የትምህርት ተቌማት የእውቀት ወይስ የፖለቲካ ሜዳ!?

November 30, 2013

ከቅዱስ ዮሃንስ

ትምህርት ዜጎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመቅረጽ ለራሳቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሃገራቸው ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ የእውቀት ማሸጋገርያ ስልት ነው፡፡ ዛሬ በስልጣኔ የገሰገሱ የአለም ሀገራት የዕድገታቸው ዋነኛ መነሻ ትምህርት ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው። ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት ፓኬጅም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በዘመናዊ አኳሃን እንዲመነደጉ ከተፈለገ በተግባር የታገዘ፣ ፈጠራና ክህሎትን የሚያዳብር ጥራት ያለው ትምህርት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡

የትምህርት መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ መጣል ከጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን ከሁለተኛው አለም ጦርነት በፊት ትምህርት የሚሰጠው በመንግስትና በሃይማኖት ተቋማት ዙርያ ለአስተዳደራዊ ክህሎት፣ ለቀኖናና ለሃይማኖት እውቀት ሲባል እንደነበረ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአፄ ሃይለ ስላሴ ስርዓት ዘመናዊ ትምህርትን በተደራጀ መልኩ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጡ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ቢሆንም የትምህርት ቤቶች እድገት ከማህበረሰቡም ሆነ ከሃይማኖት ተቋማት በገጠመው ተጽእኖ ምክንያት የመስፋፋቱ እድል አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በደርግ ወቅቱም ቢሆን የነበረው አጣዳፊ ጉዳይ አብዮቱ በመሆኑ በመማርና ማስተማር ላይ የነበሩትን መምህራንና ተማሪዎች በነቂስ አሰልፎ አብዮቱን ለማስተዋወቅ በሚል ሰበብ ወደ እድገት በሕብረት የዕውቅትና የስራ ዘመቻ አዘመተ፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ እራሱን በጥቂቱም ቢሆን ማጎልበት የጀመረው የትምህርት ስርዓት ከባድ ፈተና ውስጥ ወደቀ፡፡ በማያባራ ዘመቻ፣ ግድያ፣ አፈናና ጦርነት ተተብትቦ እራሱን ፋታ የተነሳው ደርግ፤ በቂ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትና መምህራንን ለማብቃት ጊዜ አልነበረውም፡፡ በዚህም ምክንያት መምህር አልነበሩም፡፡ ትምህርት ቤቶችና ለመማር ማስተማር ሂደቱ በሚያስፈልጉ ግብአቶችና ቁሳቁሶች አልተሟሉም፡፡ የትምህርት ስርዓቱ በአጠቃላይ እርቃኑን እንደቀረ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓተ ውድቀት አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡

የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ተብትበውና ቀስፈው የያዙት ችግሮች ከደርግ ጋር ተዳብለው ስር እየሰደዱ ቆይተው፣ ዛሬም በኢህአዴግ ውስጥ በመሸጋገር ማጣፊያ እንዳጠራቸው ቀጥለዋል ፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ በደርግ ስርዓት የለከፈው የማጥራት ሳይሆን በማብዛት፣ በማዳረስ ላይ የመተማመን በሽታ ዛሬም ወያኔን ቀስፎ እንደያዘው ይገኛል፡፡ ትምህርትን ለሁሉም ዜጐች በስፋት የማድረስ ተልዕኮን እንደያዘ የሚያስበው ወያኔ፤ የትምህርቱን የጥራት ደረጃ ለዚህ ግቡ ሲል እየጨፈለቀው ስለመሆኑ ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ሀገሪቱ ካስቀመጠችው አነስተኛ ማለፊያ ነጥብ እጅግ ያነሰ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉት የትምህርት እርከኖች ቁጥራቸው እየበዛ መምጣቱ ሳያንስ፤ ወደ መሰናዶ ትምህርት የገቡት በሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡበት አሳፋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል። ለየትምህርት ክፍሎቹ በማይመጥኑ መምህራን መማር፣ በአነስተኛ ደረጃ መሟላት ይገባቸው የነበሩት የትምህርት መሳሪያዎች እጦት አልፎም የአካዳሚያዊ ነፃነት በፖለቲካዊው ስርዓት በጥልቁ መጣስ፤ የኢትዮጵያ ትምህርት ተቋማት መሰረታዊ መለዮ ሆኗል። የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት የትምህርት ስርአቱን ቀስፈው የያዙት ችግሮችን አንድ በአንድ ነቅሶ ማሳየትና መዳሰስ ሳይሆን፤ ለስርአቱ ውድቀት በተለይም ለጥራቱ ዝቅጠት ግንባር ቀደም መንስኤዏች ተብለው ከሚፈረጁት መካከል ትምህርትን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም ላይ ትኩረት ያደርጋል።

የወያኔ መንግስት ትምህርትና የትምህርት ተቋማትን ለፖለቲካ ፍጆታ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመምህራን አመራረጥ በተለይም ለከፍተኛ ትምህርት አስተማሪነት የሚታጩ መምህራን የመለኪያው ዋና መስፈርት የፖለቲካ አቋም መሆኑን መመልከት ይቻላል። ወያኔ በዘረጋው የትምህርት ዘርፍ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ መምህራን የሚመለመሉት በፖለቲካ መስፈርት ነው። በነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ችግሮች በቀጥታ ከትምህርት ጋር የተያያዙ መሆናቸው እየቀረ ፖለቲካዊ ይዘት እየተጎናፀፉ መጥተዋል፡፡ የወያኔ የካድሬ እንቁላል መጣል እና የረጅም ጊዜ አሕዳዊ አገዛዝ ፍላጎት የራስ መከላከል ሥራዎች በይፋ ይጀመራሉ፡፡ ባለፈው በደርግ ስርዓት ውስጥም ትምህርቱ ከሶሻሊዝም ርዕዩተ ዓለም ውጪ አልነበረም። አሁንም ቢሆን ትምህርትና ተቋማት በፖለቲካውና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ -ዓለም የተቃኙ ናቸው። ከዚህም በላይ መንግስት ዩኒቨርስቲ መክፈትን እንደ ፖለቲካዊ አፍ የማዘጊያ ስልት ተጠቅሞ የፖለቲካ ድጋፍና ታማኝነትን እንደማግኛ መሳሪያ እየተገለገለበት ነው፡፡ ዛሬ በሃገራችን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መገኘታቸው እሰይ የሚያስብል ቢሆንም እጅግ አሳዛኙ ነገር ግን ሁሉም ተቋማት በፖለቲካ ተተብትበው የእውቀት አምባ መሆናቸው ቀርቶ የካድሬ መፈልፈያ ተቋማት መሆናቸው ነው። ይህም የትምህርት ጥራቱን እንዲያሽቆለቁል አድርጐታል።

ወያኔ በዩኒቨርስቲዎች እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በነጻነት እንዲያስቡ አይፈለግም፤ አይፈቀድምም፡፡ እንኳን ተማሪዎቹ ይቅርና መምህራኑ ጭምር በነጻነት የሚያስተምሩትን ለመምረጥ አይደፍሩም፡፡ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ለተማሪዎቻቸው የሚያስተላልፉትን እውቀት ሀገሪቷ ላይ ካለ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ተንትኖ ለማስረዳት የሚደፍሩት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ክፍል ውስጥ ለሚያስተምሩትም ሆነ ለሚናገሩት ነገር ልክ በቤተ ክህነት ውስጥ የአምላክን ቃል እንደሚሰብክ ሰባኪ ጥንቃቄን ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው የተዘረጋውን አስጨናቂ የአምባገነን ስርአት ከመፍራት፤ የተናገሩት ነገር ገዥው ፓርቲን የሚነቅፍ (የማይደግፍ) ከሆነ ያለአግባብ ስም ተለጥፎባቸው የእንጅራ ገመዳቸውን ስለሚበጠስ ነው። በለፈለፉ ባፍ ይጠፉ ይባል የለ። ከክፍል ውጪም በተቋማቱ አመራሮች ለሚፈፀሙ የአሰራር ስህተቶች እና በደሎች ለመተቸት እምብዛም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አመራር ተብለው የሚሾሙት የትምህርት ተቌማት ባስልጣናት የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ የመንግስት ቀኝ እጅ በመሆን የሚያገለግሉት የወያኔ ግልገል ካድሬ ናቸው። እነዚህ አካላት በሚያስተዳድሩት መምህራን ላይ ኢፍትሃዊ እርምጃ ቢወስዱም ማንም ሃይ ባይ የላቸውም።

ተማሪዎች በአብዛኛው ለትምህርታቸው የሚሰጡት ትኩረት እና ውጤታቸው ምንም አያስጨንቃቸው፤ ደንታቸውም አደለምም ለማለት ያስደፍራል። ከዚህ ይልቅ የወጣቶች ሊግ እና ማንኛውንም የመሪው ፓርቲ ተደራሽነት የሚያሳድጉ/የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ታትረው ይሰራሉ። ይህም በጓደኞቻቸው ላይ የበላይነትን እንዲያገኙ ከማድረጉም በላይ ተሰሚነትን በትምህርት ቤት ኃላፊዎች ያስገኝላቸዋል፤ ከበድ ሲልም የንግድ እና የፖለቲካ ሥራ እንዲያገኙ ይመቻችላቸዋል፡፡ ይህ በትምህርት ዘርፍ ላይ የተዘረጋው ስርዓት ለተማሪዎች የሚያስተላልፈው መልእክት ግልፅ ነው፡፡ በትምህርት ተግቶ እውቀት ሸምቶ ሀገሪቷን ለመጥቀም ከመታተር ይልቅ ርካሽ የፖለቲካ ተወዳጅነት ማግኘት የስኬት መንገድ አቋራጭ መሆኑን ነው፡፡ ለትምህርት ትኩረት መስጠት ያለውን ጥቅም ተረድተው ይሻለኛል ብለው የሕይወት መስመራቸውን የሚያስተካክሉት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አሽቆልቁሏል።

በአሁኑ ወቅት ወያኔ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚማሩት ውስጥ 85% የሚሆኑ አባላት እንዳሉት እና በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ህዋስ እንደዘረጋ ይገልፃል፡፡ እንግዲህ ይህ ፐርሰንት በመመልከት አብዛኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የስርዓቱ አካል እና አስፈጻሚ እንደሆኑ መናገር ይቻላል፡፡ እጅግ አሳዛኙ እውነታው ግን እነዚህ ሁሉ አባላት ወደ ድርጅቱ የተቀላቀሉት በፍላጐት ሳይሆን በግዳጅ ብሎም በሃገሪቱ የተዘረጋው አላፈናፍን ያለው አስጨናቂው ስርአት የሚያስከትልባቸውን የከፋ መዘዝ ለመሸሽ ከመፈለግ መሆኑ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በዩንቨርስቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው አዲስ ገፅታ፤ የተማሪዎች ጊዜያቸውን በህዋስ ውይይት እና ግምገማ ማዋላቸው፣ ከአባላት ሁሉ ልቆ ለመታየት የሚደረግ ጥረት፣ ከትምህርት ውጤታቸው ይልቅ፤ በአባልነታቸው ወደሚሰጣቸውን ነጥብ መጨነቅና አብዝቶ ማተኮር፣ ሲብስም የትምህርት ጊዜያቸውን መሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ለፓርቲ ተግባራት በማዋል የመጡበትን ዋነኛ የትምህርት አላማ በመሸሽ፤ ብቁ የካድሬ ምሩቃን ሆነው ለመውጣት ወ.ዘ.ተ መሽቀዳደም የተማሪዎች መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይህም የተሻለ ስራ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፤ በተቃራኒው ይህንን የሚሸሹ ምሩቃን ለስራ ማጣት እና ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ።

በመጨረሻም መንግስት ትምህርትና ተቋማቱን የፖለቲካ ሜዳ ከማድረግ መታቀብ አለበት፤ ከካድሬዎችም ነፃ ማድረግና የእውቀት አምባ ብቻ ሆነው መቀጠል ይኖርባቸዋል። በዘርፉ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መስተካከል እንደሚገባው፣ ተማሪዎችና መምህራኖች አካዳሚክ ነፃነት ማግኘት እንዳለባቸው፣ ተቋማቱ ዕውቀት የሚገበይባቸው እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ ሜዳ መሆን እንደሌለባቸው፣ የትምህርት ሥራ ሙያ እንጂ ፖለቲካ አለመሆኑ፣ እንዲሁም በመልካም ተምሳሌትነት ሊጠቀሱ የሚገቡ የልሂቃን /Elite/ ት/ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ሊፈጠሩ ይገባል። ትምህርት በዋናነት መፍትሄ ሰጪ ዕውቀት ካላስጨበጠና ችግር ፈቺ መሳሪያ ካልሆነ ለብዙሃኑ እንደሚታደል መሰረታዊ ሸቀጥ ካየነው አደጋው የከፋ የሀገር እድገት እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ሚና እንደማይጫወት ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የትምህርት ስርአታችን ከተደቀነበት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ማላቀቅ ግድ ነው። ይህ ብቻ ሲሆን አምራችና በእውቀት የዳበረ ዜጋ ማፍራት ይቻላል። ትምህርት ቤቶች (ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ) በግልፅም ሆነ በስውር የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ገዥ አካል ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሆን የለባቸውም፡፡ ይህ ከሆነ ግን አሁን በሃገራችን እየተስተዋለ እንዳለው ውድቀቱ የከፋ ነው።

ኢትዮጵያችን በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

ለአስተያየትዎ: kiduszethiopia@gmail.com ይጠቀሙ።

2 Responses to የትምህርት ተቌማት የእውቀት ወይስ የፖለቲካ ሜዳ!?

  1. Sime Reply

    December 9, 2013 at 11:17 pm

    Really i would like to what you written !

  2. nohope Reply

    December 1, 2013 at 11:24 am

    ቅዱስ ! የተናገርከው ሙሉ በሙሉ ትክክል ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ያየኸውን ወይም የሰማኸውንም ቢሆን ምሳሌ ማንሳቱ ላንባቢ ይጠቅማል:: ለምሳሌ የትምህርት መመረቂያ መጨረሻ ላይ ስለሚቀርበው thesis ጉዳይ ማውራት ይቻላል:: ባሁኑ ጊዜ አብዛኛው ተማሪ ገንዘብ እየከፈለ በሌላ ሰው እያጻፈ እንደሚያቀርብ መጥቀሱ አንድ ትልቅ ውድቀት ማሳያ ምሳሌ ነው::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>