Home » ጦማሮች፣ አስተያየቶች እና ሌሎችም... » ዘረኝነት የጀኖሳይድ እርሾ ነው! (ታሪኩ አባዳማ)

ዘረኝነት የጀኖሳይድ እርሾ ነው! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ ሰኔ 2009

Stop Genocide in Ethiopia

ከ26 ዓመታት የከፋፍለህ ግዛ ዘመን በሁዋላ ዛሬም እንደ አዲስ በዜጎች ህሊና ውስጥ የሚያስተጋባ ደወል ይሰማል። ኢትዮጵያውያን በሙዚቃ ፣ በግጥም ፣ በስዕል ፣ በጋዜጣ ፣ በፀሎት ቤቶች እና በማህበራዊ መገናኛዎች ወዘተ… በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአገር አንድነት መሰረቱ ተናግቷል በሚል መንፈስ ተጨንቀው በስጋት ውስጥ መሆናቸውን እያንፀባረቁ ነው። የስጋታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ብሎም መፍትሔው የት ላይ እንዳለ ጭምር እያመለከቱ ነው።

‘ተራሮችን ያንቀጠቀጠው’ የወያኔ ‘አንፀባራቂ ድል’ አሁን ደግሞ ገበሬውን አንቀጥቅጦ በተቀማ መሬት በፎቆች የተንቆጠቆጠ አንፀባራቂ ስጋት ፈጥሯል።

ይህን ኢትዮጵያዊ ስጋት ጠንቅቀው የሚያውቁት የገዢው ወገን የወያኔ አውራ ካድሬዎች አገሪቱ ሁለት ምርጫ ብቻ እንዳላት ደጋግመው አስገንዝበዋል። አባይ ፀሐዬ በተለያየ መድረክ ላይ እንደተናገረው የህወሀት ዘረኛ አገዛዝ እንዲወገድ መታገል “ሩዋንዳ ላይ ከደረሰው ዘር ላይ የተመረኮዘ ፍጅት የከፋ ጣጣ መጋበዝ ነው” ሲል።

ህወሀት ወይንም ፍጅት… ሰውየው ይህን ማስፈራሪያ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዋዛ ደጋግሞ እያነሳ ይፎክራል። http://www.ethiomedia.com/1016notes/7451.html

በዘመናዊ ጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ህወሀት ሁሉም አይነት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ በእጁ ነው። አየር ትራንስፖርት በሉት የብስ ካሻው ያገሪቱ ጥግ ተነስቶ ወደሌላው ጥግ ለመወንጨፍ የሚቸግረው ነገር የለም። አገሪቱ ውስጥ በዘረጋው የዘረፋ አውታር ለአሀዝ የሚያስቸግር ሀብት አከማችቷል። በህገወጥ መንገድ ከህዝብ የተዘረፈው የሀብት ክምችት ሂሳብ ለማስላት እንኳ የሚመች አለመሆኑን ማስረጃዎች ያመለክታሉ። የስርዓቱ ብኩንነት ራቁቱን ከሚወጣ ይልቅ በሆነው መንገድ ተጠቅሞ ህዝብ እያሸማቀቁ እና እየጨፈጨፉ መቀጠል ከለየለት ፍጅት ይልቅ ብቸኛው የህወሀት አማራጭ ሆኗል።

እንደ ሩዋንዳ አይነት ፍጅት ለመጠንሰስም ሆነ ለመፈፀም ተፈጥሮው የሚፈቅድለት ብሎም አቅሙ ያለው ጡንቻው የደነደነው ፣ ልቡ ያበጠበት ህወሀት ብቻ ነው። እናም በሁሉም አቅጣጫ ዝግጁ ሆኖ ጭፍጨፋውን ላለፉት 26 ዓመታት እና አሁንም በቀጣይነት ለማቀላጠፍ በተጠንቀቅ ተሰልፏል።

በርግጥም ወያኔ ከጅምላ ፍጅት የማይመለስ ክፉ አውሬ መሆኑን ባለፈው ዓመት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀመውን ግፍ ብቻ እንደ አብነት ጠቅሶ መናገር ይቻላል።

እንዲያውም በጎጥ ተደራጅቶ ለከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን መብቃት እንደሚቻል ህወሀት በግብር አረጋግጧል። የህወሀት አርአያነት ብዙ ጎጠኞችን አነቃቅቷል ፣ አበረታቷል… ትግራይን ነፃ ለማውጣት ዘገር ሰንቆ በረሀ የገባው ጎጠኛ በደሀው ልጅ የደም ኪሳራ መሪዎቹን በሀብት እና ስልጣን ለማንበሽበሽ ካበቃ የስልጣን ማማ ላይ በማቆሙ የሌሎች መሰል ጎጠኞችን አይን ስቧል። የህወሀት ለስልጣን መብቃት ብቻ ሳይሆን እንደ ባዕድ የወጉትን ህዝብ እና አገር ተቆጣጥሮ ባልተወለደ አንጀት ይሉኝታ ቢስ ዘረፋ ሲያደርግ እስከ ዛሬ መዝለቁ ጎጠኝነት ትክክለኛ አደራጃጀት ስልት ነው ወደሚል ዝንባሌ እየወሰደ ነው። በጎጥ መደራጀት የስልጣን ጥያቄን በተሳካ እና ዘላቂነት ማሳካት እንደሚያበቃም እየታመነበት ይገኛል።

ይሁንና ውሎ ሲያድር የወያኔው ስርዓት የተያያዘው የዘር ፣ የቋንቋ ፖለቲካ ጉዞ ዕድሜው ረዘመም አጠረ ዞሮ ዞሮ መዳረሻው አገር ማፍረስ መሆኑን ገሀድ እየሁነ ነው። አባይ ፀሐዬ ‘እናፈርሳታለን’ እያለ የሚፎክረው ውሸቱን አይደለም። እዚህ ፈረንጅ አገር በተባበረው የአውሮፓ እና አሜሪካ ምድር የተለያየ ዘር እና ቋንቋ ያላቸው ሰዎች በህግ ጥላ ስር በሰላም መኖራቸውን እያየ ‘እንበታትናታለን’ ብሎ የሚያስተጋባውም ፉከራውን ማድመቁ አልቀረም።

አደጋው አየገፋ መምጣቱን ደግሞ አፍቃሪ ወያኔ የሆኑ የህትመት መገናኛዎች ጭምር ህዝባዊውን ስጋት እየተጋሩ ይመስላል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ከጥቂት ሳምንታት በፊት እዚያው አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር አንድ ስብሰባ አዳራሽ ተገኝቶ ስርዓቱ ባለፉት 26 ዓመታት ያሰፈነውን ሲቃኝ…

“… የውይይቱ ተሳታፊዎች አሁን ብልሹ አሠራር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ጣራ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ‹‹ሙስና ሠፈር›› የሚል ስያሜ መሰጠቱን መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት የተወለዱ ልጆች አመለካከታቸው ጥሩ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ‹‹በእኛ ይብቃ› ብሎ ተባብሮ በትውልዱ ላይ መሥራት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ለጭቁን ሕዝቦች ነፃነት መስዋዕት የሆኑ ሰማዕታት ሰላምን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ የፍትሕ አካላት ግን የሰማዕታቱን ውጤት ለማስጠበቅ እየሠሩ ባለመሆናቸው ኅብረተሰቡ ምሬቱ መብዛቱንም ደጋግመው አንስተዋል፡፡ ፍርድ ቤት ውስጥ ትንንሽ አምባገነኖች በመኖራቸው፣ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የነበረው ቢፒአር እንኳን የውኃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡ reporter Sunday May 14 2017-05-14…”

“… በዚህ ሥርዓት የተወለዱ ልጆች አመለካከታቸው ጥሩ እንዳልሆነ ጠቁመው…” የሚለውን አስምሩበት።

ጥሩ ሆኖ ያልተገኘው ‘በዚህ ስርአት የተወለዱ ልጆች’ አመለካከት የትኛው ይሆን?

ሰው ሲፈጠር እና ነብስ ሲያውቅ ራሱን ባንድ ህብረተሰብ እና አገር ውስጥ ያገኛል። ስርዓቱ የልጆቹን የአስተሳሰብ አቅጣጫ እና አድማስ የመቅረፅ አስተዋፅኦ እንዳለው እሙን ነው። በዚህ ረገድ ብልሹ ለተባለው ባህሪ እና አመለካከት መፈጠር ሙሉ ተጠያቂ እና ሀላፊ የሚሆነው ስልጣን ጨምድዶ የያዘው የፖለቲካ ሀይል ብቻ መሆኑን አብሮ መቀበል ያሻል። ወያኔ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የማይበጅ የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ ማስቀመጥ የተጠያቂነቱን ድርሻ መውሰድ ብሎም የመፍተሔው አፈላላጊ አካል ለመሆን ያበቃል። አሳስቦኛል ብሎ የተድበሰበሰ ሀተታ ማርቀቅ አያስማማንም።

ይህን ስርዓት ያመጡት እና እንዲንሰራፋ ጎዳናውን የቀየሱት በዚህ ስርዓት የተወለዶት ‘ልጆች’ ሳይሆኑ የትናንቶቹ ጥሬ ‘ልጆች’ የዛሬዎቹ ጎጠኛ ‘አዛውንቶች’ ናቸው። እነኝህ የብልሹ ስርዓቱ አዛውንት መሀንዲሶች ስልጣናቸውን እና የነቀዘ ስርዓታቸውን ወደ ‘ልጆቹ’ ለማሸጋገር ግን ተግተው እየሰሩ ነው – እውነቱ ይኼ ነው። ‘ልጀቹ’ማ ከዚህ የነቀዘ ጎጠኛ ስርዓት ለመገላገል ትግል አቀጣጥለዋል። ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆኗን ጠንቅቀው አውቀዋል።

አሁንም ይኸው ሪፖርተር ጋዜጣ በሚቀጥለው ሳምንት ህትመቱ የሚከተለውን ሰብኳል፦

“ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖረው ኩሩውና ጀግናው ሕዝባችን በከፈለው መስዕዋትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው፡፡ ይህ የሚያኮራ ሕዝብ ከሚጠቀሱለት ተምሳሌታዊ አኩሪ ተግባራቱ ውስጥ አንዱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አጠናክሮ ዘመናትን መሻገር መቻሉ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ይህ አንድነት የተገኘው በግዳጅ ሳይሆን በፍፁም ፍላጎት ነው። በዚህም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ትልቅ ምሥል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ትልቅ ምሥል መከበር አለበት። በጽንፈኝነት ሊናድ አይገባም። የራስን አጀንዳ ከአገር በማስበለጥና ሕዝብን በመለያየት ለማበጣበጥ መሞከር፣ ባረጀና ባፈጀ ግትርነት ውስጥ ሆኖ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ማደብዘዝና አገርን ለባዕዳን ጥፋት ማመቻቸት ተቀባይነት የለውም፡፡ ሥልጣንን ለማጠባበቅ ሲባልም ሆነ ወይም ሥልጣን ፍለጋ በሚል ሰበብ አገርን ማዋረድ አይፈቀድም።”

“አንዳንዶች እንደሚያስቡት ይህ አንድነት የተገኘው በግዳጅ ሳይሆን በፍፁም ፍላጎት ነው።” ይለናል። እዚህ ላይ ጥያቄ ማንሳት ቢፈቀደልን ሪፖርተር “…አንዳንዶች…” ሲል ዳር ዳር ማለቱ እነማንን ለማስታወስ ይሆን?

“መጀመሪያ ትግሬ ከዚያ ኢትዮጵያዊ ፣ የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ምኑ ነው…” እያሉ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማሽመድመድ በቁማቸው ሲሞግቱ የነበሩትን ሙታን ማለቱ ይሆን?

ወይንስ ስለ አገሩ ክብር እና ዳር ድንበር አለመደፈር ሲል የተሰለፈውን ሰራዊት ከተገንጣይ ሀይላት ጋር በማበር ከውስጥ ቦርቡረው ፣ ከውጭ ጠላት አብረው ሲፋለሙ የነበሩትን ‘ተጋዳላይ የትግራይ ልጆች’?

ነገሩ እንዳይሆን አድርገው ካበላሹት የከራረመ መሆኑን ሪፖርተር የዘነጋው ይመስለኛል። አልኩ ባይነት ካልሆነ በስተቀር ለአማረ አረጋዊ ስለ ወያኔ ስርወ መሰረት እና ስር የሰደደ ፀረ-ኢትዮጵያ ትልም ማን ይነግረዋል?

ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ወድቋል። ለኛ ሰበር ዜና አልነበረም ፤ ግን እየዋለ እያደረ አደጋው ይበልጥ ጎልቶ እየገፋ በመምጣቱ አገር አልባ ላለመሆን ፣ ኮቴ ቢስ ላለመባል ደወሉ ሁሉንም እንቅልፍ እየነሳ ነው። ማንኛውም ነገር የመናጋት አደጋ ሊፈጠርበት የሚችለው መሰረቱ ተቦርቡሮ ጣሪያ ግድግዳውን መሸከም ሲሳነው ነው።

የኢትዮጵያ መሰረት ህዝቦቿ ናቸው ፣ ጣሪያ እና ግርግዳውም የህዝቦቿ ባህል ፣ ክፉ እና ደግ ታሪክ ፣ ሀይማኖት ፣ ጥሬ ሀብት ፣ ሰብአዊነቱ ወዘተ ናቸው። ህዝቦቿን በቋንቋ እና መንደር ከፋፍለህ ስታባላ ከርመህ ‘መከፋፈሉም ፣ መባላቱም ነውር ነው’ ብለህ ልታስተምረን የምትበቃበት ዛሬ ስልጣኔ ከየት ተከሰተልህ። በጠራራ ፀሀይ የሰረቅከውን አኩሪ ታሪኩን እና አንድነቱን ዛሬ ሲጨላልምብህ ‘ስለ አንድነት ዘብ ቆማለሁ’ ብትል ማን ያምነሀል።

የህዝቡን አንድነት ድር እና ማግ ሆኖ ያስተሳሰረውን በጎ ነገር ሁሉ ሲያጣጥሉ የከረሙ ሀይሎች ዛሬ በተግባራቸው ያፈሩ ሳይሆን የፈሩ መሆናቸውን እያስተዋልን ነን። በማን አለብኝነት የዘረፉት የአገር የህዝብ ሀብት ፣ ያፈሰሱት የንፁሀን ደም ፣ ያንገላቱት ብዙሀን ዜጋ በአጠቃላይ የግፍ ፅዋ ሞልቶ እንደ ጎርፍ መፍሰሱ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። የማይቀረው ተጠያቂነት በደለበ አስረጂ ሰነድ እና ኤግዚቢት ተሰናድቶ ፍትህ የሚባጅበትን ዕለት እየቆጠረ ነው።

ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት የለም የሚሉ የብሔረሰብ ነፃ አወጪ ‘ምሁራን’ ዛሬ ብናይ ሰበር ዜና አይሁንብን። መለስ ዜናዊ በለብለብ ወርክ ሾፕ እያጠመቀ ያዳቆናቸው ትናንሽ ሎሌዎች ኢትዮጵያ የተፈጠረችው እነሱ ከተወለዱ በሁዋላ ይመስላቸዋል።

ወያኔ እንደሚነግረን ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ወህኒ ስለሆነች እስር ቤቱን ደርምሶ እስረኛው ሁሉ ወዳሻው አቅጣጫ እንዲያመልጥ ተፈቅዶለታል። አፈፃፀሙን ለማቀላጠፍ ሲባል የነኛ እስረኛ የተባሉ ብሔረሰቦች ተጠሪ ነን ብለው ራሳቸውን የሰየሙ አውራውን ፀረ ኢትዮጵያ ድርጅት ወያኔን አጅበው ሸንጎ ተቀመጡ። ኢትዮጵያን ረገሙ ፣ ባንዲራዋን አዋረዱ። አንቀፅ 39 አውጀው ዳንኪራ ረገጡ። ኢትዮጵያዊ ማንነት ዋስ ጠበቃ የሌለው ዝባዝንኬ ነው እያሉ ደነፉ። ድርጊታቸው የሚያሰከትለውን መዘዝ ለመጠቆም የሞከሩ ዜጎችን በስድብ አዋርደው ለአስከፊ የበቀል ጥቃት አመቻቿቸው።

ስድስት ኪሎ እና አራት ኪሎ የቆሙት የነፃነት ስማዕታት ሀውልቶች ለጌጥ ከተማ ማድመቂያ እንደቆሙ የድንጋይ ጥርቦች ተቆጠሩ። በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያዊነት የሚንፀባረቅባቸው ታሪካዊ ቅርሶች ሁሉ ተንቋሸሹ። የአድዋ እና ሌሎችም ድል ቀናት ብሔራዊ በአላት ቢሆኑም ቅሉ አደባባይ ወጥቶ የሚዘክሯቸው በጎስቋላ ህይወት ቆዳቸው የተጨማደደ ከሞት የተረፉ የጥንት አርበኞች ብቻ ናቸው።

ለኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ መመኪያ የሆኑ ፀረ ቅኝ አገዛዝ ድሎች ያጎናፀፉን መሪዎች በ19ኛው ክፍለ ዘመን የግዛት ዘመናቸው ለምን የብሔር ብሔረሰብ ‘እኩልነት እስከ መገንጠል’ ብለው አላወጁም ነበር ተብለው እንዳላዋቂ ተፌዘባቸው። ጎጠኞች ከጥበብ ጥግ እንደደረሱ ሁሉ የታሪካዊ ነገስታትን ዘመን በስሜታዊ ማዕበል በሚዋዥቀው ፖለቲካ ስሌት ለማብጠልጠል ተሽቀዳደሙ።

‘ወድቃ በተነሳችው ባንዲራ…’ እያለ ከጉልበተኛ ይታደግ የነበረው ጨዋ ኩሩ ህዝብ አቤቱታ አለኝ ብሎ ባንዲራውን አንግቦ አደባባይ ቢወጣ ‘ካልደከመው ባንዲራውን ቀስሮ ይዙር’ የሚል መሪ ማላገጫ ሆነ። ባንዲራው ከጨርቅነት የዘለለ ትርጉም የለውም የሚል ሲታከልበት ‘ይኼ ነገር እንዴት ነው’ ብሎ ግራ የተጋባው ዜጋ ‘ነፍጠኛ’ እየተባለ ተዋከበ። ጉዳዩ ከማንቋሸሽ አልፎ በጥይት ወደ መረፍረፍ ተሸጋገረ።

የወያኔ ዘመቻ ኢትዮጵያን ከደርግ ወታደራዊ ስርዓት ፈልቅቆ ማውጣት ብቻ ሳይሆን አገራዊ ማንነትንም አለርህራሄ የመጨፍለቅ ተልእኮ ነበረው። የደርግን ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር መጣል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ዘመቻው ግን ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ አነጣጠረ። መሪያቸው ‘መጀመሪያ ትግራይ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ነኝ’ ሲል አገራዊ ማንነት ፋይዳ ቢስ ፣ የወረደ ‘የነፍጠኞች ተረት’ መሆኑን ይፋ አድርጓል። አፍታ ሳይቆይ እንዳየነው ትናንት በዜግነት ማንነቱ ይኮራል ብለን የጠብቅነው ሁሉ ባንድ ጀምበር የጎጥ ድርጅት ለመፈልፈል እንቅልፍ አጣ።

ደርግ በህወሀት ሲተካ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆናል ብለው የጠበቁ ወገኖች አልጠፉም። ችግሩ ግን የጎጠኛው ሀይል ተልእኮ ኢትዮጵያን ከመሰረቱ አናግቶ ህልውናዋን አደጋ ላይ መጣል (እነ ሪፖርተርን ሳይቀር ማስጋት ደረጃ የደረሰ) መሆኑን ለመገንዘብ ረጅም ዘመን የወሰደባቸውም አሉ።

በቅድመ 66 የብዙሀኑ ለውጥ አራማጅ ወጣት የፖለቲካ አመለካከቱ ከጅምላ ድብስብስ ንድፈ ሀሳቦች የጠራ አልነበረም። ችግሮች መኖራቸው ተጨባጭ ቢሆንም መፍትሔ እየተባሉ ከያቅጣጫው የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ግን ተጨባጭነት የሚጎድላቸው በስሜታዊነት የሚነዱ ነበሩ። የመንግስት ስልጣን ጥያቄ ማራኪ በሆኑ መፈክሮች ተውቦ በሚበተን ወረቀት ከመነዛቱ በስተቀር የምትሉትን ‘ህዝባዊ መንግስት’ አምጡ እና ስልጣን ተረከቡ ቢባል ርክክቡን ለማከናወን እኔ አለሁ የሚል በወጉ የተራጀ ሀይል ከቶ አልነበረም። ይህም በመሆኑ ማራኪ መፈክሮቹ ለአገሪቱ ካመጡት ጥቅም ይልቅ ለማያቋርጥ ውዥንብር እና ዛሬ ለምንገኝበት ማጥ ህሊናዊ እና ቁሳዊ መሰረት አንጥፈዋል።

በዩንቨርሲቲዎች እና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ሲስተጋቡ የቆዩት መፈክሮች አንዳችም የታወቀ ፖለቲካዊ አመራር አልነበራቸውም። ይስተጋቡ የነበሩት መፈክሮች ከአገር ህልውና አንፃር የቅርብ እና የሩቅ ጥቅማቸው እና መዘዛቸው ተነድፎ ግልፅ እና አሻሚነት በሌለው መልኩ ሊሰራጭ የሚችልበት መድረክም አልነበረም። ፀረ-ፊውዳል አብዮተኞች በነ ቼ ጉቨራ አምሳል ፀጉር አጎፍሮ ጥቅሶችን ከማነብነብ በስተቀር አሁንም አገሪቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ውነት መሰረት ያደረገ እና ህልውናዋን በማያሻማ መንገድ ያረጋገጠ አቋም አልነበረም።

ፍትሀዊ የፖሊቲካ ስርዓት ጥያቄ አንስቶ አገርን ወደ ተሻለ ዕድገት ለማሸጋገር አልሞ መቆም አንድ ነገር ነው ፤ የተለመደ አካሄድም ነው። በስንት ውጣ ውረድ የተቆረቆረን አገር ፣ በስንት ዜጎች ደም ተከብሮ የቆየን ነፃነት እንዳልነበር አድርጎ አንዳችም መሰረት በሌለው የፖለቲካ ዕብደት አገርን ለማፍረስ መነሳት ግን ውሎ አድሮ እንደምናየው አርቆ ማየት የጎደለው አስተሳሰብ ነው።

መሬት ላራሹ ፤ ህዝባዊ መንግስት አሁኑኑ ፣ የብሔረሰቦች መብት ይረጋገጥ… ፋኖ ተሰማራ!

የያኔው የተማሪ ንቅናቄ አገሪቱ ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን በሚያነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ በቅጡ ያልታሰበባቸው ለማሰብም ተገቢው መድረክ ያልተበጀላቸው ጉዳዮች ተሸንቁረው ይንከባለሉ እንደነበር ዛሬ ላይ ሆነን መጥቀሱ በቅንነት አገሩን ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ለማሸጋገር ይመኝ የነበረውን ትውልድ ለመክሰስ አይደለም። ትውልዱ ዘመኑ በፈቀደለት የግንዛቤ አድማስ ተወስኖ ማንሳት የሚገባውን ጥያቄ አስተጋብቷል። ተነስቶ ካየነው ጥያቄ በላይ ርቆ ለመሄድ እንዳይችል ያገዱት አያሌ ምክንያቶች ቢኖሩም ትልቁ ግን የፖለቲካ ዕውቀት ከነበራዊ እውነት ጋር ተገናዝቦ እንዴት ለኛ ጥቅም ይውላል የሚውን ከመፍታቱ ላይ ነበር።

እንዲህ ነው እንግዲህ ጥቃቅኗ ፀረ-አገር አዝማሚያ እያቆጠቆጠች ስትከማች ተጠራቅማ ዛሬ በገሀድ አገር እንበታትናለን የሚሉ ሰዎች ደረታቸውን ነፍተው ለመውጣት የበቁት ፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም እያሉ ትናንሽ የመለስ ዜናዊ ምስለኔዎች የሚመፃደቁት።

ጉዳዪ ሰበር ዜና አይደለም።

በዘር እና ቋንቋ ግንድ ማንነት የተነሳ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እና ፍጅት ሲፈፀም ሀያ አምስት አመታት ተቆጠሩ። እንደ ቀልድ እያሰለሰ ግን አለማቋረጥ ከአገር ቤት የሚደርሰን ዜና እንደሚጠቁመው ‘በዚህ በዚያ ክልል በዚህ በዚያ ብሔረሰብ አባላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተሰነዘረ…’ የሚል ዘገባ ነው። ዘር ላይ አልሞ የሚመጣ ጅምላ ፍጅት ባንድ ጀምበር የሚፈነዳ ክስተት አይደለም። በዘር ክፍፍል ተጠቃሚ መሆናቸውን ለራሳቸው ያረጋገጡ አበጋዞች የተከሉት የጥላቻ ችግኝ ለምልሞ እና የሞት ጥላ አንዠርግጎ መላ አገሪቱን ጨለማ ውስጥ የሚከተው በሂደት ነው።

ካንድ ጎጥ ተነስተው መላ አገሪቱን በከፋፍለህ ግዛ መርህ የሚያሰቃዩት ሀይሎች ከዚህ ሌላ ምን ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ እንደ ዋዛ የሚታለፍ ጉዳይ ሳይሆን እጅግ አደገኛ መሆኑን ምን ያህል እንደምንረዳ አላውቅም። ወያኔ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በደርግ ዘመን በየጎጡ ጫካ መሽገው ነፍጥ ሲወለውሉ የቆዩ አማፂያን እናም የጎጥ ገበያ መድራቱን በማጤን ባንድ ጀምበር የተፈለፈሉ ድርጅቶች አንቀፅ 39 ሰነድ ላይ እስኪፈርሙ ድረስ በእንግድነት ተምነሽንሸው በተለጣፊ ነፃ አውጪዎች እየተተኩ በያቅጣጫው ተሸኝተዋል። ጥቂቶቹ በቦሌ በደርሶ አይመለስ ቲኬት ሲሸኙ ብዙሀኑ ለወህኒ ወይንም ለስደት ተዳርገዋል።

በጎጥ ለመደራጀት ብዙ ውጣ ውረድ አያስፈልገውም። ፍልስፍና እና የፖለቲካ ንቃት ፣ አለም አቀፍ ግንኙነት እና የጂኦ ፖለቲካ ትንተና ብቃት አያሻውም። በዘር ወይንም ሀይማኖት ከለላ ለመደራጀት መሰረታዊው መስፈርቱ ዘርህን ቆጥረህ ወይንም እምነትህን መንጋ ተከትለህ መሰለፍ ብቻ ነው። በዘር የመጣ ጥሪ በፈጠራ ታሪክ እና በተቀመሙ ውሸቶች ጭምር የተከሸነ በመሆኑ ናላ የማጦዝ ሀይል አለው። በዘር ስትሰበሰብ ደግሞ ራስህን ከሌላው ዘር መነጠል እና መጥቀም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የምታነጣጥርባቸው ሌሎች ወገኖች መኖራቸው ግድ ነው። ከሌሎች ጋር የጎሪጥ መተያየት ፣ እንካ ሰላንታ መለዋወጥ ፣ ዘለፋ  ሽርደዳ ብሎም ጡንቻ ፈርጠም ሲል ቀስ በቀስ ወደ ግብግብ መዝለቅ… ዘር ለዘር። ህወሀት በትግራይ ፣ ኦነግ ፣ ሲዳማ እና ሱማሌ ክልል የነበሩትን መጥቀሱ ይበቃል።

የዘር ድርጅት ብቃት የሚለካው በሌሎች ዘሮች ላይ በሚሰነዝረው መራራ ፣ ፀያፍ እና አሳፋሪ ዘለፋዎች ልክ ነው። የጎጥ ድርጅት መሪዎች ለተከታዮቻቸው በቀዳሚነት የሚያስተምሩት ብሔራዊ ማንነትን መክዳት ፣ ማጥላላት እና ማጥቃት ነው።

አገር ከነቆየ ችግሮቹ ጋር መሰረቱን ጥሏል። በፅናት ለመቀጠል ችግሮች በየደረጃው ጊዜያቸውን ጠብቀው መፈተታት እንዳለባቸው ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰብ ግንኙነት ችግር አለ የሚሉ አሉ። ጥያቄው ለምን ተነሳ ማለት አይቻልም። ጥያቄው ከተነሳ የጥያቄውን ብልት አወራርዶ ፈትሾ ተገቢውን መፍትሔ መስጠት ያንድ ብልህ እና በሳል ህዝብ ሀላፊነት ነው። ጥያቄ ባነሱ ማግስት አገር አፍርሳለሁ ብሎ መጋበዝ ግን ያችን አገር ለማጥፋት ከሚያደቡ የለየላቸው ጠላቶች ድርጊት ተለይቶ መታየት የለበትም። ጠላት አገርህን የሚያጠቃው ለጥፋት እንጂ እንደሆነ ሁሉ ማናቻውም ፀረ አገር የሆነ አገር በቀል እንቅስቃሴ በዚሁ መልክ ሊታይ ይገበዋል። የሁለቱም ግብ አገር ማፍረስ መሆኑ ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል።

ጎጠኝነት የጄኖሳይድ እርሾ መሆኑን የሚክድ ካለ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አገላብጦ ይመርምር።

መጣጥፌን የምደመድመው የሩዋንዳን እልቂት በአይኑ ለመታዘብ የበቃው የደቡብ አፍሪቃ ጋዜጠኛ ፈርገል ኪን “የደም ዘመን፡ የሩዋንዳው ጉዞ” (Season of Blood: A Rwandan Journey.) በሚል ርዕስ ካሳተመው እውነተኛ ታሪክ መፅሀፍ ነው። ስጋት አለን የምትሉ መፅሐፉን አንብቡት…

The general consensus among those of us watching the pictures and those who had taken them was that Rwanda was a madhouse, a primitive torture chamber where rival tribes were busy settling ancient scores.

Fergal Keane (Season of Blood: A Rwandan Journey.)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Click here to connect!