መልዕክተ ቹቸቤ ለሙያዬ ቁ 8

March 21, 2012

Ke Chuchebe

[email protected]

Click here for PDF

መልዕክተ ቹቸቤ ለሙያዬ ቁ 8ሙያዬ የኔ እመቤት ደህና ነሽ ወይ? ሰላም ተመለስሽ? ለፍቅር ዘብ የቆሙ የቤተሰብና ቤተዘመድ አባላት ከሰው ስህተት…. በሚል መነሻ ለእኔ ያደርጉት የነበረው ጥበቃ የዋዛ አልነበረም። ላንቺም እንደዚያው እንክብካቤ ሳይሆን እንስፍሳፌ ሲያደርጉልሽ እንደነበረና በዚህም የተነሳ የተሳሳቱ አይኖች እንዳያርፉብሽ ሲከላከሉ እንደቆዩ ተነግሮኛል። አየሽ ሙያዬ ሰዉ ለፍቅር የሚሰጠውን ዋጋ? ተመስገን እንበላ። ከሁሉ የገረመኝ ነፃነት የምትባል አፏ እንደማር የሚጣፍጥ ልጅ ጥያቄና አደራ ነበር። የጥበቃና የቃለቡራኬ ስራዋን አጣምራ ስትሰራ ቆየች። መውደድ አይታክተኝ ነፃነትን ውድድ አድርጌአት መዝሙሯን ስትዘምርልን በሃሳቤ የተስፋ ቀስተደመና ላይ “… እነሱ ካሉ አገርህም ትኖራለች..” የሚል ጽሁፍ ነገን አስውቦ ሲያሳየኝ ሰነበተ። ጉንጮችዋ በስሜ እንዲሳምልኝ ለእናቲቱ ጥያቄዬን አቅርቤ የምኞቴ ተሳክቶልኛል። እናትየውም ተደስተው የኔን ካደረሱ በሁዋላ እንደምርቃት የልጃቸውን ጉንጮች መንደሪን እስኪመስል ሳሙት መባሉን ስሰማ የእናት ፍቅር ነውና ተመስገን አልኩኝ። እኔም እንደልጅቱ ተስፋ እንዳለን እናምናለን አምነንም ለነጻነት እንታገላለን ብዬ የዛሬውን ደብዳቤ ለውዴ መጻፌን እቀጥላለሁ።
በቀደም ማራኪን ጭንቅ ብሏት “ …. ቹቸብዬ እስቲ ምኑ ጋ ተሳስተን ነው የፍቅር ጸጋ የጎደለን? ..” ስትልህ ሆዴ ተንሰፈሰፈ አንጀቴ ተላወሰ ነበር ያልሽኝ? የኔም ስፍስፍ ነበር ያለው። አገር ጎደለና የኔ ቆንጆ አገር ነዋ አትያትም ነበር? የዛሬው ማንነታችን በትናንትናው እኛነታችን ውስጥ ነው የአለው። የትናንቱ እኛነት ደግሞ የቁልቁለት መንገድ ሆኖ ከዘመኑ ጋር ተጣረሰብንና ፍቅር ጎድሎን አገርም አጥተን ይኸው የሞት ሽረት ትግል ላይ ሆነናል።
አየሽ ማራኪ ስደት እጣው የሆነው ወጣት ከራሱ ጋር የተቆራኘው የቤተሰብና የወዳጅ ፍቅር፣ ያደገበት ሰፈር፣ የተማረበት ትምህርት ቤት የሳቀው ያለቀሰው፣ የሄደበት መንገድ፣ ያየው የተመኘው ነገር ሁሉ ትዝታ ሆኖበታል። ወጣቱ እንደ አረጋውያን በትዝታ ከኖረ ለዛሬ የሚሆነውን ፍቅር ከየት ያመጣዋል? ፍቅር እኮ አብሮነት፣ የኔ የሚሉትን መሰሰትና ነገን መናፈቅ ማለት ነው፤ አይደለም እንዴ? የምትተማመኚበት ነገ ከሌለ የዛሬውም አብሮነት ካልተቻለ ፍቅር ቢኖርሽ እንኳን የጭንቀትና የሀዘን ምንጭ ይሆናል እንጂ ደስታን አይሰጥም። ደስታ የሌለው ነገር ደግሞ ለጆሮም አይጥምም።
አሁን እኮ ብዙሀኑ በትዝታ እየኖረ አዲስ ኑሮን ለመጀመር ስደት ካገጣጠመው እንጂ አጥብቆ ከሚፈልገው ጋር አይደለም ግንኙነት የሚፈጥረው። ወይም ደግሞ ተራርቆ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ምክንያት አስተሳሰብ ተለዋውጦ መጣጣም ከማይችሉት ሰው ጋር በድሮው ግንኙነት መሰረት የሚጀመር ኑሮም መራር ይሆናል። አንዳንዶቻችን የእድሜ ሸርተቴ ሲያሯሩጠን ባወጣ ያውጣው ብለንም ነው ግንኙነት የምንመሰርተው ይሄ ደግሞ ታድያ እንደ አትራፊ ፕሮጀክት እንጂ እንደ ፍቅር ቁርኝት ሊታይ አይችልምና ኪሳራውንም በፀጋ መቀበል ግድ ይላል። ማወቅ የሚገባን ታድያ ይህ ነገር ባለማወቅና ባለመፈለግ የሚመጣ ሳይሆን የብዙዎቻችን ህይወት ከውቅያኖስ ወደ ብልቃጥ እንደተከተተ አሣ ላለመሞት የምትንፈራገጥ ነብስ እራስን ለመስጠት የሚያበቃ ፍቅር ለመጋራት አቅሙም እድሉም ስለሌላት ነው።
አይ ሙያዬ ያንቺን ነገር አሰብ ሳደርግ በትዝታ ወደሁዋለ ሄደት አልኩልሽና አረፍተነገሩን ከመጀመሬ በፊት ሳቅ ቀደመኝ። ታስታውሺ እንደሆን አንቺ ያቺን ቀይና ጥቁር ሸንተረር ያላት ፓሪ ሞድ ላይ ሹራብሽን ጣል አድርገሽበት ሰበር ሰካ ካልሽበት ይልቅ ትዝ የሚለኝ ያ ሊጥ የተረጨበት ቀሚስሽ ለማጅ ቀለም ቀቢ አስመስሎሽ ወደ ትምህርት ቤት የምትከንፊውን ሳስብ ነው ሳቄ የሚመጣው። እንደነገሩ ባሰርሺው ሻሽ ውስጥ አፈትልከው የወጡት ጠጉሮችሽ ነጻነት እስከመገንጠል ብለው ይታገሉ እንደነበሩት የልቤቃል ጠጉሮች ሲታሰቡኝ ሳቄ ይመጣል። እቴ ሙች ብቻዬን ከት ብዬ እስቅልሻለሁ። እኒያ ጠጉሮች ተገንጥለው ቢሆን ሙያዬ ምን ትመስል ይሆን እልና ዳር ዳር ያለውን ሳቅ በመንከትከት አደምቀዋለሁ። አንቺም ሳቅሽ አይደል የተገነጠሉትን እያሰብሽ? ጎሽ የኔ እመቤት እንሳቅ እንጂ የተገነጠሉ ጠጉሮች ሌላ ራስ ላይ አይበቅሉ እንዲያው ባያድላቸው ነው እንጂ ብለን የሽሙጥ ሳቅ እንሳቅ እንጂ! ሳቅ እኮ የፍቅር ማጣፈጫ ነው። ማራኪ አየሽ እንደዚህ አይነቱ ትዝታና ትውስታ ነው አብሮነትን ጣዕም የሚሰጠው።
የፍቅር መንፈስ በሰዎች ላይ ሲገለጥ ቀላልና አስደሳች ይሆናል እንጂ መሰረቱ ውስብስብና ጥልቅ ነው። የህይወታችን ድርና ማግ ባህላችን ወጋችን ልማዳችን ሲሆን ይህንን የሚቀርጸው ደግሞ አኗኗራችን ይሆናል ማለትም የምንሰራው ሥራ የከተማውና የገጠሩ ሕይወት ማለት ነው። በዚህ አያበቃም ይህንን መስተጋብር አንድ አድርጎ እንደ ጥበብ የሚያሳምረው ደግሞ መልክዐምድሩ ማለትም ወንዙ ተራራው ሸንተረሩ የአፈሩ የአበባው መዓዛ፣ ምግቡና መጠጡ ተደማምሮ ይሆናል። እናም የዚህ ሁሉ ህብር ደግሞ እኔነትን (አይደንቲቲ )ማለትም ማንነታችንን ይሰጠናል። ይህ በሰላምና በአብሮነት ከቀጠለ መዋደድ መተሳሰብ አለ ማለት ነው። ዘፈኑ፣ ቴአትሩ፣ ሲኒማው ሁሉ ስለ መዋደድ፣ ስለ አብሮነት፣ ስለ ማንነትና ስለ እድገት የሚገልጥ ይሆናል። ማህበረሰቡ በመዋደድ አብሮ የሚኖር ከሆነ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ማፍቀር በእጅጉ ቀላል ይሆናል። እናም አሞራ በሌለበትም እንኳ “አሞራ ሲያይሽ ዋለ” ስንል ከሁኔታው ጋር እንኳ ባይጣጣም መንፈሱና አብሮት ያለው ሁነት ውስጣችንን አንዳች ስሜት ይሰጠዋል። ማራኪ ለዚህ ነው ዘመነ ሙያዬ ፍቅር የሚወደስበት፣ ለፍቅር የሚሞትለት የነበረው። እኔ እምለው አወሳሰብኩት ይሆን እንዴ? ቸግሮኝ እኮ ነው ፍቅር ፈረንጆቹ የአረፍተነገር ማሳረጊያ ያህል ‘ላቭ ዩ’ እንደሚሉት ቀላል ‘አይ ሔት’ እንደሚሉትም የአፍ አፋፍ ላይ ያለ ነገር አይደለም ብዬ ነው።
ታድያ በዘመነ ሙያዬና ወዲህ ባንቺ በማራኪዋም ዘመን የሀገር ፍቅር የጦዘው ለዚያ የነበረ ቢሆንም ተማሪዎችን ሆ ብሎ ያስነሳው ግን ጠጉረ ልውጥ ፖለቲካ ሆነና ኢትዮጵያዊነት ያልነበረው መፍትሄ ተወስዶ እንደማይሆን ሆነ። የንግግር ማሳረጊያዎች ሁሉ ካመት አመት ያድርሰን! አይለየን! አገራችንን ይባርክልን!! ሰላምና ጤና ይስጠን!! መሆኑ ቀረና በይወድማሉ! ይደመሰሳሉ! ይመነጠራሉ! ይጠፋሉ! ተተክቶ ፍቅር ከመድረኩ ጠፋ እልሻለሁ። ምናልባት የመጨረሻው የወጣቶች የፍቅር ጊዜ እድገት በህብረት ላይ ይሆናል ሞት የተፈረደበት። አይ እድገት በህብረት የስንት ወጣት ህይወት አቅጣጫውን ሳተበት?
የሚያውቁ የመሰላቸው ብዙ ግብዝ ወጣቶች ለሀገር ፍቅር ብለው የወጣቱን የርስበርስ ፍቅር ገደሉ። ማፍቀር አሳፋሪ ነገርና የሚወገዝም ሆነ ፍቅር የሌለው ወጣት ደግሞ ባዶ ሆነና አወቅን ያሉ አንዳሻቸው ነዱት። ቀጥሎም መንገዳችን ጠመዝማዛ ግባችን አሩቅ ነው እያሉ ዘፈኖቹ ሁሉ የፍቅር ስሜት እንዳይኖራቸው ክላሽ ያነገቱ ባለጌ ካድሬዎች ለራሳቸው የፈሩ ኮረዳዎችን እየደፈሩ ሌላውን እያስፈራሩ የወጣቱን ስነልቡና አጋሸቡት። ደርሰናል አይዞን ነው እንጂ ሩቅና ጠመዝማዛ ነው እየተባለ ሰው ካሰበበት እንዴት እንደሚደርስ አላውቅም። ስለዚህ ሁሉም ተስፋ ቆረጠና የፍቅር ነገርም አሟጠጠ። ቢያንሰ ኢየሱስን አወድሃለሁ እያሉ ትንሽ ትንሽ ስለመውደድ ይሰማሉና ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች በገፍ ጴንጤ ሆኑ ። እንዲህ እየተባለ በመደብና በፖለቲካ አቋም የነበረ ግንኙነት በስተመጨረሻ ኢ ሠ ፓ ሚሰትና ባል እየገመገመ ያጋባ ጀመር። ፍቅር ውበት ነው ከተባለ ውበት ደግሞ በቀለማት ይገለጣል። ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውሰጥ ልብሱ በቀር በሶስት ቀለማት ተወሰነ አመድማ፣ ሰማያዊና ውሀ ሰማያዊ። ካኪ መልበስ አንድ ነገር ነው ግን እንዴት መንግስት ለሰብዓዊ ፍጡር የልብሱን ቀለም ይመርጥለታል? ያንን እሺ ሲል እኮ በቃ ከሰውነት ወርዶ ህይወቱን ለማቆየት ብቻ ነው የሚኖረው። የቀረቺው ተስፋ ድራፍት መጠጣት በመሆኗ ከስራ እንደወጣ መኖ እንደቀረበለት መንጋ እየተጋፋ ባልታጠበ ብርጭቆ ድራፍቱን ይጋት ነበር። ሰብዓዊነት እንደዚያ ነበር የተዋረደው። ቀደም ሲል የነበረው ቤተሰባዊ ፍቅር ደግሞ ለምሳ በተመደበው አንድ ሰዐት ምክንያት ሁሉም ሆቴል ተጋፊ ሆነና ሚስቶች የክትፎ ገዢ ወንደላጤዎችን ኪስ መቃኘት እየጀመሩ በቅጡ የቆመ ትዳርም እስከማፍረስ ዘለቀ።
የተጀመረው የቁልቁለት መንገድ ሆነና የመጨረሻው ተዳፋት ወያኔ ደግሞ ሁሉን ነገር በግድ በዘር እንዲሆን አደረገው። የተለያየ ዘር ኖሮአቸው የተጋቡ ምርጫቸው ወይ መፋታት ወይም ስራ መፍታት ሆነ። እንኳን አዲስ ፍቅር የነበረውም መፍረስ ግዱ ሆነ። አሁን ማን ነው የጎሳ ነገር ትዳሬ ላይ አያገባኝም የሚል ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ? አየሽ በዚህ የዘመን ሹም ሽር ውሰጥ ነው የዘመኑም ትውልድ የመጣው። ፍቅር የኮሰመነበትና ከሞት አፋፍ የደረሰበት ዘመን ተወልዶ እንኳን ምግባሩን የቃሉን ትርጉም እንኳን እንዴት ይወቀው እንላለን?
ማራኪ! የኔ እመቤት ማንም ቢሆን የዘመኑን ወጣት ፍቅር አነሰው ድሮ እንደዚህ ነበር አሁን እንዲህ ሆነ እያለ እንዲያጣጥለው ወይም አሳንሶ እንዲመለከተው ሊፈቀድለት አይገባም። የዛሬ ማንነቱ በትናንቱ የሚገለጥ ከሆነ ፍቅር ያቆየው አልነበረምና ያልወረስውን አለኝ ሊል አይችልም። እንኳን ጥልቅ የሆነና ራስን የሚያሰጥ ፍቅር ይቅርና በቅንነትና በመግባባት መነጋገር የማይችል ማሕበረሰብ ውስጥ እየኖረ ያለው የዛሬው ወጣት በሰላም ወጥቶ መግባቱም ትልቅ ነገር ነው። ኑሮ አሽቆልቁሎ ሴት ልጁ ምን ሰርታ ልታመጣ እንደምትችል አውቆ አረብ አገር ለመላክ ፈቃደኛ ሲሆንና ከዚያች ወጣት ጡረታ ሲጠብቅ እኮ ማህበረሰቡ አብቅቶለታል። በሊቢያ በፍል ውሀ የተቃጠለቺውን ሸዋዬን ስለፍቅር መጠየቅ ከቶውንስ እንደምን ይቻላል? ወንዱን ልጅ በመጥረጊያ እንጨት ሲጫወቱበት እንዴት ስለፍቅር መጠየቅ እንችላለን? በሊባኖስ መሬት ለመሬት የተጎተተችው ወጣትና ታግታ ለሞት የበቃችው አለም ደቻሳ ስለምናወጋው አይነት ፍቅር እንድትናገር ማን ይጠብቃል? አለም ድምጿ አሁን ድረስ ጆሮዬ ላይ ይጮሀል!! በደንብ አለቀስኩላት ሰውነቴ በቁጣና በንዴት እስኪንቀጠቀጥ ድረስ በእንደዚህ ያለ ሙሾ አነባሁላት።

እምቢታሽ አይሎ የጣር ቃልሽ የሰማይ ጣርያ ቀዶ፣
ልቤን መንፈሴን የሰበረው የባዶነቴን ባዶ መርዶ።
አንቺን እቴን ሳልታደግ አንቺም እኔን ላትይ ወንድምዬ፣
እንዲሁ ዘመን ከዘመን ይሻገራል ሀዘን ምሬት ሰቆቃዬ።

ምንሽ ነኝ ልበል አለምዬ ከርታታዋ እቴ አንጀቴ፣
ጠጉርሽ ሲነጭ ስትጎተች ሞትሽን ያልለወጥኩ በሞቴ።
ሲያንደባሉልሽ አፈር ላ’ፈር ስትቃትቺ ረዳት አጥተሽ፣
ዋ ለእኔው እንጂ ውርደቱ ….. አንቺማ ሄደሻል ጥለሽ።
ከቶ ምን ሃይማኖት ነው ያለኝ ምንስ አመለካከት?
ያ ሁሉ ከሆነ በሁዋላ አብሬሽ ልሆንስ ያልቻልኩት።
የወገን እሬሳ በየጉድባው በየባህሩ ዳርቻ ሲሰጣ፣
ምንስ አሰናከለኝ እኔን ማንስ ነጠቀኝ የኔን ቁጣ?
ከቶ ለማን ብለን ነው በገፍ ወደ ሞት የምንነዳ?
በቃ ብለን የማንጥለው ይህን ነቀዝ የአገር እዳ?
የወንበዴ፣ የፋሺስቶች የማፍያ የሆነች መጦርያ፣
እኮ የማን ነች ያቺ አገር የሚሏት ኢትዮጵያ?

አለምዬ ያንቺም እኮ ነበረች የየኔሰውም ኩራት፣
ቆመን መፋለም ትተን ገብተን ነው እንጂ ሽሽት።
ነብስሽን ይማረው ልበል የኔስ መማሩንም አላውቅ፣
እንዲሁ ነገር ስገምድ እልፍ አላልኩኝ ትንሽ ፈቀቅ።
አንቺስ ታግለሽ ወድቀሻል እርግማንሽ ነው የሚያስፈራ፣
በሞትሽ መነሳት ባይኖር ወገን ወገኑን ባይጠራ። (2X)

ነብሷን እግዚአብሄር በገነት ያኑርልን እንበልና ወደ እለቱ ወግ እንመለስ።
እናም ታድያ የዘመነ ሙያዬ አይነትም ባይሆን አለም ስለልጆችዋ ፍቅር ስትል ተሰዋች፣ ሸዋዬ ስለቤተሰብዋ ፍቅር ስትል ተለበለበች፣ ብዙ ወጣቶች ስለቤተሰብ ፍቅር ሲሉ መክፈል የማይገባቸውን መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው። ያ የተነገርለት አይነት ፍቅር ለዘመኑ ወጣት ቅንጦት ነው ግን በሌላ መልኩ በኒህ ወጣቶች ልብ ውሰጥ ፍቅር እየኖረ ነው።
ተደላድሏል የሚባለው ዳያስፖራም እኮ የተለየ አይደለም ስራ ያሯሩጠዋል፣ ‘ቢል’ እንቅልፍ ይነሳዋል፣ ዘመድ መርዳት አለ ከዚህ በሚተርፈው ጊዜ እንቅልፍ የሚነሳ ፍቅር ውስጥ እንዴት ይግባ? በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራዊ ሕይወትን የሚያንጹና የሚያጎለብቱ ድርጅቶችን ወይም ማህበራትን ማቋቋም አልቻለም። ሁሉም ደረቅ ፖለቲካ ይሆንበታል ነገር ግን ለፖለቲካው አመለካከቱና ለሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑትን መሰረታዊ እውቀቶች የሚጋራበትን፣ የሚያዝናናውን እያዝናናም የሚያስተምረውን አይነት ስብስብ መፍጠር አልቻለም፡፡ እኒህ ሁሉ መሰናክል ናቸው። የፍቅር ችግኙ አለ መኮትኮቱና ውሀ ማጠጣቱ ከችግሩ ዘለል ብሎ መፍትሄ ማየቱ ነው የቸገረው።
በሀገር ቤትም ቢሆን ወጣቶች አብረው የሚያድጉበት በስሜታቸውና በዝንባሌያቸው የሚገናኙበት ነጸ የሆነ ማህበር የላቸውም። ትምህርት ቤቶች ራሳችንን ለማግኘት እንድንችል የሚያበረታቱ አይደሉም። ያቺኑ የክፍል ትምህርት ተምሮ መለያየት ነው። ሰውን ለመውደድ መገናኘት ያሻዋል። የሚወደውንም ለማወቅ እንዲሁ ራሱን የሚፈትሽበት መድረክን ይሻል። በዚህ ጉዞ ውስጥ ነው መተያየት መቀራረብ መዋደድና መፋቀር የሚጎለብተው። ይህ ያልተመቻቸለት ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ወጣቶች አንዱ ሌላኛውን የሚያየው እንደ እንስሳ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቱን ለማርካት ብቻ ይሆናል። ለዚህ ነው አንዳንድ የፍቅር መለዋወጫዎች የመጨባበጥን ያህል ቀላል የሆኑትና አፈቀርኩት ሳይሆን አወጣሁት በሚል ቃል የተተካው። ወጣ ተብሎ የሚደረግ ነገር እንደ መጸዳዳት ያክል ስሙ እንስ አላለባችሁም?
ማራኪ አንቺም እኮ ያንን መልካም አጋጣሚ በልጅነትሽ ባታገኚ ኖሮ ይህን መሳዩን የጥበብ ፍቅር ቀብረሽ መኖር በተገደድሽ ነበር። ሌሎችም በሕይወትሽ በሕይወቴ በሕይወታችን መሆን ሲችሉ ያልሆኑት ነገሮች አብዛኞቹ የዚህ ውጤቶች ናቸው። ይህ የሃገራችን አውነት በመሆኑ ብዙዎቻችን በኪሳራ ነው የምንንቀሳቀሰው። መፍትሄው ነቃ ብሎ መንገድ ማስተካከል ነው ረፈደብን የምንልና ቁጭት የሚንጠን ለመጪው አስበን ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ስህተታችንን አጉልቶ ማየቱ ሳይሆን የስህተታችን መሰረቱን መመርመርና መፍትሔ መፈለጉ ይበጀናል።
እንደዘመኑ እድገትና መረዳት ፍቅር ይኖራል። ነጻ ማህበረሰብ በመኖሩ ብዙ ነገሮች በቀላሉ በመገኘታቸውና የመገናኛ ቴክኖሎጂም ሊታለም ከሚችለው በላይ በማደጉ ፍቅረኛሞች ሊነፋፈቁ፣ ሊፈላለጉና ፈታኝ በሆነ ወቅት አንዳቸው ለሌላኛው ሊያደርጉ የሚችሉት ሁኔታዎች ካለፈው በእጅጉ የቀለሉ በመሆናቸው የድሮው አይነት ፍቅር መጽሀፍ ላይ ሊቀር ግዱ ነው። ይሁን እንጂ ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ወጣቶችን ካገር አገር ማገናኘትና የፍቅር ድልድይ ሊሆን በመቻሉ አጠቃቀሙን ካወቅንበት መልካም አጋጣሚም ነው። እስኪ ፓልቶክን ብቻ እንኳን አስቢው። ሀገራችን ውስጥ እንደዚህ አይነት መገናኛዎች ቢኖሩ ስንት ጠቢባን ስንት ልሂቃን ወደ አደባባይ በመጡ ነበር። የዚያኑ ያህል ዝንባሌያቸው የተመሳሰለ ወይም አስተሳሰባቸው የተቆራኘ ወጣቶች ከዚህ በመንደርደር ወደ ውቡ ፍቅር መሸጋገር በቻሉ ነበር። ስሜታዊና ምክንያታዊ ነገሮች ሲጣጣሙና አንዱ በሌላኛው ሲደምቅ አንዱ ለሌላኛው ጉልበት ሲሆነውና አንዱ ያለሌላኛው ባዶነት ሲሰማው ነው ፍቅር የምንለው። ለዚህም ነው ፍቅር የእድሜ ገደብ የሌለው። ሰው ማሰብ፣ መፈለግና መስጠት እስከቻለ ድረስ የማፍቀር አቅም አለው የምንለው። ችግኞቹ አሉ እንዲጸድቁ በመልካም ፈቃድ ራስን ለመስጠት የተዘጋጀ ስነልቡና ያስፈልገናል። ለዚህ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ደግሞ ማህበራዊና አገራዊ ድጋፍም ሊኖረን ይገባል። ወጣቱ የፍቅር ተምሳሌቱ ይቺን ታህል ነፃነት ነው የሌለው። አቦ ወጣት እኮ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ራሱ ፍቅር ነው፣ ውበት ነው፣ ፀጋ ነው ተሰፋም ነው!! ይህን ማን ይክዳል?
አየሽ ማራኪ አሁን እንዲያው አንቺ በፓልቶክ ባታገኚው ኖሮ ቹቸብዬ ሆዴ አንተም እንድትወደኝ ልጫርልህ እንዴ ብለሽ መጠየቅሽ መች ይወራ ነበር? እኔስ ይቺ ልክፍታም ልጅ ብዬ ልክ ልክሽን ልነግርሽ ማን ቢፈቅድልኝ? ሚጥሚጣስ የቹቸቤን ወንድም አምጡልኝ ብላስ መች ትጠይቅ ነበር? አረ ስንት ነገር? ኮንቼታስ ብትሆን ልቧ ቱር እያለ ማይኩ ከእጇ ስለምን ሊወረወር ይችል ነበር? የሌሎቹንም በጊዜው አወራዋለሁ ብዬ እንጂ ከረንት አፌየርሰ ውሰጥ ፍቅር እንደተላላፊ ገብቶ ናፍቆት ቅልጥ ብሏል እኮ። ጎሽ በርቱ ተዋደዱ አልሻቸው? እኔም እጨምርበታለሁ እኛ ባንዋደድ አትራፊውስ ማን ነው? ብዬም እጠይቃለሁ።
ሙያዬ ግን እኔ እምለው ይቺ ልጅ በዘዴ ደብዳቤ ባንቺ በኩል እንድጽፍላት ሁኔታውን ያመቻቸች አይመስልሽም? አረ ሰው ተንኮለኛ ነው እኮ። የኔ ነገር ደግሞ ገና አሁን ነው የባነንኩት። ውሀ ጠጪ እንኳን ሳልልሽ። አፈር ስሆን ድካሙ ለቀቀሽ? አንቺ ባትኖሪልኝ ይሄን ሁሉ ዘመድ ከየት አፍርቼው? በስተመጨረሻ መውደዴን በድጋሚ ላረጋግጥልሽና በዚህ ምርቃት ልሰናበታ።
የጠወለገቺው የፍቅር ጽጌረዳ በመተሳሰብ ጠበል ትለምልምልን!!
ተፋቅረን የምንኖርባትን አገር ተሰባስበን አንታደጋት ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳን!!

  

6 Responses to መልዕክተ ቹቸቤ ለሙያዬ ቁ 8

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>