የጥሩነሽ በወርቅ “ማድመቅ” እና የ “አመለወርቅ” በሀሽሽ “ማሸማቀቅ!”

August 4, 2012

አቤ ቶኪቻው

ከቀናት በፊት አንድ አሳፋሪ ዜና ሰምተን ነበር። “ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት ሃሽሽ ሲያዘዋውሩ ተገኝተው በቁጥጥር ስር ዋሉ” የሚል አስደንጋጭ ዜና። ዜናው የተሰማው ከወደ እንግሊዝ ነበር። ዴፕሎማቷ ሴትዮዋ ለስሙ ስማቸው አመለወርቅ ነበር። ነገር ግን ስማቸውን መላዕክ አላወጣላቸውም እና “ድንቄም እቴ አመለወርቅ!” የሚያሰኝ ፀያፍ ስራ ሲሰሩ ተይዘው። እኛንም በአለም ፊት አሸማቀውናል!የጥሩነሽ በወርቅ “ማድመቅ” እና የ “አመለወርቅ” በሀሽሽ “ማሸማቀቅ!”

የሰላሳ ስድስት አመቷ ወይዘሮ አመለወርቅ ይዘው የተገኙት 56 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተሰኘ ሀሽሽ ነው። እስቲ እንደው አፈር ስሆን፤ ወንጀሉ ይቅር፣ እኛን ማሸማቀቅም የለመዱት ይሁንላቸው… ነገር ግን ይህንን ሁሉ ሲሸከሙ የጡንቻ መሸማቀቅ ይይዘኛል ብሎ ማሰብ ትንሽ አይገባም…!?

ይህንን ዜና የሰማሁ ጊዜ መንግስታችን እንደዚህ አይነት ዲፕሎማቶችን  በውስጡ አቅፎ ደግፎ ይዞ ሌሎች ምስኪን ወገኖች ላይ “መልካም ገፅታዬን አጠፋችሁ፣ የሀገር ደህንነት ስጋት ሆናችሁ፣ ወዘተ ወዘታችሁ” እያለ እስር ግልምጫ እና ጡጫ ማድረሱ “የሚጠምዱትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የማይባል ግፍ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

ለማንኛውም ከቀናት በፊት ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ በእንግሊዝ የሚገኙ ሚዲያዎች የመንግሰት ዲፕሎማቷ የሰሩትን አሳፋሪ ስራ በዘገባቸው ይዘው ወጥተው አንገታችንን አስደፍተውን፣ ሽምቅቅ ብለን፤ ኪሏችን ሁሉ ቀንሶ ነበር የሰነበትነው።

ትላንት ደግሞ በተቃራኒው ጥሩነሽ ዲባባ ከባልንጀሮቿ ጋር በመሆን ቀና ብለን እንድንራመድ አድርጋናለች። ባንዲራችንን ከፍ አድርጋ እኛም ከፍ ብለን እንድንታይ በተዓምረኛ እግሮቿ ተአምር አሳይታናለች።

ኬኒያዊቷ ተፎካካሪዋ ከጨዋታው በፊት ለሀገሯ ዜጎች አንድ መልዕክት አስተላልፋ ነበር። “ከአሁኑ ወርቅ እንዳገኘን ርግጠኛ ሁኑ እናም ፅዋቹን አንሱ” ብላ ነበር አሉ። በንግግሯ ልበ ሙሉነት የተደሰቱት ኬኒያውያንም ቀድመው በደስታ ሞቅ ብሏቸው ነበር ሩጫውን ሲጠባበቁ የነበሩት።

በአንፃሩ ደግሞ ጥሩዬ፤ “ውጤቱን ከወዲሁ መገመት አልችልም ሜዳ ላይ ይለያል… ደሞም እግዜር ያውቃል” በሚል ትህትና ነበር የጀመረችው። ስትጨርስ ግን ለኬኒያውያኖቹ ትህትና አላሳየችም “እለፉ” አላላቻቸውም ጥላቸው እብስ አለች እንጂ… አሁን እዚህ አልነበረች እንዴ…!? ብለው አጠገባቸው ቢመለከቷት እርሷ ዙሩን ጨርሳ ባንዲራዋን ለብሳለች!
“እኛስ ኮራን በናንተ…!” ቴሌቪዥናችን ከፈተልን እኛም አብረን ዘመርን!

እኔ የምለው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶች ላይ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ስም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለመፃፍ እጁ እምቢ ያለው ለምንድነው…!? “ክቡር ፕሬዘዳንታችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋችኋል” ብሎ ሲነግረን የጠቅላይ ሚኒስትራችንን የደስታ መግለጫ ለማየት የቋመጥን በርካታ የእርሳቸውን መልካም የምንመኝ ግለሰቦች ነበርን…! ኢቲቪ ግን ምነው እንዲህ ጠምዶ ያዛቸው…!? ችግር አለ እንዴ!?

ለማንኛውም ወዳጄ የመንግስት ባለስልጣኖቻችን “በአጠፋሪስ” ንግድ ያሸማቀቁን ከተማ ላይ አትሌቶቻችን ደግሞ በወርቅ አድምቀው ታሪካችንን ድጋሚ አድሰውልናል። እንኳን ደስ አለን! በቀጣይም ወርቁን ያብዛልን! አሜን!

4 Responses to የጥሩነሽ በወርቅ “ማድመቅ” እና የ “አመለወርቅ” በሀሽሽ “ማሸማቀቅ!”

  1. Abdu Reply

    August 4, 2012 at 2:41 pm

    Del L Ethiopia

  2. beresaw endeshaw Reply

    August 4, 2012 at 1:59 pm

    Yigeremal

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>