የእነ ሰይፉ ሰይፍ በአሮጊቷ ላይ… ቡጨቃ እና ቁምነገር (አቤ ቶኪቻው)

March 31, 2012

Click here for PDF

Abe Tokichaw's blogአንዲት ኑሮ ያጎሳቆላቸው አሮጊት፤ አንድ ፍሪጅ እና አንዲት ዳንሰኛ ባሉበት ቤት ውስጥ የሶስት አመቷን ህፃን ሲቀጠቅጡ የሚያሳይ በሳቅ የታጀበ ቪዲዮ በየ ኮምፒውተራችን ደርሶ ነበር። በዚህም የሴትየዋ አድራሻ ይገኝ ዘንድ ሁላችንም ኡኡ ብለናል። የሁላችንም ኡኡታ ከአፋላጊ ዶት ኮም ባለቤት አማላይ የአስር ሺህ ብር ስጦታ ጋር ተደምሮ የሴትየዋ አድርሻ ተገኘ። እሰይ!

አሁን ደግሞ አዲሳባ ውስጥ በሚገኝ አንድ የራዲዮ ኤፍ ኤም ጣቢያ ላይ ሙዚቃ እና ወሬ በማቅረብ የሚተዳደረው ሰይፉ ፋንታሁን አጋፋሪነት በርካታ አርቲስቶች ህፃኗን፣ ደብዳቢዋን ባልቴት እና እየቀረፀች ስትዝናና የነበረችውን ኮረዳ ጎብኝተዋቸው እንደነበር የሚያሳይ ሌላ ቪዲዮ ተለቋል።

በቪዲዮው ላይ ሰይፉ ፋንታሁን ኮረዳይቱን “ከሁሉ የሚያበሳጨው ደግሞ የአንቺ ሳቅ ነው…” እያለ ሲሞግታት ይታያል። እዝች ጋ ለሰይፉ አንድ መልዕክት አድርሼ እመለሳለሁ…

በነገራችን ላይ “ሰይፍሽ” የዚች ህፃን ጉዳይ ከመምጣቱ ከአንድ ቀን በፊት የፌስ ቡክ ዋና መነጋገሪያ አንተ እንደነበርክ ሰምተህ ይሆን? ካልሰማህ እኔን እየመረቅህ ስማ፤ እንደሚከተለው አቀብልሃለሁ።

ምን መሰለህ በአንዱ የቅዳሜ ፕሮግራምህ ታዋቂውን ፖለቲካ ቀመስ አትሌት፤ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ስለ መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ጠይቀኸው ነበር። አትሌቱም አሉ በማላገጥ “እምል ሰይፉ… ይሄ ስንፍና ነው…!” በማለት የመምህራኑን የደሞዝ ጥያቄ ሲያጣጥል ነበር። አንተም ይህንን ድምፅ ስትቀርፅ በሳቅ እየተንከተከትክ እንደሆነ ተሰማ። ልብ አድርግ አትሌቱም የሚያላግጠው አንተም የምትስቀው መምህራኑ እና ልጆቻቸው በኑሮ ውድነት ጣር ተይዘው ባሉበት ወቅት ነው።

እናልህ ይህንኑ የሚገልፅ ፅሁፍ ሀና መታሰቢያ የተባለች የፌስ ቡክ አርበኛ! ለአንተም ሆነ ለአትሌቱ ልክ ልካችሁን ነግራችሁ ህዝቡ ቁርሾ እንደያዘባችሁም አስረድታ ነበር።

ወደ ዋናው መስመር ስንመለስ… ሰይፉ በከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ አርቲስቶችን ሰብስቦ ህፃኗን የደበደቡትን ሴት እና ቀራፂዋን ኮረዳ በጥያቄ እና በወቀሳ ሲያጣድፏቸው ነበር። ልጅቷን እንዴት በሰው ትስቂያለሽ፤ አሮጊቷን ደግሞእንዴት ይቺን ህፃን ይማታሉ? በማለት ቁም ስቅላቸውን ያሰይዋቸው ነበር። በበኩሌ የአርቲስቶቹን ተቆርቋሪነት አደንቃለሁ። ግን… የሚለውን በአዲስ መስመር አብራራለሁ

ግን በተለይ ሰይፉ ሴትየዋን “በሉ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቁ” ብለህ መሬት ተንበርክከው ይቅርታ እንዲጠይቁን አድርገሃል… ለመሆኑ መቼ ነው ከ”ጋዜጠኝነት” ወደ ይቅርታ ቦርድ የተዛወርከው…? ብዬ ከጠየቅሁህ በኋላ ነውር አይደለም እንዴ!? በማለት እጨምርልሃለሁ። እውነቴን እኮ ነው የለቀከውን ቪዲዮ የሚመለከቱት ኢትዮጵያውያን ለህፃኒቱ መብት እንደሚቆረቆሩ ሁሉ ለአሮጊቷም መብት እንደሚጨነቁ አታውቅምን?

ሌላ ኮረዳይቱን “ከሁሉ ያበሳጨን ያንቺ ሳቅ ነው!” ስትላት ነበር። ይህንን ያዩ መመህራን ምን እንዳለሁህ ልንገርህ፤ ያኔ ከሀይሌ ጋር ስለ ደሞዝ ጭማሪው ባደረከው ቃለ ምልልስ “እምልህ ሰይፉ ይሄ ስንፍና ነው” ሲልህ አንተ ደግሞ ከት ብለህ ስትስቅ፤ “ከእርሱ መልስ ይልቅ የአንተ ሳቅ እንዳበሳጫቸው” መልዕክት ሰደውልሃል።

አንድ ልጨምርልህ ሴትየዋ ቤት ስትሄድ ይዘህ የሄድከው ካሜራ እና ያስከተልከውም የህግ ሰዎችን ሳይሆን የሀገሩን አርቲስቶች ነው…! አንድ ወዳጃችን ምን አለህ መሰለህ… “እንዴት ነው ነገሩ መንግስት ተቀይሮ እናንተ ነግሳችኋል እንዴ?” ብሎሃል። እውነት አለው ጉደዩን ወደ ህግ ደርሶ ተገቢው ቅጣት ለቀራጯም ሆነ ለቀጪዋ ሴት እንዲሰጥ አቤት በማለት ፈንታ እናንተው መርማሪ ፖሊስ እናንተው ዳኛ እናንተው ይቅርታ አስጠያቂ የምትሆኑት በምን አይነት አስማት ነው?

በማብቂያዬም

ውድ አርቲስቶቻችን በቪዲዮው ጭቅጭቅ ውስጥ በአረብ ሀገር ተንገላታ ለህልፈት የተዳረገችው “የአለም ደቻሳ” ጉዳይ በጣም ሲያስጨንቃችሁ እንደነበር ስትናገሩ ሰምቻለሁ። ጎበዞች! ለወገን መቆርቆር እንዲህ ነው። ግን አርቲስቶችዬ የአለም ደቻሳ ቤተሰቦች ችግር ላይ መሆናቸውን ተሰምቷል። እባካችሁ ድረሱላቸው። ቪዲዮውን ባትቀርፁልንም ችግር የለም!

5 Responses to የእነ ሰይፉ ሰይፍ በአሮጊቷ ላይ… ቡጨቃ እና ቁምነገር (አቤ ቶኪቻው)

 1. Tamiru tirfie Reply

  April 5, 2012 at 9:41 am

  Go ahead!

 2. Eyobè Brehane Reply

  April 1, 2012 at 1:52 am

  ተግባር ተግባር ተግባር ለዘላለም ትኑር!
  ዓለም ደቻሳ ወደ ዘላለም ቤት ሄዳለች ነፍስዋን በገነት ያኑረው።ይቺ ምስኪን ኢትዮጵያዊት የ፪ ልጆች እናት ጨቅላ ህፃናት ልጆችዋ ወደ ጎዳና ሳይወጡ አስቀድመን እጆቻችንን በመዘርጋት በተግባር ኢትዮጵያዊነታችንን ማሳየት አለብን ሀዘን ብቻውን አይሰፈርም አይለካም ፍቅር በተግባር ሲሆን ብቻ ነው ዋጋ የሚኖረው።የቤተሰቦችዋን አድራሻ የምታውቁ እገዛችሁን በማድረግ ልጆችዋን እንታደጋቸው ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ።ቤተሰቦችዋንና መላውን የፍት ህ ናፋቂዎችን መፅናናቱን ይስጣችሁ። ኢትዮጵያዊነት ያብባል እንጂ አይከስምም!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>