”

September 21, 2012

ጠ/ሚ/ሩ በሙስና “የተለከፉ መስመር እንዲይዙ ይደረጋል” አሉ፡፡

በጎልጉል ሪፖርተር

September 21, 2012 02:02 pm By Editor

ዛሬ አርብ ልክ ከጠዋቱ 3፡38 ላይ 374 የኢህአዴግ ወኪሎችና ኢህአዴግን እንደሚደግፉ በግልጽ የሚናገሩት አንድ በግል ያሸነፉ የፓርላማ አባል የሚገኙበት የተወካዮች ምክር ቤት አጨበጨበ። ጭብጨባውን ተከትሎ ኢቲቪ የቦሎ ሶሬውን ሰው አመላከተ። ከሃያ አንድ ዓመት በኋላ በሟቹ አቶ መለስ የፓርላማ መቀመጫ ላይ የተሰየሙት አቶ ኃይለማርያም ፈገግታ አሳዩ። አስቀድሞ የተነገረው በትረ ሹመት ስርዓቱን አሟላ። አቶ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ታወጀ።“ታላቅ ዕድል ነው!”

ቀልጠፍ ቀልጠፍ እያደረጉ ስርዓቱን የመሩት አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑትን አቶ ተገኔ ጌታነህን ጋበዙ። በሳቸው ትዕዛዝ ኃይለማርያም ቃለ መሃላ ለመፈጸም ቀኝ እጃቸውን አነሱ። ስማቸውን ጠርተው ማሉ።“…ከአገርና ከህዝብ የተጣለብኝን ሃላፊነት በቅንነት፣ በታታሪነት፣ እንዲሁም ህግንና ስርዓትን ለመፈጸም ቃል እገባለሁ” ሲሉ ሲናገሩት ቀላል የሚመስለውን መሃላ በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና፣ በድህነት፣ በዴሞክራሲ እጦት፣ በፍትህ ጥማት፣ ቀና መሪ በራበው፣ እስርና ስቃይ ባንገፈገፈው፣ የመሰብሰብና የመናገር መብት በተገፈፈ፣…… ህዝብ አቀረቡ።

3፡38 ላይ ሙሉ ጠ/ሚኒስትር የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ከአንድ ደቂቃ በኋላ “ ክቡር ጠ/ሚኒስትር” ተብለው ንግግር እንዲያቀርቡ ተጋበዙ። “የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች” በማለት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሙሉ ማዕረግ ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አስራ ስድስት ደቂቃ በፈጀው ዲስኩራቸው ቅድሚያ የወሰዱት ሹመታቸውን “ታላቅ ዕድል” በማለት ነበር።

አቶ መለስን በማሞካሸት የታጀበው የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ንግግር “… የኔ ድርሻ የአቶ መለስን ሌጋሲ/ውርስ/ ሳይበረዝ ማስቀጠል ነው” በማለት ወ/ሮ አዜብ ባለቤታቸውን በመስቀል አደባባይ ሲሸኙ የተናገሩትን ቃል በቃል አጣቅሷል። እያንዳንዱን ዘርፍ በመዳሰስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት አቶ ኃይለማርያም በእርሻና በመስኖ ልማት የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመደገፍ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡ ባሰመሩበት ንግግራቸው በጥንቀቄ ተዛልፈዋል።

ሹመታቸውን “ታላቅ ዕድል ነው” ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ሙስናን አስመልክቶ ሲናገሩ በከፍተኛ ደረጃ ኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባቸውን ዘርፎች ዘርዝረዋል። የመሬት አስተዳደር፣ የታክስና ቀረጥ አሰባሰብ፣ የመንግስት ግዢ አሰባሰብናና የፍትህ አሰጣጥ ዘርፍን በዋናነት ነቅሰው በመጥራት “በሙስናና በስነ ምግባር ጉድለት የተለከፉ ሰዎችን በአግባቡ መስመር ማስያዝ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። ህዝብ ያለማቅማማት ተባባሪ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ህዝቡን በማርካት ማገልገል እንደሚኖርባቸው ያሳሰቡት አቶ ኃይለማርይም፤ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማትና ህግን አክብረው ከሚሰሩ ካሉዋቸው የተቃዋሚ ፓርቲዋች ጋር አብረው እንደሚሰሩ ቃል ከመግባት ውጪ መንግስታቸው ተቋማዊ ለውጥ ለማድረግ ስለማሰቡ የተነፈሱት ነገር የለም።

በነጻነት እጦት ስለታፈነው የነጻው ፕሬስ በደምሳሳው አብረን እንሰራለን ከማለት ውጪ በበጎም ሆነ በመልካም ጎኑ ምንም ሳይናገሩ አልፈውታል። የመልካም አስተዳደር ችግር ሮሮ እንዳለ በማውሳት ህዝብን በቀናነት ማገልገል እንደሚገባ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት የሃይማኖት ነጻነትን እንደሚያከብርና ጣልቃ እንደማይገባ አውስተው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

አቶ መለስን መስለው ባስተላለፉት ማሳሰቢያ በሃይማኖት ስም የሚደረግን ማናቸውም ዓይነት የሽብር ተግባር እንደማይታገሱ በግልጽ አስቀምጠዋል። ተግባሩንም “በቀጥታ ከህገ መንግስት ጋር የሚያላትም ነው” ብለውታል። በማንኛውም ሽብር ነክ ጉዳዮች ላይ መንግስታቸው ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ያሳሰቡት አቶ ኃይለማርያም ሽብር ነክ ስላሉዋቸው እንቅስቃሴዎች አላብራሩም። ይልቁኑም ኢትዮጵያን ከማንኛውም አይነት ጥቃት የሚከላከል የመከላከያ ሃይል መገንባቱን በማውሳት “ከህዝባችን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላማዊና የተረጋጋች አገር መሆኗን አስመስክረን እንቀጥላለን” በማለት የመከላከያ ተቋማት ይበልጥ ሳይንሳዊ የሚሆኑበት አቅጣጫ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስገነዘቡት።

አዲስ ካቢኔ ስለማቋቋማቸው ዝምታን የመረጡት ጠ/ሚ/ሩ “የባንዲራ ፕሮጀክት” በሚል ስያሜ የሚጠራውን የአባይ ግድብ ከተያዘለት እቅድ አስቀድሞ ለመጨረስ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ እንዲቆም ጫና ስለመኖሩና ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ስላጋጠመው የገንዘብ እጥረት ግን ያወሱት ነገር የለም።

የዋጋ ግሽበትን ለማርገብ ከዘንድሮው የምርት ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚገኝ በማመልከት መልካም ምኞት ከማስተላለፍ ውጪ ግሽበቱን ለማቃለል በተለይ ስለሚተገበር ጉዳይ ያላብራሩት አቶ ኃይለማርያም በሌላ መልኩ በአገሪቱ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ለማድረግና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በእርሻ ስራ እንዲሳተፉ እገዛ እንደሚደረግ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው በዛሬው ንግግራቸው ውስጥ ታላቁ ቁም ነገር ተብሎላቸል።

የመስኖ እርሻን ስለማስፋፋትና ሰፋፊ እርሳዎች በአገር ተወላጆች እንዲጎለብት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለውጪ ባለሃብቶች በሳንቲም እየተቸረቸረ ስላለው አገሪቱ ለም መሬት ጉዳይ አቋማቸውን አላሳወቁም። በርካቶችን እያፈናቀለ ያለው የመሬት ወረራ የደም ዋጋ እያስከፈለ ያለ ከመሆኑም በላይ ምርቱ አገር ውስጥ እንዲውል የሚደረግ አለመሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲሰነዘርበት የቆየና አሁን ድረስ መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ የብአዴን ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ደመቀ መኮንን ለምክትል ጠ/ሚኒስትርነት አቅርበው አሹመዋል። አቶ ደመቀ ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያም ቃለ መህላ ፈጽመው ሹመታቸውን አጽንተዋል። በቀጣይ ከሁለት ወር በኋላ ትግራይ የሚካሄደው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ተለዋጭ መሪዎችን ካልመረጠ በስተቀር አቶ ኃይለማርያም በአሁኑ ሰዓት የደህኢዴን ሊቀመንበር፣ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የጦርሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የሚኒስትሮች ምክርቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ባለትልቁ ማዕረግ ናቸው። ህወሓት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ለኦህዴድ በመስጠት የፖለቲካውን ክፍተት ቢሞላው የተሻለ እንደሚሆን አስተያየት እየተሰነዘረ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>