በጣም አጭር “ልቦለድ”፤ “ታማሚው”

July 24, 2012

በጣም አጭር “ልቦለድ”፤ “ታማሚው”

አቤ ቶኪቻው

Posted on

ታመዋል አይናቸውን በመከራ ገለጥ አድርገው ዙሪያቸውን ለመመልከት ቢሞከሩ በጉሉኮስ ገመድ ተተብትበው አዩ። “ታስሬ ነው ያለሁት፤ ወይስ ህክምና ላይ ነኝ!?” የሚል ጥያቄ በአዕምሯቸው መጣ። ግራ ቢገባቸው “ኦ መድሃኒያለም!” አሉ…

ይሄን ጊዜ መድሃኒያለም በበርሃን ታጅቦ ከኋላው በርካታ መነኮሳትን አስከትሎ መጣ። “ውይ ጌታዬ እኔ ዘንድ ነው ያለኸው ወይስ እኔ ነኝ አንተጋ ያለሁት…?” አሉ ሞተው ይሁን በህይወት እያሉ ይዩት ተደናግሯቸው።

መድሃኒያለምም ለጠየቁት ምላሽ ሳይሰጣቸው፤ “እነዚህን ታውቃቸዋለህ!” አላቸው ወደ መነኮሳቱ እያመለከተ፤ “አዎ ጌታዬ እነዚህማ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው የዋልድባ መነኩሴዋች አይደሉም እንዴ!?” አሉ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው።

ሳቀባቸው መድሃኒያለም። ከት ብሎ ሳቀባቸው። ሳቁም  የሰማይ ማጉረምረም የመብረቅ ብልጭታን ያህል አስደነገጣቸው። ይሄኔ ሃሳባቸውን ሊለውጡ ፈልገው፤ “ማለቴ…” ብለው ጀመሩ፤ መድሃኒያለም ግን ፊቱን አዞረባቸው። እሳቸውም ቢሰማም ባይሰማም “ማለቴ…” ብለው ሊናገሩ ሲሉ እንደ አፈ ጉባኤ መዶሻ የያዘ አንድ ትልቅ ሰውዬ “ሰዓት ሞልቷል” ብሎ በያዘው መዶሻ ግንባራቸውን ነረታቸው። “አረ የጀመርኩትን እንኳ ልጨርስ…” ለመከራከር ቢሞክሩ “ሰዓት ሞልቷል” ብሎ አሁንም በመዶሻው ደገማቸው። በሃሳባቸው “አንድ ደቂቃ አንኳ…” ብለው ሲያስቡ “ስነስርዓት ሰዓት ሞልቷል ብያለሁ!” ብሎ ገላመጣቸው። “ማሰብም አይቻልም ማለት ነው…?” ብለው ሊያስቡ ፈልገው… “የአፈ ጉባኤውን” ጩኸት እና መዶሻ ፈርተው ዝም አሉ! በመዶሻ የተመታ ግንባራቸውን አሟቸዋል። ማሸት እየፈለጉ አቅም ግን ቸግሯቸው ተዉት!

መናገር ተከለከልኩ፤ እሺ መናገሩስ ይቅር ማሰብ እንዴት እከለከላለሁ? በጊዜዬ ሁሉ ከልካይ እኔ አልነበርኩምን…? ተራዬ አከተመ በሰፈርኩት ተሰፈርኩ ማለት ይሆን…!?

“ያ አላህ…” አሉ ነገሩ ግራ ግብት ብሏቸው። ለካስ አላህም እዝችው ቅርብ ነበርና… ከተፍ ብሎ ፊት ለፊታቸው ቆመ። ከበስተኋላው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች “አላህ ዋክበር… አላህ ዋክበር… አላህ ዋክበር…” ይላሉ። “እነዚህን ሰዎች ታውቃቸዋለህ…?” ብሎ አላህ ጠየቃቸው፤ “አዎ አሻበሪዎች… አክራሪዎ…” ገና ቃሉን ሳይጨርሱት አከርካሪያቸውን ቀስፎ ያዛቸው።

ቅድም አፈ ጉባኤው አናታቸውን በመዶሻ የደበደባቸው ራስ ምታት ሳይለቃቸው አሁን ደግሞ “ገና “አክራሪዎች…” ብለው ሳይጨርሱ፤ አከርካሪያቸው ተያዘ… አላህም ትቷቸው ሄደ። “አላህ ዋክበር!” የሚለው ድምፅ ግን እያቃጨለባቸው ነው። አልቻሉም…! ተኙ።

ነገሩ ቅዠት ይሁን እውነት እያንሰላሰሉ ሳለ ደሞ ያ “አፈ ጉባኤ” ማንሰላሰልም አይቻልም እንዳይላቸው ፈሩ። እየፈሩ እና እያንሰላሰሉ ተኙ።

ሲነቁ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና ላይ ደረሱበት። አንድ ባለስልጣን ወዳጃቸው ስለ እርሳቸው እየተናገሩ ነበር። በልባቸው “ዛሬም እኛው ነን የምንመራው ተመስገን…!” ሊሉ ፈልገው ከአላህም ከመድሃኒአለምም መጣላታቸው ታወሳቸውና ማንን እንደሚያመሰግኑ ግራ ገባቸው።

የባለስልጣኑን መግለጫ ሲሰሙ ግራ ተጋቡ “በጣም በመልካም ጤንነት ላይ ነው” ብለው ስለ እርሳቸው ሲናገሩ፤ “ይሄ ሰውዬ ስለ እኔ ነው ስለሌላ የሚያወራው?” ሲሉ ራሳቸውን ጠየቁ። ወድያውም በሃሳባቸው “መልካም ገፅታ ግንባታ መሆኑ ነው!” አሉና፤ እንባ ተናነቃቸው። “እኔ በጣር ተይዤ ፀልዩለት እንደማለት እንዴት ደህና ነው!” ይባላል ብለው ጮክ ብለው ሊናገሩ ፈልገው አቅም አነሳቸው።

ሳያስቡት አንድ የድሮ ግጥም ታወሳቸው

“አንተም ጨካኝ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ

እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደበህ”

19 Responses to በጣም አጭር “ልቦለድ”፤ “ታማሚው”

  1. Abdush Reply

    July 24, 2012 at 11:36 am

    Abe bertu tsinatun yistacu hulunm meswaitenet lemekfel tezegagu tigl kale mekerale by by

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>