አገሩማ የእኔ ነው

December 17, 2011

Click here for PDF

ተመስገን ደሳለኝ (ፍትህ ጋዜጣ)

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመፃፍ ያሰብኩት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡ ..ጓደኞቼን መልሱልኝ.. ብዬ በፃፍኩ በሳምንቱ ማለቴ ነው፡፡ ሆኖም በዛ ሳምንት በይደር የማይታለፍ አፋጣኝ መልስ የሚያስፈልገው ጉዳይ አጋጠመኝ፡፡ የ..አኬልዳማ.. ፊልም፡፡ ስለዚህ ይህን ርዕስ በይደር አልፌው የዛኛውን ሳምንት ለአኬልዳማ ሰዋሁት፡፡ እናም ጠቢቡ ..ቦ ጊዜ ለኩሉ.. እንዳለው ሁሉ እነሆም ጊዜው ሆነና የተዘለለው ርዕስ ተነሳ፡፡

አዎ.. ርዕሰ ጉዳዩ ..አገሩማ የእኔ ነው.. የሚል ነው፡፡ መቼም ..የትኛው ሀገር?.. የሚል ጥያቄ የሚያነሳ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ ቢኖርም አይፈርድበትም፡፡ ምክንያቱም መንግስቱ ኃ/ማርያም ወልዴም ሆኑ መለስ ዜናዊ አስረስ ዋነኛው የመንግስት ስራ ..ዜጎችን ከሀገር ማሰደድ.. ይመስል ሚሊዮኖችን ከሀገር ለማባረር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰርተዋልና ነው፡፡ መንጌ ለድፍን 17 ዓመት፤ መለስ ደግሞ 20ኛውን አመት ጨርሰው 21ኛውን ጀምረውታል፡፡

የሆነ ሆኖ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ከዚህ ቀደም (ሁለቱ ወዳጆቼ ..የተወዳጇ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መጋቢ ኤዲተር መስፍን ነጋሽ መስከረም 30 ቀን 2002 በወጣችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ..ይህ አገር የማን ነው?.. የሚል ጽሁፍ ማስነበቡ አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአውራምባ ታይምስ ሜኔጂንግ ኤዲተር ዳዊት ከበደ ..እውነት ግን ይህ አገር የማነው?.. በሚል ርዕስ መስከረም 13/2004 እና ህዳር 09/2004 በሁለት ክፍል የፃፋቸውን መጣጥፎች ተከትሎ ማራኪ መጽሔት እና ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣም በዚሁ ርዕስ ላይ ማተኮራቸው ነው፡፡

አዎ.. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ..ይህ አገር የማነው?.. የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዕዝነ ልቦና እየተመላለሰ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ላይ መወያየቱ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ እናም ብንወያይበት መልካም ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከዛ በፊት ግን ደግሜ ደጋግሜ ልንገርህና አገሩ የእኔ ነው፡፡ እመነኝ አገሩ የአንተ ነው፡፡

ይሄ እውነት ቢሆንም ግን ተነጋግረን መተማመን ያለብን ጉዳዮች አሉ፡፡ ልክ እንዲህ እንደ ዛሬው ባይተዋርነት ሲሰማህ፣ መገለል ሲደርስብህ፣ እንደመጤ ስትታይ መራራቁ ሳይሆን ተቀራርቦ መነጋገሩ እና መደጋገፉ ጠቀሜታው ብዙ ነው፡፡ እናም መጀመሪያ የአገሪቷን የባለቤትነት ጥያቄ እና የመንግስትን የስራ ግዴታ ነጣጥለህ ተረዳው፡፡ ያን ጊዜ እኔም እልሀለሁ ጥያቄህ ወይም ተቃውሞክ ..ይህ ሀገር የማነው?.. የሚል መሆኑ ይቀርና ..የመንግስት መብትና ግዴታ እስከምን ድረስ ነው?.. የሚል ይሆናል፡፡

መጀመሪያ የአዲስ ነገሩ ትንታግ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ከሀገር ከመውጣቱ በፊት ..ይህ አገር የማነው?.. በሚል ርዕስ ባስነበበን ድንቅ መጣጥፍ ላይ ያሰፈረውን እንይ ..ይህንን ጥያቄ በዚህ ሰሞን እንዳስታውሰው ያደረገኝ በአገራቸው ጉዳይ መነጋገርም ሆነ መሳተፍ ተስፋ አስቆርጧቸው ያገኘኋቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ እውነት ግን ይህ አገር የማን ነው?.. ይልና መስፍን ይጠይቃል፡፡ ጠይቆ ሲያበቃም፤ ..ቀላሉ መልስ ፣የሁላችንም፣ የሚል ነው፡፡ መሆን ያለበትም እርሱ ነው፡፡.. ሲል ራሱ ይመልሳል፡፡

መስፍን ነጋሽ ይህንን ጥያቄ ለማንሳት የተገደደው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም መራሹ አምባገነን ስርዓት፤ ወደ መለስ ዜናዊ መራሹ አምባገነን ስርዓት የተደረገው ሽግግር የስም ለውጥ ብቻ በመሆኑ መሮት ነው፡፡ በእርግጥ ስለመንጌ ጨካኝና ጨፍጫፊነት ለመረዳት ተንታኝ አያስፈልግህም፡፡ ምክንያቱም ራሱ መንጌ ይህንን ክዶ አያውቅምና፡፡ ለነገሩ እኮ የእነ መንግሰቱ ኃ/ማሪያም ስራ ልካድ ቢባልም የሚካድ አይደለም፤ የዛ ዘመን ሰቆቃ፡፡ እናም በዛ የሰቆቃ ዘመን መቃወም ቀርቶ፤ ለመቃወም በልብህ ብታስብ እንኳ ውጤቱ የጥይት አረር በግንባርህ ማስተናገድ ይሆናል፡፡ መቼም በዚህ ሁኔታ ህይወትህ አልፎ በመንግስት እጅ ስለመሞትህ ምንም አይነት ..አጣሪ ኮሚቴ.. ማቋቋምም አያስፈልግም፡፡ እለቱኑ እራሱ መንግስት በአንደበቱ (በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ) አብዮታዊ እርምጃ እንደተወሰደብህ ያውጃል፡፡ ያውም በይርጋ ዱባለ ሙዚቃ አጅቦ ..የፍየል ወጠጤ…..

የመለስ መንግስት ግን ይሄን አያደርግም፡፡ በጭራሽ አያደርግም፡፡ ድንገት አድርጎት ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ..እኔ አልገደልኩም፤ አይኔን ግንባር ያድርገው.. ብሎ ..ምሎ ተገዝቶ.. ይከራከራል፡፡ ክርክሩ አላዋጣ ሲለው ደግሞ የስልት ለውጥ ያደረጋል፡፡ ወይ የጎዳና ላይ ነውጠኛ፤ አሊያም ባንክ ዘራፊ ስለሆነ ነው የገደልኩት ወደሚል ማለቴ ነው፡፡ ሆኖም ይሄንን ብሎም ጫና ከበዛበት አጣሪ ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡ ይሄን ስል ግን አጣሪ ኮሚቴው በሚያቀርበው ሪፖርት ተመስርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ለማለት እንዳልሆነ ሊገባህ ይገባል፡፡ ይሄማ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህማ ከሆነ በሚቀጥለው ማን ደፍሮ ይተኩሳል? ስለዚህም ልክ በ97ቱ ምርጫ ጦስ ጡምቡሳስ ህይወታቸውን ያጡ ንፁሃን ዜጐችን ግድያ ህጋዊነት እና ህገወጥነት እንዲያጣራ ተቋቁሞ እንደነበረው አይነት ኮሚቴ ይቋቋምና ተፈጭቶ ተጋግሮ የበሰለ መረጃ ሲገመግም ይከርማል፡፡

ወዳጄ፡- ይሄ ኮሚቴም አጣርቶ ሲያበቃ የደረሰበት የሪፖርቱ መደምደሚያ ..መንግስት ትርፍ ሀይል ተጠቅሟል.. የሚል ቢሆንም አይድነቅህ፡፡ ምክንያቱም ለዛ ትርፍ ሀይል ማንም የሚጠየቅ የለምና፡፡ እስኪ እስከዛሬ በድፍን ኢትዮጵያ ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን አንድ እንኳ አዛዥም ይሁን ታዛዥ ለፍርድ ቀርቦ ያውቃል? መቼም ..አዎ.. ቀርቦ ያውቃል.. ብለህ እንደማትከራከር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ በ1993ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ አዛዥ ወርቅነህ ገበየው ራሳቸው በአንደበታቸው ..አደጋውን ያደረሱት ያልሰለጠኑ ፖሊሶች ናቸው.. ብለው መስክረው አንኳ ማን ተጠየቀ? ማንም፡፡ እዚህች ጋር ..ህግ አለማወቅ በህግ ከመጠየቅ አያድንም.. የምትለዋን የህግ መርህ እንዳትዘነጋት፡፡

አየህ.. ይህንን ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ በደርግ እና በኢህአዴግ መካከል ያለው ልዩነት የስልት እንጂ የባህሪ አይደለም፡፡ ደርግ ነፃ ሚዲያ የሚባል እንዳይኖር በአዋጅ ሲከለክል፤ ኢህአዴግ ደግሞ በአዋጅ ፈቅዷል፡፡ ሆኖም ሚዲያዎቹ እየተዘጉ ጋዜጠኞቹም የነፍስ አድን ሽሽት ሲያደርጉ፤ መንግስት ሆዬ.. ምን የሚል ይመስልሃል፡፡ እንደ ደርጉ ..የፍየል ወጠጤ….. እየጋበዘህ ሀላፊነቱን የሚወስድ እንዳይመስልህ፡፡ ይልቁንም ..ከስረው ነው.. ወይም ..የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው የተሰደዱት.. ይልና ራሱን ጲላጦስ ያደርጋል፡፡ ይሄ ነው የመስፍን ነጋሽም ሆነ የዳዊት ከበደ ..ይህ አገር የማነው?.. የሚል የብሶት ጥያቄ መነሻ፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግም ቢሆን ..አባቴ.. ብሶት ነው ብሏሀል፡፡ ..ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት…..

የሆነ ሆኖ መንግስት ሀገርህን የሚነጥቅበትን ስልት መስፍን ነጋሽ ሲፅፍልህ ፡-

…..እነዚህ መናፍስት የእነርሱን አንደኛ ደረጃ ባለቤትነት ለማረጋገጥ በየትም ቦታ፣ የትኛውንም መንገድ ይጠቀማሉ፤ በማንም ላይ ስም ያጠፋሉ፣ የሐሰት ማስረጃ ይፈበርካሉ፣ ይዋሻሉ፣ ያስፈራራሉ፣ ይከሳሉ፣ ይጮኻሉ፣ ይቀጥፋሉ፣ ያጭበረብራሉ… ያወራሉ፣ ይጽፋሉ፣ ያማሉ፣ ይገድላሉ…፡፡.. ይልሃል፡፡
ዳዊት ከበደ ደግሞ በክፍል አንዱ ..እውነት ግን ይህ አገር የማን ነው?.. ፅሁፉ ላይ ሀገሪቱ የማን እንደሆነች እንዲህ ሲል ይነግርሃል፡-

…..እንደ እኛ እምነት ከሆነ ይህቺ የተወለድንባት፣ በተወለድንበት ቅፅበት የዜግነት ክብር የተጎናፀፍንባት፣ ያደግንባት፣ የተማርንባት፣ የምንሰራባት፣ መከፋቷ የሚያስከፋን፣ ደስታዋ የሚያስደስተን፣ ክብሯ የሚያስከብረን፣ ውርደቷ ውርደት የሚሆንብን የመጀመሪያዋም የመጨረሻዋም ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በማንም በምንም
የማትለወጥ፣ በማንም በምንም የማትተካ፣ አምሳላችን ከአፈሯ የተቀረፀባት ውድ አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡..

የመስፍንም ሆነ የዳዊት ሀገሪቱ የማን መሆኗ ድምዳሜ ከሁላችንም ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ከእኔም፣ ከአንተም፣ ከመስፍንም፣ ከዳዊትም፣ ከመለስም…፡፡ ምናልባት ልዩነት ሊፈጠር የሚችለው በሀገሪቱ የመኖር እና ያለመኖር መብት ..ሰጪ .. እና ..ነሺ.. መለስ እና ጓደኞቻቸው ናቸው የሚል ነገር ከተነሳ ነው፡፡

በእርግጥ እነዚህ ትንታግ ጋዜጠኞች እንዲህ ሲሉ አልሰማሁም፡፡ እንዲያውም የመስፍን ትንተና ይሄንን በግልፅ የሚፃረር ነው፡፡ ..በግሌ ማንም ኢትዮጵያ የእኔም ጭምር መሆኗን እንዲነግረኝ ወይም ይህን እንዲያረጋግጥልኝ አልፈልግም፤ አልፈቅድምም፡፡.. ይሄ ሰማይ ክፍ፤ ምድር ዝቅ ቢል የማይቀር እውነት ነው፡፡

አንተም መከተል እና ማጤን ያለብህ ይሄንን ነው፡፡ መስፍን ያለህን ማለቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአንተ ነች እንዲል ለማንም እድል አትስጥ፡፡ ለኢህአዴግም ቢሆን፡፡ ይሄም ሌላ እውነት ነው፡፡ አረ ለመሆኑ.. ኢህአዴግ ማን ሆነና ነው ኢትዮጵያዊነትን ሰጪ እና ነሺ ያደረገው? ብቻ ይሄ እንዲሆን ከፈቀድክ ኢህአዴግን እንደ ፓርቲ ሳይሆን እንደ አምላክ ተቀብለከዋል ማለት ነው፡፡ አየህ ከገባህ.. ስህተቱ እዚህ ድረስ ይሄዳል፡፡ አምላክን እና ፓርቲን እስከመቀላቀል፡፡

እናም መቼም ይሁን መቼ ..ይች ሀገር የማን ነች?.. ብለህ አጠይቅ፡፡ ይች ሀገር የአንተ ለመሆኗ ማረጋገጫ አያስፈልግህምና፡፡ ለምን? ብለህም አትጠይቅ፡፡ በቃ.. ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያዊ ነውና፡፡ በተቀረ መንግስት ሲገፋ መልሰህ ግፋው እንጂ ሀገሪቱ የማን ነች? የእኔ ወይስ የእነሱ? ብለህ አትጨነቅ፡፡ በእንደዚህ አይነት ወቅት ከአንተ የሚጠበቀው መጨነቅ ሳይሆን የተነጠከውን ኢትዮጵያዊነት መልሰህ ነጥቀህ መውሰድ ነው፡፡ አሸንፈህ መንጠቅ ባትችል እንኳ ታግሎ መውደቁም ክብር ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ተሞክሮዎች አሉልህ፡፡ ከእነሱም በቂ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ፡፡

ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስን አርዕያ ልታደርጋቸው ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም እሳቸው በጃንሆይ መጨረሻም ሆነ በደርግ መጀመሪያ በሀገሪቱ ላይ መኖር እንዳይችሉ ሲደረጉ ..ይህ ሀገር የማን ነው?.. ብለው አልጠየቁም፡፡ ምንድር ነው ያደረጉት?

መለስ ያደረጉት ነገር ቢኖር ልክ እንደ እሳቸው ከተገፉ ጓደኞቻቸው ጋር ተሰባስበው ደደቢት ወደሚባለው በረሃ ወረዱና ለደርጉ መልዕክት ላኩበት፡፡ በእርግጥ መልእክታቸው ..ይህ ሀገር የማን ነው?.. የሚል አይደለም፤ ..ናና ሞክረኝ.. የሚል እንጂ፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ መለስም ሆኑ ጓደኞቻቸው፤ መንግስቱ ኃ/ማርያም እና ደርግ የሀገር ባለቤትነትን ሰጪ እና ነሺ እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ማወቃቸው ነው፡፡ ይሄ እውቀታቸውም የትም እንዲሄዱ አላስገደዳቸውም፡፡ ነገር ግን በግድ መብታቸውን እንዲያስከብሩ አነሳስቷቸዋል፡፡ ይሄ ነው አርአያ ሊሆንክ የሚገባው፡፡

የኢህአፓም ልጆች ቢሆኑ መንግስቱ ኃ/ማርያም በሀገሪቱ ላይ አዛዥ ናዛዥ ሲሆኑ ..ይህ ሀገር የማን ነው?.. ሲሉ አልጠየቁም፡፡ ምክንያቱም ኢህአፓም ደርግም የፖለቲካ ድርጅቶች እንጂ አንዱ ኢትዮጵያዊነትን ሰጪ ሌላው ተቀባይ ላለመሆናቸው ነጋሪ አላሻቸውም፡፡ እናም ኢህአፓ የትም ሳይሄድ የተነጠቀውን በሀገሩ የመኖር መብቱን ለማስመለስ፡-

ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆቺሚኒ፤ እንደቼጉቬራ ታሪክ ልትሰራ

እያለ የቻለውን ሞክሯል፡፡ ቁም ነገሩ መሸነፍና ማሸነፍ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ችግሩን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ቁምነገሩ ሀገርን እና መንግስትን ነጣጥሎ ማየቱ ላይ ነው፡፡ ሀገር ሌላ፤ የተወሰኑ ጉልበተኛ ሰዎች ተሰባስበው የመሰረቱት መንግስት ሌላ፡፡ ያውም በጉልበት የተመሰረተ፡፡

እንደምታውቀው ትላንት የብሔር ብሔረሰብ ቀን ተብሎ በጭፈራ ሲከበር ነበር፡፡ ከሳምንት በላይ ለሚሆኑ ቀናትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ደጋግመው እየቀረቡ ..ህገ-መንግስታችን አብሮነታችን አንድነታችን….. ሲሉ ነበር፡፡ እሳቸው ይሄን ካሉ በኋላ ደግሞ ከ80 ብሔሮች የአንዱ ብሔር ባህላዊ ጭፈራ ይከተላል፡፡ ይሄ ባዮሎጂም ፊዚክስም አይደለም፡፡ ይሄ የአቶ መለስ ፖለቲካ ነው፡፡ እናም የመቀበልም ያለመቀበልም መብት አለህ፡፡ ይሄንን መብት ያገኘኸው ደግሞ ማንም ታግሎልህ አይደለም፡፡ በተፈጥሮ ያገኘኸው ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነትህ፡፡ ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች ጥያቄያቸው ባሀላዊ ጭፈራዎቻችን ስለምን በቴሌቪዥን አልታዩም የሚል አይደለም፡፡

ጭፈራው እኮ ድሮም በየመንደራቸው የነበረ ነው፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በቴሌቪዥን መቅረቡ ነው፡፡ ልክ አንድ ድምፃዊ፤ አዲስ ካሴት ያወጣል፤ለዘፈኖቹም ክሊፕ ይሰራለታል፤ ወይም አይሰራለትም፡፡ በቃ ይሄ ነው ልዩነቱ፤ ከኢህአዴግ በፊት በነበሩ ገዥዎች ዘመን ማንም ሰው የራሱን ብሄር ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታል፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ ለየብሄሩ ጨዋታ ኪሊፕ ሰራለት፡፡ በተረፈ የብሄር ፌደራሊዝሙን እርሳው፡፡ መለስ ወይም በረከት በየትኛውም ክልል ስልጣን ጣልቃ መግባት ከፈለጉ ፌድራሊዝሙ አግዷቸው አያውቅም፡፡

አሁን ስለ ጀመርነው ለመብት የመታገል ጥንካሬ እናውራ፡፡ ሞራልህም ይገነባ ዘንድ ለምሳሌ አሞራው (ወልደገሪማ) የሚባለው ዝነኛ የህወሓት ታጋይ በደርግ መንግስት ቁጥጥር ስር ውሎ የተሰዋለትን እውነት ላስታውስህ፡፡ አሞራው የማዕከላዊ መርማሪዎችን (ማዕከላዊ ያሉ ሰዎች እንኳ መርማሪ ከሚባሉ ገራፊ ቢባሉ ነው በደንብ የሚገልፃቸው) በመፍራት አንዳች ያመጣው የአቋም ለውጥ የለም፡፡ መቼም አሞራው እንዲያ ሽንጡን ገትሮ ስለአቋሙ ሲናገር ኢትዮጵያ ሀገሩ ..ህገ መንግስት.. እንዳላት ጠፍቶ አይደለም፡፡ በ1979 በኢሰፓ ፊት-አውራሪነት የፀደቀ ህገ-መንግስት እንደነበረ በደንብ ያውቃል፡፡ ሆኖም ህገ-መንግስቱን የመቀበልም ያለመቀበልም የተፈጥሮ መብቱ ስለሆነ አልተቀበለውምና ተቃውመው፡፡ ለእኔ ይሄ ጥንካሬ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ስለአሞራው ከተነሳ ብዙ መነጋገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አሞራው የሚያምንበት ከሆነ የደርግ፤ የህወሓት ህግ እያለ ህግ አያማርጥም፡፡ በእርግጥ በቴሌቪዥን.. ታሪኩ በቀረበ ጊዜ የደርግን እንጂ የህወሃትን ህግወጥ ድርጊት መቃወሙ አልተገለፀምና ስለዚህ ጉዳይ እኔ ልንገርህ፡-

ደህና.. አሞራው የተንቤን ልጅ ሲሆን ትግሉን የተቀላቀለው በ1973 መጀመሪያ ነው፡፡ በወቅቱም ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር ያለው ግንኙነት የአለቃ እና የምንዝር በመሆኑ ማንኛውም የህወሓት ታጋይ የሻዕቢያን ህገ-ወጥ ድርጊት እንዳይቃወም (በሌላ አማርኛ ሻዕቢያን ማስቀየም ፍፁም ክልክል ነው) የሚያደርግ ህወሓት ያልተፃፈ ህግ ነበረው፡፡ ከእለታት አንድ ቀንም በአሞራው የሚመራ የህወሓት ታጋይ የሻዕቢያን ይዞታ እንዲጠብቅ ወደ ኤርትራ ምድር ይላካል፡፡ እነ አሞራውም የህወሓት አለቆቻቸውን ትእዛዝ አክብረው ሻዕቢያን ሲያገለግሉ ይቆያሉ፡፡ ሆኖም በአንድ አጋጣሚ የሻዕቢያ ታጋይ የህወሓት ታጋዮች ላይ ህገወጥ ነገር ሲፈፅም አሞራው ይመለከታል፡፡ ይሄን ጊዜም አሞራው የህወሓት ያልተፃፈ ህግ (ሻዕቢያን ማገልገል) የሚባለው ነገር ትዝ አላለውም፡፡ ትዝ ያለው ጭቆናን ያለመቀበል ተፈጥሮአዊ መብቱ ነውና የሻዕቢያውን ታጋይ በታጠቀው መሳሪያ ግንባሩን ብሎ ገደለው፡፡ የህወሓት ሰዎችም ሻዕቢያን ለማስደሰት አሞራው ላይ የሞት ፍርድ ለመወሰን ሲዘጋጁ አንድ መስራች ታጋይ እሳቸው ወደ ሚቆጣጠሩት አካባቢ በመውሰድ ህይወቱን አተረፉት፡፡ (ቃል በቃል እኒህ ታጋይ እንደነገሩኝ ነው ያወረድኩልህ)

ኢህአዴግ እና ኢቲቪ ግን ስለአሞራው ታሪክ ሲነግሩህ ይህችን ቆርጠዋታል፡፡ የሆነ ሆኖ ብቻ ያሻህን አርአያ አድርግ፤ ነገር ግን ሀገርን እና መንግስትን ነጣጥላቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ሀገሪቷ ያንተ እንዳልሆነች እስኪሰማህ ድረስ፣ ሀገርህን ለቀህ እንድትጠፋ እስክትወስን ድረስ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ጫና እና ማስፈራሪያ፤ አንዳንዴም ጉሸማ ሊያደርሱብህ እንደሚችሉ ቀድመህ አስብ፡፡ እነሱ ሁሌም የተቃረናቸውን፤ የራሱ አቋም፣ ያለውን፣ ያልጣማቸውን… ከማሳደድ ወደ ኋላ አይሉምና፡፡ ነገር ግን ..ሀገሪቷ የእነሱ ትሆን እንዴ?.. ብለህ ተጠራጥረህ አትተባበራቸው፡፡ ምንም ጊዜም ቢሆን፡፡

በአንድ ወቅት የቀድሞ መንግስት፤ የአሁኑን መንግስት መሪዎችን ..ገንጣይ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ ወንበዴ፣….. እያላቸው እንኳ ..ይች ሀገር የማን ነች?.. ብለው እንዳልጠየቁ አስታውስ፡፡ እነሱ ያደረጉት ነገር ቢኖር አንድ ነገር ነው፡፡ ሀገሩማ የእኛም ነው ብለው የገፋቸውን መልሰው ገፉት፡፡

እናም ከተጨቆንክ፣ ከተበደልክ ምላሹ ኢትዮጵያ የማን እንደሆነች መጠየቅ ሳይሆን፤ መልሶ መግፋት ነው፡፡ ልክ በሰኔ 1983 ኮንፈረንስ መለስ ዜናዊ እንዳሉት ማለቴ ነው፡፡ እሳቸው ያሉት ምን መሰለህ ..የታሰርንበትን እግረ ሙቅ በጉልበታችን በጥሰን ወጣን.. ነው፡፡ ወይም ሰዬ አብርሃ ከራሳቸው መንግስት ጋር ተጋጭተው ለሰባት አመታት ታስረው ሲፈቱ ..ይሄ ሀገር የማን ነው?.. ሲሉ አልጠየቁም፡፡ ይሄ መንግስት መለወጥ ነው ያለበት ብለው ተቃዋሚ ፓርቲን ተቀላቅለው ትግል ጀመሩ እንጂ፡፡ በተረፈ በቅዱስ ቁራንም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ እመን፤ ክፋት የለውም፡፡ ክፋት የሚኖረው የፖለቲካህን ጦስ ጡንቡሳስ በሙሉ ..እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው.. ብለህ ስትተወው ነው፡፡ እመነኝ ጉልበተኛ መሪዎችህን እሱ አይደለም ያመጣቸው፡፡ ራሳቸው ናቸው በጉልበታቸው የመጡት፡፡ መቼም እግዜሩ አንዱን ከአድዋ፣ ሌላውን ከአክሱም፣ ከተንቤን ከጎንደር፣

ከሂርና… ሰብስቦ እና አደራጅቶ ላከብኝ ብለህ እንዳታስብ፡፡ ልድገምልህና እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት እንዳንተ ወጣት ነበሩ፡፡ ወጣት ብቻም ሳይሆኑ አብዮተኞችም ነበሩ፡፡ እናም ተሰባሰቡና አብዮት አስነሱ፡፡ ያ አብዮትም ስልጣን ላይ አወጣቸው፡፡ ይህ በአብዮት የተገኘ ስልጣንም ..ይህቺ ሀገር የማን ነች?.. የሚል ጥያቄ እንድትጠይቅ የሚገፉ ሁኔታዎችን ፈጠረላቸው፡፡የሆነ ሆኖ ለእኔ ..ይህ ሀገር የማን ነው?.. ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ የመለስ ቃለ-መጠይቅ አርዐያ ይሆነኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የትኛው ቃለ-መጠይቃቸው ብትለኝ ለምሳሌ ያህል በ1989 መጨረሻ አካባቢ ንብረትነቱ የሻዕቢያ ለሆነው ..ሕውየት.. መፅሔት የሰጡትን ቃለ-መጠይቅ ልጠቅስልህ እችላለሁ፡፡ጋዜጠኛው ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም መለሱ፡፡

ሕወይት፡- ለአንዳፍታ ወደ ተማሪነትዎ እንመልስዎት፡፡ አቶ መለስ ከሚከተሉት ቢመርጡ? ሀ/ ዳቦ፣ ለ/ ዲሞክራሲ?

አቶ መለስ፡- እንደጊዜው እንደሁኔታው ነው፡፡ የዲሞክራሲ እጦት ወደ ባርነት የሚያስጠጋኝ ከሆነ ዳቦ አገኘህ አላገኘህ መኖር ትርጉም የለውም፡፡ ባሪያ ሆኖ ከመኖር መሞት ይሻላል፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንደዛ ስለሆነ ነው የታገልነው፤ ተገፍተህ፣ ተማርረህ፣ ባሪያ ሆነህ ከመኖር ታግለህ ድልን ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ የከፋ ግፍና መከራ ካለ ዳቦ ተገኘ አልተገኘ ትርጉም የለውም፡፡

አቶ መለስ ልክ ነዎት፡፡ በጣም ልክ ኖት፡፡ አሁንም ልድገመውና ልክ ነዎት፡፡ ..የከፋ ግፍና መከራ ካለ ዳቦ ተገኘ አልተገኘ ትርጉም የለውም..፤ የኢኮኖሚ እድገቱ 11 በመቶ ሆነም አልሆነ፤ አባይ ተገደበም አልተገደበም .. የከፋ ግፍና መከራ ..ለ.. እድገቱም ሆነ ግድቡ ትርጉም የለውም፡፡

One Response to አገሩማ የእኔ ነው

  1. Selamawit Tezera Reply

    December 21, 2011 at 7:19 pm

    That’s the best Temesgen & Im realy proud to have this kind of jornalist… “Yichi hager yemeles bicha satihon yehulachinim nat!!”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>