ለማንኛውም መለስ እንኳን ከስልጣን ወረዱ!

September 19, 2012

አቤ ቶኪቻው

ይሄ ርዕስ የሚያበሳጫቸው በርካታ ወዳጆች አሉኝ። እንግዲህ ቻል አድርጉት ከማለት ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም። ባለፉት ሰሞናት ለቅሶው ገና በረድ አለለም ተብሎ ብዙ ሰው ስለ መለስ ለስለስ ሲል ነበር። አሁን ግን ለቅሶው አልቋል። መለስም እንደማይመለሱ ታውቋል። መለሳለሱም እንግዲህ ይበቃል። (ይቺ የግጥም አድባር በቃ ንግግሬን ሁሉ ግጥም አደረገችው እኮ! የፌስ ቡክ ወዳጆች “ሎል” ማለት ትችላላችሁ)ለማንኛውም መለስ እንኳን ከስልጣን ወረዱ!

አሁን ዕለት በስንት ጊዜዬ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብመለከት ኢህአዴግ ያደረገው ሹመት ከዚህ በፊት በተቀመጠው የመተካካት መርህ መሰረት ነው ሲል ሰማሁኝ። አጠገቤ እንግዳ ሰው ስለነበር ገመናችንን አሳልፌ ላለመስጠት ስል “እሰይ እንዲህ ነው እንጂ” ስል አደነቅሁ። በሆዴ ግን “ሰውዬውም የሞቱት ለመተካካቱ ሲሉ ነው እንዳይሉን ብቻ” ብዬ አሽሟጠጥኩ። የሆነው ሆኖ ግን መለስ እንኳንም ስልጣኑን ለቀቁ።

እንዴ…

አቶ በረከት ስሞን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት ቃል ራሱ ከእኛ እንደ አንዱ አይደል እንዴ የሚመስሉት!? “ህውሀት የታገለው የህውሃትን ስርወ መንግስት ለመመስረት አይደለም!” አሉን እኮ… ሆቸው ጉድ። ጊዜ ስንቱን ያሰማል!? እውነቱን ለመናገር የአቶውን ንግግር ላነበበ ሰው መለስ መሞታቸውን ባይሰማ እንኳ እኚያ ሰውዬ ሞተዋል ማለት ነው…? ብሎ እንዲገምት ያስገድደዋል። እውነቴን እኮ ነው እንዲህ ያለውን ንግግር በእርሳቸው ጊዜ ማን ተናግሮት ያውቃል? ለማንኛውም መለስ እንኳንም ከስልጣን ወረዱ!

እንዴ…

መለስ ከስልጣን ባይለቁ ኖሮ ኢህአዴግ ውስጥ መተካካት ይነገራል እንጂ ይደረጋል እንዴ!? አረ ወዴት ተብሎ… በተለይ የጠቅላይነት ቦታውን ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ ሲሉ ሲያጓጉን እንጂ ጨክነው ሲለቁ መች አየናቸው…!?

እንዴ…

አሁንማ… ለስልጣን ራሱ “ኤክስፓየሪ ዴት” ተሰራለት እየተባለ እኮ ነው። ይኸው ዛሬ ሪፖርተር አቶ በረከት ስሞንን ጠቅሶ እንዳወራው በመለስ የስልጣን ዘመን ሰምተን የማናውቀው የሚኒስትሮች የስልጣን ጊዜ ከአስር አመት ወይም ከሁለት የምርጫ ዘመን እንዳይበልጥ ተደረገ አይደል እንዴ!? ልብ አደርጉ ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ስልጣን የሚመለከት ነው። ይህ አይነቱን “አለም” የት ሰምተነው እናውቃለን ጠቅላዩ ስልጣኒቷን እንደፍቅረኛቸው “የዘላለሜ ነሽ” ብለው እቅፍ አድርገዋት አልነበር እንዴ የኖሩት…!? በነገራችን ላይ ባለቤታቸውም “ለኔ ጊዜ አይሰጠኝም ነበር” ሲሉ በአደባባይ ይህንኑ መስክረውባቸዋል። ለማንኛውም መለስ እንኳንም ከስልጣን ወረዱ…

እንዴ…

ቢያንስ ቢያንስ ሌላ አስተዳደር እንይ እንጂ…!

በበኩሌ ተስፋ አደርጋለሁ። ተስፋ ማድረግ ብዙም ስለማይቆጥር ተስፋኝነት ጥሩ ነው ከሚሉት ወገን ነኝ።

እናም ተስፋ አደርጋለሁ… አሁን አሁን ኢህአዴግ ስጋ ፈራሽ መሆኑን በሊቀመንበሩ ፍርሻ የተረዳ ይመስለኛል። ስለዚህም የተለያዩ ማሻሻያዎችን ያደርጋል ብዬ ተስፋ ሰንቂያለሁ።ለዚህ ነው እንኳንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን ወረዱ! የምለው። ያው መቼም እንኳን ሞቱ አይባልም ብዬ ነው!

One Response to ለማንኛውም መለስ እንኳን ከስልጣን ወረዱ!

 1. በለው ! Reply

  September 20, 2012 at 3:53 am

  ^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^
  አሁን ግን ለቅሶው አልቋል።
  መለስም እንደማይመለሱ ታውቋል።
  መለሳለሱም እንግዲህ ይበቃል።!!
  ተው ቻለው ሆዴ እውነቱ ሲነገር ሰው ይከፋል እንዴ
  ኸረ ተው በለው!…ስንቱን ጉድ ችሎት እዩት ዛለ ክንዴ!
  ሰውዬው ወረደ ከቶ ማነው ያለው?
  ከላይኛው ቤቱ ሲወጣ አይተነው።
  “ህውሀት የታገለው የህውሃትን ስርወ መንግስት ለመመስረት አይደለም!” ከሥልጣን ሽግግሩ ይልቅ ከሚያከራክረን ለሥልጣኑ ‘ኤክስፓየር ዴት’ አለመኖሩ የህገመንግስቱ ክፍትአፍነት ቁጥር ፩ ነበር።!!!
  እሰይ አበጀህ የእኛ ልጅ
  ስልጣኑን ገደብክ በአዋጅ!
  እሰይ አበጀህ የእኛ ሎጋ
  ቶሎ አስምለው ይህን ሸጋ
  መጪው አይታወቀም መሽቶ እስኪነጋ!!
  ሕገ መንግስቱ ከአንቀፅ ፸፪ እስከ ፸፭ ብዙ አነጋግሯል የሚገርመው ጠ/ሚሩ ከተሰወሩ ጊዜ ጀምሮ ሞተው እስከተገኙበት ጊዜ ሕዝቡ እራሱን በራሱ ሲያስተዳድር ሰንብቷል። ኢህአዴግ ም/ጠ ሚኒስትራችን እያለ ሲያነብ ለቅሶ ሊደርሱን የመጡት ግን አውሮፕላን ላይ ሕገመንግስቱን አንበው ሲያስተምሩን ዋሉ!።ተጠባበቂ (ጊዜያዊ) ጠ/ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ ብለው አረሙልን።እዚህ ላይ ግለሰቡ የኢህአዴግ ሊ/መንበር ቢሆኑም የጠቅላይ ሚ/ር ማዕረግ ስለሌላቸው የጦር ሃይሉም ይሁን ማናቸውም ፓረቲና ቡድን የመፈንቅለ መንግስት ቢያደርግ መሪ የሌላት ሀገር በመሆኗ በሕገ መንግስቱ አይታገድም ነበር።ያለ መንግስት አልፈነቀለም!። አሁንም የሕገ መንግስቱ ክፍትአፍነት ቁጠር ፪ ይህ ነበር። አቶ በረከት ስምኦን እና አማካሪዎቻቸው አስቸኳይ ቃለ መሃላ ለማስፈፀም መጥራታቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው!!።እኔም እንቅልፍ ይውሰደኝ…እንጂ “በራቸውን ሳይዘጉ ሰው ሌባ ይላሉ” የሚባለው በአደባባይ የተፎገርነው አንሶ በዓለም ዜና ላይ ቅሌታችንን ልንከናነብ ዋይ !ዋይ! ለጥቂት!አወጣን!!እንኳንም አቶ መልስ ከሥልጣን ወረዱ !ብቻ ሳይሆን እንኳንም በሳል አማካሪ ገጠማችሁ ብዙ ቤት ሥራ አለባችሁ።!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>