መልዕክተ ቹቸቤ ለሙያዬ ቁ 9

March 27, 2012

Ke Chuchebe

[email protected]

Click here for PDF

Melekte chuchebe No. 9ሰላም ነሽ ወይ የኔ እመቤት? ጎሽ ኑሪልኝ። የላክሺው ስጦታ ደርሶኛል እሁድ እለት እንዲያውም ሰው እንዲያይልኝ አጠር ያለ ሱሪ አድርጌ አደባባይ ልወጣ ነበር። አይ የኔ ነገር ምን ተመኘሁ መሰለሽ በቃ አንዳንዴ ካልሲ ከጫማው በላይ የሚደረግ ቢሆንና ስጦታሽን ሰው አይቶ ጎሽ ቢልልኝ ብዬ አሰብኩና በራሴ ሳቅሁ። ፍቅር እኮ ሞኝ ያደርጋል አይደል? ባንቺ ምን አልሆንም ብለሽ ነው። እንግዲህ ሁሉንም ሰላም በዪልኝ። ለመሆኑ ፆም እንዴት ይዞሻል? እነ ዓላማ በርበሬ አብዝተውብሽ የድልህ እቃ አስመስለው ላኩኝ አልሺኝ? ዝም በያቸው በሽሮ ተበቅለሻቸው ዱቄት እያቦነኑ እንዲመለሱ ታደርጊያቸዋለሽ።
አረ ሙያዬ እሁድ ስል የገጠመኝን ልንገርሽ። በጸሎት አዘውታሪነቷ የማትታወቅ አንዲት እህቴ በጣም ከረፈደ ያገር ልብሷን ግጥም አድርጋ ከቤተ ክርስትያን ስትወጣ አይቻት “አንቺን መሳም እኮ ቤተስኪያን የመሳለም ያህል ነው” ብዬ ስምሽ የተባረከ ይሁን እያልኩ ወደ ጉንጮችዋ ስንደረደር ወደ ትከሻዋ ሳበቺኝና የተፈቀደልኝን ትከሻ ስሜ ስጨርስ፣ ብቻዋን ከሰዐት በሁዋላ ምን ስትሰራ ይሆን ብዬ ልዩ ፕሮግራም ነበር እንዴ ዛሬ አልኳት?
“አይ አረ ብቻዬን ስጸልይ ነበር” አለቺኝ ጎሽ ብቻሽን ሆነሽ ለሁላችን ጸለይሽልን? ጌታም የሚሰማው ባልተጨናነቀ ሰዐት ሲጸልዩ ይሆን ይሆናል አልኩኝ ቀልደኛ የሀረር ልጅ ስለሆነች።
“ አዬ ቹቸቤ እኔ እንኳን ለፕሬዝዳንታችን ነው ስጸልይ የነበረው።” አለቺኝ። ድንግጥ ብዬ አቶ ብዙነህ ምን ሆኑ? አልኩ የቤተክርስትያናችን ዋና አስተባባሪ ናቸው።
“ አይ እሳቸው ደህና ናቸው ስጸልይ የቆየሁት ለፕሬዝዳንት ግርማ ነው።” አለቺኝ። ይቺን ይወዳልና ለሳቸው ነው እንዴ የጸሎት መስመሩን የምታጨናንቂው? አባ ጳውሎስ አሉ አይደለም? አልኳት።
“…. አይ ቹቸቤ” ብላ ጀመረች በእርጋታ “… ማስተዋልህን ምን ነካው? ብልህነት ወዴት ሸሸህ? አለቺኝ። መላዕክት በሷ ተመስለው የሚያነጋግሩኝ መሰለኝ። ቤተክርስትያን አጠገብ ባትሆን ኖሮ መርቅና ነው ብዬ እጽፍ ነበር። ቀጥላም እንዲህ ተናገረች…….
“ አቦ እኔ እግዜርን ብዙ አላስጨንቀውም ስድስት ወር ብቻ እንዲያቆይልኝ ነው የጠየኩት። “ እንዴ ለምን አልኩ በጥድፊያ
“ያኔ ስልጣኑን ይለቃታላ!!” ብላ የሱማሌ ይሁን የአደሬ ስድብ ለጠፍ አደረገችበት።
“… ያሂ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሞተ ከሚባል የነበረው በነበር ቀረ ቢባል ነው ሚ’ሻል። አየህ ሰውየው ‘ሆድ ካገር ይሰፋል’ የሚባል የአማራ ተረት ስለምግብ መስሎት ለሆዱ ኖረላታ!!”
አለችና እናት ላይ የሚለጠፍ ስድብ ተሳደበች ። የሀረር ቄሶችም ቢሆኑ ይሄኔ “… አቦ እናቱንና ይሄ ሼይጣን እንዳይነጅሳችሁ…” ሳይሉ አይቀርም ጠበል እየረጩ ብዬ አነጋገሯን ይሁንታ ሰጥቼ የመሳቅ መብቴን እንደወያኔ አፈንኩት። ፈጥና ደግሞ….
“… በማዕረግ ከሚቀበር ሆዳም አልቅሶ ይቅበረው አዲሳባ ሆዳሞች ናችሁ በር ዘግታችሁ ትበላላችሁ።” አለች።
አዬ እናንተ እኮ ወዳችሁ አይደለም ሙቀቱ ደጅ እያሳደራችሁ ነው እንጂ የአዱገነት ልጆች እኮ ‘ናሺፍ’ ናቸው አልኳት እነሱ ሁሉን በጫት አይን ነው የሚያዩት ሲባል ስለሰማሁ ነዋ!! እናም አቦ እንደ ቃልሽ ይሁና!! ብዬ ተሰናበትኳት። ከቤተክርስትያኑ ቅጥር ወጣ እያልኩ ስሄድ ታድያ እኔም የሆነ ነገር ይገለጥልኝ ገባ መሰለኝ እንዲህ እያልኩ መንገዴን ያዝኩት
“እናንት የከረንት አፌየር ሰዎች ሆይ ስለምን የሙያዬን አፍቃሪ ማወቅ ትሻላችሁ? መላ ምቱስ ለማን ይበጃል? እውነት እውነት እላችኋለሁ የተጠረጠሩት ስሞች ሁሉ ቹቸቤን አይደሉም። እነሆ በማንነቱ ሳይሆን በምግባሩ መዝኑት ውደዱትም። መወደድ መታደል ነው፣ ፍቅርም በሁላችን ዘንድ የሚኖር መንፈስ ነው። ፍቅር በሀገር ነው፣ ሀገርም በልብና በምግባር ነው። እናንተም የመውደድን በረከት ያለንፉግነት ስጡ፣ ፍቅርን እንደነጋዴ ለትርፍ ሳይሆን እንደለጋስም ለስጦታ አድርጉ፣ ነብሳችሁም ሃሴትን ታገኛለች። አገራችሁም በናንተ ትኮራ ዘንድ፣ ትውልድም ፍቅርን ይወርሳልና።”
እያልኩ ወደ ኢካዴፍ ሰዎች መልዕክተ ቹቸቤን ልስደድ ይሆን የሚለውን ሃሳቤን ሳልጨርስ ካሰብኩበት ደረስኩ እልሻለሁ።
የዛሬውን ወሬ ከየት ልጀምርልሽ እያልኩ ፎቶግራፎች ስመለካከት ሀሳቤን ማሊ ውስጥ አገኘሁት። አበሻ አገር እያቀና ምድርን ለመሙላት የጀንበር መጥለቂያን ይዞ ሲጓዝ ሙቀቱና ውሀ ጥሙ እያሰቸገረው ብዙ ወገን ያለቀ ይመሰለኛል። የተወሰነው ቡድን ታድያ “… ምን አይነት ነገር ነው በቃ እዚሁ እንስፈር ወደ ፊት ብንሄድ የሚገጥመንን አናውቅም” ብለው አቧራው ሽቅብ የሚወጣበት የሙቀቱ ወላፈን ከሰው ሰውነት ውስጥ ላቦት ከሚቀዳበት ሻገር ብለው ወንዝ ዳር ይሰፍራሉ። ብዙውን ነገር ስለማያውቁት ያዩትን ሁሉ ‘ማል ኢኒ’ እያሉ ሲጠያየቁ ከቃላት ሁሉ አብልጠው የተጠቀሙት ‘ማሊ’ የሚለውን ቃል በመሆኑ የአገሩ መጠርያ ማሊ ሆኖ አረፈው የሚል ጥናታዊ ሳይሆን ነሲባዊ ትንተናዬን እሰጣለሁ። መንደርደርያዬም ‘ማሊ’ ማለት በኦሮምኛ ‘ምን’ ማለት ነው። ጥቂት ቆይቶ ዋና ከተማው ደግሞ ባማኮ ተባለ ‘አቶ ኦቦማ’ ያገሩ ባላባት መሆን አለበት ምክንያቱም ባማኮ ማለት የኔ ባማ ማለት ነው። ኦ በዘመን ብዛት ተውጣ ሳይሆን አይቀርም ብለን እንጠርጥር።
የኛ ዘሮች ከኢትዮጵያ ነው የመጡት የሚሉቱ የማሊ ሴቶች ታድያ ቁመተ ሎጋና ውብ ናቸው። ይበልጥ የሚታወቁበት ደግሞ አትንኩኝ ባይና ጀግና መሆናቸው ነው። በንግግራቸው መካከል ‘ኤዬ’ ይላሉ ኦሮሞዎችም እንደዚያው ነው የሚሉት ‘አዎን’ ለማለት። አሁን አነስተኛ መንደር እንኳ ብትሄጂ የኢትዮጵያን ዘፈኖች ትሰሚያለሸ። ዘፈናቸው ደግሞ ከኛው ጋር በጣም ተቀራራቢ ነው እንዲያውም ቋንቋ ለማያውቅ ያሳስታል። እስቲ የኦዉማ ሳንጎሬን ጣዕመ ዜማ ስሚልኛ _____________
በዚህ ነሲባዊ ትንተና ስንቀጥል ኬንያ ‘ኬኛ’ ማለትም የኛ ከሚል ቃል ነው የተወለደው። ናይሮቢም ‘ና-ሮቤ’ ማለትም ዘነበልኝ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው በማለት ቃሉን አጣቅሰን ሰፋ ሰፋ አድርገን አገራችንን ብንሰራስ ብዬ ክትክታዬን አየት አደርገዋለሁ። “ቀማመስክ እንዴ?” አልሺኝ አዬ ነገር ጠጥቼ ነው በጠራራ ፀሀይ የኔ እመቤት፤ ነገር። እንዲያው እኔ ኦነግን ብሆን መገንጠል ከሚል አሳናሽ በሽታ መሰባሰብ በሚል ያገር ፍቅር ተሞልቼ ታቹን እሰከ ማሊ ወዲህም እስከ ዩጋንዳና ታንዛንያ ድረስ ድንበሩን ሰፋ ሰፋ አድርጌ ከሕዝቤ ጋር በተድላና በደስታ ለመኖር ብታገል ይሻለኝ ነበር ስል ነበር የከረምኩ። ዘንድሮ ግን ተመስገን አዲስ ቀን አዲሰ ተስፋ እያሳየን ነው። እርግጥ ነው አሁን ዛፉ ቅርንጫፉ የሚባል ትንተና መጥቷል። ለኔ ለገበሬው ገራ ገር ምሳሌ ትመስለኛለች። ቅርንጫፎች የዛፉ ምግብ ማዘጋጃዎች የፍሬም ተሸካሚዎች ናቸውና ከተገነጠሉ ግንዱ ለምልሞ ዛፍ እስኪሆን ዘመናት ይፈጃሉ። ቅርንጫፉ በተገነጠለበትም በሸታ ስለሚገባ ለዛፉም ጠንቅ ነው። ስለዚህ ትንሹንም ትልቁንም በእኩል አይን ማየቱ ነው የሚበጀው ብለን ዛፍ ያለቅርንጫፍ ግንድ ነው ቅርንጫፍ ያለ ዛፍ ቁጥቋጦ ነው አንዱን ካንዱ አሳንሶ ሙሉ የሚባል ነገር የለም ብለን እኔና አንቺ ስለ ፍቅር እንሰብካለን። የተገነጠሉትስ መች ደላቸው? እኛስ መናፈቃችንን መቼ ተውነው። አይ ሙያዬ አንድ አዛውንት ወዳጅሽ ታች አምና የኛ ፓርቲ ግንዱ ነው ሲሉ አሁን ቅርንጫፎቹ ጸድቀው ሳለ ባለ ግንዱ የማይሆን ነገር አጎንብሰው ጨበጡና ዛሬ ወሬያቸውም ጠፍቷል አሉ። አየሽ ቃል ሃሳብ ይወልዳልና ሲናገሩት ጠንቀቅ ማለት ደግ ነው።
ሙያዬ መቸም ካንቺ የምደብቀው የለም በቀደም ማንነቷ ያልተነገረኝ አድናቂአችን ቅርንጫፍ ለመሆን በፈቀደው ልቧ የጻፈቺልኝን ማለት የጻፈችልንን ልበል እንጂ ለኔ የተባለው ላንቺም አይደል? እናም ልባሟ ወዳጃችን የውብ ይቺን ግጥም ሎቢው ላይ አንብባ ላከቺልኝ። እኔ አንቺ ስትናገሪ ፍዝዝ ብዬ ስሰማ ልብ አላልኩም ነበር። እንደዚህ ይላል።
“ቹቸቤ ቀለሙ ከሩቅ የሚጣራ
ማህተቡ ፍቅር ነው እውነቱ የኮራ
ወንጭፉ ቀለሙ የሰላ ከካራ”
ይልና ‘ዳሽ’ ተደርጎ “እኔ እንደሁ አልፈራ!!!”
በሚል ቃል ይዘጋል። ወይ የዉብ ወይም የጻፈቺው ሰው በጎደለ ሙላን እንደምፈራ አውቀዋል። እንግዲህ ዳሹ ውስጥ የጎደለው ቃል ‘ ወይ እመሰክራለሁ አለዚያም እወደዋለሁ’ መሆን አለበት እላለሁ። “ ጎሽ አንተ እኮ ማን ይችልሃል አልሺኝ? ” አዎና ደግሞ ለግጥም። ታድያ ጸሀፊዋን እንደጎደለው ቃል በሃሳብሽ ግፊበት የምን መፍራት! ፈርቶ መኖርን ለኔ ተዪው ብዬ በጥቂት ስንኞች ………
“…. ኩልል ብሎ ይወርዳል ቃልሽ እንደ ጅረት
ተቀኝ አለኝ ልቤ ዝረፋት ዝረፋት
ብረሪ ብረሪ ክነፊ እንደ አሞራ
ቤት ይመታል ግጥሙ ሲፃፍ ካንቺ ጋራ
ከገጣሚው ጎጆ ረሀብ የለም ጥማት
ከቋጠረው ስንኝ እዩለት ሲያጎርሳት…” እያልኩ እያስጨበጨብኩ ያለ ነጠብጣብ ያለ ‘ዳሹን’ ሙላ በድፍረት ወደ ጀመርኩት የማሊ ጨዋታ ዘው እልልሻለሁ፡፡

ማሊ ነዳጅ ማደያው፣ ሕንጻው ትላልቁ ፕሮጀክት ሁሉ ‘ማሊቢያ’ ነው የሚለው ማሊንና ሊቢያን አዳቅለው ነው ‘ማሊቢያ’ ያሉት። ማሊን ክፉኛ የተቆጣጠረው የሊቢያ ኢኮኖሚ ነበር አሁን የሆኑትን እንጃ። ጋምቤላን ካራቱሪስታን፣ ዋልድባን አላሙዲስታን፣ እያልን እኛም እንቀጥላለና “…ቆሞ አገር ማስቀበር አሉ ሴትየዋ!!…..”

ታድያ ከዘመናት በአንዱ ከዳካር ወደ ባማኮ በነበረኝ ጉዞ ላይ የተዋወቅኳትን አንዲት ወጣት ለጨዋታ ማጣፈጫችን አሰብኳት፡፡ ትውውቃቸን የሁለት ቀናት እድሜ ብቻ ነው የነበረው። የት እንዳለሁ አታውቅም ከምን እንደደረሰችም አላውቅም። ሰሟም ተዘንግቶኛል። እኔ እኮ ያንቺን ስም ብቻ ነው በልቤ ይዤ የምዞረው። እርግጥ ነው አሁን አሁን አንዳንድ በግል መስኮት የሚገቡ ስሞች ከአፌ አልጠፋ ብለዋል። ታድያ ያቺ ያገሬ ልጅ በነበረን አጭር ጊዜ ደግሞ ብዙ አውግታኛለች። ከዳካር ስንነሳ እንዳየቺኝ የነገረቺኝ በጠዋት ባማኮ ደርሰን ከአውሮፕላን ስንወርድ ነበር። ቀላ ያለች ደመ ግቡ ናት። አበሻዊ ውበት እንጂ ዳያስፖራዊ ድሎት ተክለ ሰውነቷ ላይ አይነበብም።
“… ጠጋ ብላ ኢትዮጵያዊ ነህ አይደል?” አለቺኝ። አዎን አልኳት።
“ በማኮ ነው የምትቀረው ወይስ ጉዞ ትቀጥላለህ?” ጉዞዬ ወደ ዳሬሰላም ታንዛንያ ነው ግን አዲስ አበባ የሁለት ቀናት ቆይታ ይኖረኛል ብዬ መለስኩላት።
“ኢትዮጵያ አይደለም ማለት ነው የምትኖረው?” አለቺኝ አይደለም ስላት የተመቻት ይመስለኛል ትንሸ ፈገግታ አሳየቺኝ። ባማኮን እንደመተላለፊያ ለማድረግ እንጂ የምታውቀው የላትም። እኔን ማግኘቷ ወንድም የማግኘት ያህል ደስ ብሏታል። አዲስ አበባ ዘመድ ለማየት እንደምትሄድ ነግራኝ የሷም በረራ በማግስቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ነገረቺኝ። እያወራን እቃችንን ጠበቅን። ከኔ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ እንደሆነች ጠየኳትና እኔን ከሚቀበሉ የስራ ባልደረቦቼ ጋር ለኔ ወደ ተዘጋጀው ሆቴል ሄድን። ለርሷም ክፍል ተገኘላት። “ … አንተን አናግራ ማን አትከተልም አልሺኝ?” አረ ተይ ባክሽ እኔ እኮ ላንቺ ሲሆን ነው እንጂ ሴቱ ሁሉ እህቴ ነው የሚመስለኝ። ለማንኛውም ብዬ ልቀጥላ!! ለማንኛውም ባማኮ አየር ብቻ ሳይሆን አቧራም የሚተነፈስባት ትንሸ ከተማ ናት። ምንም ቀለም ያለው ነገር ልበሺ በማግስቱ ጡብ ትመስያለሽ። የእኔ ቀን እግረመንገድ የተያዘና የተጣበበ የስራ ፕሮግራም ነበረውና እሷን እረፍት እንድታደርግ ነግሬያት ከሚጠብቁኝ ሰዎች ጋር ተያይዘን ሄድን።
ማምሻውን ለራት ተገናኝተን የፍተሻ የነገር ተኩስ ተለዋወጥን። ማነህ ማነሽ አይነቱን የመንደርደርያ ንግግር ማለቴ ነው። ስለ ህይወትዋ ልታጫውተኝ ዘና ያለቺው ግን ዲፕሎማት ያለመሆኔን በማወቋ ነበር። ጥርጣሬዋ ደግሞ እቃችንን የወሰደው ሰው ውስጥ ድረስ ገብቶ ስለተቀበለን ነው። እንግዲህ አወጣጣችን ኑሮአችንና አገባባችንም የተለያየ በመሆኑ መረጃ መስጠት ማንም አይፈልግም። ወደዘመድ ቤት ቀርቶ ወደ እስርቤት እንዳይኬድ ነዋ!! ይህ የገጠመኝ ለመጀመርያ ጊዜ ባለመሆኑ ዲፕሎማትነት ለወገን የሚበጅ መሆኑ ቀርቶ ወገን የሚፋጅ ከሆነ የምን እንጀራ ነው ቢቀርስ ያሰኛል። ዲፕሎማቶቹ ይህን ያውቁ ይሆን ሙያዬ? መቼም ከዚያ የሚቀር የለምና ምናልባት ከዲፕሎማትነት ወደ ስደተኛነት ሲሸጋገሩ ማወቃቸው ግን አይቀርም።
የባማኮ ምሽት ላይ ያለው የሙቀት ወላፈን እሳት አጠገብ ያለሽ ነው የሚመስለው። አብዛኛው ሰው ምሽቱን ውጪ መቀመጥ ይመርጣል። እራት ስንበላ የሕይወትዋን ጣር ከፎቁ ጣርያ ላይ ሆነን ስንቆጥር ይህች ውብ ልጅ ይህንን ሁሉ መከራ መቅመስ አልነበረባትም እያልኩ ውስጤን ቁጭት ያብከነክነኛል። በውበትዋ ውስጥ የተሸፈነው ጉስቁልናና ሀዘን ያለ ምክንያት አንዳልሆነ ያወቅሁት ያኔ ነው። የሴት ልጅ ሀዘን ስለሚጎዳኝ ችግሩንም ቢሆን እያሳሳቁ ማዋራት እመርጣለሁ ብዙ ጊዜም ይሳካልኛል። ክፋቱ ደግሞ ጨረቃ የለ፣ ከዋክብቱ ሁሉ በማሊ ሰማይ ላይ እንዳይታዩ የተከለከሉ ይመስላል ድፍን ያለ ጭለማ ነው። ጠረጴዛችን አጠገብ ያለው መብራት የኛን አካባቢ ብቻ ነው የሚያሳየው። እና በቃላቶቼ እንደመኮረኮር እያደረግኩ ነበር የማስቃት። ለማውራት ቀለል እንዲላትም የረዳት ይመስለኛል። የዚያኑ ያህል ደግሞ ሴትን በወሲብ መነጽር ብቻ የሚመለከቱ ብዙ ወንዶች በመኖራቸው ፍርሃትና መጠራጠር እንዳይኖራት አነጋገሬ ጥንቃቄም ነበረው። መቸም ታውቂ የለ ሴት ልጅ ፈታ ብላ ከተጫወተች አንዳንድ የኛ ጀግኖች ወደደቺኝ ብለው ደማቸው በየአቅጣጫው ይሯሯጥባቸዋል። በተለይ ፉት ካሉማ ስትራቴጂክ ቦታ ያዝ እንደተባለ ወታደር ጉብታዎችን ሁሉ ሊቆጣጠሩ እኮ ነው የሚፈልጉት…… ደግሞ ኮረብታማ አይደል? “ምኑ አልሺኝ የኔ እመቤት?” መቼም የኛ ኮረዳዎች አንደ ቻይና የተላገ ጣውላ አይመስሉም አይደለም እንዴ? እኮ ዝርዝር ውስጥ ለምን ልግባ?
በጨዋታችን መካከል ቦርሳዋን ፈተሽ ፈተሽ አደረገችና “የኔ ናት” እያለቺኝ የአንዲት ሕጻን ልጅ ፎቶ አሳየቺኝ:: እየሳቅሁኝ “… አንቺ ግን ገብጋባ መሆን አለብሽ …” አልኳት “… እንዴ ለምን እንደሱ አልክ?” ስትለኝ። “ላንቺ ይሄንን የሚያክለውን ይዘሽ እሷን አፍንጫ ሰሰትሽባት” ስላት ሰረቅ እያደረገች እያየቺኝ ሳቋን ለቀቀቺው። ወዲያው ዝም አለቺና “በአባቷ ወጥታ ነው ባክህ ሴኔጋላዊ ነው” አለቺኝ። የሴኔጋል ልጆች አበሻዊ ይሉኝታ ያላቸው ጥሩ ሰዎች ናቸው አልኳት። “በጣም እሱ ባይኖር ዛሬ በህይወት አልኖርም ነበር” አለቺኝ። “ ራሴንም እዚህ ቦታ ማግኘቴ ለኔ ህልም ነው የሚመስለኝ” ብላ ወደ ለመድነው የሰቀቀን ትዝታ ዘው አለች። እንዳላወቀ በመምሰል ስልክ እየነካካሁ ዝም አልኳት።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የመሬት ካርታ እየተያዘ ሲም ካርድ በሚሸጥበት ዘመን እነዚህ ሀገሮች ውስጥ የቴሌፎን ካምፓኒዎች ሲም ካርድ ከአስር ዶላር ባልበለጠ ነበር የሚሸጡት። አሁንማ በነጻም ይሰጣል። ይህች ልጅ ያልረገጠቺው የአረብ ሀገር የለም፣ ያላየቺው ስቃይ የለም። ከቤት ሰራተኛነት እስከ ሸቀጥ ማመላለስና አልፋም አስከ አደገኛ እጽ ማቀባበል ሁሉ ገብታ ነበር። የማትነግረኝ በመስመር መሃል የሚነበብ ብዙ ብዙ ክብር የሚነካ ለመንገር የማይመች ነገር በህይወቷ ማለፉን ማሰብ አይቸግርም። ከዚህ ሁሉ ሰቆቃ ለመውጣት እጁን የዘረጋላት ይህ ሰውም ያሰበው ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ሚስቱ ሆና አብራው ተመለሰች እናም ቆንጅዬ ፉንጋ ልጅ ሰጠቺው። የአበሻዊ ወንድ ስስት (እንዴት የሌላ ሀገር ሰው አገባሽ! የሚል) ይታይብኝ እንደሆን የምትፈትሽ ትመስል ነበር አመለካከቷ። እኔ ግን የዚህ አይነቱ ስሜት የለኝም። አለም እየጠበበች ነው አበሻም እየተበተነ ነውና በሄደበት ጎጆ ቢቀልስ ምን ችግር አለው ባይ ነኝ። ዘንድሮማ የሰላሌን ሜዳ እነ ገላና ሁዋንግ ቹ የጦሳን አቀበት እነ አልታየች ቻንግ ሁይ ወደ ጋምቤላ ደግሞ አንገታቸውን እየነቀነቁ እነ ኦባንግ ሲንግ እነ ኦሞት ሻሺ ካፑር ‘ሜሪ ሙሃበት እያሉ ይቦርቁበት አይደል? ነገ ደግሞ ከሳዑዲ እነ ሙስጠፋና ከሊፋ በዋልድባ ሸንኮራ ተክለው መስጊዳቸውን ገንብተው የአረብ አዛውንት ማረፊያ ለሚገነቡበት ምን ወንድነትና ወንድምነት አለኝ? አዬ አለማወቅሽ ከጸረ ስድስቱ ክትባት ጋር ፍርሀት ሳንከተብ ቀረን ብለሽ ነው ልል አልኩና ተስፋ እንዳትቆርጥ ዝም ማለቱን መረጥኩ።
“…. አየህ ቹቸቤ በችግሬ የደረሰልኝና የሀገሩን ፓስፖርት እንዲኖረኝ አድርጎ በስምንት አመቴ ሀገሬን እንዳይ የሚልከኝ እሱ ነው። ማን በሕይወት እንዳለ አላውቅም፣ ምን እንደሚገጥመኝም አላውቅም የበፊቱ ምኞቴ ማለትም አገሬን የማየቱ ነገር ሲሳካ አሁን ደግሞ ውስጤን የሚሰማኝ ፍርሀት እንቅልፍ ነስቶኛል።” አለቺኝ። መለስ አድርጋም “ግን እኮ ህይወቴ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አስቤም አላውቅም ነበር። ከማፈቅረው ሰው ጋር ካገሬ ሰው ጋር ተጋብቼ ሀዘኔን ደስታዬን ተካፍዬው በድህነትም ብቆራመት እመርጥ ነበር ግን ህይወቴ ይህ ሆነ ብላ ተከዘች። አውቃለሁ የገባችበት ትዳር ለውለታ የተከፈለ እራስን መስጠት ሆኖባታል።
ምንድን ነው ችግር ብለሸ የምትወስጂው? ብዬ ስጠይቃት አየህ ቹቸቤ አሁን ያገሬ ሰው ስለሆንክ ብቻ በጣም ተግባባን፣ ብዙ ጊዜ የማውቅህን ያህል ተሰማኝ፣ እንዲያውም ወሬ አበዛሁ አይደል? አንተ ግን ምን አይነት ሰው ነህ አናዘዝከኝ እኮ እናቴ ትሙት ገርሞኛል.. ግን በቃ አለ አይደል ባልናገር እንኳን ምን ማለት እንደፈለኩ ትረዳዋለህ ብዬ አስባለሁ። አሁን እሱ ቡና በጀበና ባፈላ ምንም አይገባውም፣ ለበዓል ሳር ብጎዘጉዝ ያስቀዋል፣ ጥምቀት ነው ብለው አይገባውም፣ ፋሲካ ብለው አይጥመውም፣ እሱ ሙስሊም እኔ ውስጤ ክርስትያን፣ ስለ ልጅነቴ ስነግረው ስሜቱን አይነካውም እሱም የሚነግረኝ አንድ ነገር አይጥመኝ በቃ ያ ሁሉ ባዶነት እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ያንተን አላውቅም እንጂ ለኔ ትናንሿ ነገር ሆድ ታስብሰኛለች። እድሜ እንጂ የምገፋ ኑሮ እየኖርኩ አይደለም አይነት ነገር ስትናገር ክፉኛ አዘንኩኝ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ ወንበሯ ሄጄ ፈቃድዋን ጠይቄ አቀፍኳት። በቃ አቅፎ አይዞሽ ከማለት በላይ አቅም የሌለኝ ፍጡር።ድሮ ሰው ለሴት ለፍቅረኛው ይሞታል አንተ ለሀገር እንኳን አትሞትም እንጀራና ወሬ ብቻ መቅደድ ያለኝ መሰለኝ የማሊ ጭለማ!! የት አባቱ እሱም ለብርሃን ቦታውን ትቶ ይሄዳት የለ!!
ሕይወትዋ ገና መጀመሩ እንጂ ማብቃቱ እንዳልሆነ ከርሷ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ያለፉ ሰዎች እንዳሉ በመንገር ገና ወጣት ስለሆነች በመቆየትና ባህሉን በማስተዋወቅ ከባለቤትዋ ጋር ጥሩ ኑሮ መኖር እንደምትችል፣ ኢትዮጵያዊም ብታገባ ኑሮ ይመቻል ማለት እንዳልሆነ ለማስረዳት ሞከርኩ። ዳካር ውስጥ አበሾች ስላሉ ከነርሱ ጋር መገናኘት ጥሩ እንደሆነ በመንገር አበረታችና አፅናኝ የሆኑ ምክሮች መከርኳት። እንደምንም ዘና ወደሚያደርጉ ጨዋታዎች መለስ ብለን ሃሳቧ ለወጥ ማለቱን ሳረጋግጥ በሚቀጥለው ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዐት መነሳት ስላለብን መተኛት እንዳለብን ነግሬያት ለእንቅልፍ ተለያየን። እንደዚያ አይነት የትካዜ ስሜት ሲሰማሽ ሁሉም በየአቅጣጫው ተበታትኖ ማፍቀር የሚችሉ ልቦች ከሚፈቀሩት ሌሎች ልቦች ጋር መንገድ ሲተላለፉ ከማይሆን ልብ ጋር ሲለጠፉ እያሰብሽ ያገኘሽው ወረቀት ላይ በልጅቷ ስም እንደዚህ አይነት ግጥም ተጭሪያለሽ ………….

ፍቅር …አንተ ጭስ ነህ ንፋስ፣ በእጅ አትጨበጥም፣
ብርሀን ነህ ጭለማ፣ ባንድ አትቀመጥም።
አልመትር ርቀትክን፣ ነህ የሰማይ ኮከብ፣
ብልጭ ድርግም ነህ፣ የማትሆነኝ ማተብ።
መመኪያዬ አልልህ፣ አላደርግህ ተስፋ፣
አትሆነኝ አልሆንህ፣ ባዝንና ብከፋ።
ከሰው ጋር እያለሁ፣ ብቸነት ከፍቶ፣
አመለጠኝ ዘመን፣ ልጅነቴን ሸሽቶ።
ንፋስ ነህ ደመና፣ የጠዋት ላይ ጤዛ፣
ይዤ እማላቆይህ፣ ምን ምኞት ቢበዛ።
ይህን ሁሉ ጓዜን፣ ይህን ሁሉ ፍቅር፣
አካፍለው ጠፋኝ፣ አጣሁና ሀገር።

እያልኩ የእህቴን ሰቀቀን የኔንም ቁጭት ይዤ ወደ መኝታዬ ሄድኩ። የራስን ለማፍቀር ያለመቻል ሳይኖሩ ማለፍ እንግዲህ እንዲህ ነው። በማግስቱ ጉዞ ወደ ሸገር ሆነ። ሆድ አስባሹ የኢትዮጵየ አየር መንገድ ግን ለሰባት ሰዐት ዘግይቶ መጣ በዚያን ጊዜ ‘ስሎው ኩከር ውስጥ እንደተጣደ ምግብ ሙክክ ብለን ነበር። ያ ነበር የመጨረሻው ቀናችን? እህቴ ሳቋ ጠፍቷል የያዘቺውን ፓስፖርት አይተው ቢጠይቁኝስ ብላም ፈርታለች። ምንም ችግር እንደሌለው አስረዳሁ። በፈረንሳይኛ አስኪጂው ግን አበሻ ነሽ ወይ ካሉሽ መካድ የለብሺም። የሌላ ሀገር ዜጋ መሆን እኮ መብትሽ ነው አልኳት። ትንሽ ትቆይና ሰልክ ስደውል እኮ ግን ሁለት ጌዜ ስደውል እናቴን አላገኘሁዋትም ውይ አምላኬ ትላለች። እጇን ሁሉ ያልባታል መሰለኝ ትጠራርገዋለች፡፡ አውሮፕላኑ ሁለት ሶስት ቦታ አርፎ ስለሚነሳ መንገዱ ረዥም ነው። ስለሁሉም ነገር ለማወቅ በጉዞ ላይ ነሽ አሁን በአንቺ ስልጣን የሚቀየር አንዳችም ነገር የለም ትንሽ አይንሽን ብትጨፍኚና ልጅሽንም አሰብ ብታደርጊያት ጥሩ ነው ብዬ አበረታታሁ። የልጇን ፎቶ ከቦርሳዋ አውጥታ አንዴ መልከት አደረገችና ሳቅ አለች። ዐይን መጨፈን ሳይሆን ሶስቱን ሰዐት ተኛቺው። በዚህ ሁኔታ ጉዞ ጨርሰን ተለያየን ሰላም ትሆናለች ቤተሰቦቿን ሰላም አግኝታለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
የብዙዎቻችን ሕይወት ከዚህ የተለየ አይደለም። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ከበቀልንበት ተነቅለን አዲስ ቦታ እንደተተከለ ችግኝ ነን። በጉዞ ላይ ልባችን ተሰብሮ መንፈሳችን ተጨፍልቆ የአበሻ ስር ስላለን ተሟሙተን ወይም እንደ ቪቫ ሚኒሊክ አባባል አፈር ቅመንም ቢሆን ነጥሮ መነሳት በመቻላችን እንጂ የመንፈስ ሕመምተኞች ነን። ሙያዬ አሁን አንቺ ሁለት አስርት አመት የለፋሽበትን መስሪያ ቤት ወደሁዋላ እያየሽ መሄድ ምንኛ ከባድ ነው? ይሁን እንጂ አንቺም ከወደቅሽበት ተነስተሽ እኔን ወደፊት እያሰብሽ በእድሜ ላይ እድሜውን እየጨመርሽ እርጅናን ድርሽ ትልና እሰከዘለአለሙ ባውንስ አደርግሃለሁ እያልሺው የከረንት አፌየር የጎበዝ አለቃ ሆነሽ ትኖሪያለሽ። ኑሪልንም እላለሁ። ሌሎቻችንም ከመሬት ለመነሳት በእጃችን ያለውንም ላለማጣት ለፍቅር ክብር እንስጥ፣ በፍቅር ስም ወንጀል አንስራ ሸቀጥም አናድርገው። ልብ አላልነውም እንጂ ለስራ ውጤታችን ሳይሆን ለሰዐት ጉልበታችን ሲከፈለን ስርዐቱ ሸቀጥ አድርጎናል። እንደሰው የሚያኖረን ግን ተስፋና ፍቅር ነውና ሰው ሆኖ ለመቆየት ስንል እንዋደድ እንፋቀር ተስፋም አንቁረጥ። የንዋይም ድሆች ብንሆንም የፍቅር ባለጸጋዎች ሆነን ለመጪው ትውልድ ፍቅርና ሀገር እናውርስ!! ብሏችሃል ቹቸቤ በዪልኝ። እንደተለመደው እንዲህ ብዬ እመርቃለሁ።
ኢትዮጵያችንና ኢትዮጵያዊነታችን የኩራታችን ምንጭ ይሁንልን!!
ተስፋና ፍቅር ተዝቆ የማያልቅ ጸጋ ይሁነን!!

4 Responses to መልዕክተ ቹቸቤ ለሙያዬ ቁ 9

 1. muhammed getahun Reply

  March 31, 2012 at 1:07 pm

  hasabu btame dseymile nwu endzihe ayntu awuktna moran listwu yigbal btame dse ymile sehufe asenbebhenale tkw brimah muhammed getahun

 2. mertework Reply

  March 29, 2012 at 11:16 am

  THink you very much for you great script! ofter all our lives are far from trouble challenges arise every day that could rob us of our joy, new Ethiopians suffring all over,God himslf will be sustain us i hope so we all miss home bock to mama ETIOPIA!but i respect you qetele! betam gobez nehe!!
  God bless our ETIOPIA!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>