የሃይማኖት እርጅና አያድርስ

March 19, 2014

ይሄይስ አእምሮ

ይህችን ጽሑፍ ባልጽፋት በወደድኩ፡፡ ግን ያበጠው ይፈንዳ እንጂ እጽፋታለሁ፡፡ በስንቱ ታፍኜ እዘልቀዋለሁ? ብዙ ሚዲያዎች እንደማይቀበሉኝ ከወዲሁ አምናለሁ፤ በዚያ ብቻ ከማሩኝም እሰዬው ነው – ትልቅ ዕድለኝነት፡፡ እውነት በጠፋችባትና ሀሰት በነገሠችባት ዓለማችን ውስጥ ለሺዎች ዓመታት ዜጎችን እሥረኛና ባሪያ አድርጎ እግር ከወርች በማሠር ኮድኩዶ ያስቀረን ጉዳይ ድንገት ተነስቶ መተቸት በትንሹ ውግዘትን ማስከተሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ And I am ready to welcome everything of anything.

በዓለም የሚገኙ ሃይማኖቶችን ብዛት ለመቃኘት ሞክሬ ያገኘሁት መልስ በጣም የሚለያይ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዓለም ዋና ዋና (ግንድ የሚባሉ) ሃይማኖቶችን ወደ 21 ሲያወርዷቸው አንዳንዶች ደግሞ ከአሥርና ከሃያ ሺዎች በላይ ያዘልቋቸዋል፡፡ አንድ ምንጭ ደግሞ 4200 አካባቢ እንደሚደርሱ ያትታል፡፡ የሆነ ሆኖ እንደመነሻዎቹ እንደአይሁድ እምነትም ይሁን እንደስንጣቂው የክርስትና እምነት ከዚያም ቀጥሎና ቆይቶ እንደመጣውም የእስልምና እምነት መሠረት የሰው ልጅ አጠቃላይ ብዛት ከሁለት ሰዎች ተነስቶ አሁን ወዳለበት ሰባት ቢሊዮን ገደማ እስኪደርስ ድረስ ከአንድ ወይም ከምንም ሃይማኖት ተነስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶችን አሁን ሊከተል መቻሉ ሃይማኖትን ከመለኮታዊነት ይልቅ ይበልጡን ሰውኛ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም፡፡ ይህን ስል የሰው ልጅ ሃይማኖት ሊኖረው እንደሚገባ የማምን መሆኔን መግለጥ እወዳለሁ፡፡ የሃይማኖትን መብዛት ግን ከሰዎች ፍላጎት በዘለለ እግዚአብሔራዊ ነው የሚል የሞኝነት እምነት የለኝም፡፡ በመሆኑም በሃይማኖታዊ የአመስጥሮ ሥልት (mystification)  ሰዎች በሰዎች ሲታለሉና ጤናማ አእምሯቸውን በማስመሰያ ወጥመድ ሲሰለቡ ስመለከት አዝናለሁ ብቻ ሣይሆን ክፉኛ እበሳጫለሁ፡፡

እውነት አትመነዘርም፡፡ እውነት አትሸቀጥም፡፡ እውነት ምን ጊዜም መልኳን አትለውጥም፡፡ እውነት በሃይማኖት መለያየት ሰበብ አትከፋፈልም፤ ተከፋፍላም አራት ሺህና አሥር ሺህ እውነቶችን አትሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ታዲያ ይህ ሁሉ የሃይማኖት ልዩነት መንስኤ የሥጋ ፍላጎት እንጂ የነፍስ ፈቃድና የፈጣሪ ፍላጎት እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡

ሰሞኑን በተለይ በውጪ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አድባራት መካከል የተወሰኑት በግልም ይሁን በቡድን የጻፏቸውን የቅዋሜና የግዝት/የውግዘት ጦማሮች (ex-communication) የሚያነብብ የእምነቱ ተከታይ በሃይማኖቱ ማፈሪያ መሪዎችና አግለጋዮች ምን ሊሰማው እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ በበኩሌ በእጅጉ ማፈርና መሳቀቅም ይገባኝ ነበር፤ ነገር ግን የዘመኑን ማብቃት ከተረዳሁ ጥቂት የማይባሉ ጊዜያትን በማስቆጠሬ ከፈገግታ ባለፈ የተሰማኝ ብዙም ነገር የለም፡፡ አጠገቤም ብዙና ብዙ ስለምታዘብና ይህን መሰሉ ዘግኛኝ ነገርም እንደሚከሰት ቀድሞውን የተተነበየ በመሆኑ አላስደነቀኝም፡፡ ይልቁናም እነዚህ ራቁታቸውን የወጡ የቀድሞ ድብቅ ነውሮች የሃይማኖት ተቋማት የሰይጣን መናኸሪያ መሆናቸውን ላላወቁ የዋሃን ጥሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሆኑና በሰዎች ማመን እንደማይገባ የሚያስረዱ ክስተቶችን በግልጽ በማየታችን የፈጣሪን ዕድሜ ለምኛለሁ፡፡ የማውቀውን ብቻ መናገር ስላለብኝ ቤተ ክርስቲያን – የየትኛውም ዘርፍ ትሁን (ካቶሊክም ኦርቶዶክስም ሉተርያንም) – በታላቁ የጨለማው ንጉሥ በዲያብሎስ መንግሥት ሥር ከወደቀች ዘመናትን እንዳስቆጠረች ካነበብኩትና ከማየውም ተነስቼ መመስከር እፈልጋለሁ፡፡ ጣፋጭ ፍሬ ዛፍ ላይ እያለ ይታወቃል፡፡ ሰዎችንም በሥራቸው እናውቃቸዋለን፡፡ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉና ለብቻ በመቆጣጠር አንድ የተማከለ ሲዖላዊ ምድራዊ መንግሥት ለመመሥረት በልጆቹ ኢሊሙናቲዎች አማካይነት ጫፍ የደረሰው የአውሬው መንግሥት ከፈጣሪ በቀር አለኝታና መመኪያ የሌላት ቤተ ክርስቲያንን ደፍጥጦ አገልጋዮቿን በብልጭልጩ አሳሳች ዓለም ውስጥ ለመክተት የሥርዓቱ የበላይ አለቃ ሰይጣን የሚያቅተው አልሆነምና በጉልህ እንደምናየው ከቫቲካን እስከ አሌክሳንደርያ ከዚያም አልፎ እስከ ኢትዮጵያና ከዚያም ማዶ በክርስትናው ብቻ ሣይሆን በሁሉም ሃይማኖቶች እጁን ሰድዶ ሁሉንም በቁጥጥሩ ሥር አውሏል፤ የተደገሰልን ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ በመሆኑና የሚጠበቅም ስለሆነ አይገርምም፡፡ የሚገርመው በዓለም ላይ የፈጠጠውን ይህን እውነት ለመገንዘብ ብዙ ሰዎች አለመቻላቸውና በዚህ ወጥመድ ውስጥ ዘው ብለው የመግባታቸው ምሥጢር ነው፡፡ ይህን ገሃድ እውነት ለመረዳት የሦስትና አራት ገጽ ጦማር ስለማይበቃ ኢንተርኔትን በመጎልጎል መዳሰስ ነው፡፡

ይሁንና በየትኛውም የክርስትና እምነት ቅርንጫፍ ውስጥ – ከንፍሮ ጥሬ እንደሚወጣ ሁሉ – በትክክለኛው የፈጣሪ መንፈስና ህግጋት የሚመሩ እጅግ ጥቂት የዓለም ዜጎች መኖራቸው አይቀርምና ለእነሱ ያለኝን አክብሮትና ፍቅር የምገልጸው ሃይማኖታዊ ተጋድሏቸውና ጸሎት ምህላቸው ለኛ ለብዙኃኑ ምሕረትን እንዲያመጣልን ሁሉን ማድረግ ለሚችለው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በመጸለይ ነው፡፡ አብዛኛው የሃይማኖት መሪ ግን ራሱ በእግዚአብሔር የሚያምን መሆኑን እስክንጠራጠር ድረስ ጭልጥ ብሎ ጠፍቷል፡፡ ጽላት የሚሰርቀውን፣ ንዋየ ቅድሳት እየዘረፈ የሚሸጠውን፣ ከየሴተኛ አዳሪውና ከየአባውራ ሚስት እየወሰለተ ቅዳሤ የሚገባውንና ድጓና መዋሲት የሚያንበለብለውን … ስንመለከት በሱ ድፍረትና በፈጣሪ ትግስት መደነቃችን አይቀርም – ያ የፈጣሪ ትግስትም የልብ ልብ እየሰጣቸው በመንበሩ የሌለ ያህል በመቁጠር ይሄውና የጥንታውያኑ ፀረ- ክርስቶስ “ጻፎችና ፈሪሣውያን፣ ቀራጮችና ሰዱቃውያን” በዘመናችን የሃይማኖት እረኞች ሰውነት ውስጥ በሥውር ተመልሰው በመግባት በክርስቶስ መምጫ ዋዜማ ላይም የአባቱን ቤት እንደዱሮው ሲሸቃቀጡበትና ሲሸራሞጡበት ይታያሉ፡፡ በዘመናችን ሰዎች ለራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ቅዱሣት መጻሕፍትን በርዘውና ከልሰው በተቃርኖዎችም ሞልተው ምዕመናንን በጭፍን ሲያሞኙ ስናይ በሰው ልጅ የዋህነት መገረማችን ከገደቡ ያልፍብናል፡፡

ወደ 97 ዓ.ም ግርግር ለአፍታ ልውሰዳችሁ፡፡ በግርግሩ ሰሞን በግርግሩ አካባቢ አንድ የንግሥ በዓል ነበር – ከታማኝ ሰዎች እንደሰማሁት፡፡ ቀሳውስት በዝማሜና በወረብ ታቦት አጅበው ወደ መንበሩ ሊያስገቡ ሲሉ የወያኔ ፌዴራል በአካባቢው የጦፈ ተኩስ ይከፍታል፡፡ ያኔ ሌላው ቄስና ምዕመን ይቅርና ታቦት ተሸካሚው ራሱ ጽላቱን ሜዳ ላይ ጥሎት እግር አውጪኙን ይሸሻል – ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ትርዒት ለወያኔና ለአባቱ ለሰይጣን ትልቅ ድል ነው – በደስታ የሚሰክሩበት ታላቅ ድል፡፡ በኋላ ላይ ነው ጽላቱ ከወደቀበት ተፈልጎና በጠቋሚ ምሪት ተገኝቶ ወደመንበሩ የገባው፡፡ ምን ማለት ነው? ብዙ መናገር አልፈልግም፡፡ አንድ የቀድሞ ወታደር ሲሰለጥን ወታደራዊ ሠልፍ ላይ በተጠንቀቅ ባለበት ጊዜ እባብ እንኳን መጥቶ ቢጠመጠምበት አንዲትም ኢንች እንዳይንቀሳቀስ ትምህርት ይሰጠዋል – እንኳንስ አይግባኙን ሊፈረጥጥ፡፡ በሃይማኖትማ እንዴቱን ያህል ይበረታ! ታዲያ ከምዕመናንና ከካህናት ይበልጥ በእግዚአብሔር የሚያምኑት የትኞቹ ናቸው? ትንሽ ነገር ነው የተናገርኩት፡፡ ሌሎች ሃይማኖታዊ ህፀፆችን ልዘርግፋቸው ብል ወኔው ቢኖረኝም አንባቢዎችን ተስፋ ላለማስቆረጥና በጭፍን ልማድ ላይ ድንገተኛ “መብረቃዊ ማጥቃት” ላለመሰንዘር ለአሁኑ ሆን ብዬ እተወዋለሁ፡፡ ግን ግን የሃይማኖቱ መምህራን ኦሪትን ከሃዲስ፣ የሰይጣንን ከእግዚአብሔር፣ እውነቱን ከሀሰት፣ ልማዳዊውን ከእውነተኛው የክርስቶስ አስተምህሮ በመለየት ሕዝቡን በትክክለኛው መንገድ ቢመሩት የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹ እነሱ መሆናቸውን ብጠቁም የሚያስነውር አይመስለኝም፡፡ ለገንዘብ ሲሉ የሚጨማምሩትን እንቶ ፈንቶና ኢ-እግዚኣብሔራዊ የአምልኮ ልማድ ሁሉ እርግፍ አድርገው ሊተው ይገባል – እንዲህ ማድረግ ያለባቸው ትዝብት ውስጥ ስለሚጥላቸው ብቻ ሣይሆን ስለማይጠቅማቸውና ፈጣሪን ስለማያስደስት ጭምርም ነው፡፡ በስሜትና በግለሰባዊ ቅዠት በእውር ድንብር እየተመራን – እየተነዳን ቢባል ይበልጥ ያስኬዳል –  እዚህ ደርሰናል፡፡ በዚህ ጉዟችንም ፈጣሪን ከእኛና ከሀገራችን አራቅነው እንጂ አላቀረብነውም፡፡ ከንቱ መኮፈስና ገመናን በአልባሳት እየሸፈኑ ሃይማኖተኛ ለመምሰል መሞከር የምንገኝበት ዘመን የሚያሳየኝ አጠቃላይ ውጤት ምሥክር ነውና የትም አላደረሰንም፤ የትምም አያደርሰንም፡፡ ያወቅነው የሚመስለን ነገር ግን ብዙ የማናውቀው ነገር መኖሩን እስካሁን አልተረዳንም፡፡ ስለዚህ መንገዳችን እሾሃማ ነው ማለት ነው፡፡ አያችሁ – “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል፡፡”

በዓለም ላይ እግራችን እስኪነቃ ብንሄድ ብዙው የሃይማኖት አገልጋይ ወደዓለም ገብቶ ጠፍቷል፤ ጠቅልሎ ወደዓለም ቢገባ ምንም አልነበረም – ዕዳው የርሱ ብቻ በሆነ፡፡ ነገር ግን በምሽትና በሌሊት በቤተ ክርስቲያን እንደቁራ በከንቱ እየጮኸ፣ ቀን ቀን ባሳቻና በግልጥ በቤተ ሣጥናኤል ያሻውን እያደረገ የተከለከለውን ለሁለት ጌቶች ያለመገዛት ወይም ያለማደር መለኮታዊ ቃል በመጣስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የዚህን መሰሉ የሁለት ዓለም ዜጋ ጸሎት ለብራቅ የሚዳርግ ካልሆነ በስተቀር ለጽድቅ የሚያበቃ ባለመሆኑ እያስመሰለ መኖሩ አደገኛ ነው፡፡ እንደሰዎች የማጭበርበርና የማስመሰል ሃይማኖታዊ ድራማ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ምናልባት ሁላችንም በጠፋን ነበር፡፡

ወደሀገራችን ስንገባ በባህልና በይሉኝታ ገመዶች ተጠፍንገን ገብስ ገብሱን ብቻ እናውራ ካላልን በስተቀር ጉዳችን ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ቤተ መቅደስን ከጥንት ጀምሮ ተቆጣጥሮ የሚገኘው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ደግነቱ እነሱ ራሳቸው “የምናደርገውን ሣይሆን የምንለውን አድምጡ” ማለታቸው በጄ እንጂ ብዙዎቹ የሚያደርጉትን ከተመለከትን አንድም ሰው ወደቤተ ክርስቲያን ባልሄደ ነበር፡፡ እኛም “የነሱን ኃጢኣት ምን አስወራን? ፈጣሪ ራሱ እንደሥራቸው ስለሚከፍላቸው አገልግሎታቸውን እንቀበል እንጂ ግድፈታቸውን ማየት የለብንም” እያልን የልብ ልብ ስለምንሰጣቸው የሰይጣን ፈረስ የሚጋልቡ ካህናትና ጳጳሣት ኪሳችንን ብቻ ሣይሆን የተቀደሰውን አልጋችንንም ሣይቀር ተጋርተው የልጆቻችንን መልክ እስኪለዋዉጡና በገዛ ቤታችን ውስጥ የማንነት ኪሣራ እስኪያስከትሉ ድረስ ነፃ እንተዋቸዋለን፡፡ በኋላ ግን በጸጸትና በንዴት የምንሠራውን አጥተን ሃይማኖት መለወጥ መፍትሔ ይሆን ይመስል ማተባችንን በጥሰን ገደል የምንገባ ሞልተናል፡፡ ግን ግን መጥኖ መደቆስ ቀድሞ ነበር ወገኖች፡፡ ‹ጅቡ ከሄደ በኋላ ውሻው እንዳይጮህ፡፡›

ቀደም ባለ አንድ የቅርብ ታሪክ ልጀምር፡፡ ዘመኑ ነው እንዳትሉኝ ነው የዛሬውን ያላስቀደምኩት ነው፡፡ ታሪኩን በቅርብ አውቀዋለሁ፡፡ የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ እልም ያለ ገጠር ውስጥ፡፡ የዛሬ ሃምሣ ዓመት ገደማ የተፈጸመ፡፡ በነገራችን ላይ እንደዚህ ዓይነቶቹን ቅንጫቢ ታሪኮች እናውራቸው ብንል በመሠረቱ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም፡፡ በየመንደሩ ከሁለትና ሦስት በላይ ይኖራሉ፡፡

የአጎቴ ነፍስ አባት ነበሩ፡፡ የወለዱ የከበዱና ከሰማይ ከምድር የከበዱ፡፡ አጎቴም በአጥቢያው የተከበረና ከአሥር ልጆች በላይ ያሉት ነበር፡፡ ቄሱም አጎቴም በሃምሣዎቹ እኩሌታ የዕድሜ ክልል ውስጥ ነበሩ፡፡ ቄሱ እንደማንኛውም ንስሃ አባት ወደ አጎቴ ቤት ለጠበልም ለዝክርም ለምንም ለምንም አዘውትረው ይመላለሱ ነበር – ወደአንተታው መግባቴ ነው እባካችሁን፡፡ በዚህ መሃል አጎቴ ይሞታል፡፡ ቀብሩ ተፈጽሞ ዐርባው እንኳን ሳይወጣ ቄሱ ሚስቱንና ልጆቹን ጥሎ አጎቴ ቤት ይገባል፡፡ ሰይጣናዊ የፍትወት ፍቅር ዐይን የለውምና ሀገር ምድር ጉድ እያለ እነዚያ የአጎቴ ሚስትና ቄሱ የፍቅር ቄጤማቸውን ያለ አንዳች ይሉኝታ ይቀጩ ጀመር፡፡ ከአጎቴ ልጆች አንድኛው ግን አንድ እርምጃ ወሰደና የሁሉንም ቤተሰብ “ያስደሰተ” አስቀያሚ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ ከዚህ በላይ መሄድ አያስፈልግም፡፡

የዛሬውንማ አታንሱት፡፡ ስንቱ ተጠቅሶ ስንቱ ሊቀር? የትኛው ተነግሮ የቱስ ሊተው? “በኃጢኣት ሊመላለስ ያልፈቀደ ካህንና መነኩሴ በነፍሱ እንደፈረደ ይቆጠራል!” የሚል ማስጠንቀቂያ የተላለፈ ይመስል ከሞላ ጎደል ሁሉም ተያይዞ የጥፋትን መንገድ የሚከተል ሆኗል፡፡ በወንጌሉ “ከእናንተ አንድስ እንኳ ካለ ኃጢኣት የሚኖር የለም፤ ሁላችሁም በኃጢኣት ሥር አድራችኋል” ተብሎ እንደተጻፈ ምድረ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከእኔው ባልተናነሰ በቁሙ በክቷል፡፡ የሚገርመኝ የምዕመናኑ ዐይን መጨፈንና ድግምት እንደተዞረበት ፈዝዞ በዕውር ድንብር መከተሉ ነው፡፡ ለነገሩ አማራጭም ከማጣት ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ከፍ ሲል እንደተናገርኩት ፍርዱን ለፈጣሪ በመተውም ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላም በኩል ለዘመናት በሥነ ልቦናው ላይ በተደፈደፈበት  የአፍዝ አደንግዝ  ስብከትም ሊሆን ይችላል፡፡ መንስኤው ምንም ይሁን ምን ምዕመናን ከእግዚአብሔር ይልቅ ጠፍተው የሚያጠፉ ካህናትን ማመናቸው እየጎዳቸው ነው፡፡

ባህታዊ ገብረ መስቀል የሚባለውን አጭበርባሪ ሌባ ብንመለከት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፡፡ (እዚህ ላይ የሕዝብ ጊዜ ገና ባለመምጣቱ ምክንያት በእውነተኛው ስሜ ይህን ጉዳይ መጻፍ እየፈለግሁ ባለመቻሌ ከፍተኛ ቅሬታ የተሰማኝ መሆኔን ሳልገልጥ ማለፍ አልፈልግም፡፡) በጊዜው ባህታዊ ተብዬውን እንደክርስቶስ ያህል ለማምለክ ከተሰለፉ ሰዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ በርሱ ምክንያት የምጣላቸው ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ “ይሄ አጭበርባሪና ሌባ ሰውዬ የሚለውን አምነህ እንዴት ትቀበላለህ? ፊደል ቆጥረህ የለም እንዴ?…” በማለት ከዚያን ጊዜ በፊት ሠራቸው የሚሉትን ገመናዎች በመጥቀስ ሲነግሩኝ ያኮረፍኳቸውና በጅልነቴ የሚያዝኑልኝም ነበሩ – ይቅር ይበሉኝ፡፡ በዚያኑ ወቅት ገደማ በምኒልክ ጋዜጣ አንዲት ሴት በዚህው ሌባ ባህታዊ ነኝ ባይ ሰውዬ የደረሰባትን ወሲባዊ ገጠመኝ ስታጋልጥ ዐይኔን መግለጥ ጀመርኩ፡፡ ቀጥሎም ተደጋጋሚ ማጋለጫዎች ወጡ፡፡ ቀጥሎም አንዲት ሕጻን ልጅ አግብቶ ሥውር ማጭበርበሩን ገሃድ ማውጣቱን ተረዳሁ – ከዚያን በኋላ “ነፍስ አወቅሁ”ና ከሰውዬው የበሸቀጠ የሰይጣን መንፈስ ተለየሁ፤ “ለሰይጣን ለሰይጣንማ የኔውስ ምን አለኝ?” በማለት – ይህን ዓይነቶቹ አታላዮች ቁጥር አይገልጻቸውም – በልጆች ቋንቋ በዬአካባቢው “ነፍ” ናቸው፡፡ ይሄ ሰውዬ ትልቁን ሰው አቶ ሽመልስ አዱኛን ሳይቀር ከጎኑ በማሰለፍ በድሆች ስም ላቋቋመው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የቦርድ ሊቀ መንበር እስከማድረግ የቻለ የተዋጣለት አሰለጥ ነው፡፡ በወቅቱ በሥሩ ያዘጋጃቸው ጋሻጃግሬዎቹ ሰውዬው ሲታሠር “መላእክት መብራት ሲያበሩላቸው ያድራሉ፤ ምግብም ከሰማየ ሰማያት በመና መልክ ይመጣላቸዋል፤ እንደተክልዬ ሰባት ክንፍ ሊያወጡ አራቱን አብቅለው ሦስቱ እያጎነቆሉ ነው …” የሚል ወሬ እያሠራጩ የአዲስ አበባን ሕዝብ አማለሉት – በቀላሉ የማይናጋ ትክለ ሰውነትም ገነቡለት፡፡ ጠንቋዮችም እንዲሁ ናቸው፡፡ ጠንቋይና ቄስና ደብተራ የሚመሳሰሉባቸው ብዙ ባሕርያት አሏቸው፡፡ ዝናቸውን በወሬና አሉቧልታ ያዛምቱና ሕዝቡን አጥንቱ ድረስ እየዘለቁ ያለ የሌለ አንጡራ ሀብቱን  ይግጡታል፡፡ እዚህ አካባቢ አንድ ወሬ አውራ፤ በሴከንድ ውስጥ ከሬዲዮና ቴሌቪዥን በበለጠ ፍጥነት አገር ምድሩን ያዳርስልሃል፡፡ ደግሞም በኛ ሀገር፡፡ በዚህ መልክ ስማቸው የመላእክትን ያህል በየቦታው ይናኛል፡፡ ባህታዊ ተብዬው የሰይጣን ፈረስ በመሳጭ አንደበቱ አዳሜን አነሆለለና በገንዘብ የተመቻቸ ኑሮውን ካረጋገጠ በኋላ “ያጠመቃት” ፈረንጅ – ወለተ መስቀል ‹ጆንሃንሰን› – ሰጠችው በተባለው ላንድክሩዘር እየተምነሸነሸ ሚስቱን አግብቶ ዓለሙን ይቀጭ ጀመር – መቅጨቱ አያስቀናም – በእግዚአብሔር ስም ማጭበርበሩ እንጂ የሚያበሳጭ፡፡ አሁንም ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ግርጌ ትልቅ ግቢ ገዝቶ አለላችሁ፡፡ እሱን መሰል አጭበርባሪ “ባህታውያንና መነኮሳት” ሀገር ምድሩን አጥለቅልቀውታል፡፡በሌባና አጭበርባሪ ቄስና ባህታዊ ሕይወቱ የተመሰቃቀለ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጪ ሊገኝ እንደማይችል ባለኝ ሁሉ እወራረዳለሁ፡፡ ግን ምን አለኝና? ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ?

ሰሞኑን ደግሞ እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደአዲስ አበባ የመግቢያ በር አካባቢ አንድ ባዶ እግሩን የሚሄድ መነኩሴ አንድ ቤተ ክርስቲን ያቋቁማል – በተለይ በአሁኑ ስድ የወያኔ ግዛት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ማለት አንዲት ትንሽ ፒ.ኤል.ሲ የማቋቋምን ያህል እንኳን አይከብድም – ሰው እንደሆነ ክፉኛ ስለተጨነቀ ይቅርና የሰው ባህታዊ የዝንጀሮ ግመሮ ባህታዊና የጦጣ መነኩሴ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ፈዋሽ ጠበል አፈለቁ ተብሎ ቢወራ ወደዚያ ሥፍራ የሚነጉደው ሕዝብ መሬት አይበቃውም – እርሱ ይርዳን እንጂ ተጨንቀናል፤ ተጠበናል፡፡ ይህንን ጭንቀት ጥበታችንን ታዲያ አሰለጦች ሃይማኖትንና የዛር ጥንቆላን ተገን አድርገው እየተጠቀሙ ሙልጭ እያወጡን ናቸው፤ አባባ ታምራትንና ማርያም ነኝ ብላ አዳሜን “የቀፈለችው”ን አስታውሱ፡፡ ይሄ “የበቃ መነኩሴ” ታዲያ የሚለብሰው ወይባ፣ በእጁ የሚይዘው ባለመስቀል የብረት ከዘራ፣ የሚታጠቀው አስኬማ፣ የሚጫማው እሾህና ጋሬጣ ነበር፡፡ ስብከቱ ያፈዝዛል – የክርስቶስን የተራራውን ስብከት ያስታውሳል የሚሉትም ነበሩ፡፡ ምዕመናን ምግብ ሲያመጡለት ይቆጣል፡፡ “‹መንኮሰ› ማለት ሞተ ማለት ነው፡፡ ለመነኮሰ ሰው ደግሞ ከባቄላ አሹቅና ከሽንብራ ቆሎ ውጪ ሥጋን የሚያወፍር ምግብና ሙቀት የሚሰጥ ልብስ አያስፈልገውም …” እያለ ሲሰብክ መላእክትን ከሰማይ ይስብና የስብከቱ ተካፋይ ያደርግ ነበር፡፡ … ምን አለፋችሁ – አሁን አንዷን ምዕመን አግብቶ የሚይዘው መኪናና ሞባይል እንዲሁም የሚለብሰው ሱፍ እኔና አንተ በሎብሣንግ ራምፓ ሃይማኖታዊ ቲዮሪ መሠረት ለዘጠኝ ጊዜያት ደጋግመን ብንወለድ አናገኘውም፡፡ ሃይማኖት ማለት እንግዲህ እንዲህች ናት ወንድሜ! ይችንስ እኔም ባገኘኋት፡፡ የመንገዱ ግማት ኅሊናዊና አካላዊ አፍንጫን ቆርጦ ስለሚጥል እንጂ ይህን ዓይነቱን ወደሀብቱ ጉዞ አቋራጭ ማን ይጠላል? ወደድህም ጠላህም የምልህ እውነትና እውነት ብቻ ነው፡፡ ብታምን የራስህ ጉዳይ፤ ባታምንም እንዲሁ፡፡ ፖለቲካና ሃይማኖት ለሥጋዊ ፍላጎቶች ስኬት እንደሚውል ካልገባህ እንደተሞኘህ ትኖራለህ ማለት ነውና የምልህን ነገር አዟዙርህ ለመቃኘት ሞክር፡፡ በሰዎች የማምታታት ተፈጥሮና የወንጀለኝነት ባሕርይ ተደናግጠህና አኩርፈህ ግን ከፈጣሪህ ጋር እንዳትጣላ አደራህን፡፡ የእርሱና የሰው መንገድ ለዬቅል ናቸውና፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ጥፋትና ልማት የሚለካ አይደለም፡፡ ለነገሩ በፈጣሪ ባታምንም መብትህ ነው፡፡ ምን አገባኝ? የሚያዋጣህን እምታውቅ አንተ፡፡

ማርክስ ይሁን ኤንግልስ “ሃይማኖት የመበዝበዣ መሣሪያ ነው” ብሎ ነበር፡፡ መቶ በመቶ እውነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙ ሃይማኖቶችን ስንመለከት የብዙዎቹ መሪዎችና አገልጋዮች ይህን ነባራዊ ኹነት የሚያረጋግጡልን ብዙ ነውሮችን ሲሠሩ እንታዘባለን፡፡ እኔ በመሠረቱ ሃይማኖትን አልቃወምም ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ አንዳች የሚፈራው ነገር መኖር እንዳለበት የማምንና ሃይማኖት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ የሃይማኖቶቹ መሪዎች የሚከተሉትን የአሠራር መንገድ ግን አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ ሃይማኖተኛ ለመሆንም በግድ በተጣመመ መንገድ በይሉኝታና በፍርሀት መጓዝ እንደሌለብኝ እረዳለሁ፡፡ ባለፈው የሰማነውን በ42 ሚሊዮን ዶላር የግል ቤት የሠራውን የጀርመኑን የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ታሪክ የምታስታውሱት ይመስለኛል፡፡ እርሱስ በሀብት ነው – ሌላ ሌላው በሆድ ይፍጀው ይቀመጥና፡፡ አለላችሁ እንጂ ሌላ አስቀያሚ ታሪክ – በነሱም በኛም፡፡ ይታያችሁ – ሆሞሴክሽዋል ካህንና ሌዝቢያን መነኩሴ ፈጣሪን በቃለ ዐዋዲው የክህነት ማዕረግና በፆታዊ የድንግልና ክብር ለማገልገል የገቡትን ቃል አፍርሰው ከህገ እግዚአብሔርና ከህገ ማኅበረሰብ ሲወጡ ፈጣሪን ምን ሊሰማው ይችላል? ሰውን በመፍጠሩስ ቢጸጸት ይፈረድበታልን? ወደዚች የጎስቋሎች ምድር ምን ዓይነት መቅሰፍት ሊልክስ እንደሚችል አስባችሁት ታውቃላችሁ? የጽዳት ዘመቻ የለም የምትል ከሆነ ስህተት ነው፡፡ የዘመነ ኖኅ የውኃ ጥፋትንና የዘመነ ሎጥ የሶዶምና ገሞራ የእሳት ድኝን ማሰብ ይገባል፡፡ ሁልጊዜ ፋሲካ የለም ወዳጄ፡፡ ጠብቅ … ግን ቶሎ እንዲሰበስብህ ጸልይ – ካንተ ይለፍ፡፡

የኦርቶዶክስ ቄስ አንዲት ሴት ማግባት ይችላል፡፡ አንዲት ብቻ! መፍታትም ሆነ ሌላ ማግባት አይችልም፡፡ እንዲያ ቢያደርግ ክህነቱ ይፈርሳል፡፡ ብትሞትበት ወይም ብትፏንንበትና ሌላ ወድዳ ብትከዳው በራሱ ንጽሕና ጸንቶ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሊመነኩስና ክህነቱን ሊያስጠብቅ ህግ ይፈቅድለታል፡፡ የካቶሊክ ቄስ ምንም ማግባት አይችልም – ሶሬላዋም እንዲሁ፡፡ ምንም! ግን ግን ያገባውም ያላገባውም ሁሉም ሌባና ቀላዋጭ ነው – እነዚህን የሰይጣን ሎሌዎች በቅርበት የማውቅበት ዕድል ስለነበረኝ በምለው ነገር ጥርጣሬ አይግባህ፡፡ አንዲት ማግባት የሚፈቀድለት ከአንዲቷ በላይ ማየትን ይፈልጋል፤ ምንም ማግባት የማይፈቀድለት ደግሞ ሁሏንም ማየት ይፈልጋል፡፡ ሌላዋም ሆነች ሁሏም በበኩሏ የሚያገባውንም ሆነ የማያገባውን ማየት ትፈልጋለች – ቀድሞውን ለፈተና ተፈጥራለችና፡፡ ጀብራራው ካህን ከርሷው ወጣ – በፈተናና ለፈተናም ባልተፈቀደለት አቅጣጫ ተጉዞ ወደርሷው ተመልሶ ገባ፡፡ እርሷም መነሻዋን አትክድምና ለምስነቱ ታበረታታዋለች፤ ታጃግነዋለች(አስቸጋሪ ቃል ተጠቀምኩ መሰለኝ – ለምስነቱ ማለት ለጥፋቱ ማለት ነው – ሁሉም ፊደላት እኩል ላልተው ይነበቡ)፡፡ ቀድሞ በፍራፍሬ፣ በኋላም ሱባኤን በማስተጓጎል አሁን ደግሞ ቃል ኪዳንን በማሳጠፍ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ለውድቀቱ ሥምረት ከጎኑ እንደወጣች በጎኑ አለችለት፡፡ የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ደጅ ሲልከሰከስ እንደሚገኝ የት ይደርሳል የተባለ ካህን በሴት ተፈትኖ በሴት ሲወድቅና መስቀሉን አልባሌ ቦታ ሲጥለው፣ በቀኖናው መሠረት ባልተፈቀደለት የሴት ጭን ውስጥ ከትቶ ሲያርመጠምጠው የምናስተውለው የታቀፈውን እሳት መቆጣጠር ስላቃተው ነው፡፡ የሥጋን ፍላጎት መቆጣጠር እጅግ ከባድ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የምንወድቀው በሥጋ ፈተና ነው፡፡ በካህን ሲሆን ደግሞ ኃላፊነቱ ስለሚከብድ ለብዙዎች መሰነካከል ምክንያት ይሆናልና ጠንቁ አነስ ሲል የሃይማኖት ተቋምን ከፍ ሲልም ማኅበረሰብን እስከማነቃነቅ ይደርሳል፡፡ “ብፁዓን አባቶቻችን” አቡነ ጳውሎስና አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ቫቲካናዊያኑ “ብፁዓን አባቶቻቸው” ፖፕ ሮደሪጎ 15ኛ እና ቤኔዲክት 16ኛ  በልበ ድፍንነት ቀልባቸው ካረፈባቸው እንስቶች ጋር ይሸራሞጡ የነበሩት የክርስቶስን ጴጥሮሳዊ መንበር ለማዋረድ በላያቸው ላይ የሰረፀው የሰይጣን ኃይል አስገድዷቸው ብቻ ሣይሆን የሥጋ ፍላጎታቸውን ለመግታት እነሱ ራሳቸውም አቅም በማጣታቸው ጭምር ነው – ለሰይጣን ፊት አሳይተውት ቀርቶ እንዲሁም የሚቻል ባላንጣ አይደለም፡፡ እነሱ እንዲህ ከሆኑ እንግዲህ በዕውቀትም በትምህርትም ከነሱ በታች እንደሆነ የሚገመተው ተከታይ ጭፍራማ እንዴቱን አይሳሳት? ብሂሉ “ እህል ቢያንቅ በውሃ ይዋጣል፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይዋጣል?” ይላል፡፡ ይለጥቃልም “ሰውነት ቢያብጥ በምላጭ ይበጣል፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጣል?” አዎ፣ ከላይ የሚጀምርን ህመም ለማከም ከባድ ነው፡፡ ከታች የሚነሣ ህመም መፍትሔው ብዙም አይቸግርም፡፡ በማስተማርም ሊመለስ ይችላል፡፡ አለበለዚያም ካልተመለሰ ማባረርም ይቻላል፡፡ የጫፍ በሽታ ግን ሁሉንም ያጠፋል፤ እንደሰደድ እሳት በቀላሉና በፍጥነት ሀገር ምድሩን የሚያዳርስ ወረርሽኝ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-አማራ፣ፀረ-ታሪክ፣ ፀረ-ሃይማኖት፣ ፀረ-መልካም ሀገራዊ ዕሤቶች በመሆኑ የርሱ ተከታዮችና ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደርሱው መርዘኛ ሆኑና ሀገር ከነታሪኳ ገደል ገባች – ቢያንስ እስከትንሣኤዋ፡፡ በዚያም ምክንያት ዓሣማና ጅብ በመላዋ ሀገር ናኝቶ ያገኘውን ሁሉ ሳይመርጥ መቆርጠም ያዘ፡፡ ይህ የመለስ ባሕርይ በቤተ መንግሥት ብቻ ሣይወሰን በቤተ ሃይማኖቱም አለተቀናቃኝ ሰተት ብሎ ገባና በአንጻራዊ አነጋገር የብርቅ ያህል ይታይ የነበረው ብልግና አሁን አሁን የማያስነውር ፋሽን ሊሆን በቃ፡፡ ሙት ወቃሽ አያድርገኝና በፓትርያርክ ቢሮ ውስጥ ምን ይደረግ እንደነበር አውቃለሁ፤ የውቢት ጓድ ፍስሐ ገዳና የእጅጋየሁ አባ ጳውሎስ ቢሮ አንድ ከሆኑ የእግዚአብሔር ቢሮ የትኛው ሊሆን ነው??  የእጅ ሰላምታ ያህል የረከሰውን ፍትወታዊ ግንኙነት እንተወውና ዛሬ ሃይማኖትን በሽፋን በመጠቀም የፈለገውን የዘረኝነት ቅርሻት የማያቀረሽ ወያኔያዊ ካህን የለም፤ የዘረኝነትን ሰይጣናዊ የመከፋፈያ ሥልት በመጠቀም ጥቅም የሚገኝባትን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታ ያልተቆጣጠረ ወያኔያዊ ማይም ቄስና ጳጳስ የለም፡፡ ከዚህ በላይ ሃይማኖትን ለብዝበዛና ለጭቆና መጠቀም ካለ ኢትዮጵያን ከላይ አስከታች የሚያውቅ ይፍረደኝ፡፡ እነታደሰ ሲሳይ በዘር ሐረጋቸው የሆኑትን ይሁኑ ተክለ ሰውነታቸው የታነፀው ግን በወያኔያዊ አስተሳሰብና በሰይጣናዊ ሁለንተናዊ አገዛዝ ነው፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያንን የተቆጣጠረው ሊቀ ሣጥናኤል ነው፡፡ ሰይጣን በጦርነት ያላገኘውን ዕድል በወያኔ አገኘና በቀላሉ ተቆጣጠራት፡፡ ይህ እውነት ሊገባው የማይፈልግ ወገኔን “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” የሚለውን ብሂል አስታውሼው ልለፍ፡፡ ኦሮሞ “ፈርዳን ኢንጌሳ መሌ ኢወራኑ” ይላል፡፡ እንደ ወንድሙ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ለማለት፡፡”

ሁሉን ቢያወሩት አያልቅም – ሆድም ባዶ መቅረቱ የሚያሳዝነን አንጠፋም፡፡ እንደመፍትሔ ልጠቁም የምፈልገው መዳን በቄስ እንዳልሆነ በግልጽ በመናገር ነው፡፡ ቄሶች እኮ የመንግሥተ ሰማይ መግቢያ ካርድ እስከመሸጥ የሚደርስ ድፍረት ያላቸው ደንቁረው የሚያደነቁሩ ናቸው፡፡ በመካከለኛው ዘመን የሮማ ካቶሊኮች Indulgnce Card – ሥርየትን የሚያሰጥ ካርድ – ይሸጡ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የኞቹ ቂላቂል ቀሳውስትም እንዳቅሚቲ ብዙ የሚሉት አላቸው፡፡ ትናንት አነበብኩት ባልኩት የውግዘት ደብዳቤ ላይ እንኳን “ካህናት ዐውደ-ምሕረቱ ላይ አሳዛኝና አሳፋሪ ስብከታቸውን ቀጠሉ። ለአብነት አንድ ላቅርብ፦ ‹እኛ ካህናት የምንለውን የማይቀበል በመንግሥተ-ሰማያት ቦታ የለውም።›” የሚል የቃቃ ጨዋታ ዓይነት ነገር ታዝቤያለሁ፡፡ የዚህን ቄስ ቃል ተቀብሎ ለመታዘዝ የሚሞክር ምዕመን ችግሩ የቄሱ ሳይሆን የምዕመኑ ነው፡፡ ለሰው ልጅ አለማወቅን የመሰለ መጥፎ ጠላት የለውም፡፡ እርግጥ ነው ማወቅም ካለማወቅ ባልተናነሰ ትልቁ ጠላቱ መሆኑ ሊካድ አይገባውም – የሕይወት ዕንቆቅልሽ እንደዚህ ነው እንግዲህ – ሕይወትን ጣዕም የሚሰጠው የዚህ ዕንቆቅልሽ የዞረ ድምር ይሆን? ይሆን ይሆናል፡፡ ከመጠምጠም መማር መቅደሙን ያልተረዱት እነዚህ ደናቁርት ካህናት ከነሱ ባልተናነሰ በማይምነት የጨለማ ግርዶሽ ውስጥ የሚኖረውን ገበሬና ባላገር ከፈጣሪ ህግጋት ውጪ ካለሥራ ቁጭ ብሎ ወደላይ ወደሰማይና ወደመንግሥት ብቻ እያንጋጠጠ እንዲኖር ፈርደውበት ከዓለም ሕዝብ በታች በችግርና በችጋር እየማቀቀ እንዲኖር አስገድደውታል – ለምሳሌ የበዓላትን ቁጥር ተመልከቱ፡፡ የወሩ ሠላሣው ቀናት አልበቃ ብለው ብዙ ተደራቢ በዓላት መኖራቸውን ታውቁ የለም? ብዙ፣ በጣም ብዙ፣ እጅግ እጅግ በጣም ብዙ የሞኝነት ሥራ በአምልኮተ እግዚአብሔር ስም ከበፊት ጀምሮ እየተሠራ ነው፡፡

በየጊዜው የሚመጡ መንግሥታትም እነዚህ ራስፑቲኖች የፈጠሩላቸው ሃይማኖተ-ማኅበረሰባዊ መደላድል ምቹ ሆኖ ስለሚያገኙት ሕዝቡን በፈለጉት አቅጣጫ እንደከብት ለመንዳት ይጠቀሙበታል፡፡ ከጓደኞቿ የወጣች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ እንዲሉ ነውና ከሕዝቡ መካከል የሚቃወማቸው ወገን ሲነሳም እየነጠሉ በመምታት ሀገርን ካለተቀናቃኝ በፈለጉት የአገዛዝ ሥልት እያርበደበዱና ሕዝብን በፍርሀት እያራዱ ይገዛሉ፡፡ በዚህ ሂደት የሃይማኖትን ሚና አለመርሳት ይገባል፡፡ ስለዚህ በነዚህ ፀረ-ሃይማኖት የሃይማኖት ሰዎች እምነት መጣል ለከፋ ጉዳት እንደሚዳርግ መረዳት አግባብ ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ ከፈጣሪየ ጋር በግሌ ከማደርገው የጸሎት ግንኙነት ውጪ እንደዱሮው ልቤን ለሰው አልሰጥም፡፡ ሰው ለራሱ ሳያውቅ የኔን ሸክም ይሸከምልኛል፣ በርሱም ሰበብ እኔ እጸድቃለሁ ብዬ ለማመን እየተቸገርኩ በመምጣቴ ግንኙነቴ ከርሱ ከራሱ ጋር እንዲሆን ወስኛለሁ፡፡ በዚያም ምክንያት ብዙ ንዴቴን ቀንሻለሁ፡፡ መቀነስ የሚቻልን ንዴት ለመቀነስ መሞከር ደግሞ ንዴትን ይቆጥባል፡፡ ከሃይማኖት ተቋሜ ጋር ያለኝ ግንኙነት ገደብ ያለውና በድርበቡ ነው፡፡ የጦዘ ፍቅር ለጠጠት እንደሚዳርግ ከተሞክሮ በማረጋገጤ በ“ያዋከቡት ፍቅር” ከሚመጣ ዳፋ ራሴን ለመታደግ እጠነቀቃለሁ፡፡ ሃይማኖቴ የግሌ መሆኑንም አምናለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች የሚሰናከሉት በአርአያነት ከፊት ለፊታቸው የሚያስቀምጡት ሰው ከጠበቁት በታች ወርዶ ሲያገኙት ከሚሰማቸው መጥፎ ስሜት የተነሣ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጎረቤቴ የነበረ የአንድ ደብር አለቃ ታላቅ ካህን የአንድ ምዕመን ሚስትን ይዞ ለሃይማኖታዊ ጉዞ(pilgrimage) ወደ ቁልቢ ይሄዳል፡፡ በዚያም ከዚያች ሴት ጋር አሼሼ ገዳሜ ሲል ቆይቶ ይመጣል፡፡ … አቶ ባል ከእንቅልፉ ሲነቃ ሃይማኖቱን ለወጠ – ፈታትም፤ ነፍሳቸውን ይማር፡፡ ይቺ ከከተማ የምታስወጣ ሃይማኖታዊ የጸሎት ጉዞ ያዘለችውን ጉድማ ብትሰሙ እናንተም ጉድ ብላችሁ አታባሩም፡፡ እንዴ –  እናውራ ካልን እኮ ብዙ ገመና – ብዙ ጉድ – ስንክሳርን እሚበልጥ ተራራ እሚያህል መጽሐፍ መጻፍ እንችላለን፡፡ (ማን ነበረች – “ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፤ ሚስቱ ዛሬ ሰምታ ልትታነቅ ነበር፡፡” ብላ ያቀነቀነችዋ አረሆ?) ከተናግሮ አናጋሪ ይሠውራችሁ፤ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ጊዜው ቀርቧል፤ እስከዚያው ግን ጠንቀቅ በሉ፡፡ ግን በርትታችሁ ጸልዩ፡፡ የሚዳነው በራስ ሥራና በግል እምነት እንጂ በደቦ አለመሆኑን ተገንዘቡ፡፡ … በቃኝ፡፡

ለገንቢ አስተያየት ምነዜም ዝግጁ ነኝ፡፡ [email protected]

7 Responses to የሃይማኖት እርጅና አያድርስ

 1. Alem Reply

  March 20, 2014 at 1:42 pm

  Dear Yiheyis,
  If you are serious and have strong evidence do not shy away from telling us as things are. I see you hesitating to say what happened. You need to name names and describe the crime. For example, Do you think the deceased Patriarch Pawlos had affairs? Do you think the current Patriarch Mathias had affairs with a Danish lady while in Jerusalem? Don’t let your readers guess what you wanted to say. Remember there are many who have been cheated and abused by clergy but have no idea this is happening to many others. Your truthful and clear evidence helps many more from being deceived by these wolves in sheep’s cloth. Thanks.

 2. Hayemanot Reply

  March 20, 2014 at 2:14 am

  Mr. Yeheyes I like your article it is well said. Can you please tell me are you supporting the wugzet or what are you trying to say. You have a right to support or not I just want to know your thought. As you said unless we stand for the truth the priests well play a game on us.

  • Yiheyis Aemro Reply

   March 20, 2014 at 6:14 am

   Haymanot, I support the wugzet, even more than that. But remember the biblical narration Jesu gave to the accusers of one lady who was charged of adultery. He said, let anyone of who had never committed a sin be the to throw the stone. I am not quoting word for word. I hope you can get me. Hence, we should be morally eligible to judge upon others. we have to look inwards before we judge others. Otherwise,if we are sure we are eligible, then the judgment we pass would be fair and just.

 3. menbi mar Reply

  March 19, 2014 at 1:29 pm

  U have the truth.But the problem is not just on church leaders only.Here abroad,some people forget the difference between religion and politics.Forexample, some people ask the church for Ato Meles “fitat” and the church don’t want to involv in such thing(in philadelphia).so some people were mad and start to open different (but same )church.The other problem is the people don’t know rule of law.when they are asked for public meeting, they don’t want to”waste” their time on board meeting. But later when the board decided something, they said no.So, in my opinion the big problem is we Ethiopians don’t have the culture of democracy, responsibly (“mebit &gideta”).The last but not least point is the government should be out of our churches.we need our own popes choose by ourselves sothat they serve the church, not governments.

 4. Eyob Reply

  March 19, 2014 at 11:12 am

  Yalkew negeroch fact binorachewim end writter mizanawi alhonkim specific hayimanot lay yatekork ayimeslehem 2nd dmo your titel na ye tsafkew neger ftmo yirarakal weyim sle andu emenet meriwoch personal blishunet bsifat bmatet bmawrat finally hayimanotu areje lmalet khone contradict yadergal meriwoch areju btil yishal neber b easy amaregna,slezih yam yarejew yante astesaseb mehonun kom bleh maseb alebeh….titileh tinitaneh l emenetu na l haymanotu kmikorekor sew antsar litalez ayigebam esti anebibew degagmeh k titilu antsar meriwochun lmetechet bleh emenetun sedebk, btam btam alawki sami nift yilekelikal ayinet honebih,free press sletebale zimbleh kmezebarek men metsa endalebih lma endmititsef, men lemastelalef endefelek mjemeria aseb. Yihe gen Jemreh abelasheh now yemibalew

  • Yiheyis Aemro Reply

   March 24, 2014 at 2:23 pm

   betam ameseginalehu Eyob. mels salseti yezegeyehut internet access slatahu newuna yikirta adrigilign. hasabih yigebagnal. emnetun tesadebik yalkegnie sihitet yimeslegnal. emnetunima akebralehu alku. chigiru yeswoch guday new, ye’agelgayochu sewoch enji emnetu embzam sihettet yelewum. yihin silih metsihafoch beswoch talka gebnet ayberezum aykelesum alilim. yemetsihafochin chigir menager biasfelig yichalal;
   lemangnawum yenegerkegnin teqebyalehu, kesihitetem lememar zigiju negnina yetenagerkew minm enkuan simetawinet bigolabetim ende melkam agatami bemewused emarbetalhu. Thank you Eyobina again.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *