መተካካት ወይስ መተካት ፣ ድርድር ወይስ ለውጥ

August 1, 2012

ተስፋዬ ታደሰ

ሃምሌ 24 ቀን 2004 (July 31, 2012)

ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ ሞቱ ከተባለ ይሀው ሁለት ሳምንት አለፈ። አደባባይ ከወጡ፣ ለህዝብ በቴሌቪዥን ከታዩ የአርባቸው ቀን ወጣ። ለነገሩ ከህዝብ ከተለዩ፤ ህዝብ ከጠላቸው ሃያ አንድ አመታቸው። በኢህአዴግ/ህወሃት በኩል መለስን እንዴት “በመተካካት” ስልታቸው እንደሚቀይሩ ሳያሳውቁ ዝም ብለዋል። የኢህአዴግ/ህወሃት ቁንጮዎች ለስልጣን ድርድር ላይ ናቸው። በእነዚህ ሳምንታት የተቃዋሚ ሃይሎች ተባብረው ለመስራት ወስነው፤ እኛንም ተራ ኢትዮጲያዊያንን የህወሃትን “ስርአት ለመተካት” ጥሪ ያቀርቡልናል ብለን ብንጠብቅም፤ በእነሱም በኩል ውሳኔ ላይ ጭጭ፤ ጭጭ ሆኗል። ለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ውሳኔና ተግባር እየጠበቀ ነው።

በውጭ አገር ያለን ኢትዮጲያዊያን ግን ዝም አላልንም። በእነዚህ ሁለት ሳምንታት አያሌ ግለሰቦች ብዙ ጽሁፎችን አቅርበዋል። መ/አለቃ አያልሰው ደሴ፤ ፕ/ር አለማየሁ ገብረ ማርያም፤ አቶ ተኮላ ሃጎስ፤ አስራደው (ከፈረንሳይ)፤ አለልኝ ሲሳይ፤ ፕ/ር መሳይ ከበደ እና ሌሎችም እጅግ ትምህርት የሚሰጡና ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን አካፍለውናል። መ/አለቃ አያልሰው ደሴ በኢሳት ቴሌቪዥን፣ ፕ/ር አለማየሁ ለቪ. ኦ. ኤ. የሰጡት ቃለ ምልልስና የሁለቱንም ጽሁፎች መደመጥ፣ መነበብ ያለባቸው ናቸው። ታዲያ እነዚህ ጽሁፎች የሚያጠነጥኑት በኢህአዴግ/ህወሃት መሪውን በመተካካት ስልቱ በመምረጥ ባለበት ጊዜ ውስጥ፣ የተቃዋሚ ሃይሎች ተባብረው መስራት እንዳለባቸውና ለመተባበር በወሰደባቸው ጊዜ የተሰማቸውን ቅሬታ የሚገልጽ ነው። የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች በአስቸኳይ ምን ማድረግ አለብን ለሚለው ጥያቄ፤ እኔም አንዳንድ ሃሳቦችን ለመሰንዘር እሞክራለሁ። በአሁኑ ወቅት ዝም ማለት ከሃገር ወዳድ አይጠበቅም።

በኢህአዴግ/ህወሃት በኩል ዝምታን የመረጡት በመካከላቸው ያለውን የስልጣን ፉክክር እስኪጨርሱ ነው ይባላል፤ ሲመረመሩትም ይመሰላል። ለስልጣን ፉክክሩ ተወዳዳሪዎች የህወሃት ዋና አባላት ስለሆኑ፤ የህወሃት መንግስት/ስርአት እያልኩ በጽሁፌ እጠቀማለሁ። አቦይ ስብሃት ነጋ ለእዚህ የስልጣን ውድድር ዋና አደራዳሪ/መዳቢ እንደሆኑ ይነገራል። የእኝህ የትግራይ ማኒፌስቶና የማሌሊት አባት፤የኤርትራ ጥቅም አስከባሪ፤ የኢትዮጲያን መሪ ለመሾም ትልቅ ሚና መጫወት መቻላቸው እንቆቅልሽ ነው። የህወሃት የመገናኛ አገልግሎት ተቋማት ኢትዮጲያዊያንን ከምንም ባለመቁጠር ስለ አገራችን አመራር ምንም መረጃ አልሰጡም። ቀሽሞቹ አይጋፎርምና ትግራይ ኦንላይን ሳምንት ያለፈበት ቃለምልልስ እያቀረቡና የኢሳት ሬድዮን ስለመለስ ሞት የዘገበውን እያስተባበሉ ነው። መ/አለቃ አያልሰው ፤ ፕ/ር አለማየሁና አቶ ተኮላ ሃጎስ ግን የኢትዮጲያ ህገመንግስት ጎደሎ እንደሆነና በአጠቃላይ ህወሃት የአገራችንን አመራር እንደሚወስን አስረድተውናል። አቶ ሰዬ አብርሃ የአንድ ሰው ህመምና ሞት እንደማያስደስታቸው ገልጸዋል። አብዛኛው ኢትዮጲያዊ እንደዚሁ በመለስ ሞታቸውም፣ ፍርድቤት ባለመቅረባቸውም ያዝናል። ሟርተኛ ያሉንን ሃዘን ሲቀመጡ እንደርሳቸዋለን፣ በኢትዮጲያዊነታቸው እናጽናናቸዋለን። መሪውንና ዋናውን የፖሊሲ ቀራጩን ያጣውን፣ የህወሃትን አምባገነን ስርአት ለማስወገድ ግን እንታገላለን። ለማንኛውም የትኛው የህወሃት ቁንጮ የኢትዮጲያ መሪ እንደሚሆን በቅርቡ እናውቃለን። ህዝባችን ግን ይህንን መሪ ስላልመረጠው፣ ህጋዊ ስልጣን እንደሌለው ያውቃል። ይህንን መሪ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ “ለመተካት” ህዝባችን ይታገላል።

የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ግን በማይገባ ሁኔታ ጊዜ አባክነናል። እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም፣ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስንመለከት የተደረጉት ጥረቶች ዝቅተኛ ናቸው። ሃገራችን ከአለቸበት አደጋና ከአጋጠማት ጥሩ የለውጥ እድል ጋር ሲወዳደር ጥረቶቹ በቂ አይደሉም። በቅርቡ፤ ከጥምረትና ኦነግ፣ ከሸንጎ፣ ከአንድንት የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ፣ ከሽግግር ም/ቤት የተስጡት መግለጫዎች ጥሩ ጅምሮች ቢሆኑም፣ ለለውጥ የትግል ፈር ለመቅደድ አይበቁም። እኛ ተራ ኢትዮጲያዊያን በእነዚህና በሌሎች ድርጅቶችና የትብብር መድረኮች ላይ ጫና ማድረግና ተባብረው ጠንካራ የለውጥ ፈላጊዎች ስብስብ እንዲፈጥሩ መወትወት አለብን።

ውጭ አገር ያለን ኢትዮጲያዊያን ይህንን ጫና መፍጠር የምንችለው በመጀመሪያ የአንድ የሚስማማን የፖለቲካ ድርጅት ወይም የሲቪክ ማህበር አባል ሆነን የነቃ ተሳትፎ ስናደርግ ነው። የድርጅት አባል መሆንና መሳተፍ፤ የድርጅቱን ፖሊሲና የትግል ስልቱን ለማወቅና ድርጅቱን ለማጠናከር ይረዳናል። ከዳር ሆኖ ፖለቲካን በሩቁ፤ ሃገራችን ግን፣ ይሄ ችግር ያ ችግር ገጠማት እያሉ የማውሪያ ጊዜ አሁን አይደለም። በእውቀታችን፤በጉልበታችን፣ በጊዜያችንና በሃብታችን ትግሉ ውስጥ በመግባት መሳተፍ አለብን። ይህንን ስናደርግ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማጠናከር እንችላለን። አባል የሆንባቸውን ድርጅቶች ላይም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጫና መፍጠር እንችላለን።

ድርጅቶች ለምን መተባበር ጊዜ ወሰደባቸው ለሚለው ጥያቄ መነሻ ምክኒያቱ ሊሆን የሚችለውንና መፍትሔውን መ/አለቃ አያልሰው ደሴ በኢሳት ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበውታል።

“ለውጥ ፈላጊው ክፍል፤ በኢትዮጲያ የወቅቱ ሁኔታ፣ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የማንም የተናጠል ድርጅት ጥቅም እሚጠበቅ የለም። ማንም ድርጅት አሁን ባለው የኢትዮጲያ ሁኔታ አስጠበቅዋለሁ የሚል የድርጅት ጥቅም እንደሌለው ሁላችንም መረዳት ያለብን ይመስለኛል። ስለዚህ ከድርጅትና ከአካባቢ ማዶ አይተን፤ በጋራ መጥተን፣ ይሄ ብሔራዊ አለኝታ የሚሆነውን ለመመስረት፣ ብሔራዊ አጀንዳ ለመቅረፅ ጥረት መደረግ አለበት።”

እዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው አንድ ድርጅት የትብብሩን አጀንዳና መዋቅር ላይ የበላይ መሆን መሞከር እንደሌለበት ነው። እያንዳንዱ ድርጅት ወይም ስብስብ በሃገርና በውጭ አገር ባለው መዋቅርና ጥንካሬ፣ በተቃዋሚነት ያሳለፈበት ጊዜ፣ እወክለዋልሁ ከሚለው ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ብዛት፣ በጋራ የሚሰሩ ጥቂት ድርጅቶች ያሉት ስብስብ በመሆኑና በሌሎች ምክኒያቶች የበላይ ለመሆን መሞከር የለበትም።

የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች እውነተኛና ዘላቂ የጋራ ትግል ማካሄድ የሚችሉት፤ በሚስማሙበት አቋም አብረው እየሄዱ፣ የሚያለያያቸውን ፖሊሲ የኢትዮጲያ ህዝብ እንዲወስንብት ሲስማሙ ነው። የህዋያሃት አምባገነን መንግስት መተካት እንዳለበት ሁሉም የለውጥ ፈላጊ ክፍል ይስማማል። የኢትዮጲያ ህዝብ ተወካዮቹንና መሪውን በዴሞክራቲክና በነጻ መንገድ እንዲመርጥ ሁሉም ይስማማል። በነጻ ፕሬስ፤ ገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ መከላከያ ሃይል፣ ፖሊስ/ጸጥታ አስከባሪና የምርጫ ቦርድ ሁሉም ይስማማል። ልዩነት ያለው፤ በብሔር ብሔረሰብ፣ በመሬትና እነዚህን በመሳሰሉ ፖሊሲዎች ነው። እነዚህን የፖሊሲ ልዩነቶች፣ የኢትዮጲያ ህዝብ የትኛው እንደሚስማማው እንዲመርጥ ትተው፣ በሚያስማማቸው፣ የስርአት የመተካት ትግል በአስቸኳይ መጀመር አለባቸው። የትግል ስልቱም መሆን ያለበት፤ አንዱ ድርጅት እስካሁን ሲከተለው የቆየውን ትቶ በጋራ ውሳኔ ይመራ ሳይሆን ትግሉ በተቀናጀ መንገድ በማካሄድ ነው።

ከላይ የዘረዘርኳቸውን፤ አንድነት፣ ተግባር፣ ለውጥ የሚል መነሻ ሃሳብ ያላቸው ተቋማት፤ የኢትዮጲያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ ሸንጎ፣ ጥምረትና የኦነግ (አንድ ወገን) ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነዚህ የጋራ ትግል ጅምሮች ማን ጋባዥ ማን ተጠሪ ይሆናል ሳይባል፣ በሃሳባቸው ብቻ ተፈርጀው መደገፍ ያለባቸው ናቸው። የሽግግር ም/ቤቱ አመራሮች የቀረብነው ባዶ ነጭ ወረቀት ይዘን ነው ብለዋል፣ ግን የሚያልሙትን የጋራ ትግል ሃሳብ ነድፈዋል። ጥምረትና ሸንጎ፣ ሌሎች ድርጅቶችም ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ፣ መሪ ማለት በእዚህ የታሪክ አጋጣሚ ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎኑ በማሰለፍ አመራር መስጠት ነው። ስለዚህ የጋራ ትግሉ በአስቸኳይ መጀመር አለበት። አለበለዚያ የሰዎችንና የድርጅቶችን ጀርባ ስንመረምር፤ አጋር መሆን የሚገቡን ድርጅቶችና ሰዎች ላይ ወደ ጎን ስንተኩስ፣ ከፊታችን ያለው ህዋሃት መሪውን በመተካካት እንዳቀደው ሃምሳ አመት ይገዛናል። ዶ/ር አረጋዊ በኢሳት ሬድዮ የሰጡት ቃለምልልስ ይሄንን ጉዳይ በዝርዝር ያቀርበዋል።

ህዋሃት ራሱን እንደ የመረጋጋት ሃይል አድርጎ ያቀርባል። የሙስሊም ወንድሞቻችንንም፣ “አክራሪነትን ለመዋጋት” በሚል ሽፋን ሃይማኖታቸውን ተዳፍሯል። በእኔ ግምት ህዋሃት ዋሃቢዝም አሳስቦት ሳይሆን፣ የአረብ ጸደይ (Arab Spring) ኢትዮጲያ እንዳይገባ ታማኝ የሃይማኖት መሪዎች ከወዲሁ ለማስቀመጥ ነው። አምባገነን ራሱን የሚያዳክመው፣ በኋላም የሚወድቀው፣ በእንደዚህ አይነት ምክኒያት፣ ስውን በማናለብኝነት ሲያንገላታና ሃይማኖቱን ሲደፍር ነው። በሙስሊም ወንድሞቻችን የተነሳው፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ እንዳሉት “የለውጥ እርሾ” ሰለ ሰላማዊ ትግል ትልቅ ትምህርት ያስተምራል። የክርስትያኑም ህዝብ ለሙስሊም ወንድሞቻችን በሃገር ውስጥ የሰጠው ድጋፍ፣ የኢትዮጲያ ህዝብን አርቆ አሳቢነት ያሳያል። በውጭ አገርም ማርች ፎር ፍሪደም (March for Freedom) እና ነጃሺ የፍትህ ካውንስል (Nejashi Justice Council) የሚያደረጉት ትብብር ፈር ቀዳጅ ነው። የጋራ ትግልን ጠቃሚነትና ለውጤት ባለቤት ያለውን ተስፋ ያሳያል። የኢትዮጲያ ህዝብ ትዕግስተኛነቱን፣ አርቆ አሳቢነቱንና ቁርሾ እንደማይጠቅመው ለማወቁ ብዙ ጊዜ አሳይቶናል። የቀይ ሽብር ሃላፊ የነበረው ለገሰ አስፋውን ከሃገር ሊኮበልል ሲል ሁለት ጊዜ ይዞ ለመንግስት ያስረከበው፣ ፍትህ የጠማው ንጹህ ወገናችን ነው። በቀል ስለማይፈልግ ነው እንጂ “ለገሰን” ያኔ አይምረውም ነበር። በነገራችን ላይ ለገሰ አስፋውና ለገሰ ዜናዊ ሃገራችን ኢትዮጲያ ላይ ትልቅ ወንጀል የሰሩ ናቸው።  ለገሰ ተብለው ክፉዎች።

የጋራ ትግልን ጠቃሚነት ሁሉም ሲናገር፣ አንዳንዶች ደግሞ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ያሳስባቸዋል። ሀርማን ኮሀን ሌ/ኮለኔል መንግስቱን በማስወጣት፤ ቪኪ ሃድልስተን በቅንጅት ጊዜ፣ ጀንዳይ ፍሬዘር በሶማሌ አልሸባብን ለመውጋት ያደረጉት ተግባራት ይህንን ጥርጥሬ እውነት ያስመስለዋል። ሲ. አይ. ኤ. ስለመለስ ሞት ያውቃል፣ አሜሪካ አዲሱን የህዋሃት መሪ ማን መሆን እንዳለበት ተጽእኖ ያደርጋል ይባላል። ዋናው ቁም ነገር ግን የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች ጠንካራ ብንሆንና ትግል ብንጀምር ኖሮ፣ አሜሪካ የረጅም ጊዜ ወዳጃቸውን ሙባረክን እንዳደረጉት ለቀህ ውጣ ይሉ ነበር። በእኔ ግምት የህዋሃት የስልጣን ድርድርና መተካካት ውስጥ አሜሪካ የለችበትም። ቪ. ኦ. ኤ. በመጀመሪያ አቦይ ስብሃትን ቃለ ጥያቄ ማቅረቡ ግን አዲስ አበባ ያሉ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ለቪ. ኦ. ኤ. ምን ቱስ ብለዋቸው ይሆን ያስብላል። ለእግዚአብሔር ጸሎት የምንጀምርበትን ቃል፣ እኚህ ሰይጣን ሽማግሌ (ወልደስላሴ ነጋ) ለራሳቸው “ስብሃት” ብለው የሜዳ ስም ማውጣታቸው አይገርምም?

ድርድር ሲባል መ/አለቃ አያልሰው እንዳሉት እኔም “በአገዛዙ ውስጥ ያሉ ዘላቂ የኢትዮጲያን ጥቅም ለማስቀደም የሚፈልጉ ይጠፋሉ ብዬ አላስብም”። አቶ ሙሉጌታ ሉሌን ለመጥቀስ “ራስ መስፍን መጋቢት 1966 ላይ የኢትዮጲያ ህዝብ ደም ያለአግባብ ብዙ ጊዜ ፈሷል ብለው ነበር”። ከደም መፋሰስ ስለሚያድነን፤ ያድርግልን እንጂ ከእነዚህ የአገዛዙ ቡድኖች ጋር ለመደራደር የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች ዝግጁ ይመስሉኛል። በቅንጅት ጊዜ ከተማሩት በመነሳት፣ በመሰረታዊ ሰብአዊ መብታቸው ግን አይደራደሩም። የኢትዮጲያ ህዝብ ተወካዮቹንና መሪውን በዴሞክራቲክና በነጻ መንገድ በመምረጥ፣ በነጻ ፕሬስ፤ በገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ መከላከያ ሃይል፣ ፖሊስ/ጸጥታ አስከባሪና በምርጫ ቦርድ አይደራደሩም። በአገራችን እብድና ሰካራም የልቡን ይናገራል ይባላል። የኤርትራው መሪ፣ ብጻይ/ጽሉል ኢሳያስ ስለ 97 ምርጫ “ወያኔ እኳኳላለሁ ብላ አይኗን ጠነቆለች” አሉ ይባላል። ስለዚህ ህዋሃት ሁለተኛ እንደ ድርጅት፤ ነጻ ምርጫ፣ ሁኔታዎች ካላስገደዱት በስትቀር አይፈቅድም። ድርድር ሲደረግ ደግሞ የሃይል ሚዛን የድርድሩን ውጤት ይወስናል። የህወሃትን ድርጅታዊ ጥንካሬ (ከመንግስት ካዝናና ኤፈርት) በህዝባዊ ሃይል መመከት አለብን። ለደሞዝ ብሎ አባልና ሰላይ የሆነ ህዋሃትን አንፈራም። አሁንም ዋናው ነገር የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች ጠንካራ መሆንና ሕዝብን ከጎናቸው በማድረግ፣ ህወሃት ወደ ድርድር እንዲመጣ ለማስገደድ መሞከር ነው።

የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች በአንድነት የጋራ ትግል በማድረግና የለውጥ ራእይ በማሳየት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ፣ ስርአቱን መተካት ይችላሉ። ይህ ካልሆነ ግን ህወሃት የውስጥ የስልጣን ድርድር በማድረግ መሪውን “መተካካት” ያስፈጽማል። የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች ምርጫችን በህወሃት ውስጥ የስልጣን ድርድር እና በለውጥ መሃል ነው።ምርጫችን በመተካካት እና በመተካት መሃል ነው። የለውጥ ፈላጊ ክፍሎች ባለንበት የታሪክ አጋጣሚ የቀረበልን ጥያቄ በአንድ “ካ” ፊደል ይመሰላል። ከመተካካት አንድ “ካ” ፊደል “ካ” አርገን ጥለን ስርአቱን ለመተካት መተባበር አለብን።

ለአስትያየት (በጎውንም፣መጥፎውንም) በ [email protected]. መይሉኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>