የቦረና አካባቢ ግጭትና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መፍትሔ

August 3, 2012

Click here for PDF

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ሐምሌ 26፣ 2004ዓም

አገራችን በየአቅጣጫው ችግር ከቧታል። ችግሩ ደግሞ እየተባባሰ እንጂ እየተወገደ አይደለም የመጣው፡፡ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ ኬኒያ ጠረፍ በቦረናና በጋሪ ጎሳዎች መካከልEthiopia, SMNE የተከሰተው ግጭትም የዚሁ አካል ነው። “የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መንገንጠል” የሚል መርዝ በተለየ ሁኔታ በአገራችን የዛሬ አርባ ዓመት አካባቢ በድርጅትና በፓርቲ ደረጃ ከተተከለ ወዲህ ዘር፣ ጎሣ፣ ጎጥ፣ … መለያችን ሆነዋል፤ ውጤቱም ቡድን ለይቶ፣ ጎሣ ጠርቶ፣ ዘር መርጦ፣ … መተላለቅ፣ መፋጀት ሆኖዋል፡፡ ሰብዓዊነትን ከጎሰኝነት ማስቀደም ካልቻልን ሁሌም ከዚህ የመተላለቅ አዙሪት ውስጥ አንወጣም።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) በሞያሌ በተፈጠረ የጎሳዎች ግጭት ቀላል የማይባል አደጋ መድረሱን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ የግጭቱን መንስዔ ስናጣራ ቆይተናል። ባደረግነው ማጣራት ግጭቱ በቦንብ፣ በከባድና ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያ የታገዘ እንደነበር አረጋግጠናል። ያረጋገጥነው እውነት የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝም ሆነ አገዛዙን የሚያገለግሉ ካድሬዎች እንደሚሉት ለወትሮው እንደሚደረገው አስከፊ መዘዝ ያስከተለው “ግጭት” በግጦሽ ሳርና ውሃ ሳቢያ የተጀመረ አይደለም።

አልጃዚራ ምስል አስደግፎ ያነጋገራቸው አዛውንት እንደገለጹት ታጣቂዎቹ መሳሪያ ያነገቡና ቦምብ የታጠቁ ነበሩ ብለዋል። አያይዘው “እኛም መሳሪያ ቢኖረን እንታኮስ ነበር” ሲሉ ተሰምተዋል። ኬንያ ለጊዜው ካረፈበት ትምህርት ቤት ውስጥ ሆኖ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ዝግጅት አስተያየቱን የሰጠ አንድ ወጣት እንዳለው ታጣቂዎቹ ባንክ፣ ትምህርት ቢሮ፣ አስተዳደርና ተመሳሳይ ተቋማት ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል፤ ዝርፊያም አካሂደዋል።

ከቀውሱ ስንጀምር – ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ ም የተጀመረው ያልታሰበ የተኩስ ልውውጥ ሃያ የሚጠጉ ሰዎችን ገድሎ፣ በርካቶችን አቁስሏል። የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎችና የኬኒያ የቀይ መስቀል ማህበር እንዳስታወቁት 30 ሺህ የሚጠጉ ህጻናት፣ አዛውንት እናቶችና አባቶች እግሬ አወጪኝ በማለት ወደ ኬንያ ፈልሰዋል። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ እንደተለመደው አንድ የፌደራል ፖሊስ መገደሉንና ሰባት አካባቢው ፖሊሶች መቁሰላቸውን ከመግለጽ ውጪ በአጸፋው የአገዛዙ የጸጥታ ኃይሎች ስላደረሱት የጉዳት መጠን የተባለ ነገር የለም። የጋራ ንቅናቄያችን ባገኘው መረጃ መሠረት የአገዛዙ የጦር ኃይል ጠንካራ ርምጃ ወስዷል፤ ጉዳቱም የከፋ ነው።

አህዮቻቸው፣ ከብቶቻቸው፣ ፍየሎቻቸው የተገደሉባቸው ጥቂት አይደሉም። በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ንብረት ተዘርፏል። ነዋሪዎቹ ወደ ኬኒያ ዘልቀው ህይወታቸውን ቢያተርፉም አብዛኞቹ ቀጣዩን ኑሯቸውን እንደቀድሞው ለመቀጠል እንደማይችሉ ተናገረዋል። ውሃ፣ ምግብና በቂ መጠለያ በሌለበት አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ወገኖቻችን ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ቢደረግም ለወደመው ቤታቸውና ለተዘረፉት ንብረት ምትክ ሳያገኙ ቀጣዩን ህይወታቸውን እንዴት ሊመሩ እንደሚችሉ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡

“አቶ መለስ አሉ፤ የሉም” በሚል ዜናና ወሬ በተወጠረችው አገራችን በሁሉም ቡድንና ወገን ዘንድ ዜጎች ዋጋ እንደሌላቸው እየታዩ ነው። የአቶ መለስ መኖርና አለመኖር ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም የልብ ምቱና የሚተነፈሰው ሁሉ ግን በዚህ ዙሪያ ላይ ሆኖ የዜጎች ዕልቂት ችላ መባሉ “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም” ከሚለው የጋራ ንቅናቄያችን መርህ ጋር የሚጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ትኩረት የሚያሻቸው የወገኖቻችን ዕልቂት በቅድሚያ ሊያሳስበን ሲገባ የሞት፣ የለቅሶ፣ የማስተባበል፣ … ዜና ብቻ አየሩን መሙላቱ ከሚሰማው የሞት ዜና በላይ የቁም ሞት መስሎ ታይቶናል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት በቴሌቪዥን “አልገመትነውም” ሲሉ፤ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ዑመር ደግሞ “ለግጭቱ መንስዔ የሆኑ አመራሮች በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል። የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሽፈራው ተ/ማሪያም በበኩላቸው “ሚና የነበራቸው አመራሮች አሉ” ብለዋል። ከራስ አልፎ “የፈረሰችውን ሶማሌ አገር እናደርጋለን”፣  “የደቡብ ሱዳንን ሰላም አስተማማኝ እያደረግን ነው”፤ “ሰላም ለማስከበር በተጠራንበት ሁሉ ቀዳሚ ነን” የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ እንዲህ ያለ የከፋ አደጋና ሰብዓዊ ቀውስ እስኪደርስ መረጃም፣ ማስረጃም የሌለው መሆኑና ያለውም መረጃ ደግሞ የተሳከረ መሆን አገዛዙ በእርግጥ ያበቃለት ለመሆኑ በራሱ ማስረጃ ሆኗል፡፡

ለወትሮው በግጦሽ ሳርና በውሃ የሚጣሉ አርብቶ አደሮች በአገር ሽማግሌ ግልምጫ ጸባቸውን ትተው አብረው ይበላሉ፤ ይጠጣሉ። የከብት ፍቅራቸው ካንተ ይልቅ የኔ ከብት ይጥገብ በሚል ከመጣላት ውጪ ቦንብና ክላሽ ወድረው ሲናረቱ ተሰምቶ እንደማያውቅ ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ይገልጻሉ። ታዲያ ዛሬ ለምን ተካረረ?

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ባሰባሰበው መረጃ ያካባቢው አመራሮች የአንዱን መሬት ለሌላው በመሸጥ ብር እየሰበሰቡ ናቸው። መሬት የገዛው ሰው ለገዛው መሬት ማስረጃ ሲጠይቅ ከዛሬ ነገ በሚል በማቆየት ያጠራቀሙት ቁርሾ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። ከዚህም በላይ መሳሪያ ንግድ ውስጥ የገቡትም እነዚሁ የአገዛዙ ወኪሎች ስለ መሆናቸው ዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። የአንዱን መሬት ለሌላው በመሸጥና፣ አንዱን ወገን በማስታጠቅ ከኋላ በመሆን ብጥብጡን ያስነሱት ክፍሎች እነማን እንደ ሆኑ እየታወቀ፣ ወደ ኦሮምያ ለመቀላቀል የሚጠይቁ ጎሳዎች ለዓመታት መልስ ባለማግኘታቸው ሁሉም አንድ ላይ ተዳምሮ እዚህ ደረጃ እንደ ደረሰ ለመረዳት ችለናል። አቶ በረከት በዚህ ሁሉ መረጃ ላይ ተኝተው “የአካባቢውና የመንግስት ኃላፊዎች ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ጎሳዎቹ ወደ ግጭት ሊያመሩ ችለዋል” ይሉናል። ህዝቡ ደግሞ “ችግሩ የባለሥልጣናት ነው። መጥተው አያነጋግሩንም፤ አያቀራርቡንም፤ ህዝቡ ሰላማዊ ነው” በማለት ይናገራል።

የጋሪ ጎሳ ሽማግሌዎች “አስቀያሚ ፖለቲካ” የሚሉት ይህ ችግር አሁን ተረጋግቷል ቢባልም ዋስትና እንደሌለ ነው የሚገልጹት። በስደት በተጠለሉበት ቦታ ህጻናት በብርድና በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው። ተመለሱ ቢባሉም “የት እንወድቃለን? ንብረታችን የለም” የሚሉ ወገኖችን መልሶ ስለማቋቋም የተነገረ ነገር የለም። የጋራ ንቅናቄያችን ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነና አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባው አበክሮ ይገነዘባል።

የጋራ ንቅናቄያችን ዘወትር እንደሚለው ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ መልስ ሊያገኝ የሚችለው ከጎሰኝነት ይልቅ ሰብዓዊነትን በማስቀደም አዲሲቷን ኢትዮጵያን መመሥረት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው ከዛሬ አርባ ዓመት ጀምሮ በተለይ በግራው የኮሙኒስት አመለካከት የተዘራውና “የራስን ዕድል በራስ በመወሰን” ስብከት የተጠመቀው የጠባብነትና የጎሰኝነት አስተሳሰብ ለአገራችን ችግር ያመጣው ምንም መፍትሔ የለም፡፡ በሌሎች መቃብር ላይ የራስን አመለካከት ለመመሥረት መፈለግም ሆነ ማቀድ አብሮ የመኖርና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ስላልሆነ ሰብዓዊ የሆነ ሁሉ አጥብቆ ሊቃወመው የሚገባ ነው፡፡ አገራችን ለራሷ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መትረፍ የምትችል ሆና ሳለ በጎሣና በመንደር እየጠበቡ ራስን ከማሳነስ ይልቅ በሰብዓዊነት ደረጃ በማሰብና አስፍቶ በማቀድ የታላቅነት መለያ የምትሆነውን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት እንዘጋጅ፡፡ እስካሁን የተደረገው የእሳት ማጥፋት ሥራ ይበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ እሳቱ እንዳይነሳ እናድርግ፡፡

ፈጣሪ ለእነዚህ የተጎዱ ወገኖቻችንን በምህረቱ ይጎብኛቸው፤ ለእኛም ልቦና ይስጠን!

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ለዚህ ደብዳቤ ምላሽም ሆነ ለተጨማሪ መረጃ ለአኢጋን ሚዲያና ሕዝብግንኙነትን ግብረኃይል ([email protected]) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን (www.solidaritymovement.org) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ፡፡

One Response to የቦረና አካባቢ ግጭትና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መፍትሔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>