ጥንታዊውና ታሪካዊው የዋልድባ ገዳም አሳዛኝ ሁኔታ

April 26, 2012

Click here for PDF

ዳግማዊ ቴዎድሮስ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ, 16/08/2004

ዋልድባ በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሃገር ሰሜን አውራጃ ከታዋቂው ራስ ዳሽን ተራራ ስር ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካው ገዳም ነው።ገዳሙ በስፋቱ በግምት የአንድwaldiba-ethiopia ወረዳ ስፋት ያክል እንደሆነ ይታወቃል። ገዳሙ ዙሪያውን በ4 ወንዞች የተከበበ ሲሆን፣በሰሜን የተከዜ ወንዝ፣በደቡብና በምዕራብ የዛሬማ ወንዝ፣በምስራቅ የማይለቨጣ ወንዝ የሚያዋስኑት ሲሆን በክረምት ጊዜ ሁሉም ወንዞች ስለሚሞሉ ሰው ሊሻገር አይችልም።የዋልድባ አዋሳኝ ወረዳውችም፣በምስራቅ የማይፀምሬ ወረዳ፣በደቡብ የአድርቃይ/ደባርቅ/ወረዳ፣በሰሜን ከተከዜ ማዶ የትግራይ አስተዳደር አካል የሆነው እንዳባጉና፣በምዕራብ የወልቃይት ወረዳ/በአሁኑ አዲረመፅ/፣በደቡብ ምዕራብ ቆላ ወገራ ወረዳ፣ ያዋስኑታል።ዋልድባ በኢትዮጵያ ካሉት ታላላቅ ገዳማት አንዱ ሲሆን በስፋቱ ግን ከሁሉም ገዳማት የሰፋና የተለየ ነው።

በታላላቅ ወንዞች ዙሪያ የተከበበው ዋልድባ በውስጡ ሶስት ታላላቅ ዋና ዋና ገዳማት ወይም የፆምና የፀሎት ቤተክርስቲያኖች አሉት እነሱም፣ዳንሻ ኪዳነምህረት፣አብረንታንት መድሃኒዓለም፣ሰቁኣር ኪዳነ ምህረት በመባል ይታወቃሉ።ገዳማቶቹ አንዱ ከአንዱ የተራራቁ ቢሆንም መንኩሳቱ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚሄዱት በእግር ነው በገዳሙ ውስጥ ምንም ዓይነት የመኪና መንገድ የለም እንዲኖርም አይፈቀድም የጉዞ እንስሳቶችም የሉም ፣ለምሳሌ ከሰቁኣር ገዳም ወደ አብረንታንት ገዳም ለመሄድ ሁለት ቀን የእግር ጉዞ ይፈጃል።በሁሉም ገዳማት በርካታ መነኮሳት የሚኖሩ ሲሆን በቅርብ በተገኘ የተጠጋጋ መረጃ በሰቁኣር ገዳም ወንድ 550 ሴት 250 የሚኖሩ ሲሆን፣በአብረንታንት ገዳም ወንድ 1950 ሴት 360 ሲኖሩ፣በዳንሻ ገዳም ወንዶች 730 ሴቶች 275 እንደሚኖኡ ታውቁኣል።በድምሩ በዋልድባ ገዳም ውስጥ ወንድ 3230 ሴት 885 የሚሆኑ መነኩሳት ይኖራሉ የሴትና የወንድ መኑኩሳት መኖሪያ የተለያየ ነው።

ገዳሙ እጅግ የተከበረና የተቀደሰ ለመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ያውቀዋል።ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኝ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ሁሉ በየአመቱ የሚከበረውን መጋቢት መድሃኒያለምን ለመሳለምና ለመሳል የሚመጣው ህዝብ እጅግ ብዙ ነው፣የምድሩ አለም በቃን ያሉ የኦርቶዶክ ሃይማኖት ተከታዮችም በብዛት የሚመንኑት በዚሁ የተቀደሰ ስፍራነው፣ከሁሉም የኢትዮጳያ ክፍለ ሃገሮች የሚኖሩ ሰወች ስሞት ዋልድባ ወስዳችሁ ቅበሩኝ ብለው ስለሚናዘዙ በኑዛዜያቸው መሰረት በጣም ብዙ ሙታን በየጊዜው አፅማችው በዚሁ ገዳም ያርፋል፣የመነኩሳት አፅምም የሚያርፈው በዚሁ በተቀደሰ ቦታ ነው።በገዳሙ ውስጥ ያለው የሃይማኖታዊ አስተዳደር የገዳሙን ቅዱስነት ይበልጥ ያሳየናል፣ በ4ቱም ወንዞች በተከበበው ገዳም ውስጥ እህል መብላት አይፈቀደም፣እንጨት መቁረጥም ሆነ የአካባቢን ፀጥታ የሚረብሽ ማንኛውም ነገር የተከለከለ ነው፣በገዳሙ ውስጥ ለመቅመስ የሚፈቀደው ቁኣርፍ የተባለ ምግብ ሲሆን አዘገጃጀቱም ያልበሰለ ጥሬ ሙዝ ተቀቅሎ ከደረቀ በሁኣላ ይፈጫል ሌላ ጫብሌ የተባለለ ከመሬት የሚጫር መራራ ስር እሱም ተቀቅሎ ይመለጥና ይደርቃል እንደገና ለ7ቀን ያክል ወራጅ ወንዝ ላይ ተነክሮ ከቆየ በሁኣላ ወጥቶ እንዲደርቅ ከተደረገ በሁኣላ ተፈጭቶ ከሙዙ ጋር
ይቀላቀላል መለኩሳናቱ በዚህ መልክ የተዘጋጀውን በየቀኑ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ብቻ አንድ እፍኝ እንዲቀምሱ ይደረጋል።

የዋልድባ ገዳም ዋናው የቅዱስ ቦታው እና እህል የማይበላበት በ4ቱ ወንዞች የተከበበው ይሁን እንጂ ከወንዞቹ ውጭም እህል ቤት የሚባሉ በዋነኛነት ጉልበት ያለው መነኮሳት የሚያለሙት መሬትና የእንስሳ ልማት አላቸው።ለምሳሌ አብረንታንት መድሃኒዓለም 3 እህል ቤት አሉት ማይለበጣ፣ደንደሮ፣ዋልቅ ሲባሉ፣ስቁኣር ኪዳነ ምህረት ደግም 2 እህል ቤት አላቸው ዛሬማና ማይግባ ይባላሉ፣ዳንሻ ኪዳነምህረትም በተመሳሳይ 3 እህል ቤት ኣላቸው።እዚህ ላይ የምንረዳው ገዳሙ ከዋናው የገዳሙ ክልል ውጭም ሰፊ የልማት መሬት እንዳለው ነው ምክንያቱም በወንዝ በተከለለው መሬት ውስጥ ምንም ዓይነት ልማት ማልማት አይቻልምና።

የዋልድባ ታሪካዊ አመሰራረትና ገድሉ

የዋልድባ አባቶች እንደሚሉን በ7ኛው ክ/ዘመን ተሳቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ጀምሮ እንደተመሰረተ አፈ ታሪክ ያወሳልናል።

ታሪኩ እንዲህ ነው፣ወሎ ውስጥ ሳይንት አካባቢ መድሃኒዓለም የሚባል ቤተክርስቲያን ነበር።እዚሁ ቤተክርስቲያን የጥምቀት ለት ጭፈራ ስለነበር ቄሶች ከህዝቡ ጋር አብረው እየጨፈሩ የቅዳሴውን ሰዓት አሳለፉት የቅዳሴ ሰዓቱ እንዳለፈ አንድ ባዕታዊ በድንገት መጥቶ እናንተ ቄሶች የቅዳሴውን ሰዓት አሳለፋችሁ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በብርቱ ተቀይሟል ሁላችሁም እየሩሳሌም ካልሄዳችሁ አትማሩም አላቸው።ከዚያም ቄሱም ህዝበ ክርስቲያኑም ህፃኑም ሴቱም ታቦቱን ተሸክሞ ሁሉም ወደ እየሩሳሌም ጉዞ ጀመረ ህዝቡ ታቦቱን ይዘው የተወሰነ መንገድ እንደጀመረ አንድ የሚያምር ልጅ በድንገት መንገድ ላይ አገኙትና ከመንገደኞቹ አንዱ አያችሁት ይህ ልጅ ማማሩ አለ ይባላል።ሳይንት በዚያው አማራ ሳይንት ተብሎ ስም ወጣለት/አማራ ማለት ያማረ/ከሚል ትርጉም ከልጁ የተወሰደ ማለት ነው።በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ወራቶችን ተጉኣዘ፣በመንገድም የሞተው እየሞተ ጉዞው ግን ወደ እየሩሳሌም ቀጥሏል።እስከ ጎንደርም ያ የሚያምረው የተባለው ልጅ በየቦታው እራሱን እየቀያየረ ብዙ ስሞች ለየአካባቢወች ወጥተዋል።ወደ መጨረሻው ህዝቡ ደባርቅ ሲደርስ ልጁ ሰውነቱ በጣም ስላብረቀረቃቸው ቦታውን ደባርቅ ብለው ጠሩት፣ሊማሊሞ ገደል ሲደርሱም ልጁ ለምልሞ ስለታያቸው ቦታውን ሊማሊሞ ብለው ሰየሙት፣ድብ ባህር ሲደርሱም ልጁ ወፍሮ አዩትና ድብ ባህር አሉት፣ዛሬማ ሲደርሱ ይህ ልጅ ዛሬማ መቸ ለቀቀን አሁንም አብሮን ኣለ በማለት ዛሬማ የሚል የወንዝ ስም ወጣ፣ይህን ሁሉ ጉዞ ካደረጉ በሁኣላ ዋልድባ ሲደርሱ ይህ ልጅ በጦር ወረወረና አንድ ዋልድባ የሚገኘውን ተራራ/ሸነቆረው/የነደለው ቀዳዳ አሁንም አለ ይባላል፣ያ የተነደለ ተራራም ስሙ ሰቑኣር ሰነቆረ ከሚል የተሰጠ ስም ነው፣መጨረሻ እዚያው ገዳሙ ውስጥ አሁን አብረንታንት እየተባለ ከሚጠራው ገዳም ሲደርሱ ያ የሚያምረው ልጅ ለህዝቡ ራሴን እየቀያየርኩ የመጣውት እኔ አምላካችሁ ነኝ አብረን አለን አላቸውና ቦታውም አብረንታንት ተባለ፣ህዝቡም አንተ እየሱስ ክርስቶስ አይደለህም ልታሳስተን ነው አሉት እሱም መሆኑን በድጋሜ ነገራቸው እየሱስ ክርስቶስ መሆንህን ለማመን እንደገና እየሩሳሌም መወለድህን አሳየን አሉት እሱም እንደገና መወለዱን በታምዕራቶቹ አሳያቸው ህዝቡም አመነ።አሁን ድረስ እዚያው መስቀሉ፣ማይዮርዳኖስንና ሌሎችም ምልክቶችን ፈጥሮ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ ሳሙኤል ቃል ኪዳን ሲሰጣቸው ይህ የዋልድባ ገዳም ነው፣ዋልድባ እህል አይበቅልበትም ሃጢያትም አይሰራበትም እዚህ የተቀበረ ሰው መንግስተሰመያትን አወርሳለሁ ዋልድባ ዳግማዊ እየሩሳሌም ትሁን ብሎ ጌታችን ቃል ኪዳን ገባላት።አባታችን አቡነ ሳሙኤልም እየሱስ ክርስቶስ ሆይ ያልተጠመቀና አንተን ያላመነ እዚህ ቢቀበር ሊፀድቅ ነው ወይ?ሲል ጥያቄ አቀረበ ጌታችንም ሲመልስ እኔ ያልፈቀድኩለትና ያንተ ወዳጅ ያልሆነ/የቅዱሳን ወዳጅ ያልሆነ/ከዚች ቅድስት ምድር ሊቀበር አይችልም ክርስቲያኑም ቢሆን 40 ዓመት እዚህ ቢቀመጥ ካልፈቀድኩ ሲሞት አንድ ቀን ሲቀረው ከቅድስቱ ቦታ ይወጣና ይሞታል ብሎ ቦታውን ባርኮ ከህዝቡ ጋር ዋልድባ ወስጥ ትንሽ በእግሩ እንደሄደ ተሰወራቸው አባቶች እንደሚሉት ጌታችን እየሱስክርስቶስ የሄደበት ከዋልድባ እስከ እየሩሳሌም ውስጥ ለውስጥ ዋሻ አለ ተብሎ ይታመናል። ዋልድባ በዚህና ከዚህም በላይ በሰፋ ሃይማኖትዊ ታሪክ የተመሰረተ ሲሆን በውስጡም ጥንታዊነት ያላቸው የብራና መፅሃፍት፣ልዩ ልዩ ጥንታዊ መስቀሎችና ሌሎችም የሃይማኖታችን የማንነት አሻራ የወደቀበት ታሪካዊ ገዳም ሲሆን በውስጡም እስካሁን ድረስ የቅስና ትምህርት ተጠናክሮ ይሰጣል።

ወያኔ የአገራችን ታሪካዊና የማንነታችን አሻራ የሆኑ ሃብቶቻችን ማውደም ከጀመረ ውሎ አድሯል፣ዛሬ የአገራችን አቢያተ-ክርስቲያናት በውስጣቸው የነበሩትን ታቦተ ፅላትና የቤተ-ክርስቲያን ሃብት ንብረት በታቦት ሻጮች የወያኔ ካድሬ ቄሳውስቶች የሚፈፀመው ዘረፋ ፀሃይ የሞቀው ሁኗል፣ሁሉም የአገራችን ቤተ-ክርስቲኣናት ዛሬ ራቁታቸውን ቀርተዋል።ወያኔ ቢተ-ክርስቶያንን የማጥፋት ተልዕኮውን አሁን ደግሞ በገዳማት አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

ከላይ እንደገለፅኩት የዋልድባ ገዳም በአገራችን ካሉት በታሪካዊነቱም በታምርነቱም እጅግ የላቀው ነው።የመለስ ዜናዊ ስርዓት ይህንን ገዳም ለማርከስ ያደረገውን ጥፋት እንመልከት::

ወያኔ እሱ የማይፈልገውን ነገር ለማጥፋት የሚዘይደው ዘዴ ያን የማይፈልገውን የሚመስል በእሱ አስተሳሰብ የተስማሙ ሰወችን በማደራጀት የህግ ከለላ በመስጠት የፈለገውን ማስፈፀም ነው፣፣ለዚህም በፖለቲካ ፓርቲወች የተከተለውን መመልከት ይቻላል የዶ/ር መራራ ጉዲናን ኦብኮን ለማጥፋት ሌላ ኦብኮ አቁኣቁኣመ፣አረና ትግራይን ለማጥፋት ሌላ አረና ፈጠረ፣ቅንጅትን ለማጥፋት ሌላ ቅንጅት ፈጠረ..እንደዚህ እያለ ይቀጥላል፣፣በዋልድባም የፈፀመው ይህንኑ ነው።ከ1990 ዓ/ም ጀምረው ከትግራይ ለመነኩሳትነት ወደ ዋልድባ ሰወች ተላኩ እነኝህ መለኩሴ ነን ባዮች በገዳሙ ውስጥ ሁነው ገዳሙ እንዴት ወደ ትግራይ ሊወሰድ እንደሚችልና የህወሃት ፍላጎት ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሴራቸውን ሲያሴሩ ከቆዩ በሁኣላ በ1992ዓ/ም ሌላ ከወልቃይትና አካባቢው ሰፋሪ ሁነው ከመጡ ትግሬወች በተውጣጣ እዚያው ዋልድባ ገዳም ውስጥ አብረንታንት መድሃኒያለም የሚባል ቤተክርስቲያን እንመሰርታለን አሉ፣፣የገዳሙ መነኩሳትም ለምን መድሃኒያለም እያለ ሌላ ለምን አስፈለገ ሲል ቢጠይቅም የወያኔ ድጋፍ ይዘው በሃይል በዚሁ ዓ/ም አብረንታንት ገዳም ውስጥ ሌላ መድሃኒያለን ሰሩ።በ1992 መጋቢት መድሃኒያለም የአመቱ ክብሩ ስለነበረ ብዙ ህዝብ ከየአገሩ መጥቶ ስለነበርና በሁኔታው ህዝቡ ተናዶ ስለነበር ሆ ብሎ የወያኔውን ቤተክርስቲያን አፈራረሰው።እንደሰማውት ሰው ለበረከት እያለ አንዳንድ ደንጋይ/እንጨት ብቻ/አነሳ በዚህ ህዝባዊ ቁጣ የወያኔ እቅድ ቢከሽፍም ከባዕለ ክብረቱ በሁኣላ የወያኔ ፀጥታ ገዳሙን በመክበብ ሁኔታውን ቀስቅሰው ቤተክርስቲያኑ እንዲፈርስ አድርገዋል ያላቸውን አባቶች ክመነኑበት ገዳም በሃይል እያሰረ ወደ ማይፀምሬ ወስዶ አሰራቸው ይህንን ያዩና የሰሙ የገዳሙ መነኩሳት ሴቱም ወንዱም በእግራቸው ወደ ማይፀምሬ ሂደው ያሰራችሁኣቸውን መነኩሳት ከፈታችሁ ፍቷቸው ያለበለዚያ እኛንም አብራችሁ እሰሩን ብለው እምቢ አሏቸው ወያኔ ለማስፈራራትና ለመከፋፈል ቢሞክርም መነኩሳቱ አንድ ሆኑ።መለኩሳቱ ለህይወታቸው ችግር አልነበራቸውምና ወያኔ ደጋግሞ ቢያስፈራራም ሊበገሩለት አልቻሉም።በመጨረሻም እርቅ አድርጉ ብሎ በእርቅ እንዲስማሙ አደረገ፣፣እርቁም ከገዳሙ የሚገኘውን የስለት፣የልማትና ከበረከት የሚገኘውን ገቢ ለትግራዮቹ ለማካፈል በቀረበላቸው ሃሳብ መሰረት ተስማሙና በዚህ መነኩሳቱም ወደ ገዳማቸው ገቡ።እንግዲህ ይህ ሁኔታ በተፈፀመ 10 ዓመት ሳይሞላው ነው በዚሁ ታሪካዊ ገዳም ላይ ዛሬ ሌላ የጥፋት ተንኮል የተጠነሰሰው፣ይሀውም ሰሞኑን በስፋት እንደሰማነው የዛሬማን ወንዝ በመገደብ ወልቃይትን ለማልማት የሚለው ተኖል የተፀነሰሰው። ልማቱ እውነት ከሆነም የዋልድባን ምዕራባዊ ክፍል ያካተተ ነው በተለይ ዳንሻ ኪዳነ ምህረትን ሙሉ በሙሉ የሚጨምር ነው፣እኔ እንደማምነው ግን ይህ የጥፋት ሴራ የቆዬ የህወሃት ህልም ነው፣ህልሙም ራስዳሽንን ጨምሮ ሰሜናዊ ጎንደርን ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ የማካለሉ ፍላጎት አካል ነው።አሁን ባለን መረጃ ደግሞ ዋልድባ ውስጥ ሰፊ የወርቅ ክምችት ተገኝቷል ይህ ደግሞ ወያኔን ይበልጥ አስክሮታል።

ወገኖቸ የህወሃት ስርዓት ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የማያስከብር ይልቁንስ የአገራችን ህዝቦች እርስበርሳቸው በጠላትነት እንዲተያዩ እያደረገ በሚሰራው የቤት ስራ የስልጣን ጊዜውን በማርዘም የቡድን ፍላጎቱን ማሟላት ነው።ስለሆነም ይህንን አሳፋሪና አሳዛኝ የጥፋት ተልዕኮ ተባብረን ልንመክተው ይገባል።

[email protected]

One Response to ጥንታዊውና ታሪካዊው የዋልድባ ገዳም አሳዛኝ ሁኔታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>