አቶ ኃይለማርያም፤ “ሜዳውም ፈረሱም ያው…” ታድያ በቅጡ ይጋልቡ!?

September 18, 2012

አቤ ቶኪቻው

ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ቤተመንግስቱ በራፍ ላይ ቆመዋል። ለነገሩ እንኳ ሰውየው ደጃፍ ላይ ከቆሙ ቆይተዋል። ነገር ግን የኢህአዴግ ሰዎች “አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይቆይ…” ብለው ደጅ ሲያስጠኗቸው ሰነባበቱ። ይገበሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ቢያንስ ኢቲቪ እና የመንግስት “ባሉካዎች” የጠቅላይ ሚኒስሩን ሞት በሰሙ በሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ ነበር። ነገር ግን ይኸው ዛሬም ገና ፓርላማው ጠቅላይነታቸውን እስኪያፀድቅላቸው እንደ ቆሎ ተማሪ ደጅ መቆም ግዴታቸው ሆኗል።አቶ ኃይለማርያም፤ “ሜዳውም ፈረሱም ያው…” ታድያ በቅጡ ይጋልቡ!?

አቶ ሀይለማሪያም የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትን ስልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሲሲቲቪ” ለተበለ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል “የእኔ አመራር የጋራ አመራር መርህን የተከተለ ነው” ካሉ በኋላ፤ “እንደሚታወቀው የመለስም አመራር ለግለሰብ የበላይነት ቦታ የማይሰጥ የቡድን ስራ የጎላበት አመራር ነበር” ብለው የማናውቀውን ነገር ነግረውናል። እውነቱን ለመናገር እኛ የምናውቀው አቶ መለስ “ሁሉን ቻይ” የነበሩና ሁልገዜም ብቻቸውን እንጂ በጋራ ሲሰሩ አላየንም። እርግጥ ደንብ ነውና ሙትን ሲያነሱ ደግ ደጉን ነው። ስለዚህ ስለ መለስ የሚያወሩት በሙሉ ፅቡቅ ፅቡቁን ቢሆን ግድ የለም…

መምህር ኃይለማሪያም ሆይ መለስን ለአሁኑ እንተዋቸው እና በእርስዎ ጉዳይ እናውጋ… እናልዎ… አሁን ሜዳው ሜዳውም ፈረሱም በእጅዎ ነው። እንግዲህ በቅጡ መጋለብ የእርስዎ ፈንታ ነው።

መምህር ሆይ ይቅርታ አንድ ጊዜ ወደ መለስ መለስ እንበልና አንድ ነገር ሹክ ልበልዎትማ ባለፈው ጊዜ የመለስ ለቅሶ ላይ ጥቁር በጥቁር ለብሶ “እንባ የተራጨው” ህዝቡ ሁላ ከኢህአዴግ ጎን ነው ስለዚህ እንዳሻኝ እሆናለሁ ብለው እንዳይሸወዱ… ልብ ያድርጉልኝ “እንባ የተራጨው” የምትለዋ ቃል ራሱ ያለችው በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ነው። ለምን ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ እንደገባች በአዲስ መስመር ላይ ልንገርዎት…

በጉለሌ ክፍለከተማ በሆነው ቀበሌ ውስጥ የቀበሌው አስተዳደር ለመለስ ለቅሶ ድንኳን ደኩኖ ነበር። ታድያልዎ… አስለቃሹ የቀበሌ አስተዳደር በየቤቱ እየዞረ “በዛሬው ዕለት ጋዜጠኞች ስለሚመጡ ሁሉም ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ በድንኳን ውስጥ እንዲያለቅስ” ሲል አዘዘልዎ። የቀበሌው ሰውም ታዛዥ ነውና እሺ ብሎ ጥቁር ልብስ ያለው ልብሱን ልብስ የሌለው ደግሞ ፊቱን አጥቁሮ ወደ ለቅሶው ድንኳን አመራልዎ። ምን ዋጋ አለው አንድ ሁለት ሶስት ተብሎ ለቅሶ ሲጀመርልዎ ከአስለቃሽ ኮሚቴ አባላት አንዱ “እባካችሁ አሁን ጋዜጠኞቹ ደውለው መምጣት አንችልም ስላሉ አታልቅሱ፤ ነገ ሲመጡ እናለቅሳለን አሁን ካሜራ በሌለበት ብናለቅስ ዋጋ የለውም” ብለው አስቆሙልዎ…! ለዚህ ነው “በእንባ ሲራጩ” የምትለዋን ቃል ለማንኛውም ብዬ ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባኋት። እናም አቶ ኃይለማሪያም ሆይ እንዳይሸወዱ…

የእርስዎ ነገር የሚወሰነው ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ የሚያመጣብዎም ሆነ የሚያመጣልዎ ቀጥሎ በፈረስዎ እና በሜዳዎ ላይ በሚያሳዩት ትዕንት ነው።

ለምሳሌ ከመለስ በኋላ በነበረው “የአስከሬኑ” አስተዳደር ጊዜ ከማተሚያ ቤት ደጃፍ እንዲጠፉ የተደረጉት እና ድሮውንም ትንሽ ጭል ጭል ሲሉ የነበሩ ነፃ ፕሬሶች ቢያንስ ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ ማድረግ አለብዎ…

ሌላ ደግሞ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችን መፍታትም ምንም ሳይጨነቁ ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነው። ዳሩ ትዳርን መፍታት እንጂ ምስኪን እስረኛን ለመፍታት ምን ያስጨንቅዎታል? ዝም ብለው ዛሬ ነገ ብለው ቀጠሮ ሳይሰጡ፤ ሽማግሌ ገለመሌ ሳይሉ ይፍቱዋቸው።

በነገራችን ላይ የስዊድን ጋዜጠኞች ተፈቱ አሉ እሰይ እንዲህ ነው እንጂ… ግን ያኔ አቶ መለስ “የነጭ ደምም የጥቁር ደምም አንድ ነው” ብለው ደስኩረውልን አልነበር እንዴ..!? እንዴት ነው ነገሩ ለመታሰር ጊዜ ነው አንድ የምንሆነው?

ለማንኛውም ቢያንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች ካደረጉ ሌላውን ደግሞ ቀስ ብለው ይሰሩታል። አደራ የኑሮ ውድነቱን ነገር ለመግታት የተቻሎትን ሁሉ ያድርጉ። ካልተቻሎት ደግሞ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገለልተኞች ብቻ ግን ለዚህ መፍትሄ ያላቸውን ባለሞያዎች እገዛ ይጠይቁ…!

እንደ እርሳቸው ሁሉን ነገር እኔ ብቻ እና እኛ ብቻ አይበሉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ ይጥሩ ይጣሩም።

አለበለዛ ሀበሻ ይተርትብዎታል “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ይሎታል። እውነት እውነት እልዎታለሁ ተርቶ ብቻ የሚተዎት አይመስለኝም። ወጡን ለማጣፈጥ የራሳቸውን ቅመም ማበጀት የጀመሩ ብዙ ጎበዛዞች አሉ (ይሄ ሚስጥር ነው።) አራዳ ከሆኑ ግን የቀማሚዎችንም ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ።

እንግዲህ ይበርቱ! እንጂ ሌላ ምን እላለሁ…!

2 Responses to አቶ ኃይለማርያም፤ “ሜዳውም ፈረሱም ያው…” ታድያ በቅጡ ይጋልቡ!?

 1. Taddele G. Hiwot Reply

  September 26, 2012 at 4:29 am

  ኢትዮጵያ ራስዋን የቻለች ክብ ዓለም ናት። በክቡ ዓለም አፍሪካም ሆነ አሜሪካ፣ ኤሲያም ሆን አዉስትራሊያ የዓለም እምብርት ነዉ ምክንያቱም ሌሎቹ ሁሉ በዙሪያዉ ስለሆኑ። ዴሞክራሲ ባልረታዉ ዓለም ግን ሃያላን አገሮች ብቻ ናቸዉ እንደዓለም እምብርት የሚታዩት።በዱሮዋ ኢትዮጵያ የንጉሱ ድንኳን የቆመበት ቦታ ነበር እንደእምብርት የሚታየዉ። የንጉሱን ዘር የሚጋራዉ ነበር ማእከል ሆኖ ሌሎቹን የሚያስተዳድረዉ። በአድዋ ጦርነት አዉሮፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ባፍሪካ መሬት ድል ያደረገዉ ኢትዮጵያ የሚባለዉ ያገር ስም ሃያል በመሆኑ በዘራቸዉ ማእከልነት የሚገዙት እያደሩ ለኢትዮጵያ ታማኝነታቸዉን በተግባር ያሳዩ ነበር። ብዙ አመት በማእከልነት ኢትዮጵያን የገዙት ለኢትዮጵያ ታምኝ በመሆን ለወለዳቸዉ ያማራዉ ክፍል ከሌሎቹ የተለየ ኢሃዴግ ለትግራይ ያደረገዉን አድሎአዊ ግንባታ ሳያደርጉ የስልጣን ጊዜያቸው አለፈ። የዴሞክራሲ አገዛዝ በእዉነት በሚጋንባት ኢትዮጵያ ነጥብ ጣቢያ ወረዳዎች ሁሉ እንደማእከል ስለሚታዩ ኢትዮጵያዊ ከየትኛዉም ዘር ቢሆን እንደማእከል እንዲያገለግል ከተመረጠና ስራዉንም በትክክል ካካሄድ የማይከበርበት ምክንያት የለም።
  በፈረንሳይ በሰባት ዓመት አንዴ ፕሬዝዳንት ይመረጥና አሮጌዉ ፕሬዝዳንት ለአዲሱ ፕሬዝዳንት እጅ ነስቶ አዲሱን ፕሬዝዳንት አሮጌዉ ፕሬዝዳንት በዋናዉ በር አስገብቶ አሮጌዉ በኋላ በር ይወጣል። ታጋሽና ጥበበኞቹ ኢትዮጵያዉያን የዉነተኛዉን ዴሞክራሲ አገዛዝ እንደሚያዩ ምንም ጥርጥር የለኝም። አምላክ ሃገራችንን ሕዝብ አንድ ሕዝብ ያርግልን።
  ታደለ ገብረ ሕይወት
  የማነዉ ኢትዮጵያዊዉ ደራሲ።

 2. በለው ! Reply

  September 19, 2012 at 1:27 am

  የተቀበሩትን ነፍስ ይማር ብለን በቀጥታ ወደ ሹማምንቱ እናመራለን እንኳን ደስ ያለዎ/ችሁ ! ክቡር ሀይለማርያም መኮሳተር አያምርብዎትም ያቺ በቆረጣ የሚሾፉትና ፈገግታዎ ትምጣብኝ ድንቡሽ ቡሽ ካለው ምክትልዎ ጋር…! “ልጁ ፍንጭቱ ነው ምልክቱ.ያዝ ያዝ ጠበቅ አርጉት.. ፈረሱ ላይ ስታወጡት!” … ብቻውን አይወጣም ይመከራል! ይደገፋል !ይቃኛል!ተባለ እርስዎም እንዳረጋገጡት ለመስዋትነት ወደ መሰዊያው ወስነው (ቆርጠው) እንደተቀመጡ ተናግረዋል። ላለፉት ፳፭ ቀናት ሰውዬው ካሉበት ሆነው ሲመሩን አልፎም እስረኛ ለማስፈታት ለፕሬዘዳንቱ አቅርበው ሲያፀድቁ ለጄኔራሎች ሹመት ሲሰጡ ምንም ዕረፍት አላገኙም! ወይ ታጋይ አይሞትም! ለአንዳንዶች ቆመው አደለም ሞተውም ሥራ ከፍተዋል ፎቶግራፋቸው ፣ታላቁ መሪ የተጠቀሙበት ጫማ…መነፅር፣ ማበጠሪያ ተቸበቸበ አሉ። “ሴትየዋ ለቅሶ ሊደርሱ ቀበሌ ሄደው ንፍሮ በሰፊው ቀርቦ አዘነተኛው አንሷል ሊወጡ ሲሉ ነፍስ ይማር ማለታቸውን ዘንግተው! አንቺ ስንቄ ዕድሜ ለታላቁ መሪያችን ራዕይ እስቲ ለልጆቼ በዚህ በፌስታል ንፍሮ አርጊልኝ “ብለው ልጆቻቸውን መገቡ ። ስንዴውስ ቢሆን በእርዳታ ያገኘነው አደለምን ?
  አመራርን በተመለከተ…. “የመለስም አመራር ለግለሰብ የበላይነት ቦታ የማይሰጥ የቡድን ስራ የጎላበት አመራር ነበር” group leadership!” የእኔ አመራር የጋራ አመራር መርህን የተከተለ ነው””collective leadership”
  እዚህ ጋ አቤ ቶክቻውን ጥሩልኝ ” ….
  * ፈጣሪያቸው ያለበት ሰባተኛው ሰማይ ላይ ደርሰው ምን እያደረገ እንደሆን ሊሰልሉት ያሴሩትን ፈጥኖ ደርሶ ቋንቋቸውን ደበላለቀው። ከዛስ…? ከዛማ አንዱ ብሎኬት አምጣ ሲል ውሃ ሲያቀብለው፣ ሙገር ሲሚንቶን አቀብለኝ ሲል የቀበና አሸዋ ሲያመጣ ግንቡ በየት በኩል ይግባቡ በየት በኩልስ ይገንቡ!? ሀሳባቸው ከንቱ ሆኖ ቀረ። ምን አልባት ይቺ አመራር ትሆን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ባህል፣አብሮ መኖር ሉዓላዊነት ቅጥ አንባሩን ያጠፋው? ? ለመሆኑ በሀገራዊ እርቅ አብሮ በመስራት በመወያየት ሁሉም ለዛች ሀገር እንደሚያገባው እኛ እና እነሱ የሚባል ቀርቶ የመፃፍ፣የመጠየቅ በቂ ምላሽን የመስጠት የተጠያቂነት ባሕል በአዲሱ አመራር ይሠፍን ይሆን?? ነባር የጦር ሜዳ ጀግኖችን አሰናብቶ ወጣት መተካቱ ሳይሆን የሐሳብና የአቀራረብ ለውጥ ያሰፈልጋል። ሀገረን በተመለከተ የመጣችሁበት ነገድ፤ ዘር፤ ክልል፤ ከተጠያቂነት አያድንም ለውጥ ካልታየ ነቀፌታውም ይቀጥላል የተሻሻለም ሲገኝ የግድ ድንኳን ጥሎ ጭፋሮም ባያስፈልገው እንትፍትፍ ማለታችን አይቀርም ይህ “የበላ ቢያብል እንባው ይመስክር!” “ያረረና የከሰለ የታየው በጧፍ በሻማ ነው!” አሉ እንግዲህ እናንተም እንደሻማ ባትቀልጡም እንደመብራታችሁ በፈረቃ ምሩን ግን አታማሩን በህብረት (አመራር በደቦ) እንዳትወቅጡን ////? “መሌ ማረን ማረን የራዕይህ ነገር እኛንም ገደለን ” እንዳይባል አደራ! አደራ! በቸር ይግጠመን።
  “እንኳንም ከገብረማርያም ‘ግሩፕ’ ወደ ሃይለማርያም ‘ህብረት’ አሸጋገራችሁ” ! !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>