ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስተሳሰባችንን በማናወጥ ወንጀል” ሊጠየቁ ይገባል ተባለ!

August 15, 2012

አቤ ቶኪቻው

ይህንን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የሰማሁት ሰፈሬ እንጦጦ ኪዳነምህረት ፀበል ነው። ተጠማቂዎች በአጋንንት እና በሌሎች ርኩስ መናፍስት አይምሯቸው ይናወጥ እና በአስጠማቂዎች ፍዳቸውን ያያሉ። “ያናወጥከውን አዕምሮዋን መልስ…! ልቀቅ…! ውጣ!” ይባላል። ከዛም ወዶ ሳይሆን በግዱ ይለቃል። ያናወጠውን አዕምሮም ይመልሳታል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስተሳሰባችንን በማናወጥ ወንጀል” ሊጠየቁ ይገባል ተባለ!

ዛሬ ደግሞ ጋዜጣ በማሳተም የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ አደርጋለሁ ብሎ መከራውን ሲያይ የነበረው ወዳጃችን ተመስገን ደሳለኝ “የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በማናወጥ” ወንጀል ተከሷል።

ይሄንን ነገር እርኩስ መናፍስት ብቻ የሚያደርጉት ሲመስለን የነበርን እኛ፤ በነገሩ ግራ ተጋብተን እንዴት አድርጎ አስተሳሰባችንን እንዳናወጠ አቃቤ ህግ የሚያቀርበውን ማስረጃ ለመስማት ተቻኩለናል። የተሜን የክስ ሂደት አስመልክቶ እየተከታተልኩ የአቅሜን ያህል “አንጀት ላይ ጠብ የሚል” መረጃ ለማቀበል እሞክራለሁ።

አሁን ግን ነገሩን ያነሳሁት “የህብረተሰቡን አሰተሳሰብ ማናወጥ” የሚለው ክስ እኛ ለእርኩስ መናፍስት እንጂ ለምድራዊው ሰው የሚቀርብ ስላልመሰለን ትተነው እንጂ በአሁኑ ግዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስተሳሰባችንን ያናወጠ ማን አለ!? ብለው የሚጠይቁ አንዳንድ ወዳጆችን በመስማቴ ነው።

እኔ የምለው የምር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር አስተሳሰባችሁን አላናወጠውም!? መታመማቸው ሲድበሰበስ ሲድበሰበስ ከርሞ በኋላ ላይ ይፋ ወጣ! ምን ሆነው እንደታመሙም የሚነግረን አካል አላገኘንም። ስለዚህም የተላያዩ ግምቶችን እየገመትን አስተሳሰባችን ቀላል ተናወጠ እንዴ! (በነገራችን ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ህመም ዋና ምክንያት በአበበ ገላው ቁጣ አስተሳሰባቸው ተናውጦ ነው እናም አቤ ራሱ አስተሳሰብ በማናወጥ ወንጀል ሳይከሰስ አይቀርም የሚሉ ጭምጭምታዎችን እየሰማን ነው።)

እና ታድያ በአስተሳሰብ መናወጥ የተነሳ የአልጋ ወይም ወይም የፍሪጅ ቁራኛ የሆኑት አቶ መለስ ላለፉት ሃምሳ አምስት ቀናት ተሰውረው በአስተሳሰባችን ላይ ክፉኛ የመናወጥ ወንጀል ሰርተው ተገኝተዋል የሚል ክስ እየቀረባበቸው ነው።

ቆይ እዝች ላይ አንድ የወዳጄ እናት ምን እንዳሉ ልንገርዎትማ… ወይዘሮዋ አቶ መለስ “በህይወት የሉም” ብለው ከሚያምኑት ወገን ናቸው። የውጪ ሀገር የህክምና ወጪን እንዲሁም በሞት ጊዜ አስከሬን በፍሪጅ ውስጥ ሲቀመጥ የሚያስወጣው ወጪ ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ያውቁታል። ታድያ ይሄ ነገር በጣም ሲያስጨንቃቸው ከርሞ ልጃቸውን ጠርተው… “እኒህ ሰውዬ በህይወት እያሉ አገሪቷን አቆረቆዙ የሚለው ክስ እልባት ሳያገኝላቸው አሁን ደግሞ አልሸጥ እንዳለ ኮካ በፍርጅ ውስጥ ተቀምጠው ይሄንን ሁሉ ወጪ ማስወጣታቸው እግዜር ይወደዋል?” ብለው ጠይቀዋታል… ልጃቸውም በዚህ ጉዳይ አይምሮዋ ተናውጦ ይሄው መሽቶ በነጋ ቁጥር “በፍሪጅ ውስጥ ያሉት” ጠቅላያችን የሚያስወጡንን ወጪ እያሰላች ተጨንቃለች።

እውነት ግን አቶ መለስ በአሁኑ ሰዓት የትኛው ቁራኛ ናቸው… ? የአልጋ ወይስ የፍሪጅ ቁራኛ!? ይሄንን ሁሉ ክፉ ደግ የሚያናግሩን እራሳቸው ናቸውና ሃላፊነቱን ይወስዷታል።

ትላንት አቦይ ስብሃት ሲናገሩ በአቶ መለስ አለመኖር የተነሳ ምንም የተፈጠረ አለመረጋጋት የለም ብለዋል። አንድ ከአዲሳባ የመጣ ወደጄም እንደነገረኝ ሁሉ ነገር እንደቀድሞው ነው የሚመስለው አገሪቷ “አስከሬን እየመራት አትመስልም!” ብሎኛል። የምር ግን ለህዝባችን ምንኛ ሽልማት ይበቃው ይሆን… ጠቅላዩ ሲጠቀልሉቱም ሲጠቀለሉበትም በሃሳብ ብቻ እየተናወጠ ዝም!

እናልዎ ወዳጄ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሸግ በብዙ መልኩ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ማናወጡ እየተነገረ ነው። አንዳንድ ወዳጆች የሚሆነው አይታወቅም እያሉ ከባንክ ብራቸውን እያወጡ እንዲሁም ለክፉው ቀን የሚሆን ቀለብ እያሰናዱ እንደሆነ ከታማኝ ምንጮች ሰምቻለሁ። ይሄ ሁሉ ለምን ሆነ ቢባል አቶ መለስ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ስላናወጡት የሚል መልስ እናገኛለን!

በዚህ ክስ አቶ በረከት ሰምኦን እና አቦይ ስብሀት ስለ አቶ መለስ አጥጋቢ የሆነ መረጃ ባለማቅረባቸው፤ በዋና ተባባሪ አናዋጭነት እንዲሁም አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ሪፖርተር እና ፎርቹን ደግሞ አንዴ ገቡ አንዴ ወጡ አንዴ ገገሙ አንዴ አገገሙ በሚል ማምታታት በመካከለኛ አናዋጭነት እንዲሁም ኢሳት ቴሌቪዥን መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሎ ህብረሰቡን ካጓጓ በኋላ መጠነኛ መጠራጠር በማሳየቱ በመጠነኛ አናዋጭነት እንዲከሰሱ እየተጠየቀ ነው።

ስለዚህም ዋና ወንጀል ፈፃሚው አቶ መለስ ዜናዊ በተገኙበት ቦታ በምድር ላይ ካሉ ፖሊስ በሰማይ ከሆኑም ደግሞ መንፈስ ጠፍሮ ይዞ እንዲያስረክባቸው “እየተጠየቀ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው!”

3 Responses to ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስተሳሰባችንን በማናወጥ ወንጀል” ሊጠየቁ ይገባል ተባለ!

  1. Abdurehim nasir Reply

    August 16, 2012 at 8:07 pm

    I LIKE IT

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>