ሰበር ዜና፣ ግንቦት 7 ወያኔ ላቀረበው “እንደራደር” ጥያቄ መልስ ሰጠ

December 2, 2013

የወያኔ አገዛዝ በመልዕክተኞቹ በኩል ላቀረበው የ“እንደራደር” ጥያቄ ከግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ምላሽ

ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ የገነባዉ ሥርዓት በከፍተኛ ችግሮች የተወጠረ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመሪው ሞት በወያኔ መሀል ያስከተለው ቀውስ፤ የሕዝብ ሁለገብ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበት መሄድ የፈጠረበት ስጋት እና ምርጫ በደረሰ ቁጥር የሚደርስበት ጭንቀት መጨመር ተደማምረው ውጥረቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እያደረሱት መሆኑን የሚያሳዩ በቂ ምልክቶች አሉ። የእስካሁኑ ተሞክሮዓችን እንደሚያሳየው ወያኔ ውጥረት ሲበዛበትና መዉጪያና መግቢያዉ ሲጠፋዉ ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችን “እንወያይ፣ እንደራደር” በማለት ለውጥረት ማስተንፈሻ ጊዜ የሚገዛ መሆኑን ነው። ሰሞኑን በወያኔ አገዛዝ መልዕክተኞች በኩል የደረሰንን “የእንደራደር” ጥያቄ ንቅናቄያችን በዋናነት ያየው ወያኔ እንደለመደው ድርድርን ለውጥረት ማስተንፈሻነት ለመጠቀም እየሞከረ መሆኑን ነው።Ginbot 7 logo

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ትግልና በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ዉይይቶች ቢመጣ የግንቦት 7 ምርጫ መሆኑን ንቅናቄያችን በተደጋጋሚ ግልጽ አድርጓል። ግንቦት 7ን ሁለገብ ትግል ውስጥ እንዲገባ ያስገደደው የወያኔ እምቢተኝነትና እብሪት ብቻ ነው።

የግንቦት 7 ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰሞኑ የወያኔ የእንደራደር መልዕክት እንደደረሰው በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባጠቃላይ እንጂ ግንቦት 7ን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነ ከድምዳሜ ላይ ደርሷል። ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሚያደርገው ትግልና እየከፈለ ካለው መስዕዋትነት ጋር በቀጥታ ግንኙነት አለው። በመሆኑም፤ ለቀረበልን ጥያቄ ግልጽ መልስና፤ ድርድር ስለሚባለው ጉዳይም ያለንን አቋም ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ለማቅረብ የሚያስችል ተጨማሪ አጋጣሚ አድርገን ወስደነዋል። በዚህም መሠረት ለቀረበልን ጥያቄ የሰጠነዉን መልስና አቋማችንን በድርጅታችን ድረ ገጽ ላይና በሌሎች መገናኛ ብዙሀን በኩል በይፋ ለመግለጽ ወስነናል።

በድርድር ስለሚመጣ ለውጥ ያለን የመርህ አመለካከት:

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዳደረግነው ድርጅታችን ከምሥረታው ጀምሮ የትግል ስልቱን ሲወስን እምነቱ አድርጎ የተነሳው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በሀገራችን በሰላማዊ መንገድና በድርድር ቢመጣ በእጅጉ የሚፈልገውና የሚመኘው መሆኑን ነው:: ድርጅታችንን ወደ ሁለንተናዊ ትግል የገፋው በመግቢያው ላይ እንደገለጽነው የወያኔ እብሪት ብቻ ነው:: የቀረበልን ምርጫ በባርነትና በውርደት መኖር ወይም ለነፃነት እየታገልን መሞት ቢሆን ኖሮ ንቅናቄያችን የሚመረጠው ምን ግዜም ለነፃነትና ለአገር አንድነት ታግሎ በክብር መሞት መሆኑን በተደጋጋሚ ለሕዝብ ግልጽ አድርገናል። ይህ የማይናወጥ አቋማችን ደግሞ ለይምሰል የተቀመጠ አቋም ሳይሆን ከልባችን የምናምንበትና ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አባላቶቻችንን ያሰባሰብንበት አቋም ነው። ዛሬ በትግሉ ግንባር የምንንቀሳቀሰውና ወደ ግባችን የሚወስደንን ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰድን ያለነውም በዚሁ አቋማችን ዙሪያ ነዉ።

ይህ አቋማችንና እምነታችን በአንድ ላይ ጎን ለጎን የሚሄዱ ሁለት መርሆችን አጣምሮ የያዘ ነዉ። አንደኛው፣ ሂደትን በሚመለከት ሁሌም ለድርድር ክፍት መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ ይህ የድርድር ሂደት እንዲያው ለለበጣ የሚደረግ ሳይሆን ወደሚፈለገው ነጻነት በአነስተኛ መስዕዋትነት ሊያደርስ ይችል ከሆነ በሩን ላለመዝጋት እንጂ፣ በምንም አይነት ዋና ውጤቱን፤ ማለትም ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ማድረግን፤ የሚቀይር ወይንም ከዚያ ያነሰ ውጤትን ለመቀበል መፍቀድን ፈጽሞ የማያመለክት መሆኑን ነው::

በእኛ በኩል ድርድሩን አስፈላጊና ጠቃሚ የሚያደርጉት መነሻ የፖለቲካ እሳቤዎችም ከእነኝሁ ሁለት መንታ ገጽታዎች የሚመነጩ ናቸው:: በድርድር ለሚገኝ ፍትሀዊና እውነተኛ ውጤት ክፍት መሆናችንን ሁሌም እናሳያለን፤ ነገር ግን ይህን የምናደርገው የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት መከፈል አለበት የሚለውን መሠረታዊ የአካሄድ መርህ በመመርኮዝ እንጂ መርሀችንን ለድርድር ለማቅረብ እንዳልሆነ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል::

ስለዚህም:

ሀ)    የድርድሩ ውጤት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በአስቸኳይ እውን ማድረግ መሆን ይኖርበታል:: ይህ ዋናው ግብ ሆኖ ከዚህ በመለስ የሚኖሩ በሂደት የሚገኙ አነስተኛ ግቦች ሊኖሩ ይችላሉ (ለምሳሌ የፖለቲካ እስረኞች ማስፈታት…ወዘተ):: ሆኖም በምንም አይነት ለእነኝህ መለስተኛ ግቦች ተብሎ ዋናውን ግብ የሚያሳጣ ወይንም ጊዜውን ያላግባብ የሚያስረዝም ድርድር፣ ድርድር ነው ብሎ ድርጅታችን አይቀበልም። ስለዚህም ዋናው የድርጅታችን ዓላማና ግብ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ፣ በፍጹም ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም:: በሥልጣን ላይ ባለው ኃይል በኩል ወደዚህ ግብ ለመድረስ ቁርጠኝነቱ በሌለበት ሁኔታ በሚደረግ ማንኛውም አይነት ድርድር ውስጥ ግንቦት 7 አይሳተፍም::

ለ)  በግንቦት 7 እምነት ማንኛውም ድርድር ወያኔ ከግንቦት 7 ጋር በተናጠል የሚያደረገው ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያካተተ መሆን ይኖርበታል:: ድርጅቶችን በተናጠል እየለያዩ “እንደራደር” ማለት በራሱ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ስሌትን የያዘ እሳቤ እንጂ፣ በዘላቂነት አገሪቱን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አገር ለማድረግ መፈለግን አያመለክትም:: ለአንድ ድርጅት ለብቻው የሚመጣ ወይም የሚጠቅም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለም:: ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ፍላጎት ያለው ድርድር በአገሪቱ ያሉትን የተለያዩ የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ኃይሎችን ያካተተና ያመኑበት መሆን ይኖርበታል:: የሚደረገው ድርድርም ማን በስልጣን ላይ ይውጣ ወይንም የፖለቲካ ስልጣንን ባሉት ኃይሎች መሀከል እንዴት እናከፋፍለው የሚል የስልጣን ቅርምት ድርድር ሳይሆን፤ ሕጋዊና የሕዝቡን የሥልጣን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣን እንዴት እንደሚያዝ ፍትሀዊ የሆነ ሂደትን ለማስጀመር የሚደረግ ድርድር መሆን አለበት::

ሐ) ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይህ ጉዳይ የሚመለከተው አንድን ድርጅት ወይንም የፖለቲካ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው:: ይህ እስከሆነ ድረስ እንዲህ አይነት ድርድር ከሕዝቡ በተደበቀ ሁኔታ በሚስጥር የሚካሄድበት ምንም ምክንያት የለም::

2)   ከዚህ በፊት ከወያኔ ጋር ከተደረጉ ድርድሮች ያገኘናቸው ተመክሮዎችና ከዚህ በመነሳት ወደፊት በሚደረጉ ምንም አይነት ድርድሮች እንዳይደገሙ ለመጠበቂያ የሚሆኑ ከአሁኑ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች

ከማንኛውም ወገን ጋር የሚደረግ ድርድር የተደራዳሪዎቹ ምንነት፤ ውስጣዊ ባህርያቸውን፤ ከተለምዶ ተግባራቸው ያላቸውን ተአማኒነትና ወደዚህኛው ድርድር ያመጣቸውን ምክንያቶች በበቂ ከመገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚታይ ጉዳይ ነው:: ቃሉን አክባሪና ተዓማኒ ከሆነ ሰው ጋር የሚደረግ ድርድርና ያለፈው ታሪኩ ምንም አይነት የተዓማኒነት ባህርይ ከማያሳይ ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድርም ሆነ ለድርድሩ የሚደረግ ዝግጅት ለየቅል ናቸው:: ይህ ማለት ግን ተዓማኒነት ካለው ኃይል ጋር ብቻ ነው ድርድር የሚካሄደው ማለት አይደለም:: በፍጹም ተዓማኒ ካልሆነ ኃይል ጋር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር ግን ድርድሩ በእርግጥም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መሆኑን የሚያሳዩ ጠንካራ መጠበቂያዎች (System of Verification) እንዲሁም ግልጽ የመተግበሪያ ሥርዓቶች (Implementation Mechanism) ሲደረጉለት ብቻ ነው ከምር ሊወሰድ የሚችለው:: ከዚህም ባሻገር ግን መጀመሪያውኑ ወደ ድርድር የሚመጣው ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሳይሆን በእዉነተኛ መንፈስ ከድርድር የሚመጣውን ውጤት በመፈለግ መሆኑን የሚያሳዩ “የመተማመኛ” ምልክቶች ሲያሳይ ነው በእርግጥም ወደ ድርድር የመጣው ከልቡ ድርድሩንና ከድርድሩ የሚመጣዉን ዉጤት ፈልጎ መሆኑን ለማመን የሚያስችለው::

ወያኔ ከተቀናቃኝ ወገኖች ጋር “ድርድር” ሲያደርግ የመጀመሪያ ጊዜዉ አይደለም:: እኛ እስከምናውቀው ድረስ ምናልባት በኃይል ይበልጡኛል ብሎ ከሚያምናቸው ወገኖች ጋር ካልሆነ በስተቀር፣ በረሃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም ጊዜ ለቃሉ ታማኝ፤ ለመርሁ እውነተኛ፤ ለደረሰበት ስምምነት ተገዢ ሆኖ አያውቅም:: ይልቁንም ሶስተኛ አደራዳሪ ወገኖችን በሚያሸማቅቅና በሚያሳፍር መልኩ ውሸትን እንደ አዋቂነት፤ ማጭበርበርን እንደ ብልጠት፤ የተስማማበትን በገሀድ ማፍረስን እንደ የአመራር ብልሀት አድርጎ የሚያይ፤ ምንም እፍረትና ጨዋነት የሚባል ነገር ያልፈጠረበት እኩይ ኃይል ነው:: ከራሱ የድርጅት ጥቅምና በስልጣን ከሚገኝ የዝርፊያ ሀብት ማካበት ባሻገር፤ ለአገር ዘላቂ ጥቅም ብሎ የራሱን ጥቅም አሳልፎ የሚወስደው ምንም እርምጃ እንደሌለ በተግባር በተደጋጋሚ ያረጋገጠልን ኃይል ነው:: በግንቦት 7 ውስጥ ያለን ወገኖች ይህንን የወያኔ ባህርይ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ሌሎች ጽፈውት ያነበብነው ሳይሆን፣ እራሳችን በተግባር በተሳትፈንበት ሂደት ያገኘነው ጥልቅ ግንዛቤ ነው:: ይህንን ደግሞ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ከድርጅቱ ታሪክ ጋር የተጣበቀ፤ በአመራር አባላቱ ላይ እንደ ግል ባህርይ የሰረጸ መሆኑን እስክንገነዘብ ድረስ በተደጋጋሚ የተመለከትነው ነው:: ስለዚህም ከዚህ ኃይል በኩል የሚመጣን የ “እንደራደር” ጥያቄ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ለገባበት የፖለቲካ ውጥረት ማስተንፈሻ፣ ለውሸት ፕሮፓጋንዳው መጠቀሚያ፤ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ መሰብሰቢያ፤ የዴሞክራሲ ታጋዮችን ትጥቅ ማስፈቺያና ወኔ መስለቢያ አድርጎ እንዲጠቀምበት በፍጹም አንፈቅድለትም:: ስለዚህም ከላይ በመርህ ደረጃ ከጠቀስናቸው ሶስት ጉዳዮች በተጨማሪ ምንም ዓይነት ድርድር ከመደረጉ በፊት ወያኔ ጉዳዩን ከምር የወሰደው መሆኑን የሚያሳዩ “የመተማመኛ” እርምጃዎች መውሰድ አለበት ብለን እናምናለን::

እነኝህም፣

ሀ)  ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት:: ይህ ደግሞ በግልጽ     የሚታወቁ እስረኞችን ብቻ ሳይሆን በድብቅ የተቋቋሙ ማጎሪያና ማሰቃያ ቤቶች ያሉትን ሁሉ ማጠቃለል አለበት።

ለ)  በሕዝብ በተለይ በተቃዎሚ ኃይሎች ላይ ወያኔ በየቀኑ እያካሄደ ያለውን ወከባና እንግልት ባስቸኳይ ማቆም፣ ሰብዓዊና የዜግነት መብታቸውን ማክበር አለበት።

ሐ)   በፖለቲካ ምክንያት ከዚህ በፊት የተወሰዱ ሁሉም ዓይነት ፍርድ ተብዮ ውሳኔዎች እንዲሻሩ ማድረግ፤ በሂደት ላይ ያሉ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ምንም አይነት ክሶችን ማቋረጥ አለበት።

መ)   ሕዝብን በፍርሃትና በስጋት ለማቆየት ሆነ ተብለው የወጡ አፋኝ ህጎችን በአስቸኳይ ማንሳት አለበት።

ሠ)   ማንኛውም ድርድር ገለልተኛ የሆኑ ሶስተኛ ወገኖች ባሉበት፤ የድርድሩ ሂደት በምስልና በድምጽ ተቀርጾ በገለልተኛ ወገኖች እጅ ብቻ የሚቀመጥ፣ የድርድሩ ቦታም የተደራዳሪ ወገኖች በጋራ በሚስማሙበት ቦታ መሆኑን መቀበልና ይህንንም በግልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ አለበት።

እነኝህ ከላይ ያስቀመጥናቸው በወያኔ በኩል የሚወሰዱ “የመተማመኛ” እርምጃዎች ለተቃዋሚዎች ተብሎ የሚወሰዱ እርምጃዎች አይደሉም:: ወያኔ እነዚህን እርምጃዎች ለመውሰድ ቁርጠኝነት ሳይኖረው ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት የሚደረግ ድርድር ላይ ከምር ይሳተፋል ብለን ማመን በፍጹም ስለማንችል ነው ::

እስከዚያው ድረስ ግን ግንቦት 7ም ሆነ ሌሎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት በቁርጠኝነት የምንታገል ኃይሎች፣ ወያኔ እነኝህን የመተማመኛ እርምጃዎች እስኪወስድና ቀደም ብለው በተቀመጡት መርሆች መሠረት በሚደረግ ድርድር በተግባር ሊመነዘር የሚችል ስምምነት፣ አልፎም ለምንም አይነት ማጭበርበርና መንሸራተት እድል የማይሰጥ ጠንካራ መጠበቂያዎች መኖራቸው እስኪረጋገጥ ድረስ፣ የጀመርነውን ትግል ይበልጥ አጠናክረን የምንገፋበት እንጂ በምንም አይነት ለአንድ አፍታም ቢሆን በድርድር ስም የማንዘናጋ መሆኑን አበክረን እናስታውቃለን::

የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣

ኅዳር 23፣ 2006 ዓ:ም

የመግለጫውን PDF ከዚህ ላይ ያንብቡ

7 Responses to ሰበር ዜና፣ ግንቦት 7 ወያኔ ላቀረበው “እንደራደር” ጥያቄ መልስ ሰጠ

 1. minnai Reply

  December 3, 2013 at 9:16 pm

  G7 should never be deflected from its mission. the woyane thugs are like a headless chicken. they do not even have a recognised leader, who are you going to negotiate with. The politbureau of Tigre people liberation is factionalised and secretive and very often they do not follow any rules of engagement.

  we have been hearing that Lencho Letta, who leads a separatist oromo group has been secretly negotiating to get a seat in the woyane parliament for years, without success.

 2. lantabure Reply

  December 3, 2013 at 11:44 am

  መቼም ግንቦት 7ትን በምን ቃል እንደምገልጸው ቃላት ያጥረኛል፡፡ ለከፋፋይ አምባገነን የሚገባው መልስ ከዚህ የበለጠ የለም፡፡ ከዚህ በፊት እነሱ ብቻ የተጨቆኑ ይመስል ለብቻቸው ሲደራደሩ ለነበሩት (ለምሳሌ መ.ኢ.አ.ድ. ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል በ2002 እንደኛ አቆጣጠር፤ ለኦ.ብ.ነ.ግ. በቅርቡ 2005) ትምህርት ይሁናቸው፡፡

  ወያኔ እውነቱን ከሆነ ከግ7 ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው መደራደር ያለበት የመውደቂያ ቀን ስትቃረብ እየከፋፈሉ “እንደራደር” ያውም ጊዜ ለምግዤያ ካልሆነ ወያኔ እንደሆነ መውደቄያው ደርሶአል፡፡

  በድጋሚ ግ7 bravo

 3. በለው! Reply

  December 3, 2013 at 7:34 am

  **ግንቦት ፯ ሲደመር ግንቦት ፳ ይሆናል ግንቦት ፳፯ ይታሰባል ህዳር ፳፫ ታጠነ በለው!
  >> ህወአት/ወያኔ/ኢህአዴግ አሸባሪ ሆነ ማለት ነው!? “ከአሸባሪው የግንቦት፯ ጋር የተገናኘ፣ማኒፌስቶውን ያነበበ፣ ያስነበ፣ አብሮ ሻይ ቡና እንኳን ያለ የአሸባሪው አዋጅ ይከለክላል። ” ሼም የለሽ ከማል ከተጨቆኑና ከተረሱ ብሔር የብሔረ ሰዎች የሕግ ምሁር። የቀድሞው ባለዕራዩ ተ/ሚኒስትር ከኤርትራ መነግስት ፐሬዘዳንት ጋር ለመነጋጋር ፶ ግዜ ሞክረው ነበር።እኔም አስመራ ድረስ ሄጄ እግሩ ላይ ወድቄ እለምናለሁ” አቶ ኅያለመለስ ዜናው ደስአለኝ። “የኢህአዴግ መንግስት ለድርድር ከ፸፩ ግዜ በላይ ልመና አቅርቧል”
  ህወአት አሰልጣኝ የቀጠናው አተራማሽ አቶ ኢሳአስ አፈወርቂ። “፸ግዜ ልመና ማቅረባችን ትዝ ይለኛል ፸፩ግዜ መሆኑን እርገጠኛ አደለሁም አልቆተርኩም እነሱ ቆጥረውት ይሆናል።አራት ነጥብ። የጠተቀለሉት /ሚኒስትር አቶ መለስ

  *ለግንቦት፯ የቀረበው የ፫ተኛ ግዜ “የእንደራደር “ጥያቄ ምን እንደሆነ ?ለምን እንደሆነ? በማን እንደሆነ ?እንዴት እንደሆነ? ባይታወቅም አቶ ኅይለማርያም ደስአለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ በራዕዩ እየተመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ህወአት/ወያኔ የውጭ ጉዳይና የብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ሆነው እንደፎከሩ፣ እንደተወራጩ፣ ፈገግታቸው ቀንሶ፣ ፍንጭታቸው መግጠም፣ መጀመሩ ይገርማል። በእርግጥም” ከፊትም ከኋላም ሆናችሁ ምሩኝ” አሉ። በአንድ ወነበር በ፫ ተሽከርካሪ ብሔር ብሔረሰብ ክላስተር በ፪ ተለዋዋጭ ምክትል የብሔር ጎማ በ፩ መደገፊያ ፕሬዘዳንት ተደርጎላቸው ይውተረተራሉ። አቶ ኢሳያስ ካልመጣህ መጣሁ አሉ።

  *ግንቦት አልፎ በወርሃ ኅዳር ሲታተን ይህ መታሰቡ መልካም ነው። ግን የግንቦት ፯ አሸባሪነት በፓርላማ ተሰረዘ? ኦብነግና ኦነግ የፓርላማ አባል ሊሆኑ ነው? ወይንስ መሳሪያ የሌለውን የተኩስ አቁም ስምምነት ነው?ግን እውስጥ ያሉት እነማን ሆኑና ባትሉኝ!?
  ————__________________——————
  **ይህ የጠ/ሚኒ አማካሪዎች ሽረባ ፉገራ ይመስላል። መቼም ጠ/ሚኒስትሩ እንደዚያ ደንፍተው አሁን በእሳቸው አመራር ላይ ውሃ የሚደፉ ከሆነ ትዝብት ነው ። ድሮስ ሰውዬው ከምንም አይቆጠሩም ማታ ማታ ሲገረፉ ነው ቀን የሚለፈልፉት ማለት ነው። **ይች የተዳነቀችና የተሰበረች ዜና ሕዝቡ ምን አለ? ደጋፊ ነው ተደጋፊ የሚንጫጫው? መሀል ሰፋሪውስ ምን አደረገ? ተለሳላሹ?ብሔርተኛው?ጽንፈኛው? ሙሰኛው? ነጋዴው? ኢንቨስተሩ? ዴያስፖራው? አርቲስቱ?ኪራይ ሰብሳቢው? ጥቅመኛው? እያሉ ሰሞኑን ሥራና አፍ ይከፈታል።
  *** “ድርድር” ምንድነው? አትንኩኝ አልነካችሁም? ካልነካችሁኝ የተፈረደባችሁ ከሞት ቅጣት ወደ እድሜ ልክ ይቀየራል?አሸባሪነታችሁ ተሰርዞ ተባባሪ ፓርቲ (በአንድ ፖለቲካ ጥላ ሥር ትሰባሰባላችሁ) ትሆናላችሁ ማለት ይሆን? የሥልጣን መካፈል ይሆን? ኢህአዴግ የ፭ዓመቱ ህዝብ የሰጠው ኮንትራት እንደማይታደስ ገባው? የኮንትራት ተፎካካሪዎችን አስወጥተን ከምንወጣ አስገብተን እናስወጣቸው ብለው ይሆን? አሸባሪን ለማጥፋት አሸባሪ መሆን አማራቸው? ግንቦት፳ ሲደመር ግንቦት ፯= ግንቦት ፳፯ መድህኒያለም ለየት ያለ ማሊያ አስለብሶ ደግሞ ለ፳ ዓመት ሊያስለቅሰው ይሆን?
  ****የኢህአዴግ የመጨረሻዋ የሥልጣን ሹም ሽር (ክላስተር ቦምብ) አልተመቸችኝም። የስኳር ሚኒስትር የሃይማኖት መሪዎች የበላይ አካል። የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ የውጭ ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት ተጠሪ፣ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግርኳስና የፖለቲካ አቅጣጫ የአካባቢው አየር ሁኔታ ተቆጣጣሪ ጨምሮ ይሰራል። አቤት የኅብረት አመራር (አመራር በደቦ)
  (ሀ)ኢህአዴግ አለውን እስረኛ እስኪያረጋግጥ አህያ ቀንድ ታወጣለች!
  -ለመሆኑ እስረኛውንና የእስር ቤቱን ቁጥር በውል ያውቀዋል?
  ( ለ) በተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ወከባና እንግልት ባስቸኳይ ማቆም፣ ሰብዓዊና የዜግነት መብታቸውን ማክበር፡
  -ድንቄም! ለመሆኑ ትርጉሙን ያውቁታል? ዜግነት! መብት!ሰብዓዊነት!ሉዓላዊነት!ሰንደቅ!ሀገር! ጉድ እኮ ነው ድርድሩ ቀርቶ መማማሩ በተቻለ በለው!
  (ሐ) ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ምንም አይነት ክሶችን ማቋረጥ አለበት።
  -”በሀገር ውስጥ በፖለቲካ የታሰረ አንድም ሰው የለም!መታሰርም የለበትም!አለመታሰር ሕገመንግስታዊ መብቱ ነው። እሺ እስር ቤታችሁን አስጎብኙን? “የዓመቱ አቦ ስለሆነ የእስር ቤቱ ተረኛ ኀላፊ ጸበል ሊቀምሱ ሄደዋል። ከነገ ጀምሮም የዓመት ፍቃድ ሞልተዋል።” ይቺ ነች ኢህአዴግ !እንዲህ ከሚቀሳፍቱ ጋር ነው ‘ድርድሩ’!?ለዚያውም አንዱ የተናገረውን ሌላው ያስተባብላል።
  (መ) አፋኝ ህጎችን በአስቸኳይ ማንሳት አለበት።!
  -ህወአት ማኒፌስቶ (ሕገመንግስት) የሚከበረው ግን የማይተገበረው ለእያንዳንዱ ፻፮ አንቀጽ ፻፮ ሕጎች/መመሪያ/ ደንቦች /ወጥተውለታል። ይህ ማለት ለእያንዳንዱ ንዑስ አንቀፅ ማጥፊያ ህግ አለው።
  (ሠ)የድርድሩ ሂደት በምስልና በድምጽ ተቀርጾ በገለልተኛ ወገኖች እጅ ብቻ የሚቀመጥ፣
  - እንኳን ስለሀገር አብሮ ለመሥራት”ድርድር” ቀርቶ የግለሰቡን ራእይ ለማስቀጠል ፮ሚሊየን ኢህአዴግ አባላት ንፍጥና ለሀጫቸውን ባዶ ሳጥን ላይ በሁሉም ክልልና በቤተመንግስት ሜዳ ላይ ሲያዝረከርኩ ታይተዋል። ይህ ሀገራዊ ራእይ ከሆነ የሚያስማማውም የሚያለያየውም ሀሳቦች ለህዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው።ሽፍንፍን በአክፋይ ዳቦ ዘመን ቀረ በለው!ዓለም አንድ መንደር ሆነች ተባለ አሉ ኢቲቪ ቆርጦ በሚቀጥለው “የግንቦት ፳፯ ሃረካት ፊልም” እዳይሰራበት ዘመኑ የሥራ ፈጠራ አደለምን አሁን ከዚህ ተሰባሪ ዜና በኋላስ ስንቶች ቆመው አድረዋል!? አክራሪ ደጋፊዎችና አክራሪ ተቃዋሚዎችስ ካራ አይመዙምን?
  ለሁሉም ሠላም በቸር ይግጠመን ከሀገረ ካናዳ<<<>>>>>>>

 4. Biru Reply

  December 3, 2013 at 12:01 am

  This is the work of the only healthy, farsighted, and real political org that Ethiopia has never seen. Good job, G7. Ginbot 7 is a trusted political org that has assembled the best minds of the nation, many of them are very credible people even in their social life. The 7 highest leaders of G7 are the most astute and able leaders that definitely broke the old tradition and brought practical politics to the otherwise hate infested Ethiopian politics. Go Ginbot, I am with you

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>